የአማራ ሕዝብ የጥፋት ኃይሎች የግጭት አጀንዳ ሊያከሽፍ ይገባል!

 ሀገሪቱ ወደ ብልጽግና የጀመረችው ጉዞ ገና በጠዋቱ በብዙ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ስለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። በዚህም ሀገር እና ሕዝብ አየከፈሉ ያለው ዋጋ በብዙ መልኩ ትናንቶችን ሊያስመኝ ወደሚያስችል መንሸራተት ሊወስድ እንደሚችል ይታመናል።

ለውጥ በራሱ ከአንድ የገነገነ አሮጌ አስተሳሰብና አስተሳሰቡ ከሚወልዳቸው ድርጊቶች ራስንና ማኅበረሰብን መታደግ መንገድ ከመሆኑ አንጻር፤ ሀገራዊ ለውጡ በብዙ ተግዳሮቶች የመፈተኑ እውነታ ግር ሊያስብ የሚችል አዲስ ክስተት አይደለም። በለውጥ ሂደት ውስጥ የተለመደና የሚጠበቅ ነው።

ለዚህም ነው በለውጥ ወቅት የሚከሰቱ ተግዳሮቶችን አሸንፎ ለመውጣት ከሁሉም በላይ ለውጡ ይዞት የመጣውን ትሩፋት በአግባቡ ተረድቶ፤ ለስኬቱ የሚሆን ቁርጠኝነት መፍጠር፤ በፈተናዎች ብዛት እጅ ከመስጠት ይልቅ በፈተናዎች እየጠነከሩ ተስፋን ማጎልበት የሚያስፈልገው።

የእኛ የዛሬው የለውጥ ምዕራፋችን፤ የመጣንባቸው ውስብስብ ያልጠሩ የታሪክ ምዕራፎችን በማጥራት ነገዎቻችንን ብሩህ ለማድረግ ካላቸው ከፍ ያለ ተስፋ አንጻር በብዙ ተግዳሮቶች የመፈተናቸው እውነታ ተጠባቂ ነው። በተለይም ባለፉት 27 ዓመታት ከመጣንባቸው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅሎች አንጻር ለውጡን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች ማጋጠማቸው እንግዳ ጉዳይ አይሆንም።

እነዚህን ውስብስብ ያልጠሩ የታሪክ ምዕራፎች ነገ ላይ ተስፋ ላደረግናቸው ቀናቶች የመማሪያ መድብል ከማድረግ ይልቅ፤ የፖለቲካ መቆመሪያ ካርድ አድርጎ የመውሰድና ከእነርሱ አትራፊ ለመሆን የሚደረጉ ያልተገቡ እና በነውር የተሞሉ ጥረቶች ለውጡን እያጋጠሙ ያሉ ዋነኛ ተግዳሮቶች ናቸው።

የትናንት ህመሞቻችንን ዛሬ ላይ ዓለም በደረሰባቸው የአስተሳሰብ ፈውስ ከማከም ይልቅ፤ ሕመሞቹ ፈጥረውት ያለፉትን ቁስል በማከክና በማመርቀዝ፤ ሀገርና ሕዝብን እንደ አዲስ የበሽታው ገመምተኛ በማድረግ፤ ነገዎቹን በተስፋ ከመጠበቅ ይልቅ ብዙ ዋጋ ያስከፈሉትን ትናንቶች ናፋቂ ለማድረግ፤ በዚህም ለውጡን እና የለውጡን አስተሳሰብ ለማምከን የሚሰሩ ኃይሎች ጥቂት አይደሉም።

እነዚህ ኃይሎች ከሀገሪቱ ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ እሴቶች እንግዳ የሆነ ጽንፈኛ አስተሳሰቦችን በግልጽ በአደባባይ፣ በድፍረትና በማን አለብኝነት በመስበክ፣ ሕዝብን በሕዝብ ላይ፤ ሀይማኖትን በሀይማኖት ላይ በማነሳሳት ሀገርን ወደ ማያባራ ሁከትና ብጥብጥ በመውሰድ በዚህ አትራፊ ለመሆን ባላቸው አቅም ሁሉ እየተንቀሳቀሱ ነው።

የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም በአውሮፓና በአሜሪካ ከተሞች መሽገው ”ከበሬ ወለደ ” ትርክታቸው ጀምሮ በአሉባልታና በፈጠራ ወሬ ሀገርን ከግጭት አዙሪት ለማውጣት የሚደረገውን ጥረት ፈተና ውስጥ ለመጣል የሚታትሩ ብዙዎች ናቸው። ከዛም አልፈው ራሳቸው የግጭት ምንጭ በመሆን ለሀገር ሰላም እና ለሕዝቦች አብሮ መኖር ስጋት ሆነዋል።

ብዙዎች እንደሚስማሙት ሀገር በዚህ ወቅት የምትፈልገው ችግሮች ቢፈጠሩና ጥያቄዎች ቢኖሩ እንኳን በወንድማማችነት መንፈስ ተቀራርቦ በመነጋገር መፍትሄ ማበጀትን ነው፡፡ ይሁን የጥፋት ነጋዴዎች ጽንፍ በረገጡ መንደርተኛ አስተሳሰብ ተወስደው፣ የሀገሪቱን ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ተቻችሎ የመኖር ባህል በሚያፈርስ የጥፋት ትርክቶች ሲጠመዱ ታይተዋል።

የጥይት ድምጽ በማይሰማባቸው የአውሮፓና የአሜሪካ ከተሞች ተቀምጠው በደራላቸው የዩ-ቲዩብ ገበያ እና በጽንፈኛ አስተሳሰቦቻቸው በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሚሰበሰብ ገንዘበ የጥፋት ተልእኳቸውን በተደራጀ መንገድ ለማስኬድና ከግጭት ለማትረፍ የሚጥሩም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡

አንድ ጊዜ የፖለቲካ ልሂቅ፤ ሌላ ጊዜ የሰብአዊ መብት ተሟጋች፤ ደግሞ ሌላ ጊዜ አዋጊ የጦር ጀነራል ለመሆን ምንም አይነት ይሉኝታ የማይሰማቸው እነዚህ ኃይሎች፤ በሀገርና በሕዝብ ላይ የሚያስቡት ጥፋት አቅም ማግኘት ከቻለ ወንድም በወንድሙ ላይ እንዲነሳ በማድረግ ጥላቻ ፈጥረው፣ ዘርተው፣ ሀገርና ሕዝብ ፍሬውን እንዲያጭድ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።

እነዚህ ኃይሎች ምንም አይነት ኃላፊነት የማይሰማቸው፤ በጥላቻ መንፈስ የሚመሩ፤ ከግጭት ውጪ ማሰብ የሚያስችል ፍጥረታዊ ስብእና የሌላቸው ናቸው፡፡

የአማራ ሕዝብም እነዚህ ኃይሎች በክልሉ አምጠው የወለዱትን ግጭት እና ግጭቱ በተጨባጭ የክልሉን ሕዝብ እያስከፈለ ያለውን ዋጋ በአግባቡ በመገንዘብ ራሱንና ክልሉን ከነዚህ ኃይሎች ሊታደግ፤ ይህን በማድረግም በቀደሙት ዘመናት አባቶቹ ለሀገር የዋሉትን ከፍ ያለ ውለታ አስጠብቆ ሊቀጥል ይገባል !

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 13/2015

Recommended For You