የአፍራሽ ኃይሎችን ሴራ ለመቋቋም

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከተከሰተው ጦርነት በኋላ ሕዝቡ ምንም ችግር ይከሰታል ብሎ ባይገምትም ዛሬም ሀገሪቱ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በአማራ ክልል ችግር ውስጥ ነች። አንዱን ችግር ተሻገርኩ ስትል ሌላው የሚጋረጥባት ሁነት ሲታይም ዕጣ ፈንታዋ የሆነች ሀገር መስላም እንድትታይ እያደረጋት ይገኛል።

ችግሩ መንግሥት የፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር ብርቱ ቁርጠኝነቱን እያሳየ ባለበት ሁኔታ ፣ ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ፍትህ የማስፈንና ተጎጂዎች እንዲካሱ የማድረግ ሥራም እየተሰራ ባለበት ሁኔታ መሆኑ ደግሞ ችግሩን የበለጠ አሳሳቢ አድርጎታል።

ሂደቱ እውነትን በማፈላለግ እና ቁርሾን በመርሳት ወደ እርቀ-ሠላም ባመራበት ሁኔታ ይገጥማል ተብሎም አይጠረጠርም። ያውም በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ ለማካሄድ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ባለበት ወቅት መከሰቱ ግራ አጋቢነቱን ከፍ ያደርገዋል።

በርግጥ ችግሩ ቀደም ሲል በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከተከሰተው ጦርነት ጋር ሲነፃፀር አሳሳቢነቱ ከፍያለ ባይሆንም ፣ ዜጎችን ሰላም በመንሳት ላልተገባ የንብረት ውድመት ሞት መዳረጉ በቀላሉ እንዲታይ የሚያደርገው አይደለም።

ተግባሩ ዝርፊያ፣ ቅሚያና ውንብድና ከጀርባው ያስከተለ፤ የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት እየተገዳደረ ከመሆኑ አንጻር ፤ በመንግሥት ኃላፊነት ላይ ጫና አሳድሯል።

ችግሩ መንግሥት አፋጣኝና አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ በመገደዱ ወደ ክልሉ የጸጥታና መከላከያ ኃይሎችን በማሰማራት በአጭርና በወሳኝ መልክ ችግሩን እየቋጨው ይገኛል። ሕዝቡ በሠራዊቱ ላይ ተስፋውን በመጣልም ወደ ዕለት ተዕለት እንቅስቀሴው እየገባ ይገኛል።

በነገራችን ላይ ብዙዎቻችሁ የዚህ ጽሑፍ አንባቢዎች ችግሩ እና የችግሩስ ባለቤት ማን ነው የሚል ጥያቄ በአእምሯችሁ መመላለሱ አይቀርም። ከችግሩ በስተጀርባ ያለውን ኃይል አንዳንዶች የጠራ ውሃ መጠጣት የማይፈልግና ሌሎች ዜጎቿም እንዲጠጡ የማይሻ አደፍርስ ብለው የሚጠሩት አሉ።

እንደ እኔ፣ እንደኔ በእርግጥ በፕሪቶሪያው ስምምነት ወደ ሰላምና መረጋጋ እየሄደች ያለችውን ሀገር የሚያውክና የሚረብሽ አካል አደፍርስ ቢባል አያንሰውም። የማይመጥነው ስያሜም ሊሆንበት የሚችል አይመስለኝም።

እዛም እዚህም መንገድ በመዝጋት እንቅስቃሴ የሚያስተጓጎል ፤ተራ ሁከት ፈጣሪ ፣ወንበዴ፣ ዘራፊና ቀማኛ ነው የሚሉትም አሉ። ይሄም ተግባሩ በደንብ አድርጎ እሱነቱን የሚገልጥ አይመስለኝም።

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከተከሰተው ጦርነት በኋላ የተፈጠረ ከፍተኛ ችግሮች አሉ። አፋጣኝ ድጋፍና ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ሰብአዊ ቀውሶችን ለመፍታት በመንግሥትና በተለያዩ አካላት የሚደረግ እርዳታ የማድረስ ጥረት ፤ ኢኮኖሚውን በማረጋጋት ለኑሮ ውድነት ማቅለል መፍትሄ ለሆነው የክልል ክልል እንቅስቃሴ ሕዝቡና መንግሥት ርብርብ ላይ ናቸው። ለዚህ ሁሉ እንቅፋት የሆነ አካል ስያሜው ቢያንሰው እንጂ አይበዛበትም።

ከዚሁ ዓይነቱ ሥራው ጋር አያይዘውም በሽብርተኝነት መፈረጅ አለበት ሲሉ ወገባቸውን ይዘው የሚሞግቱ ክፍሎች መኖራቸውም ይነገራል። ሹመትና ሽልማት አበክሮ የሚሻ የስልጣን ጥመኛ ነው የሚል ትንታኔ የሚሰጡም አሉ።

እነዚህኞቹ ገማቾች ሹመትና ሽልማት ከምን ተነስቶ ነው የሚፈልገው ፤ስልጣን ዝም ብሎ ከመሬት በመነሳት ተፈልጎ የሚመጣ ነው ወይ ሲሏቸው የሚሰጡት ምላሽ አላቸው። ከነዚህ አንዳንዶቹ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተደረገው ጦርነት ራሱንም ፣ወገንና ሀገርንም ከጥቃቱ ለመታደግ የታገለ ስለመሆኑ ይናገራሉ።

ሹመትም ሆነ ሽልማት የሚሻው ይሄንኑ እንደ ውለታ ቆጥሮ የመሆኑን ምስጢር ይጠቅሳሉ። ሀገር በማዳን ተልዕኮው ድፍን የኢትዮጵያ ሕዝብ መሳተፉ ይታወሳል። ታዲያ የተለየ ሽልማትና ሹመት የሚፈልገው ማን ስለሆነና ምን የተለየ ነገር ሰርቶ ነው። ይህንን በማጣቀስ ማብራሪያ ሲጠይቋቸውም ያኔ ግንባር ቀደም አስተዋጽኦ ከነበራቸው የአንዱን ቡድን ስም ያነሳሉ።

የተለየ የሚያደርገው ያለበት አካባቢ ለጦርነቱ ቅርብ የነበረና ቀጥተኛ ተጠቂም በመሆኑ ጉልህ ትግል ማድረጉን ያወሳሉ። ግን ደግሞ ግብሩን እንጂ መጠሪያ ስሙን ፈፅሞ አይጠቅሱም። ሌሎች በበኩላቸው በትግሉ ከነበረው ብርቱ አስተዋጽኦ አንፃር ተነስተው ታግሏል የሚሉትን ክፍል ሲገምቱ “ፋኖ” ነው ይላሉ።

ሆኖም በጦርነቱ ብርቱ ትግል አድርጎ የጋራ ድል ለመቀዳጀት ያስቻለው ፋኖ በታሪኩ ሹመትም ሆነ ሽልማት ታሳቢ አድርጎ የሚታገል እንዳልሆነ ሁላችንም እናውቃለን። በመሆኑም ሰዎቹ የሚሉት አካል ማን ሊሆን ይችላል ብለን በየፊናችን ራሳችንን መጠየቃችን አይቀርም።

በርግጥ ያኔም ቢሆን በጦርነቱ ወቅት በ“ፋኖ” ስም ሕዝቡን በመዝረፍ ፣በመቀማት፣በመግደልና በማሰቃየት የሚሳተፉ ቡድኖች ነበሩ። እነዚህን ቡድኖች ለሀገሩና ለወገኑ ነፍሱን አስይዞ ከሚፋለመው ፋኖ ለይቶ ማየት ይገባል። ለሀገሩና ለወገኑ ያደረገውን ትግል ክብሩና ባህሉ አድርጎ ከሚቆጥረው እንጂ በጊዜያዊ ሹመትና ሽልማት ከማይለውጠው ቆፍጣና ማራቅም ያሻል።

የቡድኑን ባህሪና እንቅስቃሴ በቅርብ የሚያውቀው መንግሥት ዘራፊ ቡድን እያለ ይጠራዋል። ያኔም በፋኖ ስም ሲዘርፍና ሲቀማ ለነበረ፤ አሁንም ይሄንኑ ተግባሩን አጠናክሮ ለቀጠለ ቡድን ስያሜው ይመጥነዋል።

በ27ቱም ሆነ ባለፉት አምስት ግን ደግሞ ፈተናቸው ለረዘመ የለውጥ ዓመታት የተፈጠሩትን አኩራፊዎች በፋኖ ስም ከሚነግደው ወንበዴ ጋር ደምሮም ማየት ያስፈልጋል።

በዚህ በኩል የሀገርን ድንበር የሚጠብቀውና የሚያስከብረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መግባቱም ለክልሉ ሕዝብ ሰላም ነው። ምክንያቱም ባለፉት ዓመታት ውስጥ ሀገራችን በተለየ መልኩ ከገጠማት ሕገወጥነት ችግር አንፃር ሠራዊቱ በየመንደሩ እየገባ የብዙ ዜጎችን ህይወት ሲታደግ መቆየቱ መዘንጋት የለበትም።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የቤት ሥራውን መውሰዱ ብዙ ችግሮችን የሚያቃልል መፍትሄ ያመጣል የሚል እምነት አለኝ። ከወዲሁም የሰብአዊ ርዳታ መተላለፊያዎች እንዲከፈቱ አደርጓል። ከቦታ ቦታ የሚደረገውንም እንቅስቃሴ በተገቢው መንገድ አሳልጦታል። ችግሩ በሌሎች አካባቢዎች እንዳይሰፋ፤ እንዳይኖርም ትምህርት ይሰጣል።

 ሠላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 12/2015

Recommended For You