በዓላት በተለያየ መልኩ የሕዝቦች አብሮነት የሚገለጽባቸው ናቸው:: ይሄ አብሮነት ደግሞ የሚመነጨው ከውስጥ ሰላም ነው:: ምክንያቱም በዓላት በተለይም ሕዝባዊ በዓላት ቁጥሩ ከፍ ያለ ሰው (ከሺዎች እስከ መቶ ሺዎች) በአንድ ላይ ተሰብስቦ የሚያከብራቸው መሆኑ የሕዝቦች አንድነትን የሚያስተጋቡ ናቸው::
በዚሁ ልክ ደግሞ በዓላቱ በሕዝቦች መካከል ሰላማዊ መስተጋብር የሚታይባቸው፤ እና በዚሁ ሰላማዊ ድባብ ተጀምረው የሚጠናቀቁ መሆናቸው የበዓላቱን የሰላም አውድነት የሚናገር ነው:: በመሆኑም እነዚህ ሕዝባዊ በዓላት አንድም የሕዝቦች አንድነትና አብሮነት የሚገለጽባቸው፤ ሁለተኛም የሰላማዊ ሁነቶች መከወኛ የሰላም አውድነታቸው በእጅጉ ጎልቶ ይገለጣል::
እነዚህ ሁለት ዐበይት ጉዳዮች ደግሞ የሚነጣጠሉ አይደሉም:: ምክንያቱም አንድነት ያለ ሰላም፣ ሰላምም ያለ ሕብረት መገለጥ አይችሉምና ነው:: ሰላም ከሌለ በኅብር ደምቆ መቆምና በዓል ማክበር አይቻልም፤ በአንድ መሰባሰብ እና የጋራ ኩነት ከሌለም የሰላማዊ ግንኙነት ገጽ አይታይም::
ሕዝባዊ በዓላት በአንድ መሰባሰቢያ ናቸው ሲባል ደግሞ፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዝሃነት ጎልቶ በሚገለጽባቸው ሀገራት ውብ የሆነ መስህብ አውድም ናቸው ማለት ነው:: ይሄ ውብ መስህብ ደግሞ በአለባበስ፣ በአጨፋፈር፣ በጥቅሉ በማኅበራዊም ባህላዊም እሴት ምክንያት የሚገኙ ድንቅ የማንነት መገለጫዎች የሚንጸባረቁበት ነው::
ይሄ ውብ መስህብ ሰላምና ፍቅር በዋጁት አብሮነት ሲገለጥ ደግሞ ለሰው እይታ ሳቢ የሆነ የቱሪዝም ሀብት ነው:: ቱሪዝም ደግሞ ለአገር ገጽታ ግንባታ፣ ለኢኮኖሚ እድገት እና ለዲፕሎማሲ (በተለይ ለሕዝብ የሕዝብ ዲፕሎማሲ) ማሳለጫ አቅምነቱ የላቀ ነው::
ኢትዮጵያ ደግሞ በዚህ ረገድ አቅም የሚሆኑ በርካታ ሕዝባዊ በዓላት ያሏት አገር ናት:: እነዚህ በዓላት ደግሞ በተለያየ መልኩ የሚከወኑ፤ በተለያየ አውድ የሚገለጡ፤ በተለያየ ማኅበራዊ መሠረት ያላቸው፤ ግን እንደ ሀገር ከፍ ያለ የሰላም፣ የአብሮነት እና የቱሪዝም ሀብትነት እሴትነታቸው ልቆ የሚታዩ ናቸው::
ከሰሞኑ የሚከበሩር የደብረ ታቦር (ቡሄ) በዓል፣ እንዲሁም የአሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሻደይ፣ ሶለል እና ሺኖዬ በዓላት በዚሁ ልካቸው የሚታዩ ናቸው:: ይልቁንም እነዚህ በዓላት በተለየ መልኩ የልጆችና የወጣቶች በዓላት ተደርገው ስለሚወሰዱ፤ እነዚህ ወጣቶች አብሮነትን፣ ሰላምንና በኅብር ደምቆ መገለጥን የሚለማመዱባቸው መሆናቸውን ልብ ማለት ይገባል::
ለአብነት፣ የደብረ ታቦር (ቡሄ) በዓል፣ የልጆች በዓል ተብሎ ይታወቃል:: ይሄ በዓል በዋናነት ወንዶች ልጆችና ወጣቶች በአብሮነት ሆነው ችቦ እያበሩ፣ ጅራፍ እያጮኹ፣ እየጨፈሩና ሌሎችም ባህላዊ ተግባራትን እየከወኑ በደስታና በፍቅር የሚያሳልፉት፤ ወላጆችም (በጥቅሉ ማህበረሰቡ) ለልጆቹ ሥጦታ እና ምርቃት የሚቸሩበት የደስታና የአብሮነት በዓል ነው::
የአሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሻደይ፣ ሶለል እና ሺኖዬ በዓላት ደግሞ በዋናነት በትግራይ፣ በአማራ እና ኦሮሞ ልጃገረዶች የሚከበር በዓል ነው:: በመሆኑም በዚህ በዓል ሴቶች ተውበው የሚታዩበት፤ በዓደባባይ ወጥተው ደስታና ስሜታቸውን የሚገልጹበት፤ እየዞሩ የሚጫወቱበት፣ ከማኅበረሰቡም ስጦታና ምርቃት የሚቸሩበት፤ ከፍ ሲልም የሕይወት አጋራቸውን የሚያገኙበትም ነው::
የደብረ ታቦር(ቡሄ) በዓል በወጣት ወንዶች ሲከበር የብርሃን፣ የሰላም፣ የነጻነት ዘመን መምጣትን በማሰብ ነው:: የአሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሻደይ፣ ሶለል እና ሺኖዬ በዓላት በልጃገረዶች ሲከበሩም፤ የክረምቱን መገባደጃ ቀናት ላይ በየአካባቢው ሁሉ የሚታየው ልምላሜንና የአዲስ ዓመት አዲስ ብስራት ዋዜማን በልጃገረዶች ጨዋታ የማብሰሪያ በማድረግ ነው::
በድምሩ እነዚህ በዓላት የአሮጌው ዘመን ማለፍ፤ የአዲስ ዘመን መምጣትን አብሳሪዎች ናቸው:: ከአሮጌው ዘመን ጋር ደግሞ አብረው ማለፍ ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ:: መገፋፋት፣ መጠራጠር፣ ቂም፣ ጸብ፣ ጥላቻ፣ መፈናቀል፣ ጦርነትና ሌሎችም እኩይ ተግባራት የአሮጌው ዘመን ግሳንግሶች አብረው መሻር አለባቸው::
በአንጻሩ አዲሱ ዘመን አዲስ ተስፋ ነው:: በአዲስ ተስፋ ውስጥ አብሮነት፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነትና ወንድማማችነትን የመሳሰሉ ከፍ ያሉ እሴቶች አብረው እንዲገቡ ያስፈልጋል:: ምክንያቱም በዚህ መልኩ ወጣት ሴቶችም ወንዶችም እነዚህን በዓላት ሲያከብሩ በኅብረትና አንድነት ነው::
ይሄ ኅብረትና አንድነት ያለ ፍቅር፣ ያለ መተሳሰብ፣ ያለ የውስጥ ሰላም የሚታሰብ አይደለም:: እናም በዓሉ የወጣቶቹ አንድነት፣ አብሮነትና ሰላም መገለጫ ነው:: ስለሆነም እነዚህ በዓላት ሲከበሩ የሰላምና የአብሮነት እሴታቸው ከፍ ብሎ ሊገለጥ፤ የቱሪዝም መስህብነታቸውም ሊጎላ የተገባ ነው:: ይሄንን በተግባር ማሳየትም ከሁሉም የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 12/2015