ሰላም መልከ ብዙ ነው፤ ግብሩም ፍጹም ጤና፣ ፍጹም ዕረፍት፣ ፍጹም ዕርቅ፣ ፍጹም ፍቅር እና አብሮነት፣ ፍጹም ደኅንነት፣ ፍጹም ተድላ፣ ፍጹም ደስታ ወዘተ በሚባሉ መገለጫዎች የሚገለጥ ነው። ምክንያቱም ሰላም ሲኖር ደስታ፣ ሰላም ሲኖር ወንድማማችነት፣ ሰላም ሲኖር አብሮነትና ፍቅር፣ ሰላም ሲኖር ፍጹም የደኅንነት ስሜን፣ ሰላም ሲኖር ተድላና ሃሴት በሰው ልጆች ይነግሳሉ።
ይሄ በሰው ልጆች የሚገለጽ የሰላም ሁኔታ ደግሞ እንደ ማኅበረሰብ፣ እንደ ሕዝብ፣ እንደ ሀገር ከፍ ያለ የብልጽግና እሳቤና ልዕልናን ያጎናጽፋል። ሰላም የሞላበት ግለሰብ ሰላማዊ ቤተሰብን ይመሰርታል። ሰላም የሞላበት ቤተሰብ ሰላማዊ ማኅበረሰብን ይፈጥራል። ሰላም የሞላበት ማኅበረሰብ ደግሞ ሰላም የነገሰበት አካባቢን እና ሀገርን ይመሰርታል። ሰላም የበዛለት አካባቢና ሀገር ደግሞ ከዛሬ ባሻገር ስላለው እውነት የሚገነዘብ ትውልድ ባለቤት ስለሚሆን ምሉዕ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ይተጋል፤ ትጋቱም ፍሬ ያፈራል።
ዛሬም ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የሚያስፈልጋቸው፤ አብዝተው የሚሹትም ይሄንኑ ነው። ምክንያቱም የሰላምን ዋጋ በእጅጉ የተገነዘቡባቸው በርካታ ሁነቶችና ክስተቶችን አይተዋል። ሰላም ጠፍቶ፣ ወንድማማችነት ሻክሮ፣ አብሮነት ተፈትኖ፣ መነጋገርና መደማመጥ ርቆ፣ ይቅርታና እርቅ ባዕድ ሆኖ፣ በአንጻሩ መገፋፋትና ኹከት ነግሶ ቃታ እስከ መማዘዝ ደርሰው የሰላም እጦትን ክፋት በራሳቸው ደርሶ ተረድተውታል።
በዘመናት ጉዞ ውስጥ የተከሰቱ ግጭትና ጦርነቶች ያስከተሉትን ሰብዓዊ ጉዳት፤ ኢኮኖሚያዊም ኪሳራ እና ማኅበራዊ ምስቅልቅል ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈላቸው ተመልክተዋል። እናም ግጭትና ጦርነት ያለውን ጥቁር ገጽ ከሌላ ሳይሆን ከራሳችን፤ የሰላምን ብርሃናማ ገጽም ከራስም ሆነ ከሌሎች በልካቸው መገንዘብ የተቻለባቸው አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል።
አሁን ላይ የሚያስፈልገው ደግሞ እነዚህ በልካቸው የተረዳናቸውን የሰላም ብርሃናማ ገጽ እንዲሁም የግጭትና ጦርነትን ጽልመትነት በሁላችንም ዘንድ ሰርጸው ከጽልመቱ ልንርቅ፣ ከብርሃናማው አውድ ልንውል የሚገባ መሆኑም አምኖ መቀበሉ፤ ለዚህም ራስን ማስገዛቱ ላይ ማተኮር ነው። ምክንያቱም ተጋጭተን እና ተዋግተን ብዙ ያጣንባቸው፤ ተዋድደንና በአንድ ቆመን ብዙ ያተረፍንባቸው አጋጣሚዎች የዚህ ዐብይ እማኞቻችን ናቸው።
ሌላው ቀርቶ ከለውጥ ማግስት ያሉ አምስት ዓመታትን ማየት ቢቻል ችግሮቻችንን ቁጭ ብለን መነጋገር ባለመቻላችን ምክንያት እዚህም እዚያም የታዩ ግጭቶችና ጦርነቶች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን ሕይወት ቀጥፈዋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትንም ከሞቀ ቤት ንብረታቸው አፈናቅለው ለስደት ዳርገዋል። በትሪሊዮን ብር የሚገመት የሀገርና ሕዝብ ንብረት ለውድመት ዳርጓል። የዜጎች ማኅበራዊ መስተጋብሮች ትልቅ ፈተና ገጥሞታል።
ይሄ ዘርፈ ብዙ ኪሳራ የፈጠረው ደግሞ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተን ባለመነጋገራችን ነው። ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተን፣ ለሕዝቦች አብሮነትና የጋራ ተጠቃሚነት አስበን ተንቀሳቅሰን ቢሆን ኖሮ፤ በአጭር የተቀጠፉ ወገኖቻችን፣ ከሀብት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎቻችን፣ ወደ ትቢያነት የተለወጠው የሀገር ሃብት፤ እንደ ሀገር ከድህነት ለመውጣት በምናደርገው መውተርተር ላይ ተጨማሪ አቅም ሆኖ ጉዟችንን ያስፈነጥርልን ነበር።
ይሁን እንጂ ዛሬም ስለ ሰላም ለማውራት፤ ስለ ሰላም ለመሥራት አልረፈደም። ሰላም ቅድመ ሁኔታ የላትም። ሰላም የምትፈልገው ንጹህ ልብና ቀና እሳቤን ነው። ንጹህ ልብ ስለ ይቅርታ እና እርቅ አብዝቶ ይናፍቃል። ቀና እሳቤ ደግሞ ለሰላም የሚዘረጉ እጆችን በበጎ መልካቸው ይቀበላቸዋል። ይሄ ሲሆን ልቦች ይተባበራሉ፤ አዕምሮም ለመልካም ነገር ይገዛል፤ እጆችም ለልማት ይዘረጋሉ። የእነዚህ ድምር ውጤት ደግሞ እንደ ሀገር እውን ልናደርግ የምንሻውን ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና ለማረጋገጥ የተባበረ አቅምን ይፈጥራል።
እናም ከትናንት የተሻገሩ፤ ዛሬም የተፈጠሩ፤ ጠባሳቸውን ወደ ነገ ለማሻገር የሚውተረተሩ አያሌ ጉዳዮቻችን ሰላማችንን እንዲያደፈርሱ፤ ከልማትና ብልጽግና መንገዳችን እንዲያስተጓጉሉን ዕድል ልንሰጣቸው አይገባም። ዛሬ ላይ በሰሜኑም፣ በምዕራቡም የሚታዩ ግጭትና አለመረጋጋቶች ምንጫቸውም ከዚሁ ከትናንት፣ ከዛሬ እና ከነገ ምልከታችን የሚቀዱ መሆናቸውን ተገንዝበን ልንገራቸው ይገባል።
የጋራ ሀገር የሚገነባው በትናንት «ታሪክ» ላይ በመነታረክ አይደለም። ዛሬን ተሻግረን ብሩህ ነገን የምንፈጥረው በቁርሾ ላይ ተመስርተን ስንዋጋ አይደለም። ብልጽግናችንን የምናረጋግጠው ነገን በእኛነት እንጂ በእኔነት ልኬት እያሰብን ስንሰራ አይደለም። ይሄ ሲሆን ደግሞ አሁን እንደምናየው ከአንድነት ይልቅ ጥግ ይዞ ወደ መሻኮት፤ ከመተባበር ይልቅ ወደ መገፋፋት፤ ከሰላም ይልቅ ወደ ግጭትና ጦርነት ነው የሚወስደን። ሰላም ጠፍቶ ግጭት ቦታውን ሲይዝ ደግሞ የሚጠፋው ሰው ነው፤ የሚወድመው ሃብት ነው፤ የሚናጋው ማኅበራዊ መሠረታችን ነው። በመሆኑም ለማሳካት ለምንናፍቀው ብልጽግና እውን እንዲሆን የሰላምን ዋጋ ለአፍታም መዘንጋት አይገባም!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11/2015