የአማራ ክልል ርዕሰ መዲና የሆነችው ባህር ዳር ከተማ የቱሪስት መስህብ መሆኗ ይታወቃል። ከሰሞኑ በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት አንዳንድ ከተሞች ላይ የሰላም መታጣት ታይቶ እንደነበር ሁሉ በዚህች የጣና ዳር ፈርጥ በሆነችው በባህር ዳር ከተማም ያለመረጋጋት ተከስቶ እንደነበር ይታወቃል። ይሁንና በየከተሞቹ እየተካሄዱ ባሉ ውይይቶች እና መንግሥት ሰላምን ለማስፈን እያደረገ ባለው ጥረት መረጋጋት እየሰፈነ መጥቷል።
አዲስ ዘመን በፅዱዋ እና ውቧ ባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ባለው የልማት ሥራ እና ከተማዋን ለነዋሪው ምቹ የማድረግ እንቅስቃሴ እንዲሁም አሁን ያለው የሰላም ሁኔታን አስመልክቶ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ከሆኑት ከዶክተር ድረስ ሳህሉ ጋር ቆይታ አድርጎ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡-ባለፉት ሁለት ሳምንታት በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ የባህር ዳር ከተማም በተወሰነ መልኩ ሰላም ርቋት እንደነበር ይታወቃል፤ አሁን በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ትገኛለች?
ዶክተር ድረስ፡- የከተማዋን ሰላም እና ጸጥታ ከማስጠበቅ አኳያ የአንድ ሕዝብ ሰላምና ደህንነቱ የሚጠበቀው ሕዝቡ በራሱ ተባባሪ ሲሆን ነው የሚል እምነት አለኝ። በሁሉም ነገር ጸጥታ ኃይሎች ብቻ ይሠራሉ ማለት አይደለም። እኛ ከዚህ የተነሳ ከከተማ አስተዳደሩ እስከ ቀበሌ ድረስ ባለው መዋቅር ሰፊ የሕዝብ ውይይቶችን አካሂደናል። በተጨማሪ የጸጥታ መዋቅራችንን ገጽታ ገንብተናል፤ አስተካክለናልም።
ነገር ግን ይህ ሁሉ ሥራ ያለኅብረተሰቡ ተሳትፎ እና ድጋፍ ዋጋ የለውም። ስለዚህ ኅብረተሰቡን በጸጥታ ጉዳይ ከመንግሥት አካላት ጋር በትብብር እንዲሠራ ያላሰለሰ ጥረት እያደረግን እንገኛለን።
አሁን ባለው ሁኔታ ከተማችን ሰላማዊ ሒደት ላይ ትገኛለች ማለት ይቻላል። በእርግጥ የሰላም እጦት በብዙ መንገድ ሊመጣ ይችላል፤ እኛ ግን ከኅብረተሰቡ ጋር በመመካከር ላይ እንገኛለን።
ይሁንና ሁሌም በዚህ መንገድ ብቻ መሄዱ ሰላም ሆኖ ይቀጥላል ማለት አይደለም። በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለ ጥንካሬ ወሳኝ ነው። ስለሰላም ሲባል በቅንጅት መሥራቱ እስከቀጠለ ድረስ ግን ሰላሙ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። በሰላም ጉዳይ ወደኋላ ማለት የሚመጣ ከሆነ ደግሞ የሰላማችን ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ስለሆነም ሰላምን በማስከበር ረገድ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የኅብረተሰቡ ክፍል ከከተማ አስተዳደሩ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ይቀጥል ስል ጥሪዬን ማስተላለፍ እወዳለሁ።
እንደሚታወቀው ባለፉት ጊዜያት በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ በከተማችንም ችግር ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን ሰላሙ በጣም አስተማማኝ ነው። ጥሩ ነው ብቻ የሚባል ሳይሆን በጣም ጥሩ ነው ማለት ይቻላል። በከተማችን የትራንስፖርት አገልግሎቱ በአግባቡ ተጀምሯል። የተለያዩ ተቋማትም ሥራ ጀምረዋል።
በዚህ አጋጣሚ ለባህር ዳር ከተማ ነዋሪው የማስተላልፈው መልዕክት ቢኖር ሰላም ዋጋው ትልቅ መሆኑን መቼም ቢሆን ልንዘነጋው የማይገባ ጉዳይ መሆኑን ነው። ያለሰላም ምንም ነገር ማከናወን አይቻልም። ከምንም በላይ ሰላምን ማስቀደም ተገቢ ነው። እያንዳንዱ አካል ለሰላም መጠበቅ ትኩረት የሚሰጥ ከሆነ የሚናፍቀውን መልካም ነገር ሁሉ ማሳካት ይቻለዋል። ሰላም ተጠበቀ ማለት ትርፋማ መሆን እንደማለት ይቆጠራል።
በተለይ ወጣቱ ኃይል ሀገሩንና አካባቢውን መጠበቅና ከማንም በላይ ደግሞ ለሰላሙ ትኩረት መስጠት እንዳለበት መግለጽ እወዳለሁ። ከዚህ ውጪ የትኛውም ዓይነት የሃሳብ ልዩነት ቢኖርበትም እንኳ ጉዳዩን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ በማምጣት መወያየት የሚቻል መሆኑን መዘንጋት የለበትም። ችግርን በውይይት መፍታት እንጂ ለማንኛውም ጥያቄ ጉልበትና ብጥበጥን ተጠቅሞ ለመፍታት መሞከር በሰላም ወጥቶ ለመግባትም ሆነ ለሀገር እድገት የማይበጅ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
ስለሆነም የሰላም መደፍረስ ለዜጎች ሁሉ የማይበጅ በመሆኑ ሁሉም ለሰላም መስፈን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል። ሰላምን ከሚያደፈርስ ድርጊት ሁሉም ተቆጥቦ ለሰላም ቅድሚያ ቢሰጥ የሚናፍቀውን መልካም ነገር ማግኘት ይቻላል። በዚህ መልኩ ሰላምን ይበልጥ ለማጽናት ደግሞ ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ተደርጓል። በቀጣይም ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን ሰላምን ለማረጋገጥ ተጠናክሮ የሚሠራ ይሆናል። በአሁኑ ወቅት በባህር ዳር ከተማ ቀድሞ የነበረው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
አዲስ ዘመን፡- ከተማዋን ውብና ለነዋሪዎቿ ምቹ ከማድረግ አኳያ ምን ተሠርቷል? በቀጣይስ ምን ያህል ለማስዋብ ታስቧል?
ዶክተር ድረስ፡- የከተማ አስተዳደራችን ከተማዋን ውብ እና ማራኪ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ነው። በዚህ ክረምት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የሁለተኛ ዙር አረንጓዴ ዐሻራ ምክንያት በማድረግ በከተማችን ውስጥ ለመትከል አቅደን የነበረው ከሦስት ሚሊዮን በላይ ችግኝ ነው። ኅብረተሰቡን በማንቀሳቀስም ለመትከል ያቀድነውን የችግኝ መጠን በተገቢው መንገድ ማሳካት ችለናል።
ነገር ግን እንደባህር ዳር ከተማ አስተዳደር እዚህ ላይ ብቻ ተወስነን የመቆም ፍላጎት የለንም። በከተማችን የተጀማመሩ መሠረተ ልማቶች በተለይም የጌጠኛ ድንጋይ፣ የአስፓልት ሥራዎችን እንዲሁም የጠጠር መንገድ ሥራዎችም አሉ። በመሆኑም መንገዶቹን እየተከተልን ኅብረተሰቡንም እያሳተፍን ችግኞችን እየተከልን እንገኛለን።
ከዚህ ውጪ በከተማ አስተዳደራችን ውስጥ ከአምስት ሔክታር በላይ የሚሆን የአረንጓዴ ቦታ ፓርክ በማልማት ላይ እንገኛለን። ይህ ፓርክ እየተጠናቀቀ በመሆኑ በቅርቡ ለምረቃ እናበቃዋለን የሚል እምነት አለን። ይህ ለከተማዋ የመጀመሪያ በጣም ሰፋ ባለ መንገድ የተሠራ ፓርክ ነው ማለት ይቻላል። እንዲህም ሲባል ልክ አዲስ አበባ ላይ እንደተሠራው የአንድነት ፓርክ ዓይነት ይዘት ያለው ሲሆን፣ እሱን በአርዓያነት ተከትለን በመሥራትና በማጠናቀቅ ላይ እንገኛለን።
በአጠቃላይ ከተማ ውስጥ እያንዳንዱ ነዋሪ በቤቱና በግቢው ችግኝ በመትከል ከተማዋ በጋ ላይ ያላትን የአየር ንብረት ምቹ ለማድረግ አስበን እየሠራን ነን። በተለይም የችግኝ ተከላውን ጉዳይ የከተማችን ሕዝብ ባህል አድርጎ እንዲወስደው በትኩረት በመሥራት ላይ እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- ፓርኩ በውስጡ ያካተተው ምን ምን ናቸው? እየተሠራ ያለውስ በምን ያህል በጀት ነው?
ዶክተር ድረስ፡- ፓርኩ አረንጓዴ ቦታ ያለው ነው፤
ዛፎች ተተክለዋል። አምፊ ቲዓትር የምናካሒድበት ቦታ አለው። እስካሁን ድረስ ወጪው ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ ነው። ፓርኩን የሠራነው ሁለት ቦታ ሲሆን፣ አንደኛው 4 ነጥብ 7 ሔክታር አካባቢ ላይ የዋለ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከአንድ ሔክታር በላይ የሚሆን ቦታ የያዘ ነው። በድምሩ ወደ ስድስት ሔክታር የሚጠጋ ነው።
የፓርኩ መገንባት ለአካባቢው ውበት የሚሰጥ ነው። በተለይም ወጣቱ የእረፍት ጊዜውን ማሳለፊያና መዝናኛ ሆኖ ያገለግላል። ከዚህ ጎን ለጎን ማንበቢያም ስፖርት መሥሪያ መሆን የሚችል ነው። ይህ በመሆኑ የፓርኩ መገንባት ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት እንዲኖራት የሚያስችል ነው።
አዲስ ዘመን፡- በጣና ዙሪያ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ሲነገር ቆይቷል፤ ከምን ደረሱ?
ዶክተር ድረስ፡- በጣና ዙሪያ ከተጀመረው ፕሮጀክት የመጀመሪያው ሥራችን ማኅበረሰቡ እየዞረ ጣናን እንዲጎበኝ ብሎም እንዲዝናናበት ለማድረግ አራት ነጥብ ሁለት ኪሎ ሜትር የሚሆን የእግረኛ መንገድ በጌጠኛ ድንጋይ መሥራት ሲሆን፣ እርሱን እየተገበርን እንገኛለን። ከዚህ ውጪ ገበታ ለሀገር በሚል መርህ እየተከናወነ ያለው የጎርጎራ ፕሮጀክት ያህል ስፋት ባይኖረውም ከሱ መለስተኛ የሆነውን ዓይነት ፕሮጀክት እንዲያለማው ለግል ባለሀብት ሰጥተነዋል። ቦታው ቀደም ሲል ግዮን ሆቴል የነበረበት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግንባታው ተጀምሯል፤ ፕሮጀክቱ ራሱን የቻለ መዝናኛ ያለውና የጀልባ ወደብ አገልግሎት የሚሰጥ ነው። ልክ እንደ ጎርጎራ ፕሮጀክት ዓይነት መናፈሻ ቦታ ያሉትም ነው። ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት የሚችል ሆኖ እየተሠራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- በከተማዋ ውስጥ እየተከናወኑ ያሉ የተለያዩ ሥራዎች ለቱሪዝም ዘርፉ ምን አስተዋጽኦ ይኖረዋል ይላሉ?
ዶክተር ድረስ፡- አጠቃላይ በከተማችን የቱሪዝም ፍሰቱን በማሳደጉ በኩል ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። ምክንያቱም ከተማችን ከዚህ በፊት ያልነበራት አሁን ግን ደረጃቸውን የጠበቁ ከውጭ ለሚመጡ ባለሀብቶች እና የሀገር መሪዎችም ጭምር በአግባቡ ማስተናገድ የሚችሉ ግንባታዎችን እየገነባን እንገኛለን። ስለሆነ ባህር ዳር ከተማ ያልነበራትን እያገኘች ትገኛለች ለማለት ያስደፍራል። ይህ ደግሞ የቱሪስት ፍሰቱ እየጨመረ እንዲመጣ ያደርጋል ተብሎ ይታመናል። በቀጣይም የተሻለ እንቅስቃሴ ይኖራል ተብሎ ይታሰባል።
እንደሚታወቀው ባህር ዳር ያለው የቱሪስት ፍሰት ከሌላው ከተማ አኳያ ሲታይ ከፍ ያለ ነው። በእርግጥ ባለፉት ዓመታት በኮቪድ ወረርሽኝ እና በሰሜኑ የሕልውና ዘመቻ ምክንያት ቱሪዝሙ ተፋዝዞ ነበር። ቢሆንም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት መነቃቃት ታይቶበት ቆይቷል።
አዲስ ዘመን፡- በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደከተማዋ ምን ያህል አልሚዎች መጥተዋል? ምንስ የተመቻቸላቸው ነገር አለ?
ዶክተር ድረስ፡– ከዚህ ቀደም ወደ ባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት የሚመጣው በቅስቀሳ ነበር፤ በአሁኑ ወቅት ባህር ዳር ላይ በቅስቀሳ የሚመጣ ሥራ አይደለም። እንደሚታወቀው የኢንዱስትሪ ፓርኮች አምስት ቦታ ላይ አሉ። ያም በመሆኑ በርካታ ባለሀብቶች መጥተዋል፤ እንዲያውም የኢንዱስትሪ ፓርክ ሰጥተን ጨርሰናል። ከዚህም የተነሳ ተጨማሪ አዲሰ ጥናት ላይ እንገኛለን። ለዚሁ ዓላማ ተጨማሪ መሬት እያዘጋጀን እንገኛለን።
ወደከተማችን የሚመጣው እውነተኛ አልሚ መሆኑ ከታወቀና ማሽን ማቅረብ የሚችል ከሆነ እንዲሁም ትክክለኛ የቢዝነስ ማንነቱን ከተረዳን አስፈላጊውን ሁሉ እናሟላለታለን። ቅድሚያ ቦታ እንዲሰጠው እናደርጋለን፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮችም ውስጥ እንዲስተናገድ ይደረጋል። በአገልግሎቱ ዘርፍ ከሆነ ማልማት የሚፈለገው በከተማው ውስጥ ከለየናቸው ቦታዎች በምደባ እንሰጣለን። ለምሳሌ ከተማዋ በዩኔስኮ የትምህርት ከተማ ተብላ የተመዘገበች ናት። በመሆኑም በዚህ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 28 የትምህርት ፕሮጀክቶችን ለይተን እስከ ኮሌጅ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ያለውን ባለሀብቱ ተሰማርቶ እንዲሠራ ሰጥተናል።
በተመሳሳይ በሆቴል ዘርፍ ያለውን ሁኔታ እየገመገምን ነው። ያልተሟሉ ሰነዶች ስላሉ እነርሱን የማጥራት ሥራ በመሥራት ላይ እንገኛለን። በቅርቡ ወደ አስር የሚጠጉ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ባለሀብቶቹ እንዲገነቡ ቦታ የመስጠት ሁኔታ ይኖራል።
የባህር ዳር የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ምንም የሚያስቸግር ነገር አይደለም። ትልቁ ችግር ባህር ዳር ላይ ኢንቨስትመንትን ከማስፋፋት አኳያ የኃይል አቅርቦት ማስፋፋት ላይ እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ማጋጠሙ ነው። እንዲሁም መሬት ከልሎ ቶሎ ከመስጠት አኳያ ካልሆነ በስተቀር ባለሀብቱን አነሳስቶ አምጥቶ ሥራ በማሠራት ረገድ በከተማችን ውስጥ ምንም ችግር የለም ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- የኃይል አቅርቦትና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታት ምን ያህል ርቀት ተጉዛችኋል?
ዶክተር ድረስ፡- ለምሳሌ የመብራት ችግርን ለመፍታት ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ የ‹‹ሰብስቴሽ››ን ግንባታ እንዲገነባ ሥራ እየሠራን ነው። ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ስለፈቀደልን በመሥራት ላይ እንገኛለን። ተጨማሪ መሬት ከልለን በአሁኑ ወቅት እያስጠናንም ነው፤ በመሆኑም የካሳ ክፍያ ሒደትን ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነን።
እኛ ልንፈታው ያልቻልነው የውጭ ምንዛሬ ችግሩን ነው፤ ይህ የፌዴራል መንግሥቱ ጉዳይ ስለሆነ በከተማ አስተዳደሩ የሚፈታ አይደለም። በመሆኑም ጉዳዩ በሒደት የሚታይ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው ከጣና ሐይቅ ዓሣ ይመረታል፤ ይህ የዓሣ ምርት እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር ድረስ፡– የዓሣ ምርትን በተመለከተ የሚከታተለው በኤጀንሲ ደረጃ በመሆኑ ኤጀንሲ ተቋቁሟል። የዓሣ ምርቱ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ፍጆታ ከማሟላት በዘለለ የሚፈለገውን ያህል ገበያው ላይ ትልቅ ተጽእኖ እያሳደረ አይደለም። በተለይ ወቅቱን ያልጠበቀ የዓሣ ማስገር ሥራ ጋር ተያይዞ የዓሣ ምርት የመመናመን ሁኔታ ታይቶበታል። በመሆኑም ጉዳዩን ገምግመን ከዓሣ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤትና ከሚመለከታቸው የክልል አካላት ጋር ከሰኔ እስከ መስከረም ባለው ጊዜ ውስጥ የዓሣ ማስገር ሥራ እንዳይሠራ እየተከታተልን ነው። በእርግጥ ከዚህም በላይ ብዙ መሥራት ይጠይቀናል። ምርቱ እየጨመረ ሳይሆን እየቀነሰ በመምጣቱ ይህንን ሊያሻሽል የሚችል ሥራ መሥራት እንዳለብን ስለተረዳን በትብብር እየሠራን ነው።
ከሰኔ እስከ መስከረም ዓሣ እንዳይሰገር የመከልከሉ ምስጢር በዓሣ ምርቱ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ስላለ ነው፤ ይህ ወቅት የዓሣ የመራቢያ ወቅት ነው። ስለዚህም መታገድ አለበት። ምክንያቱም በመራቢያ ወቅቶቻቸው ዓሣ የምናሰግር ከሆነ እንቁላል የሚጥሉበትና ብዙም ጫጩቶች የሚፈለፈሉበት ወቅት በመሆኑ ብዛታቸውን ለመጨመር የሚያስችል ጊዜ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ጊዜያት የእንቦጭ አረምን ለማጥፋት የተለያዩ ሥራዎች መሠራታቸው የሚታወቅ ነው፤ በአሁኑ ወቅትስ ከተማ አስተዳደሩ ከዚህ ጋር ተያይዞ ምን ሠርቷል?
ዶክተር ድረስ፡- እንደሚታወቀው የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ በርካታ ሥራ ተሠርቷል። እኛም የማጽዳት ሥራ ሠርተናል። ይሁንና አረሙ የመስፋፋት ባህሪ ያለው በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ሊጠፋ አልቻለም። በዚህ ዓመት ግን ያለንን ኃይል ተጠቅመን በከተማችን በኩል ዳር ላይ ያለውን በኅብረተሰብ ተሳትፎ የክልሉ የጣና ሐይቅ እንክብካቤ ጽሕፈት ቤት ጋር ተደራጅተን ለማስተካከል ሞክረናል።
እንደሚታወቀው የጣና ሐይቅ የእንቦጭ አረም ያለው በባህር ዳር ከተማ በኩል ብቻ አይደለም። ሐይቁ ብዙ ዞኖችን የሚያዋስን ነው። ለምሳሌ ማዕከላዊ ጎንደርንና ደቡብ ጎንደርን የሚያካልል ነው። እኛ ደግሞ በከተማው ዳር ያለውን በሙሉ አጽድተነዋል። ሌላውን መረጃ ደግሞ ሌሎች ይኖራቸዋል ብዬ አስባለሁ። በከተማ አስተዳደሩ በኩል ያለውን ግን ሙሉ ለሙሉ አጽድተነዋል ማለት እችላለሁ። የድርሻቸውን እንዲወጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች አስተባብረን መሥራት በመቻላችን ውጤታማ መሆን ችለናል። እንዲያም ሆኖ የመስፋፋት በባህሪ ያለው የአረም ዓይነት በመሆኑ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በሚያስብል መልኩ ማጥፋት ያለመቻሉ ግምት ውስጥ ሊገባ ይገባል። በቀጣይም በትኩረት መሥራትን የሚጠይቅ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በባህር ዳር ከተማ ማኅበራት ቤት ለመሥራት ብዙ ጊዜ ጥያቄ ሲያቀርቡ ይስተዋላል፤ በከተማ አስተዳደሩ በኩል ምን ያህል ጥያቄዎቻቸውን ለመመለስ አቅዳችኋል?
ዶክተር ድረስ፡- የማኅበራትን ጥያቄ በተመለከተ በባህር ዳር ከተማ፣ በመሸንቲ፣ ጢስ ዓባይና ዘጌ ላይ ሳይቶች አሉን፤ በእነዚህ በአራት ሳይቶች ከዚህ በፊት ለበርካታ ዓመታት ተደራጅተው የነበሩትን በሙሉ ሕጋዊ እውቅና ተሰጥቷቸው ሲጠባበቁ የነበሩትን ወደ 21 ሺ የሚጠጉ ዜጎችን ጥያቄ መልሰናል።
ወደኋላ ዘግይቶ የነበረው ባህር ዳር ዘንዘልማ ሳይት ላይ እና መሸንቲ ላይ የሰጠነው ወደ 16 ሺ አካባቢ የሚጠጋ የሰው ኃይል ያለበት ቦታ ነበር። እሱንም የማጣራት ሥራ አጠናቀን በአሁኑ ወቅት የካርታ ዝግጅት እና የግንባታ ፈቃድ የመስጠት ዝግጅት ላይ እንገኛለን። በአሁኑ ወቅት ቦታው ተሰጥቷቸው አለአግባብ ያገኙ ሰዎች ተለይተው እንዲታገዱ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው፤ ችግር የሌለባቸው ደግሞ ነጥረው ወጥተው በቀጣይ የግንባታ ፈቃድ እና የካርታ ሥራ የምንሠራ ይሆናል። እነዚህ ቦታውን ያገኙ ሲሆን፣ በቀጣይ ደግሞ ፈቃድ የሚሰጣቸው ከ470 በላይ ማኅበራት ይሆናሉ።
አዲስ ዘመን፡- ሕገ ወጥ ግንባታ እና ፕላንን ባልጠበቀ መልኩ በሚገነቡ አካላት ላይ ምን ዓይነት አሠራር እየተከተላችሁ ነው?
ዶክተር ድረስ፡- ሕገ ወጥ ግንባታን በተመለከተ ከዚህ ቀደም የተገነባ ቢሆንም በቀጣይ የምናስተካክለው ይሆናል። አሁን ግን ሲገነባ እየተከታተልን እያረምን ነው። በአሁኑ ወቅት የወጣ ስትራክቸራል ፕላን አለ። ከዚያ ውጪ የሚካሄድ ግንባታ የለም። የሚፈቅድም ክፍልም አይኖርም። ደንብን ተላልፎ የሚገነባ ካለ ደግሞ የደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት እየተከታተለ ያፈርሳል። በዚህ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ የማኅበራት ቤትን ጨምሮ ከስድስት ሺ ቤት በላይ ቤቶችን አፍርሰናል።
አዲስ ዘመን፡- በከተማዋ ለምን ያህል ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተቻለ?
ዶክተር ድረስ፡– የሥራ ዕድል ፈጠራን በተመለከተ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ46 ሺ በላይ በቋሚ እና በጊዜያዊ ተፈጥሯል። ይህ ከእቅዳችን አኳያ ሲታይ ከ90 በመቶ በላይ አፈጻጸም ያለው በመሆኑ የተሻለ እንቅስቃሴ መኖሩን አመላካች ነው።
የተፈጠረው የሥራ ዕድል በተለያየ ዘርፍ ነው። ለአብነት ያህል በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍና በአገልግሎት ዘርፍ ነው። ማኑፋክቸሪንጉ የሚያካትተው ብረታ ብረት፣ ጣውላ ሥራ እና ሌሎችንም ነው። በተለይ ከቴክኒክና ሙያ ተመርቀው ወደ ሥራ የሚገቡ ኃይሎች በዚህ ዘርፍ ተጠቃሽ ናቸው።
ለአንድ ዜጋ የሥራ ዕድል ተፈጠረለት ማለት ሠራተኛው ከቤተሰብ ጥገኝነት ወጥቶ የራሱን ኑሮ መምራት ይጀምራል እንደ ማለት ነው። ሠርቶ መዋል ከጀመረ ደግሞ ሀገር የምትጠብቅበትን ግብር መክፈል ቻለ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ከተማዋን በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚጠቅማት ይሆናል።
ይሁንና አሁንም ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፤ አጠቃላይ የሥራ አጡን ምጣኔ ስናሰላው ምንም እንኳ ካለፉት ዓመታት የተሻለ ነው ብለን ብንወስድም በሀገሪቱ ካለው የሥራ አጥ ምጣኔ ጋር ሲተያይ በርካታ የቤት ሥራ የሚቀር መሆኑን የሚያሳይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ በአዲስ አበባ የተለያየ ከተማ ከንቲባዎች ተሰባስበው የልምድ ልውውጥ መካሄዱ ይታወሳል፤ ከእነዚህም መካከል የባህር ዳር ከተማ አንዱ ነውና ከተማው ከየትኞቹ ከተሞች ምን ዓይነት ልምድ መውሰድ ቻለ? ለማስፋፋትስ ምን እየተሠራ ነው?
ዶክተር ድረስ፡- አንደኛ አድርገን የወሰድነው ተሞክሮ በተለይ የቤት ልማት ላይ ከተሞች እንዴት እንደሚሠሩ ነው። ሁለተኛው ደግሞ የከተማ ፕላን አተገባበር እና የከተማ የሥራ አመራር ሥርዓትን የተመለከተ ሲሆን፣ ሦስተኛው ከተማን ‹‹ሪስትራክቸር›› ማድረግ ማለትም መልሶ ማልማትን በተመለከተ ልምድ ቀስመናል። በተለይ መልሶ ማልማትን በተመለከተ ነባሩ ከተማ እየተጨናነቀ እና እየተወሳሰበ ሲመጣ ለነዋሪው የተሻለ የኑሮ ደረጃን ለመፍጠር ግድ ስለሚል አዲስ የአስተዳደር ከተማ እየፈጠሩ እንደሆነ ልምድ መቅሰም ችለናል። በመሆኑም ዓለም ከደረሰበት የከተማ እድገት ደረጃ ጋር በተመጣጠነ መንገድ ከተማን በአዲስ መገንባት እንደሚቻል አይተናል። ይህንን ለመገንባት ደግሞ ከመንግሥት ውጪ ከሕዝብ የግል አጋርነት (Public-private partnerships) እንዲሁም ለጋሾችና ባለድርሻ አካላትን አቀናጅቶ እንዴት የተሻለ ከተማ መፍጠር እንደሚቻል ተሞክሮ ወስደናል።እኛ አዲስ ስትራክቸራል ፕላን ያጸደቅነው ባለፈው ዓመት ነው።
ይህ ፕላን ሳይሸራረፍ እንዲተገበር ማድረግ ወሳኝ ነው። ከተማን በመልሶ ማልማት ወቅት የሚነሱ ሰዎች ሳይፈናቀሉ እንዲለማ ማድረግ ተገቢነት ያለው ሥራ ነው። ከዚህ በኋላ ከተማውን በምናሰፋበት ወቅት ታሳቢ ማድረግ ያለብን ለምሳሌ የመንገድ ሽፋን በተመለከተ፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ ከውሃ እና ኤሌክትሪክ ኢንስታሌሽን ጋር ተያይዞ አስቀድመን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባን ሰፋ አድርጎ ማየት እና ማቀድ እንደሚገባን አስተውለናል። ሁሌም በጀት ላይ የምንንተራንስ ስለሆንን ከበጀት ወጣ ባለ መልኩ ሥራውን አስፍቶ ማሰብና ተጀምሮ በደረሰበት ቦታ ሥርዓት እንዲፈጠር ለማድረግ ሰፋ ያሉ ነገሮችን በጥልቀት የመመልከት ባህል እንዲዳብር ለማድረግ ሥራ እየሠራን ነው። ስትራክቸር ፕላን ማለት የከተማው መዋቅራዊ ፕላን ማለት ነው። መዋቅራዊ ፕላን ማለት ደግሞ አንድ ከተማ እንዴት እንደሚመራ መሬቱን ከፋፍሎ የሚያሳይ ነው። ለምሳሌ አረንጓዴ ቦታው የት ይሁን እያለ የመሬት አጠቃቀምን የሚወስን ነው።
ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ፕሮጀክቶችንም እያቀድን ነው። በተለይ ስማርት ሲቲን ከመፍጠር አኳያ እንቅስቃሴዎችን ለመጀመር እየተዘጋጀን እንገኛለን። እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጡን ከማዘመን እና ከሙስና የጸዳ በማድረግ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት እንዲነግስ ለማድረግ የቀሰምነው ልምድ አለ። በተለይ የዲጂታል አገልግሎትን በሰፊው ማሰብ እንደሚገባ ትልቅ ልምድ ወስደናል። ይህን ወደእኛ ከተማ አምጥተን ለመተግበር አቅደናል።
ከባህር ዳር ከተማ ሊወሰድ የሚችል ምርጥ ተሞክሮ ብለን የምንወስደው ደግሞ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እና የመሠረተ ልማት ማኔጅመንትን ነው። አሁን የጀመርነው የአረንጓዴ ቦታ ሥራና ቱሪዝምን ለማስፋፋት የምንከተለው ስልት እንደተሞክሮ ሊወሰድ የሚችል እንቅስቃሴ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በጣም አመሰግናለሁ።
ዶክተር ድረስ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11/2015