ከእውቀትም፣ ከጥናትም የራቁ የመመረቂያ ጽሑፎች

 በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት መሥራት የሚያስችሉ ተግባራት ከተጀመሩ ሰነባብቷል። ለዚህ ማሳያነትም ለአምስት አመታት ጥናት በተደረገበት ፖሊሲ ተደፍፎ ተግባራዊ የተደረገው አዲሱ የትምህርት ሥርዓት በዋነኛነት ይጠቀሳል። አሁን ባለው እውነታ አዲሱን የትምህርት ሥርዓት ፖሊሲ ወደ ትግበራ በማስገባት ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት እየተሠራ ይገኛል።

በዚህ የትምህርት ሥርዓት ትግበራ ላይም ግብረ ገብነት፤ ሀገር በቀል እውቀትና ሙያ፣ የቀለም ትምህርትና ቴክኖሎጂ፤ ምርትና ተግባር እንዲሁም ጥናትና ምርምር ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።

በትምህርት ሥርዓቱ ብቃት ያላቸውና በዓለምአቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ምሩቃንን ለማፍራት በሚደረገው ጉዞም፤ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናዎች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር በማድረግ በአዲስ መልክ ፈተናው እንዲሰጥ ማድረግ የመጀመሪያውና ዋነኛው ተግባር ሆኗል።

ከዚህ በተጓዳኝ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ማወቅ የሚገባቸውን እውቀት የቀሰሙ ስለመሆናቸው ለማረጋገጥ ይረዳ ዘንድ በያዝነው ዓመት የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ተዘጋጅቶ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል። በዩኒቨርሲቲዎች ቆይታቸው ያወቁትን እንዲተገብሩ የሚጠበቀው ምሩቃንን ቦታ በሃሰተኛ ማስረጃ ታግዘው ቀድመው የያዙ እና በሥራ ከባቢው ላይ አሉታዊ ገጽ እየሳሉ ያሉ ግለሰቦችን ለይቶ ከማውጣት አኳያም የትምህርት ማስረጃን የማጥራት ሥራዎች እየተከወነ ነው።

በዚህ ረገድ ከትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን የተቋማት ቁጥጥር ኢንስፔክሽን ክፍል የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ የትምህርት ማስረጃ የቁጥጥርና የማረጋገጥ ሥራ ከተሠራባቸው 22 ሺህ የትምህርት ማስረጃዎች መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት ሀሰተኛ መሆናቸው ተረጋግጧል።

የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቸሩጌታ ገነነ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት ቃለ ምልልስ መመልከት እንደተቻለው፤ እነኝህ የትምህርት ሥርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ የሚደረጉ ጉዞዎች አበረታችና ውጤታማ የሚባሉ ናቸው።

ወደ ዋናው ጉዳዬ ስመለስ፣ በየአመቱ በርካታ ተመራቂ ተማሪዎች ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው ይወጣሉ። እነዚህ ምሩቃን ታዲያ ተመርቀው ከየትምህርት ተቋሞቻቸው ከመውጣታቸው አስቀድሞ፣ በተማሩበት የትምህርት መስክ የመመረቂያ ጥናታዊ ጽሑፍ እንዲያዘጋጁ ይደረጋል። የዛሬ ጽሑፌ ትኩረትም በዚህ ላይ ያተኮረ ይሆናል።

ምክንያቱም እነዚህ የመመረቂያ ጽሑፎች እንደ ፈተናና መሰል ጉዳዮች ሁሉ የኩረጃ እና ቅጂ የተሞሉ ስለመሆናቸው፤ አንዳንዴም ተመራቂዎች ከመመረቂያ ጥናታዊ ጽሑፋቸው ጋር ሳይተዋወቁ በሌሎች ተሠርተው የሚቀርቡላቸው ስለመሆኑ በተለያየ መልኩ ሲገለጽ መስማት የተለመደ ሆኗል። በአግባቡ ተሠርተዋል የሚባሉትም ቢሆኑ ከሼልፍ ወርደው ለውጤት ሲበቁ አይታይም። በመሆኑም እንደ ሌሎቹ የትምህርት ጥራት ማሻሻያዎች ሥራዎች ሁሉ በእነዚህ ጥናታዊ ጽሑፎች ጥራትና ይዘት ላይ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል የሚል እምነት አለኝ።

ይሄን ለማለት ያስደፈረኝ፣ አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ የመመረቂያ ጥናታዊ ጽሑፎች ተግባራዊ የመሆናቸውን እውነታ ጨምሮ የጥራትና ደረጃቸው ጉዳይ እምብዛም ትኩረት የሚሰጠው አይደለም። ምርምርና ጥናቶቹ ሲካሄዱ በርካታ የሰው ኃይል፣ ዕውቀት፣ ጊዜ ገንዘብ ፈሶባቸው ነው። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ግን ጥናቶቹን በተለፋባቸው ልክ ወደ ትግበራ የማስገባቱ ሂደት ትኩረት ተሰጥቶት የሚከናወን አይደለም።

ሊታሰብ የሚገባው ጉዳይ በተለያዩ ጊዜያት በተመራቂ ተማሪዎች አማካኝነት የሚደረጉ ጥናቶች ትምህርቱን ለማጠናቀቅና ለመመረቅ ሲባል ብቻ የሚካሄዱ አለመሆኑ ነው። ይልቁንም በአቅራቢያቸው በሚገኝ ማኅበረሰብ ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ መሠረታዊ ጉዳዮችን በመቃኘትና የጥናት ርእሶችን በማዘጋጀት በውይይትና በጥልቅ ሃሳብ የዳበረ ጠንካራ ጥናት ሊካሄድ ግድ ይላል። ለዚህ ደግሞ የተማሪዎቹና የጥናታዊ ጽሑፉ አማካሪዎቻቸው ሚና የላቀ መሆን ይኖርበታል።

የሚሠራው ጥናትም ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ካዳበሩት ዕውቀትና ሲማሯቸው ከቆዩት የትምህርት ዓይነቶች ጋር በማቀናጀት መፍትሄ ሊሆን የሚችል ሃሳቦችን ማመንጨት አለበት። ከዚሁ ጋር ተያይዞም የጥናት ውጤቱ ለሌሎች ተሞክሮ የሚሆን፣ እንደምሳሌ የሚጠቀስና ለተጨማሪ የምርምር ሥራዎች የሚያነሳሳ ሊሆን ይገባል።

የዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች በተለያዩ ዓመታት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ጥናታዊ ጽሑፎችን ያዘጋጃሉ። እነዚህ ጥናታዊ ጽሑፎች ከመዘጋጀታቸው አስቀድሞ በቂ ጥናት የተደረገባቸው፣ ተደጋግመው ያልተሠሩ፣ ከሌሎች ጥናቶች ያልተቀዱና በቀጥታ ያልተወረሱ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል።

በተለምዶ እንደሚታወቀው ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሑፎቻቸውን ፈጽሞ አያውቋቸውም። በጥናቱ ስለሚካተቱ ይዘቶችና መሠረታዊ ጉዳዮችም ትኩረት የሚሰጡ አይደሉም። እንዲህ ዓይነቶቹ ተማሪዎች ጥናቱን በገንዘብ የሚያሠሩ በመሆናቸው አንዳች ዕውቀትን ሳይጨብጡ ተመራቂ በመሆን ይጨርሳሉ ።

አሁን ባለንበት ዘመን የመመረቂያ ጽሑፍን በገንዘብ ክፍያ አሠርቶ የማጠናቀቅ ሂደት ብርቅ የሚባል አይደለም። ይህን እውነታ በተጨባጭ የሚያመላክቱ ሕገወጥ ተግባራትም በግልጽ እንደሚካሄዱ ይታወቃል። ምክንያቱም ዛሬ ላይ በሀገራችን በየመብራትና ስልክ ምሰሶዎች ከሚለጠፉ «የመመረቂያ ጽሑፍ እናማክራለን» ማስታወቂያዎች ባሻገር፤ የተማሪውን ዕውቀት እንተካለን የሚሉ፣ የአንዱን ጥናት ከአንዱ በመንጠቅ በአደባባይ የሚሸቅጡ በርካታ ድህረ ገጾች ይፋ ሆነዋል።

በዘመናችን የተማሪዎችን የመመረቂያ ጽሑፎች እናማክራለን በሚል የሽፋን ገጽ የመመረቂያ ጽሑፎችን የሚሠሩ ነጋዴዎች ድርጊቱን ለመፈጸማቸው የሚሳቀቁ አይመስሉም። ይህ ዓይነቱ ልማድም ዕወቀትን በገንዘብ በሚለውጡ ተማሪዎች ዘንድ ያለው ትርጓሜ ከተለመደው ዓይነት የቢዝነስ ሂደት የሚዘል አልሆነም። እንዲህ ዓይነቶቹ ሕገወጥ ተግባራት እየተስፋፉ ቢሆንም ከሚመለከታቸው አካላት ሕጋዊ ርምጃ ያለመወሰዱ እውነታ ጉዳዩ ሕጋዊ እስኪመስል አጠናክሮታል። እንዲህ መሆኑ ደግሞ ዕውቀት በገንዘብ እንዲሸቀጥ፣ ጥራት ያለው ጥናት እንዳይኖርና ሕገወጥ የሚባል ተለምዷዊ አሠራር እንዲበራከት በር ከፍቷል ።

ይህ ዓይነቱ ሕገወጥ ድርጊት በየዘርፉ ለሚዘጋጀው የሀሰተኛ ትምህርት ማስረጃ መስፋፋት ምልክት ነው። በቀላሉ እየተሠራ ለሚመለከታቸው ጠያቂዎች በገንዘብ የሚሸቀጠው የትምህርት ማስረጃ፣ በርካቶችን ከማይመጥናቸው የከፍታ ማማ አውጥቷል። በዚህ የተረማመዱ ሕገወጦች ጫፍ በመድረሳቸው ምክንያትም በአግባቡ ተምረው የተመረቁ ወገኖች የሥራ ዕድል ተጣቧል። ሥራ አጥነት በጉልህ እንዲስፋፋም ምክንያት ሆኗል።

በዕውቀት ያልተሟሸ፣ በምርምር ያልተደገፈ ጥናት ደግሞ ውጤቱ ውሸትና ኪሳራ ነው። ይህ ደግሞ ለማንነት የማይጠቅም፣ ለሀገርና ወገን የማይበጅ አሳፋሪ ምግባር ነው። እናም ድርጊቱ ከወዲሁ ልጓም ካልተበጀለት በዕውቀት ያልተመሠረተ፣ በጥናት ያልተደገፈ ባዶ ወረቀትን የማስፋፋት ሂደቱን እያላቀው እንደሚቀጥል አያጠራጥርም።

ጥራታቸው በአግባቡ የተረጋገጠና ደረጃቸውን ጠብቀው የተካሄዱ ጥናቶች ለሌሎች የመረጃ ምንጭ ይሆናሉ። መሠረታቸው የጠነከረ፣ ሀቀኝነት ያለባቸው ሥራዎችም ለትውልድ የሚተላለፉበት አጋጣሚ የሰፋ ይሆናል። እንዲህ ሲሆን ደግሞ ዕውቀት በከንቱ አይባክንም፤ ወገን በግልጽ አይከስርም፤ ሀገርም ከተማረው ትውልዷ የምትጠብቀውን ፍሬ በወጉ ታፍሳለች። እናም ይህ እንዲሆን የመመረቂያ ጽሑፍ የተበላሸ መንገድ ፈር እንዲይዝ ማድረግ ለነገ ሳይሆን ለዛሬ የተገባ ሥራ ነው።

 መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 11/2015

Recommended For You