እንደ ምርታማነቱ የገበያ ትስስሩም ትኩረት ይፈልጋል

ለውጥ ከቆየ አስተሳሰብና አስተሳሰቡ ከወለደው ሥርዓት ፈጥኖ ወጥቶ አዲስ አስተሳሰብን በማህበረሰብ ውስጥ የማስረጽ ሂደት ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ የተለያዩ ተግዳሮቶች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ይጠበቃል።አንዳንዴም ሁኔታዎች ወዳልተፈለገ መንገድ አምርተው ያልተገባ ዋጋ ሊያስከፍሉ የሚችሉበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡

በሀገራችንም ለውጥን ተከትሎ በተከሰተው አለመረጋጋትና በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተካሂዶ በነበረው ጦርነት ምክንያት በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ቀውስ አስከትሏል።በሰው ሕይወት ላይም ጉዳት ደርሷል። ችግሩ በሀገሪቱ በተጀመረው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይም ከፍተኛ ጫና አሳድሯል። በሀገር ገጽታ ላይም አሉታዊ ተጽእኖ አሳርፏል። ይህ ሁሉ ፈተና ለውጥን ተከትሎ የመጣ ነው፡፡

ሀገሪቱ በውስጥም በውጭም የገጠሟትን ፈተናዎች ተከትሎ፣ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የተፈጠረው ችግር በዜጎች የእለት ተእለት የኑሮ እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ ጫና አሳድሯል።በራስ ወዳዶች ዘዋሪነትም የንግድ ልውውጥን ፣ ምርትና ምርታማነትን ለማዳከም በተካሄደው ርቀትም ሀገርን ብዙ ዋጋ ያስከፈለ ነው።

በውስጥ የገጠማትን አለመረጋጋት ተከትሎም ፊታቸውን ያዞሩባት ወዳጅ ሀገሮችም የእርዳታና የድጋፍ ማእቀብ በማድረግ የበለጠ መከራዋ እንዲበዛ አድርገዋል።በሀገር ውስጥም አጋጣሚውን ተጠቅመው የንግድ ልውውጥ እንቅስቃሴን በመግታት ጫና ለመፍጠር የተንቀሳቀሱ ኃይሎች ያሳደሩት ተጽእኖ ቀላል አይደለም፡፡

ጫናዎቹን ተቋቁሞ ለማለፍ መንግሥት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ትግበራ ነው።መርሀ ግብሩ በኢኮኖሚው ውስጥ ዘርፈብዙ ጥቅሞች ያሉት መሆኑ በተለያየ መንገድ የተገለጸ፤ በተግባርም በተጨባጭ እየታየ ያለ ነው፡፡

መርሀ ግብሩ ዓለም አቀፍ ስጋት እየሆነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል፤ ከዚህም ባለፈ ፣ የተራቆተና የተጎዳ መሬት መልሶ እንዲያገግም በማድረግ ለግብርናው ዘርፍ ጠቀሜታው ብዙ ነው።ለኢትዮጵያ አረንጓዴው ወርቅ እየተባለ ለሚነገርለት የቡና ተክልም ጥላ ሆኖ በማገልገል፣ ለቤት ውስጥና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉትን የደን ውጤቶች በሀገር ውስጥ ለመተካትና ለሌሎችም ጥቅሞች ለማዋል አበርክቶው ሰፊ ነው፡፡

ከአራት አመት በፊት የተጀመረው የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ሳይቋረጥ ለተከታታይ አራት አመታት በመከናወን ላይ በሚገኝ በዚህ ወቅት በሁለተኛው ምዕራፍ የፍራፍሬና አትክልት ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ተጠናክሯል።መርሀ ግብሩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ልማቶች በማከናወን የህዝቡ ኑሮ እንዲሻሻል፣ ብሎም ሀገራዊ ምጣኔ ሀብትን ከማሳደግ ጎን ለጎን በሥርዓተ ምግብ ላይም ለውጥ እንዲመጣ የሚያስችል እንደሆነ በዘርፉ ባለሙያዎች ተደጋግሞ የተነገረ ጉዳይ ነው፡፡

እኔም ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቅት ላይ በምትገኘው ሞጆ ከተማ ዙሪያ ላይ ለሰብል ልማት ይጠቀሙበት የነበረውን መሬታቸውን ለአቮካዶ ተክልና ለአትክልት ልማት በማዋል ሲያደርጉ የነበረውን እንቅስቃሴ የማየት እድሉን አግኝቻለሁ።አርሶአደሮቹ እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የማንም ግፊት አላስፈለጋቸውም። ጥቅሙንና አስፈላጊነቱን በተለያየ መንገድ ያገኙት መረጃ ወደ ልማቱ እንዲገቡ እንዳስቻላቸው ነው በስፍራው በነበርኩበት ወቅት የተገነዘብኩት፡፡

ቀድመው ወደ አቮካዶ አትክልት ልማት የገቡ የአካባቢው አርሶ አደሮች ከፍሬው ተቋዳሽ መሆን መጀመራቸው ደግሞ ለአካባቢያቸው አርአያ መሆን ችለዋል።አዲስ የጀመሩትም እንደቀደሙት ተጠቃሚ ለመሆን የነበራቸው ፍላጎት ከፍተኛ እንደሆነ ነበር ከገጽታቸው መረዳት የቻልኩት።የአርሶአደሮቹ የልማት እንቅስቃሴ ፍላጎት ሌላው ማሳያ በኩታገጠም የግብርና ዘዴ አትክልትና ፍራፍሬ ለማልማት ዝግጁ ሆነው ወደ ሥራው መግባታቸው ነው፡፡

ኩታገጠም የግብርና ዘዴ ለልማቱ የሚያስፈልገውን የውሃና የተለያየ ግብአትን በጋራ ለማቅረብ፣ ምርት ከደረሰ በኋላም ገበያ በጋራ ለማፈላለግና ለላኪዎችም ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በማገዝ የተለያየ ጥቅም እንዳለው አምነውበት የገቡበት ሥራ እንደሆነም በቆይታዬ ተረድቻለሁ፡፡

በዘመቻ እየተከናወነ ያለው አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በተናጠልም በጋራም ንቅናቄ በመፍጠር ድርሻ አበርክቷል።ምርታማነትን ለማሳደግ የሚለውን ግብ ለማሳካት የማህበረሰብ ተነሳሽነት ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል።በዚህ ምልከታዬ ያልታየና ሊተኮርበት ይገባል የምለው አለ።ይሄም አንደኛው በጥራት ማምረት ሲሆን፤ ሌላው የውጭ ገበያ ዕድልን በማስፋት የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ መሰራት እንዳለበት ነው፡፡

አልሚዎች የሚያነሱትም ሆነ እውነታውም የሚያሳየው ጥራት ላይ ያለው ጥርጣሬ የውጭ ገበያው ላይ ተግዳሮት እየፈጠረ ነው። ከአልሚዎች መረዳት እንደቻልኩት በአሁኑ ጊዜ ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው ዋጋ ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚቀርበው የተሻለ ገበያ እያስገኘ ነው፡፡በዚህም ለውጭ ገበያ ከማቅረብ ይልቅ ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረቡ ተመራጭ እየሆነ ነው፡፡አቅርቦቱ በሀገር ውስጥ መሆኑ ሸማቹ በመጠንም በዋጋም ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችለዋል፡፡ይህም መንግሥት በኢኮኖ ሚውም ሆነ በሥርዓተ ምግብ መሻሻል ለውጥ ለማምጣት የያዘውን እቅድ ለማሳካት የሚያግዝ በመሆኑ ይበረታታል፡፡

በመግቢያዬ ላይ እንዳነሳሁት የሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት መሠረት ያደረገው በግብርናው ዘርፍ ላይ በመሆኑ የግብርና ውጤቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ ደግሞ ሌላው ተልእኮ በመሆኑ በዚህ ረገድም ሊፈተሽ ይገባል።በአምራቹ በኩል ለውጭ ገበያ ለመላክ ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ቢሆንም የዋጋው ማነስ ፍላጎቱን እየቀነሰ ነው።የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ያለው አበርክቶም እንደሚጠበቀው እየሆነ አይደለም፡፡ለዚህ ደግሞ ክፍተቱ ጥራት ላይ አተኩሮ መሰራት ይኖርበታል፡፡

የግብርና ውጤቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች የጥራት ጉዳይን ብቻ ሳይሆን በአምራቹ በኩል በብዛት አምርቶ በተመጣጣኝ ዋጋ በመሸጥ ከመጠቀም ጥቂት አምርቶ በውድ ዋጋ በመሸጥ ትርፍ ለማግኘት ያለው ፍላጎት ከፍተኛ እንደሆነ ይስተዋላል።ላኪው በውድ ዋጋ ገዝቶ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ተግዳሮት እየገጠመው እንደሆነም እያነሳ ነው።

ይሄም ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚሰራው ሁሉ፣ ምርቱ ገበያ እንዲያገኝ ማድረጉ ላይም መስራት እንደሚገባ አመላካች ነው።በመሆኑም ከምርታማነት ጎን ለጎን ለገበያ ትስስር ትኩረት ተሰጥቶ መስራት ለነገ የሚባል አይሆንም፡፡

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 10/2015

Recommended For You