የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሀገሩ ዳር ድንበር የሚዋደቅ፤ ከራሱ በፊት ሀገሩን የሚያስቀድም፤ ቅኝ ገዢዎችንና ሌሎች ወራሪ ኃይላትን አሳፍሮ የሚመልስ ጀግና ሕዝብ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ሀገራት ነጻነትና እኩልነት የሚታገሉ፤ በአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት የሆኑ ኩሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡
ይህም ጀግንነትና አይበገሬነት በተባበሩት መንግሥታት የግዳጅ ተልዕኮ ጭምር በመከላከያ ሠራዊቱ በኩል የተገለጠ፤ ለዚህም እውቅና ያገኘበት ነው፡፡ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን በሩዋንዳ፤ በቡርንዲ፤ በላይቤሪያና በሶማሊያ ተሰማርቶ ጀግንነቱን አስመስክሯል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጀግንነቱን ያህል ሰላም ወዳድም ነው፡፡ በየትም ሥፍራ ቢኖር፣ የትኛውንም እምነት ቢከተል፣ በተለያዩ ቋንቋዎች ቢገለገል፣ ባህሎቹና ልማዶቹ ቢለያዩም ለሰላምና አብሮነት ሰፊ ቦታን ይሰጣል፡፡ ሰላም የእሴቶቹ አንዱ አእማድና መገለጫ ነው፡፡
ሆኖም ከዚህ የኢትዮጵያውያን ባህል ባፈነገጠ መልኩ ፍላጎታቸውን በነፍጥ ማሳካት የሚፈልጉ ቡድኖች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ከውይይት ይልቅ ነፍጥ ማንሳት የሚቀናቸውና ሰላም ወዳዱን ሕዝብ የሚረብሹ፤ አብሮነቱን የሚያውኩ፤ የኢትዮጵያን መረጋጋትና ሉዓላዊነት የሚገዳደሩ ቡድኖች እዚህም እዚያም አቆጥቁጠዋል፡፡
እነዚህ ወገኖች ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በሚፈጥሩት ሁከትና ብጥብጥም ልማት ተደናቅፏል፤ የሰዎች ወጥቶ መግባት ተስተጓጉሏል፤ አለፍ ሲልም የሀገር ህልውናም አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ ሆኖም ጀግናም፣ የሰላም ዘብም የሆነው ሕዝብ እና ሕዝባዊነቱ ጥያቄ ውስጥ የማይገባው የመከላከያ ኃይሉ ችግሮቹን ፈር እያስያዘ ሕዝብን ሰላም ሀገርንም አንድ አድርጎ ዘልቋል፡፡
ሆኖም ሕዝብ ሳይሾማቸው ለሕዝብ ቆመናል የሚሉ ቡድኖችና ፖለቲከኞች ችግርን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ነውጠኛ ደጋፊዎችን የማሰባሰብ ሴራ ውስጥ ስለሚገቡ፣ በኢትዮጵያ እዚህም እዚያም ግጭቶች በርክተው ይታያሉ፡፡ እነዚሁ ኃይሎች ኃላፊነት የጎደላቸው ስለሆኑም ግጭትና መገዳደልን ጨምሮ የሀገርን ተስፋ የሚያጨልሙ ድርጊቶች እንዲበራከቱ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ ከማሰብ ይልቅ ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነት ስለተጠናወታቸውም ቆመንለታል ያሉትን ሕዝብ ሳይቀር በቁሙ ሲዘርፉ ተስተውለዋል፡፡
እነዚህ የግጭት ነጋዴዎች ከመተማመን ይልቅ ጥርጣሬ፣ ከትብብር ይልቅ መገፋፋት፣ በግልጽ ከመነጋገር ይልቅ መተማማት ስለሚቀናቸው የማህበራዊ ሚዲያዎች እና ለእነርሱ ዓላማ የተመቹ ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ሕዝቡን አላስፈላጊ ወደሆነ ጥርጣሬ ውስጥ በመክተት አንዴ በብሔር ሌላ ጊዜ በሃይማኖት እየከፋፈሉ የዘመናት አብሮነቱን ሊነጥቁት ሲሯሯጡ ይታያሉ፡፡ በእነዚህ ስግብግቦች የተነሳም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከባድ ጊዜን ለማሳለፍ ተገድዷል፡፡ እያሳለፈም ይገኛል፡፡
እነዚህ ቡድኖች ከዚህ ድርጊታቸው የሚያስቆማቸው የጸጥታ ኃይል ሲመጣ ደግሞ ግበረ አበሮቻቸውን ሰብስበው ስም የማጥፋት ዘመቻ ውስጥ ይገባሉ፡፡ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ለብሶ ታላላቅ ድሎችን የተጎናፀፈውን ጀግና የመከላከያ ሠራዊታችንን በማጠልሸትም ኢትዮጵያን ለማሳነስ በቀቢጸ ተስፋ ሲሯሯጡ ታይተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡ እጅግ ሰላማዊና ለሕግ መከበር ትልቅ ትኩረት ስለሚሰጥ ለአመፅና ለብጥብጥ ሥፍራ የለውም እንጂ፤ የእነዚህ አካላት ድርጊት ሀገርን የማፍረስ አላማ ጭምር ያለው ነው፡፡ ስለዚህም ሀገር በሰላም ውላ እንድታድርና እድገትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ እነዚህን የሰላም ጸሮች በጋራ መመከት ይገባል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎንም ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልም እንደ ሀገር ሊጎለብት ይገባል፡፡ የስልጣኔም አንዱ መለኪያም ይኸው ነው፡፡ በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ውስጥም ሆነ በሌሎች መስኮች የተሰማሩ ወገኖች፣ ከነፍጥ ይልቅ ለውይይት ቅድሚያ መስጠት አለባቸው፡፡
ኢትዮጵያ ከፊቷ የተጋረጡ በርካታ ችግሮች ያሉባት ሀገር ናት፡፡ የሀገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ጊዜ መስጠት አለባቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት አለ፡፡ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከተካሄደው ጦርነት አላገገምንም፤ ሥራ አጥነት አሁንም አሳሳቢ ነው፤ አሁንም ከድህነት ያልወጣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ አለ፤ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ድርቅ ደጋግሞ እያጠቃን ነው ፡፡
ስለዚህም እነዚህን ችግሮች ለመሻገርና የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሰላም ወሳኝ ነው፡፡ ሰላም ለማምጣት ደግሞ በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመሣሪያ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ቁጭ ብሎ የመነጋገር እና የመወያየት ባህል ማዳበር ይገባል፡፡ ከውይይት ይልቅ ፍላጎታቸውን በመሣሪያ ለማስፈጸም የሚከጅሉ ቡድኖችንም ሕዝቡ ዕውቅና ሊነፍጋቸው ይገባል፡፡ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ቅድሚያ የሚሰጥ ትውልድ፤ እንደ ሕዝብም ይሄንኑ ባህል ማድረግ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ነሐሴ 10/2015