«የብሔራዊ መታወቂያ ከሕዳሴ ግድቡ ቀጥሎ ትልቅ ብሔራዊ ፕሮጀክት ነው» -አቶ ሔኖክ ጥላሁን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የምዝገባ ዳይሬክተር

የብሔራዊ መታወቂያ ሰሞነኛ አጀንዳ ነው፡፡ ነገር ግን በመታወቂያው ምንነትና አስፈላጊነት ላይ ግልፅነት ባለመፈጠሩ በአንዳንዶች በኩል መነጋገሪያ እየሆነ ነው፡፡ እኛም ይህንኑ መነሻ በማድረግ የብሔራዊ መታወቂያ ፋይዳውን፣ ከዚህ ቀደም በየመኖሪያ አድራሻ ይሰጥ ከነበረው መታወቂያ የሚለይበትን፣ እንዲሁም ብሔራዊ መታወቂያን ተደራሽ በማድረግ ረገድ ስለተሰራው ሥራ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የምዝገባ ዳይሬክተር ከአቶ ሔኖክ ጥላሁን ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው ለንባብ አብቅተናል፡፡

 አዲስ ዘመን፡- እስኪ በቅድሚያ ብሔራዊ መታወቂያ መገለጫው ምን እንደሆነና ፋይዳውን ቢገልጹልኝ?

አቶ ሔኖክ፡-ብሔራዊ መታወቂያ ዲጂታላይዜሽን ላይ ቁልፍ ሚና የሚጫወት እጅግ ትልቅ ለውጥ ያመጣ የዲጂታል የማንነት መለያ ነው፡፡ ሀገራዊ ፋይዳውም ትልቅ እንደሆነ የታመነበት በመሆኑ ፕሮግራሙን ለመተግበር ሠፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ካለፈው አንድ ዓመት ጀምሮ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ሥር ከመደራጀቱ በፊት፤ በተለያዩ ተቋማት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ሥር ሆኖ ሲሠራ ቆይቷል፡፡አሁን አስፈላጊነቱና አወንታዊ ተፅዕኖ በደንብ የተለየ በመሆኑ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ሥር ቢደራጅ የተሻለ ውጤት እንደሚያመጣ ታምኖ በዛው ሥር እንዲቋቋም ሆኗል፡፡በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ሥር በመቋቋሙ በሁሉም ዘርፍ ላይ ለመተግበር አመቺ ይሆ ተገኝቷል፡፡

ፕሮግራሙ ኢትዮጵያውያን እና ሕጋዊ ሆነው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎችንም ያካትታል። ፕሮግራሙ አገልግሎትን ለማቀላጠፍና ሁሉንም በእኩል ለማስተናገድ ያስችላል፡፡ ፕሮግራሙ አካታች በመሆኑ ማንም ቢሆን በሥርዓቱ ውስጥ የመግባት መብት አለው፡፡ እኛም በተለያየ ዕድሜ ላለ ማንኛውንም ሰው የማስተናገድ፤ ሁሉንም የማካተት ግዴታ አለብን፡፡

የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ምንድን ነው? ከተባለ ነዋሪዎችን ለመለየት የሚያስችል ነው፡፡ ፕሮግራሙም በዋናነት የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት አገልግሎትን ለማቀላጠፍ የሚያግዝ፣ ልዩነት ሳይፈጥር የግለሰቦችን ማንነት ማረጋገጥ የሚያስችል ነው፡፡ ይህንን የምናደርግበት ሁለት መሠረታዊ ባዮግራፊ እና ዲሞግራፊ የሚባሉ የሥነሕዝብ መረጃዎች አሉ፡፡ እነኚህም በጣም ውስን ናቸው፡፡ ሙሉ ስም፣ ፆታ፣ ዕድሜ እና አሁን ያለ ወይም ዓመታዊ የመኖሪያ አድራሻን የያዘ ነው፡፡ዜግነትንም ይጠቅሳል፡፡ እነኚህን አራት ወይም አምስት ዋና ዋና መረጃዎችን ብቻ እንሰበስባለን፡፡

መረጃዎችን የመሰብሰብ ሥርዓት በመላው ዓለም በብዙ ሀገራት ተተግብሯል፡፡ ተግብረውት ትልቅ ውጤት ያገኙ ሀገራት የመኖራቸውን ያህል ያልተሳካላቸውም አሉ፡፡ እኛ ደግሞ አርፍደን ወደ ሥራው ብንገባም ብዙ የምንማርባቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ትምህርት የምንወስደው ከተሳካላቸው ብቻ ሳይሆን ካልተሳካላቸውም ጭምር ነው።

መረጃ ሲበዛ ለሰዎችም ምቾት አይሰጥም፤ መረጃውም በትክክል የተጣራ አይሆንም፡፡ በመታወቂያ ትምህርት ደግሞ የመረጃ ውስንነት የሚባል ትልቅ መመሪያ አለ፡፡ ለሥራው የሚያስፈልጉ ውስን መረጃን ብቻ መሰብሰብ ውጤታማነትን ይጨምራል፡፡ የመረጃ ቁጥር ማነስ በጣም አስፈላጊ የሆነ የመለያ መታወቂያ መርህ ነው፡፡ በዚህ ላይ ተሞክሮ ወስደናል፡፡ ሌሎች አስራ ሰባት መረጃዎችን ሰብስበው የጀመሩ ሀገራት አሉ፡፡ ነገር ግን ይህን ተግባራዊ እናድርግ ብንል፤ መረጃ በትክክል የሚሰጥ ሰው ቁጥር ውስን ነው፡፡

መረጃውን መሰብሰብም ረዥም ጊዜ ይወስዳል፡፡ ይሄ ደግሞ በፕሮግራሙ ውጤታማነት ላይ ተጽእኖ ያሳድራል። በዚህም በውስን መረጃ ብሔራዊ መታወቂያው እየተዘጋጀ ነው፡፡ ሥራው እየተሠራ ያለው በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ሕጎችን እና ሥርዓቶችን እንዲሁም አሁን ላይ ያሉትን ፍላጎቶችና ዓለም አቀፍ ተሞክሮን መሠረት በማድረግ ነው።

አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ወደ ዲጂታላይዜሽን እና ግሎባላይዜሽን የመቀላቀል ሁኔታንም ታሳቢ በማድረግ ጭምር ነው፡፡ ፕሮግራሙ ለዚህ ሁሉ የሚሆን መስፈርትን ያሟላል፡፡ ሌሎችም የግለሰቡን ማንነት ለማወቅ ሶስት ባዮሜትሪኮች አሉ። ከእያንዳንዱ ሰው የተለዩ ተፈጥሯዊ የባዮሜትሪክ መረጃዎችን እንሰበስባለን፡፡ የመጀመሪያው የጣት አሻራ ሲሆን፣ አስሩም የጣት አሻራ ነው የሚወሰደው፡፡ የቀኝ እጅ አራት ጣት፤ የግራ እጅ አራት ጣት እና የሁለቱም እጅ ሁለት አውራ ጣቶችን ያካትታል፡፡ ሌላኛው መለያ የሁለቱም የዓይን ብሌን አሻራ ሲሆን፤ ሶስተኛው የፊት ገፅታ ፎቶ ነው፡፡

የሥነሕዝብን መረጃ ልዩ በሆነ መልኩ ለማረጋገጥ የሚያስችለን የባዮሜትሪክ መረጃ የምንላቸው እነኚህ ሶስቱ ናቸው፡፡ እዚህ ላይም ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ስንወስድ አንዳንድ ሀገራት የተወሰኑትን መለያዎች ሲሰበስቡ፤ እኛ ግን ሶስቱንም መለያዎች እየወሰድን ነው፡፡ ምክንያቱም ሰው በተለያየ ምክንያት በተፈጥሮ ወይም በአደጋ የእጅ አሻራና የዓይን አሻራ ላይኖረው ይችላል፡፡ ስለዚህ ከሶስቱ ቢያንስ አንዱን የሚያሟላ መረጃ እንዲገኝ ሶስቱንም እንዲወሰድ አድርገናል።

ከተሰበሰበው ቢያንስ ከአንዱ መረጃ ጋር ተመሳሳይነት እንደሌለው እና ከሌሎች ጋር ልዩ መሆኑን እናረጋግጣለን። በምዝገባው ጊዜ እያንዳንዱ ሰው እነኚህን መረጃዎች ይሰጣል። እነዚህ መረጃዎች ወደ ዳታ ማዕከል ይገባሉ፡፡ልዩ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሲስተም ላይ የሚሠራ ሥርዓት አለ፡፡ በእርሱ ሥር ሲያልፉ እና ልዩነታቸው ሲጠናቀቅ ልዩ የፋይዳ መለያ ቁጥር ይኖራቸዋል፡፡ ስለዚህ ሰዎች ተመዘገቡ የምንላቸው ልዩ ፋይዳ መለያ ቁጥር አግኝተው ወደ ተመዝጋቢው ስልክ የተላከ ከሆነ ነው፡፡

መለያ ቁጥሩ የሚሰበሰበው ሳይሆን፣ በቴክኖሎጂ በተዘረጋ የአሰራር ሥርዓት (ሲስተም) ነው፡፡ ይህን አሠራርም ከተመዝጋቢው እና ከሲስተሙ ውጭ ማንም አያውቀውም። ስለዚህ የዲጂታል መታወቂያ ልዩ መለያ ነው፡፡ በዚህ መታወቂያ አንድ ግለሰብ ከሌላው በተለየ መልኩ ማን እንደሆነ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ጥቅም ላይ እየዋሉ ካሉ መታወቂያዎች በምን ይለያል?

አቶ ሔኖክ፡-ከሚለይባቸው አንዱ በመረጃ አሰባበሰቡ ነው፡፡ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ነው፡፡ መታወቂያውም ካርድ አለመሆኑ ሌላው መለያው ነው፡፡ ዲጂታል መታወቂያ ቁጥር ላይ የተመሠረተ ሲሆን፤ ቁጥሩን የያዘ ሰው ዲጂታል መታወቂያ እንዳለው የሚረጋገጠው፡፡ በቀላሉ ለማረጋገጥ ያሚያመችም ነው፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያሉትን የመታወቂያ ሥርዓቶች ለማረጋገጥ ረዥም ጊዜ ይወስዳል፡፡ ለማረጋገጥ የሚኬድበት ርቀት የሰጠው አካል ጋር በመሔድ፣ ፋይል በማገላበጥ፣ በትክክል የተሰጠው ከየት ነው? የሚለውን ለማጣራት ጊዜና ገንዘብ ይጠይቃል፡፡መታወቂያውን አስመስሎ የመሥራት ሁኔታም ሊኖር ይችላል፡፡

ብሔራዊ መታወቂያን በፍፁም አስመስሎ መሥራት አይቻልም፡፡ የግለሰቡን ማንነት እኛ ጋር ባለ የመረጃ ቋት በቀላሉ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ባንክ ሔዶ አገልግሎት ለማግኘት ሲፈልግ ፋይዳ ቁጥሩን ነው የሚጠየቀው፡፡ ፋይዳ ቁጥሩን ከሰጠ በኋላ አንደኛውን ባዮሜትሪክ ይሰጣል፡፡ ከዛ በእርግጠኝነት ባዮሜትሪኩ እና የፋይዳ ቁጥሩ ኤሌክትሮኒክስ በሆነ መንገድ ሥርዓቱ እኛ ጋር ካለው ሥርዓት ጋር በማቀናጀት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡እንዲህ ዓይነት የዲጂታል ማረጋገጫን ያቀፈ የመታወቂያ ሥርዓት ነው እየገነባን የምንገኘው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ተደራሽነቱ ምን ይመስላል?

አቶ ሔኖክ፡-በጣም አጣዳፊ በመሆኑና ቶሎ ወደ ሥራም መገባት እንዳለበት በመታመኑና በዚህ ዲጂታል ዘመን ማግኘት ያለብንን ጥቅም ቶሎ እንድናገኝ በመታሰቡ ፕሮግራሙ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት እንዲገባ ተደርጓል፡፡ መጀመሪያ እንደሀገር የተቀመጠው ግብ የዲጂታል መታወቂያው በሁሉም የዕድሜ ክልል ላሉ ሰዎች ተደራሽ ማድረግ ነው፡፡ አምስት ዓመት እና ከዚያ በላይ ያሉ ሰዎች ባዮሜትሪካቸው መለያ መሆን ስለሚችል በዚሁ ይመዘገባሉ፡፡ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ልጆችም ቢሆኑ በወላጆቻቸው ወይም በአሳዳጊዎቻቸው ሊመዘገቡበት አሠራር ተቀምጧል፡፡ ዕድሜያቸው ሲፈቅድ በራሳቸው እንዲተካ ይደረጋል፡፡ በዚህ መልኩ ነው ሁሉም ተደራሽ የሚሆነው፡፡

ፕሮግራሙ ስትራቴጂክ ተደርጎ የተቀረፀው ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲኖር ለማስቻል በመሆኑ፤ ሰዎችን መዝግቦ መቀመጥ ሳይሆን፤ የዲጂታል መታወቂያ ቁጥር አገልግሎት ሰጪዎችም ሆኑ አገልግሎት ተቀባዮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ መታወቂያው አገልግሎትን ለማቀላጠፍ የሚያገለግል ነው ስንል፤ በዋናነት አገልግሎት የሚጠቀመው ማን እንደሆነ መለየት ይገባል፡፡በዚህም አገልግሎት የሚፈልግ ወደ 80 ሚሊዮን ሰው ይኖራል ብለን ገምተናል። በዚሁ መሠረት በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እ.አ.አ በ2025 ከ70 ሚሊዮን እስከ 90 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ለመመዝገቡ አቅደናል፡፡ ይህ ቁጥር የተጋነነ ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን የተጋነነ አይደለም፡፡

አሁን ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ 120 ሚሊዮን አካባቢ ነው፡፡ በሁለት እና በሶስት ዓመት ውስጥ የሕዝቡ ቁጥር ከዚህም በላይ እየጨመረ እንደሚሔድ ይገመታል፡፡በዋናነት የአገልግሎት ተጠቃሚዎች ማለትም ለአቅመ አዳም ለደረሱ ሰዎች ቅድሚያ ሰጥተን በትኩረት እንሠራለን፡፡በቀጣይ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ሁሉ ወደ ሥርዓቱ ይገባሉ፡፡

ይህ ሥራ ውጤታማ ይሆናል ስንል በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ሥር ያለ አንድ ፕሮግራም ብቻውን በአገሪቷ ዳር ድንበር ሁሉ ሄዶ ይሠራል ማለት አይደለም፡፡ የተለያዩ መንገዶችን እንጠቀማለን፡፡ የመጀመሪያው እኛ በራሳችን የምናደርገው የምዝገባ ሥርዓት ነው፡፡ ሁለተኛው እና ዋናው ግን ከሌሎች አብረውን ከሚሠሩ አጋር አካላት ጋር የምናከናውነው የምዝገባ ሥርዓት ነው፡፡ ለምሳሌ የፋይናንስ ተቋማት ወይም ትልልቅ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ሊሆኑ ይችላሉ። በሥራቸው ያለውን ተጠቃሚ ወይም ተገልጋይ ከእኛ ጋር በመተባበር መመዝገብ እንችላለን፡፡ ሶስተኛው ገበያ ተኮር (ኮሜርሻላይዝድ) አድርገን፤ አቅም ያላቸው የመንግሥት ብቻ ሳይሆኑ የግል ድርጅቶችም የምዝገባ ጥራቱን ጠብቀው እና ሥርዓቱን (ፕሮቶኮሉን) አክብረው እንዲሰሩ ይደረጋል፡፡ ስለዚህ የምዝገባ ሥርዓቱ ላይ ብዙ ተዋናኞች ይሳተፋሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በየጊዜው እየተሠሩ ስላሉ ሥራዎችና የሥራውንም ስፋት ቢነግሩን?

አቶ ሔኖክ፡- አንድ የቴክኖሎጂ ሥርዓት ሲተገበር በቀላሉ ተነስቶ በሰፊው አይተገበርም፡፡ከላብራቶሪ ጀምሮ በተለያዩ የሙከራ ሂደቶች ማለፍ አለበት፡፡ በመጀመሪያ በቢሮ ደረጃ የሙከራ ሥራ ተሠርቷል። በተወሰኑ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስን በሆኑ ሰዎች ሞክረናል። ከዚያም ያንን ሙከራ አዳብረን፤ ቴክኖሎጂውን በደንብ ካወቅን በኋላ፤ ለመስክ ሙከራ ወደ 100 ሺህ ሰዎችን መዝግበናል፡፡

ይህ ምዝገባ ትልልቅ መሥሪያ ቤቶች እና ከተሞች ላይ ብቻ ሳይሆን ትልልቅ የፋይናንስ ተቋማት ላይ፣ የማህበረሰብ አገልግሎት፣ የሴፍትኔት ፕሮግራም ላይ እንዲሁም አብዛኛው ሕዝብ በገጠር ያለ በመሆኑ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት በሌለባቸው አካባቢዎችም ጭምር በመሄድ ተግባራዊ የሚሆነው እንዴት ነው? በሚል የሙከራ ምዝገባ ተካሒዷል፡፡ኦሮሚያ እና ሲዳማ ሌሎችም ቦታዎች ላይ ሄደን ሥራዎችን ሠርተናል፡፡ ከዚህም ትምህርት በመውሰድ የምዝገባ ሥርዓቱን በማስተካከል፤ እዛ ላይ ያሉ ዝርዝር መስፈርቶችን በማሟላት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን የመለየት ሥራዎችን ስንሰራ ቆይተናል፡፡

በዋናነት ወደ ገጠር ሲገባ ማህበረሰቡ የሚቀበለው እንዴት ነው? ቴክኖሎጂውስ እንዴት ይሁን? የኤሌክትሪክ ሃይል በሌለበት አካባቢ ሲስተሙ በቀጥታ መሥራት አይችልም፡፡ ስለዚህ ሥራዎችን በመሥራት ሲስተሙ ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል መሥራት እንዲችል ከምዝገባ ቁሳቁስ ጀምሮ ሰፋፊ ልምዶችን አግኝተናል፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ሀገር አቀፍ ትግበራ እየተሸጋገርን ነው፡፡ ቀደም ሲል ውስን የመመዝገቢያ መሣሪያዎች ነበሩን፤ አሁን ቁጥራቸውን እየጨመርን ነው፡፡ በፊት 40 ነበሩ፤ አሁን ወደ 400 ደርሰዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር ወደ አንድ ሺህ አሳድገን በሰፊው እንሠራለን፡፡

ሌላው አቅም መገንባት እና የፕሮግራሙን የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡ ለምንሠራው ሥራ የሚሆነውን ሥርዓት መሬት ላይ ማውረድ እና አስፈላጊውን የሰው ሃይል ማደራጀት የግድ ነው፡፡ ጉዳዩ የቴክኖሎጂ ሥራ ነው፡፡ ይህንን ለማሟላት እና ለመለየት፤ ከፍተኛ የሰው ሃይል የሚፈልግ ሲሆን፤ ሰዎችን የማሰባሰብ እና ቡድን የመገንባት፤ ሀገር ውስጥ ባለ አቅም እና ከውጭም በምንገዛቸው አገልግሎቶች የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማትን ማደራጀት ላይ እንሠራለን፡፡

ይህንን ሁሉ እንሠራለን ስንል ከጀርባ ያለውን ይህንን ሥርዓት የሚደግፈው የቴክኖሎጂ አቅምን እና ሥርዓት ነው። እርሱን የመዘርጋት ሥርዓት ላይ በሰፊው ብዙ ሥራዎች ስንሠራ ቆይተናል፡፡ ቴክኖሎጂ ሲባል የምንጠቀመው ክፍት የሆነ (ሞቲፍ ሶርስ) የተባለ ሥርዓት ነው፡፡ እርሱን ከኢትዮጵያ ፍላጎት ጋር እንዲስማማ የማድረግ ሥራ ሠርተናል፡፡ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ወይም በብዙ ሀገራት የተተገበሩ እና የተቀመጡ ፕሮግራሞችን መጠቀም የተለመደ ነው፡፡ በብዙ ዶላሮች አንድ የሲስተም አቅራቢ ይኖራል፡፡ ሲስተሙ ከጫፍ እስከ ጫፍ የሚያገለግል ይሆናል፡፡ ነገር ግን የሆነ ነገር መለወጥ ከተፈለገ ይከለክላል፡፡ ምክንያቱም ባለቤትነቱ የዛ ተቋም ነው፡፡

ይህ እየሰበሰብን ያለነው እጅግ አስፈላጊ የሆነ የግለሰብ መረጃ ነው፡፡ ማንም ጋር መንግሥት ጋር እንኳን የሌለ መረጃ ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ለሶስተኛ ወገን ለዛውም ከውጭ ለሚመጡ አገልግሎት ሰጪ መስጠት፤ ከፍተኛ የሉዓላዊነት አደጋን ያመጣል፡፡ ስለዚህ ይህንን ሥርዓት ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ በራሳችን ለማስተዳደር በጣም ብቁ የሆነ የውስጥ አቅም እንዲኖር ጥረት አድርገናል፡፡ስለዚህ በዋናነት የመረጃው ባለቤት ራሱ ተመዝጋቢው ቢሆንም መረጃው የሚቀመጠው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡የምታስተዳድረውም ራሷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ በአጠቃላይ የቴክኖሎጂ ሥርዓቱን በራስ አቅም በባለቤትነት በመያዝ ሲስተሙን ተቆጣጥረን የምናስተዳድረው እኛው ነን፡፡ ሌላ የውጭ አካል አይደለም። ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለንን ትስስርም እያጎለበትን ነው፡፡

ይህ ሥርዓት ሲመጣ የአሠራር ሥርዓታቸውን የሚያቀላጥፍላቸው ብዙ ዘርፎች አሉ፡፡ ለግለሰቦች አገል ግሎት የሚሠጥ ተቋም የሚሠጠውን አገልግሎት ለማን እንደሚሠጥ ማወቅ ይፈልጋል፡፡ያንን የሚያቀላጥፍ ሥርዓት ላይ እየሠራን ነው፡፡ስለዚህ ተቋማት ወደ እዚህ አገልግሎት እንዲመጡ እና የአገልግሎት ሥራቸውን ከዚሁ ሥርዓት ጋር እንዲያቀናጁ ንግግሮች እና የአሠራር ሥርዓቶች ያስፈልጋሉ። ምናልባት የውስጥ ደንቦቻቸውን ሊያስተካክሉ ይችላሉ። ይህን እንዲያደርጉ ሰፊ ሥራዎችን እየሠራን ነው። እዚህ ላይ አንዱ የሚጠቀሰው የፋይናንስ ዘርፉ ነው፡፡ ሰሞኑን የብሔራዊ ባንክ ብሔራዊ መታወቂያ ቀዳሚ የባንክ መታወቂያ እንዲሆን አውጥቷል፡፡ይህንን በጋራ እየሠራን ሲሆን፤ በምዝገባ ሂደቱ ላይ ባንኮች ተሳትፈው በአጭር ጊዜ ውስጥ ደንበኞቻቸውን ወደ እዚህ ሥርዓት ያስገባሉ፡፡

ሌላው ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር እንደዚሁ በትብብር እየሠራን ነው፡፡ ገቢዎች የሚሠራላቸው ተቋም ስለሌለ እስከ አሁን የግብር ከፋይነት ቁጥርን (ቲን ነበርን) እና የዐሻራ መለያን (ባዮሜትሪክስ)ን ራሳቸው ገቢዎች እየሠሩ ነበር። አሁን ግን የብሔራዊ መታወቂያ ተቋም እየሠራ በመሆኑ፤ ከዚህ ሥራ እየወጡ ነው፡፡ እኛ ማንነትን የማረጋገጥ ሥራ እየሠራንላቸው፤ እነርሱ ዋነኛ ገቢን ወደመሰብሰብ ሥራቸው ትኩረት እንዲያደርጉ በፋይዳ ቁጥር የግለሰቡ ማንነት ተረጋግጦ፤ በኋላም ወደ የግብር ከፋይነት ማንነት ምዝገባ እየገባን ነው፡፡

ከትምህርት ሚኒስቴር ጋርም በጋራ የተማሪዎች የመታወቂያ ምዝገባን እያካሔድን ነው፡፡ ተማሪዎችን የመለየት ሥራ እየሠራን ነው፡፡ እኛ መሠረታዊው የማንነት መለያውን ስንሠራ፤ ትምህርት ሚኒስቴር ደግሞ በትምህርት ዙሪያ ያላቸው መረጃ ላይ ያተኩራል፡፡ ሌሎችም ብዙ ዘርፎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

በተጨማሪ ከምንሠራው ሥራ ጋር በተጣጣመ መልኩ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየሠራን ነው፡፡ ይህ ሥርዓት ማዕቀፍ አድርጎ የሚያስተዳድረው ትልቁ የሕግ አግባብ የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ሕግ 1284/2015 አለ፡፡ሕጉ አስፈላጊውን የሕግ ሥርዓት አልፎ፤ በሕዝብ ተተችቶ፣ አገልግሎቱን ለሚጠቀሙ የተለያዩ ተዋናዮች በየክልሉ ባሉ የሕግ አካላት ታይቶ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አልፎ ፀድቆ ሥራ ላይ ውሏል፡፡ እነኚህን እና የመሳሰሉ ብዙ ሥራዎችን እየሠራን ቆይተናል፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ መስመር ይዘዋል፤ ወደ ሀገር አቀፍ ትግበራ እየተሸጋገርን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እንደገለጹልኝ እስከ አሁን ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተመዝግበዋል፡፡ምዝገባው በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ነው የተከናወነው?

አቶ ሔኖክ፡– ከላይ እንደገለፁኩት በጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት ሥር ሆነን መሥራት ከጀመርንበት ከመስከረም ወር ጀምሮ የተሰራ ሥራ ነው፡፡በላብራቶሬ ደረጃ እንመዘግባለን ብለን ስንል ወይም ደግሞ በቢሮ ደረጃ ሁለት፣ሶስትና አምስት የመንግሥት ተቋማት እንመዘግባለን ብለን ባደረግነው እንቅስቃሴ ሁለት መቶ እና ሶስት መቶ ነው የመገብነው፡፡የአሠራር ሥርዓታችንን እያስተካከልን፤ የሚያስፈልገን መሣሪያ ምን ዓይነት መሆን እንዳለበት እየለየን፤ ምዝገባው ለሰው ምቹ የሚሆነው እንዴት ነው? የሚለውን እያየን ነው፡፡

ከትናንሽ ጀምረን በሙከራ 100 ሺህ እስክንደርስ ከቀጠልን በኋላ፤ ከባንኮች ጋር ስንሰራ በዘጠኝ ባንኮች ከ63 በላይ ቅርንጫፎች ላይ የምዝገባ ጣቢያዎች አሉ፡፡በገቢዎች ሚኒስቴር አዲስ አበባ በሁሉም በየክፍለ ከተማው ባሉ ቅርንጫፎች በክልል ደግሞ 547 ቅርንጫፎች አሏቸው። እነርሱ ካሏቸው መካከል ወደ ተመረጡ 200 አካባቢ የሚጠጉ ቢያንስ ሁለት ዋና ዋና ከተሞች ላይ ገቢ ሰብሳቢ ቅርንጫፎች ላይ እየሠራን ነው፡፡

ድሬዳዋ ከተማ መስተዳድርን እና አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ላይ የተመረጡ ቅርንጫፎች ላይ በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ወደ ሥራ ይገባል ብለን እንገምታለን፡፡ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን የተባለው የእዚህ ሁሉ ድምር ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሶስት ሚሊዮን ይሞላል የምንለው ምዝገባው በየቀኑ እየተካሔደ በመሆኑ ነው፡፡ አጋር አካላት የምንላቸው እነትምህርት ሚኒስቴር እና ሌሎችም በእነርሱ በኩልም የሚመዘገቡ ሰፋ ያሉ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ምዝገባዎች አሉ፡፡

ከፊታችን በሚመጣው ዓመት በጣም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሰው እንመዘግባለን ብለናል፡፡ በ2018 ዓ.ም ደግሞ ከ70 እስከ 90 ሚሊዮን ለመመዝገብ ፕሮግራም ቀርፀን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡አሁን የምንመዘግበው በ400 መመዝገቢያ ማሽን አካባቢ ነው፡፡በአጭር ጊዜ ከአጋሮቻችን ጋር በመተባበር ይህንን እያሰፋን የምንሄድ ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ምዝገባው በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲካሄድ የተለያዩ ግብዓቶችን ጨምሮ የሠው ሃይል ያስፈልጋል፡፡ መሠልጠን ያለበት የሰው ሃይል በሙሉ ሠልጥኖ፤ በሁሉም ክልሎች እየተተገበረ ነው ማለት እንችላለን?

አቶ ሔኖክ፡– ትክክል ነው፡፡ሥራው እንዲተገበር የተለያዩ ግብዓቶች ያስፈልጋሉ፡፡የመጀመሪያው የምዝገባ መሣሪያ ማሟላት ነው፡፡እነዚህ ከውጭ ተገዝተው የሚገቡ ሲሆን፤ በራሳችን የመንግሥት በጀት፣ በድጋፍ ሰጪ አካላት እና በአጋር አካላት በባንኮች በኩል ቁጥሩን ቶሎ ስንጨምር በሺዎች የሚቆጠሩ ኪቶች ይኖሩናል፡፡ያንን የማድረግ ሥራ ላይ ነን፡፡ ከዛ ውጪ እነኚህ መሣሪያዎች ላይ የሚያስፈልገው ቴክኖሎጂ ሶፍትዌሩን መጫን እና ለአገልግሎት ምቹ የማድረግ ሥራ በእኛ ባለሙያዎች የሚሠራ ነው፡፡

እዚህ ላይ ሥልጠና አንዱ ነው፡፡ሰዎችን መልምሎ ለሥልጠና ማዘጋጀት ሌላኛው ነው፡፡ቁጥሩ እየጨመረ ሽፋኑ እያደገ በሔደ ቁጥር፤ እያሰፋን የምንሔደው እኛ ብቻ ሳንሆን ድጋፍ ሰጪ አካላት እና አጋር አካላትም ጭምር ናቸው።ይህን የምናደርገው ውስን በሆነ በአንድ ተቋም አቅም ነገሮችን ማሳካት ፈተና እንደሚሆን ስለምናውቅ ነው፡፡ከሌሎች ከተሳካላቸው እና ካልተሳካላቸው ሀገራት ትምህርት በመውሰድ በራሳችን አቅም፣ በአጋሮች እና በድጋፍ ሰጪዎች ሌላው ቀርቶ የግል የፋይናንስ ተቋማት ሳይቀሩ ገብተው ሠልጥነው ወደ ሥራው እንዲገቡ እያደረግን ነው፡፡

ለዚህ እስከ አሁን የሄድንባቸው መንገዶች ማሳያ ናቸው። ለምሳሌ በገቢዎች በክልል ገቢ ሰብሳቢ ባለሥልጣናት ሥራ ጀምረናል፡፡ ከ500 በላይ ሰዎች ከየክልሉ ተመልምለው መጥተው ሥልጠና እና ለተወሰኑት ደግሞ መመዝገቢያ ኪቱን ሰጥተን ወደ ሥራ አስገብተናቸዋል፡፡ስለዚህ የእዚህ ልምድ እያካበትን ነው፡፡

በቀጣይ በስፋት ለማሠልጠን የሥልጠና ሞጁል የማዘጋጀት፤ የሥልጠና ሥርዓቱን የማበልፀግ፤ ሲወጡ ሥራው ላይ በደንብ መሥራት እንዲችሉ ምን ምን ነገሮች መያዝ አለባቸው የሚለው ላይ ከንድፈ ሃሳብ ጀምሮ መሣሪያዎችን በተግባር እስከ መጠቀም ድረስ የሚሰጣቸው ሥልጠና፤ ከዛ ባሻገር የሥራ ቦታው ላይ በትክክል ገብተው የሚሠለጥኑበት ቀን ጭምር ለይተናል፡፡ ይህንን ሁሉ አዘጋጅተን ከ500 በላይ ሰዎች ወደ ሥራ አሠማርተናል፡፡

በተመሣሣይ 300 የሚሆኑ ከየባንኩ ተመልምለው የመጡ ሰዎችን አሠልጥነን ወደ ሥራ አስገብተናል፡፡ስለዚህ ነገ ሥራው ሲሠራ ከአራቱ ኮርነሮች ለምሳሌ ትግራይ ክልል ሥራው ሲሰራ የሆነ ሰው ከአዲስ አበባ መሄድ አይጠበቅበትም፡፡ ሥራውን የሚያከናውነው በዛው ያለ የአካባቢውን ቋንቋ የሚያውቅ ሰው ሥልጠናውን ወስዶ ወደ ሥራ መግባት ይችላል፡፡ጋምቤላም ሆነ በሌላ ክልል ያሉ ሰዎች ተወዳድረው ሠልጥነው ገብተው ሥራው ላይ የሚሠማሩበት ዕድል አለ፡፡

ሌላኛው ለምዝገባው የሚያስፈልግ የምዝገባ ዕቃዎችን ማዘጋጀት ነው፡፡ መሣሪያው ሳምሶናይት ዓይነት ሳጥን ሆኖ 20 ኪሎ አካባቢ ነው፡፡ የተለያየ ዓይነት ነው፡፡ በተጨማሪ ወንበር እና ጠረጴዛ እንዲሁም በቂ ብርሃን ያስፈልገዋል፡፡እነዚህን አብረውን ከሚሠሩ ከባንኮች እና ከገቢዎች ጋርም በጋራ እየተባበርን እና እያሟላን ወደ እዚህ ሥርዓት እየገባን ነው፡፡ብዙ የሚያስፈልጉ ነገሮች አሉ፡፡በመተባበር እያሟላን ሥልጠናዎችንም እየሠጠን ነው፡፡

 አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ በሁሉም ክልሎች ተጀምሯል ማለት ነው?

አቶ ሔኖክ፡- አሁን ከገቢዎች ጋር አያይዘን በሁሉም ክልሎች ጀምረናል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ከባንኮች ጋር በዋናነት አዲስ አበባ ውስጥ እየሠራን ነው፡፡ በቀጣይ ከተወሰኑ ወራቶች በኋላ ማሽኖቹ ሲገቡ እና የሠለጠኑ ሰዎች ሲሰማሩ ከባንኮች ጋር በአገሪቷ ዙሪያ ሁሉ ሥራው ይሰፋል። ከሌሎች ጋርም እንሠራለን፡፡ ለምሳሌ በማህበረሰብ ተጠቃሚነት ፕሮግራሞች እና በሠብዓዊነት ዘርፍ እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች በመላው ሀገሪቱ የምንደርስበት ሁኔታ ይኖራል፡፡

አሁን በክልሎች ከገቢዎች ጋር እየሠራን ሲሆን በደንብ አገልግሎቱ እየተሰጠባቸው ያሉ ቦታዎች ውስን ናቸው፡፡ቤኒሻንጉል እየተሠራ ነው፡፡ አማራ ክልል በተወሰኑ ቦታዎች በባህርዳር አካባቢ እየተሠራ ነው፡፡ ሌሎቹም ሁሉም ወደ ሥራ ይገባሉ፡፡ ጋምቤላ የደህንነት ጉዳይ ችግር ስለነበር፤ በጋምቤላ አልተቻለም፡፡ ከዛ ውጪ ሁሉም ክልሎች ሥልጠናውን ወስደዋል፡፡ አሁን የሚያስፈልገውን ቦታ ማደራጀት እና ግብዓት ማሟላት ነው፡፡ ለምሳሌ ኦሮሚያን እና አማራን የመሳሰሉ ትልልቅ ክልሎች ላይ መሣሪያውን ወደየቦታው ማድረስ ትንሽ ጊዜ እየወሰደ ነው፡፡ በጥቂት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ሁሉም ክልሎች ወደ ትግበራ ይገባሉ ብለን አስበናል፡፡

ትግራይ ክልል መቀሌ ላይ ተጀምሯል፡፡ወደ ሌሎች አካባቢዎች በሂደት ይሰፋል፡፡ደቡብ ክልል ፤ ደቡብ ምዕራብ እና ሌሎችም ክልሎችም እየጀመሩ ነው፡፡ምናልባት ዛሬ እያንዳንዱ ክልል ያለበትን ሁኔታ ማጣራት እንችላለን፡፡ በሁሉም ክልል የመጀመር ሂደት ላይ ነን፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአጠቃላይ እናንተ አብራችሁ ከምትሠሯቸው ተቋማት ጋር ተጠቃሎ፤ ስንት የምዝገባ ማዕከላት አሉ?

አቶ ሔኖክ፡– በባንኮች ከ63 በላይ የምዝገባ ቦታዎች አሉ፡፡ የራሳችን ደግሞ ለሕዝብ ክፍት የሆነ በኦንላይን ቀጠሮ ይዘው መጥተው የሚስተናገዱበት ሁለት ጣቢያ አለ።አንደኛው ዋናው ፖስታ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ሁለተኛው የቤተመንግሥት መግቢያው የመኪና ማቆሚያ ዩኒቲ ፓርክ ላይ ሁለት ጣቢያዎች አሉ፡፡ማንኛውም ሰው ቀጠሮ አስይዞ ገብቶ መመዝገብ ይችላል፡፡ ከዛ ውጪ ከገቢዎች ጋር የሠራነው በአዲስ አበባ ከ14 በላይ ቦታዎች አሉ፡፡

በጠቅላላው ግን አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ ቅርንጫፎች አሉ፡፡በእያንዳንዱ ማዕከል ቢያንስ አንድ ኪት ተቀምጦ በትግራይ ክልልም ሆነ በምዕራብ ደቡብ ክልል አዲስ አበባ እና ድሬዳዋን ጨምሮ በየክልሉ እና በየከተማ አስተዳደሩ ወደ ሁለት መቶ አካባቢዎች ይሆናሉ። ወደ 200 የሚጠጉ ቦታዎች ላይ ከገቢዎች ሚኒስቴር እና በየክልሉ ካሉ የገቢ ሰብሳቢ ባለሥልጣናት ጋር በመተባበር እንዲሁም ከባንኮች ጋር በመተባበር እየሠራን ነው፡፡

 አዲስ ዘመን፡- እንደገለጹልኝ ኪቶችን ጨምሮ ለአገልግሎቱ ግብዓት የሚሆኑ መሣሪያዎች ከ400 በላይ መመዝገቢያዎች ገብተዋል፤ ምን ያህል ወጪ ወጣባቸው?

አቶ ሔኖክ፡- ኪቶች የሚገዙት በዶላር ነው፡፡አንድ ኪት እስከ 1 ሺ ዶላር ሊያወጣ ይችላል፡፡በትክክል ቁጥሩን መናገር አልችልም፡፡ አንዱ ፈተና ይኸው ነው፡፡ ከፍተኛ ገንዘብ ይጠይቃል፡፡ ነገር ግን በየዘርፉ ከሚያመጣው ጥቅም አንፃር፤ ተደምሮ ለሀገር የሚኖረው አስተዋፅኦ አንፃር መታየት አለበት፡፡ የመመዝገቢያ መሣሪያዎች ውድ ናቸው። ነገር ግን የብሔራዊ መታወቂያ ሥርዓቱን ከጀርባ ሆነው የሚደግፉ ቴክኖሎጂ እና መሠረተ ልማቶች ያስፈልጋሉ፡፡

መረጃዎቹን ወይም ዳታውን ለማስቀመጥ የማከማቻ ማዕከል ያስፈልጋል፡፡ በቀጥታ (ኦንላይን) አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፤ ትልልቅ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ደንበኞቻቸውን ለማረጋገጥ የሚፈልጉበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ በሚሊዮን እና በቢሊዮን የሚቆጠር ማንነትን የማረጋገጥ ጥያቄ ሊመጣ ይችላል፡፡ ይህንን ሁሉ አገልግሎት የሚደግፍ መሠረተ ልማት ለምዝገባ ከሚወጣው ወጪ በላይ ብዙ ገንዘብ ይጠይቃል፡፡ እነዚህ በዶላር የሚገዙ እቃዎች ናቸው፡፡ሌላው የሥራ ሂደት (የኦፕሬሽን) ወጪ ነው፡፡ የሚሠማራው የሰው ሃይል ብዙ ነው፡፡ ሌሎችም ብዙ ወጪዎች አሉ፡፡

አንድ የጥናት ተቋም አለ፡፡ በተለያዩ ሀገራት ላይ ጥናት ተሰርቷል፡፡ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርት ሁለት መቶ ቢሊዮን አካባቢ ነው፡፡ በዚህ የዲጂታል መታወቂያ ምክንያት ብቻ ስድስት በመቶ የኢትዮጵያን አጠቃላይ ምርት ያሳድጋል የሚል ጥናት በውጭ አጥኚዎች ተጠንቷል። አሁን ደግሞ ቢጠና ከዛ በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ እግረ መንገዳችንን የሀገር ውስጥ አጥኚዎችንም እንጋብዛለን፡፡

ይህ ለምን ይሆናል ከተባለ፤ አንደኛ ወጪን ይቀንሳል። ባልተረጋገጠ ማንነት የሚወጣ ብዙ ወጪ አለ፡፡ለምሳሌ ይህን ያህል ለሆነ ሰው ርዳታ ተሰጠ ይባላል፡፡ነገር ግን እንደሚባክን እና እንደሚሰረቅ ይታወቃል፡፡ይህ መለያ ካለ ተረጂ ማን ነው የሚለው በትክክል ይታወቃል። በአንዱ ሌላ ሰው መጠቀም አይችልም፡፡ ስለዚህ በትክክል ሰርቪሱ ለተጠቃሚው መድረሱን ማረጋገጥ ይቻላል። በአስተዳደርና በመሃል የሚባከነውን መቀነስ ይቻላል፡፡ለምሳሌ ባለፈው ዓመት ብሔራዊ ባንክ እንዳስታወቀው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በሃሰተኛ ማንነት ወጥቷል፡፡ሥራው ከተሠራ ይህንን ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት ይቻላል።

እቅድንም በተረጋገጠ ቁጥር ላይ መመሥረት ይቻላል። ስለዚህ ትክክለኛ እቅድ ሲኖር ውጤታማ ሊሆን የሚችል እቅድ ማውጣት እና እቅዱን ማሳካት ይቻላል፡፡ለጤና አገልግሎት፣ ለግለሰቦች ጤና ከአንዱ ተቋም ወደ ሌላ ተቋም የጤና ታሪክን ለመላክ፣ ለብድር አገልግሎት ማለትም ለትክክለኛው ሰው ለማበደር፣ ለግብርና ግብዓት ስርጭት፣ በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ያለውን ማጭበርበር ለመቀነስ፣ ቀጣሪዎችም በትክክል የሚቀጥሩትን እንዲያውቁ እነኚህ ሁሉ ሲደመሩ በሁሉም ዘርፍ ላይ ሚና ይኖረዋል፡፡ብሔራዊ መታወቂያ ሲመጣ አዳዲስ የዲጅታል መድረክ ይፈጠራል፡፡ብዙ ሰዎች ወደ ፋይናንሱ ይገባሉ፡፡ከደህንነት ስጋቶች አንፃር ወንጀል የሚሰራ ሰው ይታወቃል፡፡ትልቁ ጥቅም አገልግሎቱን ትራንስፎርም ማድረጉ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በብሔራዊ መታወቂያ ላይ የማንነት ስርቆት እንዳይከተል ምን ጥንቃቄ እየተደረገ ነው?

አቶ ሔኖክ፡– የመጀመሪያው በሕግ እና በአሠራር ሥርዓት የመረጃን ጥበቃ ማረጋገጥ ነው፡፡የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ሕግን ማየት ይቻላል፡፡ይሄ መረጃ ባለቤትነቱ የተመዝጋቢው አካል፤ ከተመዝጋቢው ወገን እውቅና ውጪ ማንኛውም ሰው ሊያገኘው የማይችል፤ እኛ ብንመዘግብም ከተመዝጋቢው እውቅና ውጪ እንደፈለግን እየመነዘርን ለማንም መስጠት አንችልም። ይህ በሕግ የተደነገገ ነው፡፡ ይህንን ደግሞ በአሠራር ሥርዓት የምንደግፈው የመጀመሪያውን መረጃ ስንሞላ ስምምነት አለ ፤ ከተመዝጋቢው ጋር ያለተመዝጋቢው ፈቃድ ለማንም እንደማንሰጥ ቃል እንገባለን፡፡

ሌላው ጥበቃው በቴክኖሎጂ ነው፡፡ መረጃውን የሚያገኙ ሰዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እና በሕግ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ጭምር እያሳወቅን የምንሰጣቸው እያስፈረምን ነው፡፡ ለምሳሌ መዝጋቢዎች ሠልጥነው ሲሄዱ ጋምቤላ የሄደው ኪት ላይ ማን እንደሚመዘግብ ይታወቃል፤ የራሱ የመክፈቻ የይለፍ ኮድ አለው፤ እያንዳንዱ ምዝገባ የመዘገበው ማን ነው? በምን ሰዓት ነው? ከየት ነው? የሚለው ይታወቃል፡፡ ሥርዓቱ ላይ የሚሰሩ የእኛ ባለሙያዎችም መረጃ የሚያገኙት በጣም ውስን የሆነ ነገር ላይ ነው፡፡ በተለይ የግል መረጃን መንካት መለወጥ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ለሰባቱም ቀን ለ24 ሰዓት የደህንነት ጥበቃ ይደረግለታል ማለት ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እጅግ እናመሰግናለን።

አቶ ሔኖክ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 15 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You