የደም ፖለቲካ ከኪሳራ ውጪ ተስፋ ያላት ሀገር አይሰራም

 ሀገር የፖለቲካ ጽንስ ናት። እንዴትም ብንኖር ከፖለቲካ እሳቤ መራቅ አንችልም። ለሀገርና ሕዝብ የቀና ልብ ካለን በመልካም ፖለቲካ መልካም ሀገር መፍጠር እንችላለን። በተቃራኒው ራሳችንን ብቻ ካስቀደምንና ለጊዜአዊ ሥልጣን ቅድሚያ የምንሰጥ ከሆነ ከሥርዓት ውጪ የሆነ ሀገርና ሕዝብ እንፈጥራለን። ሁለቱ ፖለቲካዊ ጽንሰ ሃሳቦች የተለያዩ ናቸው። በአንዱ ውስጥ ታሪክ ሲኖር በአንዱ ውስጥ ታሪክ የለም ካለም የሞትና የጦርነት ታሪክ ነው፡፡

ፖለቲካችን የደም ፖለቲካ ነው።በመሞትና በመግደል የጀገነ። ኢትዮጵያዊነትን ሽረን በራስ ወዳድነት የምናቀነቅነው የጽንፈኝነት ፖለቲካ ሀገር ሳይሰጠን እልፍ ዘመናት ተቆጥረዋል። ከአብሮነት ሌላ ማንነት የማታውቅ ሀገር ዛሬ በፖለቲካ ሽፋን የብሄር ማንነት ተሰጥቷት ጸንታ መቆም ተስኗት ስትንገዳገድ ማየት ያስቆጫል፡፡

ኢትዮጵያዊነት መሠረቱ ፍቅር እንጂ ጥላቻ አይደለም። በፍቅር ተቧድነን ነው ሀገርና ሕዝብ የሆነው። በአንድነት ተራምደን ነው ባለታሪክ የተባልነው። ሀገር እንደሰሩ እንደነዛ የአብሮነት ክንዶች አንድነት ነው የሚያዋጣን። ታሪክ እንዳስቀመጡ እንደነዛ አእምሮና ልቦች ወንድማማችነት ነው የሚበጀን፡፡

የተረማመድንበት የአብሮነት ዳና በኢትዮጵ ያዊነት ተሸምኖ የተቋጨ ነው። ታሪኮቻችን በጋራ የጻፍናቸው የአብሮነታችን ነጸብራቆች ናቸው። እንዴትም ብናስብ ከዚህ እውነት አንወጣም። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት የአንድ ሳንቲም ሁለት መልኮች ናቸው። እኚህ መልኮች ደግሞ እኔና እናንተ ነን። እኚህ መልኮች እኔነት ያልነካቸው፣ ዘረኝነት ያልጎበኛቸው የአንድ ግንድ ቅርንጫፎች ናቸው፡፡

ከታሪካችን አንዱ አማኝነት ነው። በአማኝነት ውስጥ ደግሞ ፍቅር ቀዳማይ ጥበብ ነው።ራሱን ለፈጣሪው ሰጥቶ በአዛንና በቅዳሴ የሚኖር ሕዝብ ስለፍቅር ማስተማር ለቀባሪ ማርዳት ነው የሚሆነው። ፍቅርን አውርተን ሳይሆን ኖረነው ለዓለም ያሳየን ሕዝቦች ነን። ዛሬ ያ ጉምቱ ፍቅር በጥላቻ ለሀጭ ጨቅይቶ ድሮነታችንን አደብዝዞብናል፡፡

ልጅ ወላጁን እንደሚመስል ሁሉ እኛም የፈጠረን ነው የምንመስለው። ዋናው ጥያቄ የፈጠረን ምን አይነት ነው? የሚለው ነው። የፈጠረን በሃሳቡ፣ በምግባሩ መልካምና ቅዱስ የሆነ ነው። ለልጆቹ የሚሆን ብዙ ራሮት አለው። በፍቅርና በይቅርታ የጸና ልዕለባህሪ ማንነት አለው።

እኛም ከዚህ ማንነት ውስጥ ማንነት ያገኘን ነን። ከፈጣሪ ብኩርና ሰው መሆንን ስንታደል መልካሙን ሥራ ሰርተን እንድናልፍ ነው። በአምሳል ፈጣሪን እንደምንመስል ሁሉ በግብርም እሱን መመሰል ከሞት ማምለጫ ብቸኛው መንገዳችን ነው። እውነቱ ግን ሌላ ነው፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ በወንድማማቾች ደም የቄራ ሜዳ ሆና ለዘመናት ዘልቃለች። ጦርነት ከሚሉት ሰይጣናዊ እሳቤ መውጣት አቅቶን በወንድሞቻችን ላይ ቃታ በመሳብ ጀግንነታችንን ስናሳይ ዘመን አሳልፈናል።

ምናችንም የፈጠረንን አይመስልም።እርሱ አይደለም ሌሎችን ሊገድል ቀርቶ ለሚያሳድዱት ይቅርታን የለመነ።የናቁትን ያከበረ፣ የጠሉትን ያፈቀረ ከምንም በላይ ደግሞ ክፉዎችን “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ሲል ወደአባቱ የጸለየ ነው።

እኛ በፈጣሪ የጌትነት ባህሪ ሃሳብ እና ምክር ከምንምነት ወዙን ለብሰን ከአለመኖር ወደመኖር እድል ያገኘን ነን። ምግባራችን ግን የፈጠረንን አይመስልም። አይደለም ጠላቶቻችንን ልንወድ፣ አይደለም ለጠሉን ይቅርታ ልናደርግ ቀርቶ ከወንድሞቻችን ጋር በሰላም መኖር እየከበደን ነው።

የአባታችን ልጅ ካልሆንን እምነታችን ዋጋ አይኖረውም። የፈጠረንን ካልመሰልን መኖራችን ትርጉም የለውም። ዛሬ ላይ የምንባላባቸውን ነገሮች በፍቅር ዓይን ብንመለከታቸው ብዙ እና እልፍ ሆነው ከእኛ አልፈው ለሌሎች የሚተርፉ ሆነው እናገኛቸው ነበር።

ዛሬ ላይ የምንጣላበትን ፖለቲካ በይቅርታና በወንድማማችነት መንፈስ ብናጤነው ብዙ በረከትን ደብቆ እናገኘው ነበር። ዛሬ ላይ እየሞትንባቸው እና እየተጎሳቆልንባቸው ያሉ ብሄር ተኮር የእኔነት እሳቤዎች በፍቅር ዓይን ብንመለከታቸው እኛን ከመጉዳት ባለፈ እርባና እንደሌላቸው እንደ ርስባቸው ነበር፡፡

የሰውነት ትልቁ ብኩርና ፍቅር ነው።ፍቅር የሌለበት ሰውነት በየትኛውም መመዘኛ የሰውነት መስፈርትን አያሟላም። የሰውነት ቀዳማይ ዓላማ በፍቅር መኖር ነው። የሀገራችን ትልቁ መከራ ፈርሀ እግዚአብሄር የሌለበት በትዕቢት እና በማንአለብኝነት የጨቀየ ፖለቲካና ምግባር ነው፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራችን መልከ ብዙ ሀገር ናት። የተለያዩ መልኮች፣ የተለያዩ ባህሎች የቀለሟት ባለቀለም መልክ ናት። ህብረታችን አንድነታችን በሀገራችን ፖለቲካው ውስጥ ከፊት እስካልመጣ ድረስ ከዚህም የባሰ መከራ ነው የሚጠብቀን። ኢትዮጵያ ሰፊ ናት። በፍቅር ከኖርንባት፣ በወንድማማችነት ከተቻቻልንባት እኛን አጥግባ፣ እኛን አርክታ፣ እኛን አዘምና፣ እኛን ታድጋ ለሌሎች የሚተርፍ በረከት እና ጸጋ፣ ህብስት እና ሙላት ያላት ክበድ ናት፡፡

እዚም እዛም የምንሰማቸው ሞቶች፣ ስቃዮች፣ መፈናቅሎች በሆነ ልክ ባልሆነ ሃሳብ እና ተግባር የተፈጠሩ እንጂ ዝም ብለው እንደ እንጉዳይ በቅጽበት የተከሰቱ አይደሉም። መንግሥት የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ ወገቡን ታጥቆ መነሳት ለነገ የማይለው የቤት ሥራው ሲሆን ሕዝብም ለሰላም በሚከፈል የአንድነት እና የአብሮነት መድረክ ላይ ሃሳብ በማዋጣት ኢትዮጵያን በማስቀጠሉ ሂደት ላይ ሚናውን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡

ሀገር በአንድ ሃሳብ አትጸናም። ዓለም የጸናችው በብዙ ሃሳቦች፣ በብዙ እምነቶች፣ በብዙ እሳቤዎች ተደግፋ ነው። እኛም ሀገር ለመስራት ሃሳብ ማዋጣት ቀዳሚው ሚናችን ይሆናል። ባልተዋጣና የአንድ ቡድን የበላይነት በተንጸባረቀበት መድረክ ላይ ሀገር አይሰራም።

ልብ ገዝተን በፍቅር ጸንተን ያለንን መቁጠር ብንችል ኖሮ ያለዋጋ ባሳለፍነው የእርስበርስ ጦርነት እንቆጭ ነበር። በይቅርታና በትእግስት ከዛሬ ወደነገ የሚያሻግር አእምሮና ልብ ብንታደል እስካሁን ባሳለፍነው የጥላቻና የሃይል ፖለቲካ አንገት እንደፋ ነበር። ባሳለፍነው የፖለቲካ ጨዋታ ነጥብ ከመጣል ባለፈ ያተረፍነው የለም። ዛሬም ያን የሞት ካርድ በመምዘዝ ለአዲስ የፖለቲካ ጨዋታ የምንሰናዳ ነን።

ኢትዮጵያ የምትባለው ትናንት ከፍ ብላ ዛሬ ዝቅ ያለችው ባለታሪክ ምድር በልጆቿ አንገት እንድትደፋ ማን ፈረደባት? ተነጋግረን እንዳንግባባ፣ ተወያይተን እንዳንስማማ አዚም ያሰራብን ማነው? ጎራዴዎቻችን የተሳሉት ወንድሞቻችንን ለመቅላት ነው። መሣሪያዎቻችን የተቀባበሉት ለእርስ በርስ ጦርነት ነው። አፎት እና ሰገባዎቻችን በወንድሞቻችን ደም ሌላ መልክ አበጅተዋል። ለምን?

እስኪ በፍቅር መሞትን እንልመድ።ከጥላቻ ሞት ወጥተን በፍቅር የምንሞትበት ጊዜ አሁን ይሁን። ስለወንድሞቻችን ግድ የሚሰጠን፣ ስለ ወገኖቻችን የምንጨነቅበት ጊዜ ይምጣ። የፈጠረን ያስተማረን እንዲህ አይነቱን ፍቅር እኮ ነው። መግደል አልተማርንም። በሌሎች ስቃይ ሳቃችን እንዲመጣ እግዜር አላስተማረንም። መነሻችን ፍቅር ነበር መድረሻችንም እርሱ ነው፡፡

በፍቅር እስካልሞትን ድረስ ሀገር መፍጠር አንችልም። የፍቅር ሞት ነው ሀገር የሚሰጠን። የአንድነት ሞት፣ የወንድማማችነት መንፈስ ነው የተሰወረብንን እውነት የሚመልስልን። ሰው ሞት የሀገር ሞት ነው። ሰው ስንገል ሀገር እየገደልን ነው። በእስካሁኑ የእርስ በርስ ሞታችን ኢትዮጵያን ነው የገደልናት። የሀገር ሞት እንዴት ያለ እንደሆነ እስኪ የቅርብ ጊዜውን የሰሜኑን ጦርነት እናስታውስ።

በሰሜኑ ጦርነት ኢትዮጵያ ሀገራችን ብዙ ነገር አጥታለች። ከሰው ሞት እስከ አካል መጉደል። ከኢኮኖሚ ድቀት እስከ ማህበራዊ ጉስቁልና። ከፖለቲካ ቁርሾ እስከ የታሪክ ጠባሳ እልፍ አጥተናል። እያንዳንዳቸውን ብናወራባቸው ወይም ደግሞ ብንጽፍባቸው ብዙ ሊያስወሩን እና ሊያጽፉን የሚችሉ ሀገራዊ ነውሮቻችን ናቸው። ባለፈው ዘመን ጦርነት ትናንት ላይ ብዙ ዋጋ እንደከፈልን የአደባባይ ሀቅ ነው። ድህነት እና ኋላቀርነት በዚህ ልክ ዋጋ እያስከፈሉን ያሉት በዛ ዘመን ፖለቲካ እና ትኩሳቱ ነው፡፡

ዛሬ ላይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነብን ድህነት እና የኑሮ መወደድ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው። በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም መንግሥትን ጨምሮ ሌሎች በጎ ፍቃደኞች እየተሳተፉ ነው። ይሄ ገንዘብ እና እውቀት፣ ይሄ ጉልበት እና ርብርብ ለሌላ ነገር ውሎ ቢሆን ሀገራችን ካለችበት አንድ ርምጃ መራመድ በቻለች ነበር፡፡

ጦርነት ነፍስ ብቻ አይደለም የሚበላው ታሪክ ያበላሻል። ከዛሬ የራቁ አዲስ ትውልዶችን የመመረዝ ኃይል አለው። ጦርነት የሌለበትን ፖለቲካ በጋራ መሥራት የኢትጵያን መጻኢ እድል መወሰን ነው። የዝቅታችን ሥፍራ ጥላቻ ወለድ ነው። ልባችን ከጥላቻ፣ አእምሯችን ከዘረኝነት ካልጸዳ የድሮዋን ኢትዮጵያ መመለስ አንችልም። እንደ ጥላቻ የሰው ልጅ ነፍሱን የሚቀጣበት ለበቅ የለውም፡፡

በድህነት እና በኋላቀርነት እየተቀጣን ያለነው በጥላቻ ፖለቲካ ነው። ፖለቲካችን ከጥላቻና ከዘረኝነት፣ ከጦርነት እና ከኃይል ፈቀቅ ካላለ ራሳችንን የምንታደግበት ሌላ መንገድ የለንም። አድሮ ቃሪያ ለሚለው ተረት ጥሩ ማሳያዎች እንሆናለን። አድሮ ቃሪያ ለውጥ እና መሻሻል የሌለው ማንነት ነው። ከትናንት እስከዛሬ ሀገር በመቀየር መንፈስ ውስጥ የቆምን ነን። ትግላችን፣ ምክክራችን ከዝቅታ ካላነሳን አድሮ ቃሪያ ማለት ያ ነው፡፡

ከደም ወደ ሰላም፣ ከጥላቻ ወደፍቅር እስካልተሸጋገረን ድረስ ከዕረፍት ምኩራባችን አንደርስም። በብዙ ሞኝነት ውስጥ የቆምን ነን። ፖለቲካ የሚዳብረው በመመካከርና በመወያየት እንደሆነ ገና አልገባንም። የራስን ሃሳብ እና የጥቂት ቡድኖችን ፍላጎት በህገወጥነት ማራመድ የዘመነና የለውጥ ፈጣሪ ፖለቲካ መገለጫ አይደለም፡፡

ሞኝነታችን ላይ ብንደርስ እንዴት ጥሩ ነበር። ልክ የሆነውን ደብቆ ልክ ያልሆነ ነገር እያሠራን ከሰው በታች ያደረገን የትዕቢት፣ የራስ ወዳድ ፖለቲካችን ቢቀየር እንዴት መልካም ነበር። ዓለምን ያደመቀ ባህልና ሥርዓታችንን ሽሮ እርስ በርስ እንድንጨካከን፣ እርስ በርስ እንድንገዳደል ያደረገን የሞኝ ፖለቲካችን ቢሻር ያኔ ዳግም ልደታችን ነበር።

ልብ የሙላት ካዝና ነው። ፍቅር ካለበት ደግሞ እንደ እግዜአብሔር መንበር ነው። አንድ ሀገር ለመሥራት የተለያዩ ልቦች ያስፈልጉናል። የተለያዩ ሃሳቦች ከተለያዩ ልቦች ነው የሚወጡት። በእነዛ የተለያዩ ሃሳቦች ላይ ቆመን ነው ለሁላችን የምትበቃውን አንድ ሀገር የምንሰራው። በፍቅር ልቦች የፍቅር ሀገር እስካልሠራን ድረስ ከመከራ ማምለጫ መንገድ የለንም፡፡

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 15 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You