የሁሉንም ልዩ ትኩረት የሚሻው የማህበራዊ ሚዲያው ሴረኞች አጀንዳ

 አሁን ያለንበት የዲጅታል ዘመን የሰውን ልጅ በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር በዓለም ዙሪያ ያለን ግንኙነት ማቀላጠፍ የሚያስችል ነው። ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው ጊዜ፣ ጉልበት እና ወጪን የሚቆጥቡ ቴክኖሎጂዎች በቀላሉ በመጠቀም በዓለም ዙሪያ የፈለጉት መረጃ በፍጥነት የሚያገኙበት እየሆነ ነው። ይህ ደግሞ የሰው ልጆች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ከቴክኖሎጂ ጋር ያለው ቁርኝት እንዲጨምር እና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት እንዲጎለበት ምክንያት ሆኗል፡፡

ይህም ቀደም ሲል ሰዎች ከዓለም ዙሪያ ያሉ መረጃ ለማግኘት ይጓዙበት የነበረው ዙሪያ ጥምጥም መንገድ አጭር በማድረግ ርቀትና ጊዜ ሳይገደባቸው በቀላሉ የሚፈልጉትን የሚያገኙበት ማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች እንዲበራከቱም አድርጓል፡፡ እ.ኤ.እ 2022 መጀመሪያ አካባቢ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች አሀዛዊ መረጃ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ያህል መድረሱን ነው፡፡

ፌስቡክ፣ ቴሌግራምና ኢንስታግራምን እና ቴክቶክ የመሳሰሉ የማህበራዊ ሚዲያዎች ተጠቃሚዎች የሚያጠቃልለው ይኸው መረጃ፤ በሀገሪቱ 30 ሚሊዮን ያህል የኢንተርኔት ተጠቃ ሚዎች መኖራቸውንም ያመላክታል። ይህን ያህል የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መኖር ደግሞ ዲጅታላይዜሽንን ከማስፋፋት አንጻር እንደሀገር ያለንበትን ደረጃ የሚያሳይ ነው፡፡

በርግጥ አጠቃላይ ከሆነው የሀገሪቱ የሕዝብ ቁጥር አንጻር የተጠቃሚው ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም፤ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚው አጠቃቀም ግን ከጥያቄው ውስጥ የሚገባ ጉዳይ መሆኑ ውሎ አድሯል ፡፡ የማህበራዊ ሚዲያን ዓላማውን እና አስፈላጊነት ተረድተው ለበጎ ዓላማ የሚጠቀሙ ያሉትን ያህል በተቃራኒው ለእኩይ ዓላማቸውና ግባቸው ለማስፈጸሚያ የሚጠቀሙበት አካላት እየተበራከቱ ነው፡፡ ለዚህም ሩቅ መሄድ ሳያስፈልገን በሀገራችን በተደጋጋሚ ከሚከሰቱ ግጭቶች ጀርባ ያሉትን የማህበራዊ ሚዲያ ሴረኞች መመልከት በቂ ነው፡፡

አበው ‹‹ ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ›› እንዲሉት ሆኖ የዘመኑ የማህበራዊ ሚዲያ ሴረኞች የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም ይህንን አባባል በተግባር የሚተረጉሙ “የበለው በለው” አይነት መርዛማ ፣ አጋዳይና አባባሽ አጀንዳቸውን መርጨታቸው የተለመደ መጥቷል፡፡ እነዚህ ሴረኞች ይህንን ሴራ ከጀመሩት ረዝም ያለ ጊዜን ያስቆጠሩ ቢሆንም እንዳሁኑ ባስ ብሎ ዓይኑን አፍጥጦና ጥርሱን አግጥጦ አፈሙዙን ሕዝብ ላይ ደቅኖ ሀገር ለማፍረስ የተሰራበት ጊዜ ግን ያለ አይመስለኝም፡፡

ሴረኞቹ እቤታቸው ቁጭ ብለው ተዝቆ የማያልቅ ብር እየተከፈላቸው ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቅመው መንግሥት ከሕዝብ፣ ሕዝብ ከሕዝብ፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት፤ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት አጀንዳ አድርገው አስበው፣ አሲረውና በእቅድ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ የተለያዩ ስልቶች እየቀየሱ ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ ከምንም ጊዜውም በላይ ያለና የሌለ ኃይላቸውን አጠራቅመው ሆን ብለው የሚነዙት የጥፋት አጀንዳ ሕዝብ እና ሀገር ዋጋ የሚያስከፈል ፤ እያስከፈለን ያለ ጉዳይ ነው፡፡

የእነዚህ ሴረኞች አካሄድ እጅግ አደገኛና ሀገር የማፍረስ ተልዕኮን ያነገበ መሆኑ ደግሞ በእጅጉ ጉዳዩን በትኩረት እንደናየው የሚያደርግ ነው፡፡ መነሻቸውን የሚያደርጉት ብዙ አጀንዳዎች ያላቸው ቢሆንም የወቅቱ የሀገሪቱ ትኩሳት የሆኑ አጀንዳዎች በመከተል ሀገርና ሕዝብን ወደ ባሰ ግጭትና አዘቀት የሚያስገቡ ድርጊቶች እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም ሰሞኑን በአማራ ክልል የተነሳውን ግጭት መመልከት ይቻላል፡፡ በክልሉ የተነሱ ግጭቶችን ለማባባስ የሚያ ስችላቸው አጀንዳ ቀርጸው ሕዝቡን ለማነሳሳት መንግሥት ቅርሶችን አውድሟል አስከሚል ድረስ ሀሰተኛ መርዝ በመርጨት አደገኛና አባባሽ አጀንዳዎች ሲነዙም እንደነበር እናስታውሳለን። ይህም አካሄዳቸው ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡

በተመሳሳይም ለአንድ ብሔር ወገንተኛ ሆነ የብሔሩን ጉዳትና ጭቆና በማንሳት ተቆርቋሪ ሆኖ በመቅረብ አንዱን ብሔር ከሌላ ብሔር ለማጋጨት የሚያስችላቸውን አደገኛ አካሄድም ይከተላሉ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያሉ በሕዝብ ከሕዝብ እያጋጩ የሚፈልጉትን የፖለቲካ ትርፍ ለማፈስ የማይረጩት መርዝ የለም፡፡ ይህንን እኩይ ተግባራቸውን የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡

እንደዚህ በሀገርና በሕዝብ ላይ እየቀለዱ ብዙዎችን ለሞት ፤ ብዙዎችን ደግሞ ለስደት ዳርገው ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስን እየፈጠሩ ሀገር ለማፍረስ የሚጥሩ ሆድ አደሮች መኖራቸው የሚገርም ባይሆንም ሌሎች ደግሞ አውቀውም ሆነ ሳያውቁም እነዚህ ሴረኞች እየተከተሉ ‹‹እንዲህ ሆኗል –እንዲህ ሊሆን ነው›› እያሉ ባልተጣራ መረጃ ሕዝቡን ለማወክ የሚጥሩ መኖራቸው ለችግሩ ተጨማሪ ከብደት ሆኗል፡፡

እነዚህ ኃይሎች ሀገርን ወደ ሁከትና ጥፋት የሚወስዱ አጀንዳዎችን በተደጋጋሚ ይዘው አደባባዮችን ለመሙላት የሄዱባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው፡፡ ‹‹ውሻ በበላበት ይጮሃል›› እንደሚሉት ሆኖ ለፖለቲካ ትርፋቸው ብለው ሕዝብና ሀገር ላይ ጦርነት ከፍተው የመርዝ ብልቃጣቸውን እየረጩ መሆኑ የማይካድ ሃቅ ነው፡፡

እነዚህ አካላት የሚያሰራጩትን ሀሰተኛ መረጃ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እውነተኛ መረጃ አድርጎ በማቅረብና ለሌሎችም ከማጋራት ይልቅ እኩይ ድርጊታቸውን ማጋለጥ ቢቻል ሕዝብና ሀገር መታደግ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ባይቻል እንኳን ቢያንስ የድርጊታቸው ተባባሪ አለመሆን ይቻላል፡፡

ሀገር እንደ ሀገር የነበረባት መከራ እጅግ ከባድ መሆኑን መገንዘብ የሚያቅተው ያለ አይመስለኝም። በጦርነት አዙሪት ውስጥ የቆየችው ሀገራችን ችግሮቿን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ደፋ ቀና በምትልበት በዚህ ጊዜ ደግሞ በእነዚሁ ባለአጀንዳ ሴረኞች ወደ ኋላ እንድትመለስ እየጎተተች ነው፡፡

በማህበራዊ ሚዲያ አማራጮችን የሚጠቀም የህብረተሰብ ክፍል ሁሉ ይህንን ጉዳይ ሳያጤን ቀርቷል የሚል እምነት የለኝም፡፡ አሁን ላይ ያለው የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚው እነዚህን አካላት በዝምታ ሊያልፏቸው አይገባም ባይ ነኝ። በሀገርና በሕዝብ እየቀለዱ የሚኖሩት እስከመቼ ነው፡፡ ዝምታችንስ እንከምንድረስ ነው የሚለውን እያንዳንዳችን በጥልቀት ማሰብ ያለብን ጉዳይ ነው። ከእንግዲህ ድርጊታቸውን በማጋለጥ የሚረጩት የመርዝ ብልቃት እነሱን መልሰው እንዲጋቱት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ይህ የሚሆነው ሁላችንም በትብብርና በመደጋገፍ ስንስራ ነው። ሁሉም ዜጋ ሀገርን በማሻገር ለትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት አለበት፤ እያጋጠሙ ያሉ ብዙ ጋሬጣዎችን በመሻገር ለድል መትጋት ይጠበቅበታል፡፡ ይህንን ማድረግ ደግሞ ለነገ የማይባል ኃላፊነታችን ነው፡፡

እነዚህን የእኩይ ድርጊት ባለቤቶች በማሳፈር እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱ ማድረግ ይገባል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ጊዜው አሁን ነው፡፡ የትብብርና የአንድነት መንፈስን ተላብሰን በርትተን ከሠራን ሀገራችንን ከእነዚህ ሆድ አድሮች መታደግ እንችላለን፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ሀገራችን ወደ ብልጽገና የምታደርገውን ጉዞ የምናሳካበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ባይ ነኝ፡፡ አበቃሁ! ቸር እንሰንብት።

 ትንሳኤ አበራ

 ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 15 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You