ሰላም አማራጭ የሌለው አዋጩ መንገድ ነው!

 ሰላም ከሌለ ነገ የለም። ስለ ነገ ማሰብም ማቀድም የሚቻለው በሰላም ውስጥ ነው፡፡ ለዚያም ነው ሰላም የሁሉ ነገር ዋስትና ነው የሚባለው፡፡ ሠርቶ የመለወጥ፣ ወልዶ የማሳደግ፣ ወጥቶ የመግባት፣ በአጠቃላይ ሰላም በሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ተግባር ውስጥ ከምንተነፍሰው አየር ያልተናነሰ ዋጋ አለው፡፡

በሀገር ደረጃ ባለፉት ዓመታት ሰላምን ለማስፈን የሰላም ሚኒስቴር ከማቋቋም ጀምሮ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል። ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የዳበረ ዴሞክራሲን የማጽናት፣ የላቀ ብሔራዊ መግባባትን የመፍጠር፣ የሰላም ግንዛቤና ሁለንተናዊ ተሳትፎን የማሳደግ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል።

በተጨማሪም ማኅበራዊ ሀብቶቻችንንና ባህላዊ እሴቶቻችንን በመገንባት ሂደት በተለይም የሰላም እናቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት ተቋማት በባለቤትነት እንዲሳተፉና እንዲያግዙ በማድረግ ለዘላቂ ሰላም ምቹ ምህዳር ተፈጥሯል። ከሲቪክ ማኅበረሰቡ ጋር በመሆን ሰላምን በማስፋፋት፣ ግጭትን በመከላከልና ዴሞክራሲን በማስፈን ላይ በቅንጅት ለመሥራትም ተሞክሯል።

ሰላም ማለት የግጭት አለመኖር ማለት አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት ባልነበረባቸው ዘመናት ሁሉ፣ ለግጭት የሚዳርጉ ቅራኔዎች መብላላታቸውን አያቋርጡም፡፡ በመሆኑም ጊዜ ጠብቀው ለግጭት መንስኤ መሆናቸውን በዘመናት ታሪካችን ታዝበናል። ሆኖም ቅራኔን በመነጋገርና በመወያየት ከመፍታት ይልቅ በኃይል መፍትሔ መፈለጉ ውድ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ግጭቶች ሌላ ግጭት እየወለዱ የግጭት አዙሪት ውስጥ ተነክረን ሰላም አልባ ዘመናትን አሳልፈናል። ይህም በድህነታችን እንድንቀጥል ካደረጉን የልማት ወጥመዶች መካከል አንዱና ዋነኛው እንዲሆን አድርጓል።

የእርስ በርስ ግጭት አንድን ሀገር ከፍተኛ የኢኮኖሚ ውድመት ውስጥ እንደሚከትና በተለይ የርስ በርስ ግጭቱ እየተራዘመ በመጣ ቁጥር ከግጭቱ የሚያተርፉ አካላት እየበረከቱ ስለሚመጡ ለቀጣዩ ግጭት መፈጠር በር የሚከፍት ሲሆን ታዝበናል፡፡ ለዘመናት ሲዘሩ የቆዩ የጥላቻና የመከፋፈል ዘሮች ፍሬ አፍርተው ህብረተሰባችንን ያስተሳሰሩት ክሮች እየላሉና እየተበጣጠሱ የመጡበትና ተስፋ መቁረጥ የተንሰራፋበት ስለሆነ ከበድ ያሉ መንገራገጮችን ልንቋቋም የማንችልበት ደረጃ ላይ እንዳያደርሱን ለሰላም ትኩረት መስጠት ግድ ይለናል። ይህም “ምክንያታዊ” ሆነን ሰላምንና የሰላምን መንገድ መከተል አማራጭ የሌለው መሆኑን ያሳየናል፡፡

በዚህ ረገድ መንግሥት ፍትሃዊነትን በማስፈን፣ ዴሞክራሲን በማስረፅ፣ የፍትሕ ተቋማትንም ገለልተኛ እንዲሆኑ በማድረግ ለዜጎች ለሰላም ትኩረት መስጠቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በሰላም ዙሪያ የሚሠሩ አካላት የሃይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች በእርግጥ አሁን ባለንበት ሁኔታ ሰላምን ለማስፈን ከእኛ ምን ይጠበቃል? ብለው ራሳቸውን መጠየቅና ተግተው መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡

ሰላማዊ ትግል ዋጋ እንደሚያስከፍል የታወቀ ቢሆንም ምናልባት ጦርነት ከሚያስከፍለው ሊበልጥ እንደማይችል ፀሐይ የሞቀው ሃቅ ነው። በሰላማዊ መንገድ የተገኘ ድል ዘላቂነት ይኖረዋል፣ ይህ ብቻም ሳይሆን ሰላማዊ ትግል የማካሄድ እንቅስቃሴ የሚመሠረትበት መርህ ከሰው ልጅ የኑሮ ግብና ዓላማ፣ ከሕይወት ምንነት፣ ከሰላምና ግጭት/ጦርነት ተቃራኒነት አንጻር ሲታይ የሰላም መንገድ ሚዛን መድፋቱ ሊዘነጋ አይገባም፡፡

ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ሁሌም ሰላም ወዳድ እንደሆኑ አያሌ የታሪክ ክስተቶች ምስክር ናቸው። ይህንንም ባለንበት ዘመን እንኳን ደጋግመው አሳይተዋል። ኢትዮጵያውያን ያልሻረ ቁስል ይዘው እንኳ እጃቸውን ለሰላም ከመዘርጋት ተቆጥበው አያውቁም፤ የሰላምን ዋጋ ያውቁታልና።

ነፍጥ ከማንገብ ምንም ትርፍ እንደማይገኝ መናገር ለቀባሪው የማርዳት ያህል ነው። ጦር በመስበቅ አምራች የሆነው ወጣቱ ክፍል እንደቅጠል ከማርገፍና የሀገር ኢኮኖሚን ከማድቀቅ የዘለለ ፋይዳ አልተገኘበትም። በየአቅጣጫው ለሰላም የሚከፈለው መስዋዕትነት ግን ከምንም በላይ ሃያል ነው፡፡ የኢትዮጵያ የሰላም ፖሊሲና የማስፈጸሚያ ፍኖተ-ካርታን ማዕከል ያደረገ፣ ሰላምን በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በማኅበረሰብና በተቋም ደረጃ በማስረጽ፣ የዜጎችን፣ ወጣቶችን በጎ ፈቃደኝነትንና የመስጠት ዜግነታዊ ኃላፊነትን የሕይወት ዘመን ባህል እንዲሆን በማድረግ የትውልዱ የቤት ሥራ ነው፡፡ ማኅበራዊ ሀብቶች፣ እሴቶችና ብሔራዊ ጥቅሞች በተልዕኮ ስምሪት ውስጥ ተካተው በመተግበር ሁለንተናዊ ዘላቂ ሰላምን የመገንባት ሥራ ተግባራዊ ማድረግን ይጠይቃል።

ሰላምን ለማምጣት ከታሪካዊ ቅራኔዎቻችን ይልቅ ለታሪካዊ መግባባታችን ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም፣ ፍቅርና ብልጽግና ትመኛለች፡፡ ለዚህ ምኞት ተግባራዊነትም ኢትዮጵያዊ በሙሉ እንደ እህትና እንደ ወንድም በአንድነት ለመነጋገር፣ ለመሥራት እንዲሁም በጋራ ለመጠቀም በንጹህ ልቦና መዘጋጀትን ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም የጋራ አሸናፊነት መሣሪያ የሆነውን ሰላም ማንገብ ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ ራስን ከግጭት ነጋዴዎች ለማራቅ ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል። ሁሌም ግን ምርጫው አንድ ነው፣ እሱም የበለጠ ዋጋ የማያስከፍለውን የሰላም መንገድ መከተል!

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 15 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You