
አዲስ አበባ:- የትኛውም አካባቢ የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠልና ግሽበቱን ለመቆጣጠር ግጭት ማቆምና ሰላም ማስፈን ይገባል ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ክቡር ገና ገለጹ።
አቶ ክቡር ገና ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ሰላም ማስፈን ከተቻለ የኢኮኖሚ ችግሮችን ለመፍታትና ኢንቨስትመንትን ለማስፋትም ዕድል ይኖራል።
የዋጋ ግሽበት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እንደሚገኝ ያነሱት አቶ ክቡር፤ ለዚህም ብዙ ምክንያቶች አሉ፤ አንዳንዶቹ እንደነዳጅ ጭማሪ ያሉት ከሀገራችን ቁጥጥር ውጪ የሆኑና ውጫዊ ምክንያት ያለው ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ነገር ግን በጦርነት ምክንያት የሚፈጠረው ግሽበት ምርት እንዲቀንስ አድርጓል። ወደገበያ የሚገባው ምርት ከበፊቱ ያነሰ በመሆኑና ፍላጎትም ስለሚጨምር የነጻ ገበያው የሚያመጣው ግሽበት እንደሚስተዋልም አስረድተዋል።
ሰላም ባለመኖሩም ብዙ ባለሀብቶች ሥራ ለመጀመር፣ የሥራ ዕድልም ለመፍጠር አይሯሯጡም። በመሆኑም ግጭት ሲፈጠር ምርትን መጠቀም እንጂ ማምረት አይኖርም፤ በመሆኑም ሰላም ይበልጥ በማስፈን ምርታማነትን ማጎልበት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የሰላም መደፍረሶች መቆም አለባቸው ያሉት አቶ ክቡር፤ ነጋዴውም ወደ ንግድ ስራው መመሰስ እንደሚጠበቅበትና ኢንቨስትመንት መስፋፋት እንደሚኖርበት ገልጸዋል።
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ ከዚህም በላይ ሊሄድ የሚችለውን ግሽበት መንግሥት በተለያየ ዘዴ ተቆጣጥሮ ይዞታል። በቀጣይም ግሽበቱን ሊቆጣጠርባቸው የሚችልበት ሁኔታዎች አሉ።
አዳዲስ ኩባንያዎች ተከፍተው ሥራ መጀመርና መንቀሳቀስ ሲጀምሩ ግሽበቱ እንደሚቀንስ ነው የጠቆሙት።
ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የሚታዩ የሰላም እጦቶች ኢኮኖሚውን እንደሚጎዱና ግሽበቱን ለመቆጣጠር አዳጋች ሁኔታ ስለሚፈጥሩ ይበልጥ በቁጥጥር ስር መዋልና ለኢኮኖሚ ዕድገት ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዳለበት አሳስበዋል።
በሰላም እጦት ለተቸገሩ የማህበረሰብ ክፍሎች የሥራ ዕድል መክፈት፣ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ማገዝ የሚችሉበት ሁኔታ ማመቻቸት፣ ትምህርት ቤቶችን አድሶ ልጆቻቸው ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
የጤና ማዕከላት በተጠናከረ ሁኔታ ሥራ እንዲጀምሩ፣ ሃኪሞች ዳግም ወደ ስራቸው እንዲመለሱ የማድረግ ተግባራት ማከናወን እንደሀ ሀገር ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
በዚህ ሁሉ ሂደት ዜጎች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ኢኮኖሚው እንዲጠናከር የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 10/2015