ሴቶች በፖለቲካዊ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ መስኮች ያላቸውን ተሳትፎና የመሪነት ሚና እንዲሁም ሀገሪቱ ውስጥ በሚካሄዱ የልማት ተግባሮች ውስጥ ያላቸውን ተጠቃሚነት ከፍ በማድረግ ረገድ መንግሥት ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን አድርጓል፤ በማድረግ ላይም ይገኛል። ይህም እንደ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል ሁሉ ሴቶችም ሀገራቸውን በመምራት፣ በልማት ላይም ንቁ ተሳታፊ በመሆን እያደረጉ ያለውን ሁለንተናዊ ጥረት የሚደግፍ ከመሆኑም በላይ ለሀገር እድገት የሚኖረው ሚና የጎላ ነው።
በሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረውን የሴቶችን የተጠቃሚነት መብት ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች በተለያዩ ዘርፎች ላይ ተጠቃሚነታቸው የተረጋገጠ ሲሆን ወደፊትም እነዚህ መብቶቻቸው በተጠናከረ ሁኔታ ይረጋገጡላቸው ዘንድ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት ሰፋፊ ጥረቶች በመከናወን ላይ ናቸው።
ይህም ሴቶች ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስችሏቸዋል። ለምሳሌ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በስልጠና፣ የብድር አገልግሎት በማመቻቸትና የቁጠባ ባህላቸውን የሚያበረታታ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ በገቢ ራሳቸውን የቻሉ ይሆኑ ዘንድም ያልተቋረጠ ጥረት በመደረግ ላይ ነው።
በሕገ መንግስቱ ጥበቃ ያገኙት እንደ ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደርና የመቆጣጠር መብታቸውም ሙሉ በሙሉም ባይሆን ስለመረጋገጡ ግን ብዙ ማሳያዎች አሉ። በሌላ በኩልም ሴቶች በትምህርት ዘርፉ ራሳቸውን አብቅተው ከወንዶች እኩል በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ላይ እንዲገኙ በማድረጉም በኩል በርካታ ሥራዎች የተከናወኑ ከመሆኑም በላይ አመርቂ የሚባሉ ውጤቶችም ተመዝግበዋል።
የሴቶችን እኩል የመሬት ተጠቃሚነትን መብት ለማረጋገጥ የክልል መንግሥታት የመሬት ተጠቃሚነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት በአባወራዎችና በእማወራዎች ስም በጥምር የመመዝገብ ርምጃ በመውሰዳቸውም፤ ሴቶች ከትዳር አጋራቸው ጋር የሚያፈሩት ሀብት ላይ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖራቸው አስችሏል ።
የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ ነው። በዚህም በተሳተፉባቸው ቦታዎች ሁሉ ተሰሚነትን፤ ተፈላጊነትን ከማግኘታቸውም አልፎ ተርፎም ለሀገር በርካታ አበርክቶዎችን ማዋጣት ችለዋል።
ይህንኑ በተመለከተ የሀላባ ዞን ሴቶችና ሕጻናት መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ወይዘሮ ዘቢባ መሀመድ እንደሚሉት በዞኑ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማስፋት የሚያግዙ በርካታ ሥራዎች ይከናወናሉ። መምሪያው በሕግ የተሰጡት ተግባርና ኃላፊነቶች መሠረት በማድረግ የተሻሉ ሥራዎችን እየሰራ ነው።
እንደ ወይዘሮ ዘቢባ ገለጻ ሴቶችን በእውቀት በማብቃት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ ከማድረግ ጀምሮ ወደ አመራርነቱም እንዲመጡና ችግሮቻቸውን እና ውስንነታቸውን በራሳቸው እየፈቱ ለሌሎች ብርሃን የሚሆኑበትን ሁኔታ በማመቻቸቱም በኩል ሰፋፊ ሥራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑ ያብራራሉ።
የሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ሥራ መምሪያው ከሚሰራቸው ሥራዎች ውስጥ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ፕሮግራም የሚሳተፉ ሴቶች ብድር እንዲያገኙና የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፤ ከጥቃቅን ወደ አነስተኛ፣ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ፣ ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚሸጋገሩበት አቅጣጫ ተቀምጦም ተግባራዊ እንዲሆን በመደረጉ በመስኩ ያላቸው ተጠቃሚነት ከፍተኛ ሊሆን ችሏል ይላሉ።
በዚህ ረገድ ያገኘኋቸው መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ መንግሥት በጥቃቅንና አነስተኛ ልማት መስክ 50 በመቶ የሚሆነውን የሥራ ዕድል ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረገ እንዲሆኑ በማሰብ በከተማ ልማት ፓኬጅ ግብ ውስጥ እንዲካተት ስለመደረጉም ያብራራሉ።
በዚህ ግብ መነሻነትም በርካታ ሴቶች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል የሚሉት ወይዘሮ ዘቢባ በመንግሥት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ ካለው የሥራ ዕድልም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የዞኑ ሴቶች እንዲሳተፉና እንዲጠቀሙ ስለመደረጉም ነው ያስረዱት።
በሌላ በኩልም በተለይም በገጠሩ አካባቢ ሴቶች በቤት ውስጥ ያሉባቸውን ጫናዎች ለማቃለል የሚያግዝ የንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እንዲኖር በማስቻል የሴቶች ሕይወት ቀላል እንዲሆን ለማድረግ መቻሉንም ይገልጻሉ። ይህም ሴቶች ረጅም ርቀት ተጉዘው የሚያባክኑትን ጊዜና ጉልበት በመቀነስ በምርት ተግባር ላይ እንዲያውሉ አድርጓቸዋል እንደ ወይዘሮ ዘቢባ ገለጻ።
ከዚህ በተጨማሪ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገት በማሳየቱ፤ በርካታ የገጠር ከተሞችንና ቀበሌዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ከመቻሉም በላይ፤ የሴቶችን ተጠቃሚነት የጎላ እንዲሆን አድርጎታል። የአገልግሎቱ መስፋፋት ሴቶችን ወጪ፣ ጊዜና ማገዶ ቆጣቢ በሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዲጠቀሙ አስችሏቸዋል።
በማህበራዊ መስክም ሴቶች ተሳትፏቸውና ተጠቃሚነታቸው እየጎለበተ መጥቷል የሚሉት ወይዘሮ ዘቢባ በተለይ “ሴት ልጅ ወደ ማጀት” የሚለውን ጎታች የህብረተሰቡን ባህልና አመለካከት በመቀየር፣ የትምህርት ተሳትፏቸውን የሚገድቡ እንቅፋቶችን የማቃለልና የመደገፍ ተግባራት ገቢራዊ ተደርጓል።
በሌላ በኩልም የሴቶችን መብት ከማስከበር አኳያ የመውረስ መብታቸው እንዲረጋገጥ በዚህም ሀብትን በጋራ አፍርተው የማስተዳደር እድልን አግኝተዋል። ይህ በቀደመው ጊዜ ለወንዶች ብቻ የተፈቀደ ከመሆኑ አንጻር በአሁኑ ወቅት ሴቶችንም ማሳተፍ መቻሉ ትልቅ እመርታ መሆኑን ይናገራሉ።
ሴቶች በሕገ መንግሥቱ በግልጽ የተቀመጡላቸው መብቶች በሙሉ መሬት ወርደው ተግባራዊ ይሆኑ ዘንድም በተለይም በዞኑ እስከ አሁን ድረስ ችግር ሆኖ የቆዩ ለምሳሌ እንደ ውርስ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና የመሳሰሉት ዘመኑን የሚመጡኑ እንዳልሆኑ በማስተማር ሴቶችን ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ሰለባነት ነጻ የማድረግ ሥራዎች መከናወናቸውን ያብራራሉ።
በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች አካላዊ ብቻ አይደሉም የሚሉት ወይዘሮ ዘቢባ ሥነ ልቦናዊም እንዲሁም ጾታዊም ጥቃቶች አሉ፤ እነዚህ ሁኔታዎች መጠናቸው መብዛት ማነሱ ሳይሆን ሁሉም ለሴቷ ፈተናና ጉዳት ናቸው በመሆኑም እነዚህን ድርጊቶቹን በማስቆም በኩል ዞኑ ከፖሊስ አቃቤ ሕግና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ስለመሰራቱም ይናገራሉ።
በዘንድሮው ዓመት ብቻ በዚህ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ ሁለት ሰዎች እስከ 16 ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ ተደርጓል፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ ወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ከመሆኑም በላይ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በዘለቄታዊነት ለመቀነስም መምሪያው በሙሉ አቅሙ እየሰራ ስለመሆኑ አስረድተዋል።
ከተሳትፎ አኳያ የሴቶች አጀንዳዎች በሁሉም ዘርፎች እንዲካተቱና የሴቶችም ተጠቃሚነት በሁሉም ደረጃ እንዲረጋገጥ የሚያደርጉ ሥራዎች መሰራታቸውን ወይዘሮ ዘቢባ ጠቁመው ሴቶች በተለይም በትምህርቱ ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በሚማሯቸው ትምህርቶች ዙሪያ የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲያገኙ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ ሴቶች በሁሉም ዘንድ ግንባር ቀደምና በተሰማሩበት ዘርፍም ውጤታማ እንዲሆኑ ቤተሰብ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ቤተሰብ ሴት ልጆቹን ከወንዶቹ እኩል ያለምንም ተጽዕኖ ወደ ትምህርት ቤት እንዲልክና እንዲከታተል የሚያደርግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራም በየጊዜው እንደሚሰራ ነው ያብራሩት።
በዚህ ሥራም ከፍ ያሉ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው ያሉት ወይዘሮ ዘቢባ ውጤቱን እየተመረኮዝን በየዓመቱ በሴቶች ቀን (ማርች 8) እውቅናን እየሰጠን ስለምንሄድ ውጤታማነቱም ከአመት አመት እየጨመረ ነው ብለዋል።
“በዞኑ እንደ ግርዛት፣ ጠለፋ እና ሌሎችም ዓይነት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሰፊው ይስተዋላሉ፤ ከግርዛት ጋር ያለውን በሕጻናት ፓርላማ ፣ አስገድዶ መድፈርንና ድርብ ጋብቻን በተመለከተ ባሉት የሴቶች አደረጃጀቶች በሙሉ ሥራዎች እንዲሰሩ በማድረግና ሴቶችም በዚህ ላይ ራሳቸውን ከመጠበቅና ከመከላከል ብሎም ድርጊቱ ሲፈጸም ያለምንም መሸማቀቅ ወጥቶ በማጋለጥ በኩል ሚናቸውን እንዲወጡ ሰፊ ጥረቶች እየተደረጉ ነው” ብለዋል።
እዚህ ላይ ግን ይላሉ በተለይም አንዳንዶቹ ድርጊቶች የባህል ድጋፍም ያላቸው በመሆኑ እንደ ዞንም እንደ መምሪያም ለመሻገር ገና ብዙ ሥራን የሚጠይቁን ናቸው። ነገር ግን የሴቶቸን መብትና ደህንነት ከመጠበቅ አንጻር በተለይም የሕግ ጉዳዩን ትኩረት ሰጥተነው እየሄድንበት ነው፤ ከሕጻናት ግርዛት ጋር ተያይዞ ደግሞ ወረዳውም አሰራሩን ትራንስፎርም እያደረገ በመሆኑ የተሻለ ለውጥን ያመጣንበትና ወደፊትም ትልቅ ውጤት እናያለን ብለን የምንጠብቀው ነው ይላሉ።
በቀጣይ ዞኑን በተለይም ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊት በተለይም ከግርዛት ጋር ያለውን ትራንስፎርም ለማድረግ እየሰራን ነው። ይህንን ለማስፈጸምም ከአመቱ እቅዳችን ላይ የአስቸኳይ የሩብ ዓመትና የመንፈቅ እያልን እያወጣን በመሯሯጥ ላይ በመሆናችን ከፈጣሪ ጋር ግቡን እንመታለን ይላሉ።
መምሪያው የሴቶችን ሁለንተናዊ ደህንነት ለማስጠበቅ በዚህን ያህል ደረጃ ይሩጥ እንጂ በርካታ ክፍተቶችም አሉበት የሚሉት ወይዘሮ ዘቢባ ለምሳሌ የበጀት የተሽከርካሪ የባለሙያና ሌሎች ችግሮች አሉበት። ነገር ግን ያለውን ባለሙያና አመራር አቀናጅቶ በመጠቀም የእምነት ተቋማትና የሀገር ሽማግሌዎች ጉዳዩን የራሳቸው አድርገው እንዲሰሩበት በማድረግ ችግሮቹን ለማለፍ ከፍ ያለ ጥረት እየተደረገ ነው ይላሉ፡፡
“የሴቷ ጉዳይ የእሷ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ነው የሚል የወንዶች ተሳትፎ በጣም ያስፈልጋል። የሴቶችን ጉዳይ የሚመለከት ተቋም ስለተቋቋመ ብቻ ችግሩን እናልፈዋለን የሚፈለገውንም ለውጥ እናመጣለን ማለት አይቻልም። በመሆኑም ተቋሙም ተሻጋሪ ችግሩም እንደዛው ተሻጋሪ በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በያገባኛል መንፈስ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል” ይላሉ።
ወንድ ባል ነው ፣ ወንድምም ነው፣ በመሆኑም መዋቅር አለው ብሎ መተው ብቻ ሳይሆን የሴቷ ጉዳይ የእናቴ የእህቴ የልጄ ጉዳይ የእኔም ነው ብሎ ከማንም ቀድሞ በማሰብ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል በማለት መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 9/2015