አዲስ ዘመን ድሮ

 ለቀስተኛው ተሰባስቦ ደረቱን እየደቃ በማልቀስ ላይ ሳለ፤ የሞቱት አዛውንት በድንገት ተነስተው የተሰበሰበውን ሕዝብ በማየት በአግራሞት ‹‹ምንድነው ጉዱ›› ሲሉ ሟች መልሰው ጠይቀዋል….እንዴትስ ሊሆን ቻለ? አዲስ ዘመን ድሮ ለየት ያለ ጉዳይ ይነግረናል፡፡ ለዛሬ መልሶ ቅኝታችንን በ1958 ዓ.ም የአዲስ ዘመን ገጾች ላይ አድርገናል፡፡ በዋናነት ደግሞ አንባቢያን ሃሳባቸውን እንዲሁም ጥያቄዎቻቸውን እንደ ልብ ከሚያንሸራሽሩበት ከወይዛዝርት ገጽ ላይ ካገኘናቸው ሃሳቦች ለዛሬው ይሆናሉ ያልናቸውን እንደሚከተሉ አስፍረናል፡፡

ከሞቱ ከ3 ሰዓት በኋላ ቆይተው ተነሱ

ከኢትዮጵያ የወሬ ምንጭ

በወለጋ ጠ/ግዛት በቀለምት አውራጃ በበሌ ቦሼ ወረዳ በባላምባራስ ተፈሪ ቀኖ መልከኝነት ውስጥ ነዋሪ የሆኑ የስድሳ ዓመት ዕድሜ ያላቸው አቶ ጉያሳ ደመቅሳ የተባሉ አረጋዊ በደረሰባቸው ሕመም ከዚህ ዓለም በሞት ስለተለዩ፣ ወዳጅ ዘመድ ተሰባስቦ ዕንባውን እያፈሰሰ ሲላቀስ እንደ ደንቡ ሬሳው ታጥቦ ከተገነዘ በኋላ አስክሬኑን በሬሣ ሳጥን ውስጥ ለማስገባት ሲሞከር ከሞቱ ከ3 ሰዓት በኋላ ነፍስ ዘርተው ስለተንቀሳቀሱ ግንዙ ተፈቶላቸው ዓይናቸው ሲገለጥ ለለቅሶ የመጣውን ሰው ተመልክተው፣ ይህ የተሰበሰበው ሕዝብ ምንድነው በማለት መገረምን ሲጀምሩ፣ አሁን ተሰብስበው የሚያዩዋቸው ሁሉ እርሶ ከዚህ ዓለም ተለይተዋል በማለት ሊሸኙዎት የመጡ ናቸው።

ለመሆኑ ሲታጠቡና ሲገነዙ ደግሞም የለቅሶውን ሁካታ አልሰሙምን?፣ ምንስ ይታይዎት ኖሯል?፣ የትስ ደርሰው ነበር?፣ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ

 የሰጡት መልስ፤ አንድ ሰው በትልቅ ሣር ቤት ውስጥ በምሰሶው ስር በወርቅ መልክ በተቀረፀ ወንበር ላይ እንደተቀመጠ አንድ ሰው በግራ በኩል ቢያቀርበኝ ያለቀኑ ለምን አመጣችሁት እያለ ሲናገር እንደ ሕልም ይታየኝና ይሰማኝ ነበር።

ከዚህም በተቀረ አንደ ሰው ጅግራ በሚያዝበት ወጥመድ ታሥሮ ቀርቧል። አቤት አቤት ይላል። ነገር ግን በጥፋትህ ትቀጣለህ፤ ሒድና እንጨት ቆርጠህ አምጣ ተብሎ ሲላክ በሠንሠለት የታሠረ ነብርም አይቻለሁ።

ከዚህ በኋላ በማውቀው የአባቴን ጦር በሚመስል ጠምጥሞ ወደ ባሕር ሲጥለኝ አሁን ከእንቅልፌ የተነሣሁ ይመስለኛል በማለት ተናግረዋል። (አዲስ ዘመን ጥር 14 ቀን 1958ዓ.ም)

ለወይዛዝርት ገጽ አዘጋጅ

አዘጋጅ ጳውሎስ ኞኞ

፠እንደ ትዳር ጓደኛ አድርጌ የምወዳት ያቺኑ ድንክዬ ቆጤን ነው። ምክንያቱም ስፋቷንም ቁመቷንም በኔው መጠን ስለሠሯት የጥቅምትን ብርድ እንኳን ሳታስገባ ከምሽቱ 3 ሰዓት የተንጋለልኩባት ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ድረስ ያለኝን ጠባዬን ለማንም ሳትገልጥ ችላኝ ትኖራለች። ታዲያ ሚስት የተገባ እንደሆን እኔ ከሌላ ቆጥ ላይ ብተኛ እንቅልፍ አይወስደኝም። ይህን ጠባይ የሚችል የትዳር ጓደኛ በዓምድዎ ይገኝ ይሆን? እርስዎስ ምን አስተያየት አለዎት?

መ.አ

– እንዲያው ለመሆኑ አልጋ ብቻ የሚችለው ጠባይዎ ምንድነው?

(አዲስ ዘመን ጥቅምት 4 ቀን 1958ዓ.ም)

፠አንዲት የተማረች ወይዘሪት ለእኔ ረዳትነት መሥሪያ ቤታችን ቀጥሯት ሥራዋን ከማሸነፏም ሌላ ዓመልዋ በጣም የታረመ ነበር። በመሐሉ እኔ ፈቃድ አግኝቼ ወደ ትውልድ ሀገሬ ሔጄ አንዲት ልጅ አጨሁኝ።

ተመልሼም ሥራዬን ስጀምር የረዳቴ ጥሩ ዓመልዋና የሥራ ፍላጎት ተቀይሮ አገኘሁት። በፊት ሳምንት የምትሠራው ወር ይወስድባት ጀመር። ዓመሏ ከመበላሸቱም ሌላ ኩርፊያዋ በዛብኝ። ምን ማለቷ ነው?

ጋ.አ(ከሐረር)

-ምን አስለምደዋት ኖሯል? አገባሻለሁ ብለዋት ነበር እንዴ? ሁለታችሁ የምታውቁት አንድ ሚስጢር አለ። ታዲያ እንዴት መፍረድ ይቻላል።

(አዲስ ዘመን ጥቅምት 4 ቀን 1958ዓ.ም)

፠ሰላም ለርሶ ይሁን። ለጥያቄዎቼ አጥጋቢ መልስ እንደሚሰጡኝ አምናለሁ። እንዲያው በመድኃኒ ዓለም ይዠዎታለሁ ረዘመ ብለው ጽሑፌን እንዳይሰርዙት።

ቁመቴ ረጅም ነው። እንዲያውም አንድ ሜትር ከ74 ሳንቲ ሜትር እሆናለሁ። ስለዚህ ከጓደኞቼም ሆነ ከሌላ ሰው ከ-ዘ፣ የወሎ ፈረስ፣ ጀርመን፣ አውስትራሊያ የሚለው የቅጽል ስም አንገፍግፎኛል። አዘጋጁንም የምጠይቅዎት በሀገራችን በኢትዮጵያ ቁመተ ረጅም ሴቶች የሉ ይሆን? እኔ ባለሁበት ከተማ ግን ከኔ በቀር ለመድኃኒትም አይገኝም። ምን ይበጀኝ ይመስልዎታል? በዚህ ግምት ባልም የሚገኝ አይመስለኝም። ባንድ በኩል የወደደኝ አይጠላኝም ባይ ነኝ።

ወይዘሪት የሮም ወርቅ ተፈሪ(ድሬዳዋ)

– በመድኃኒ ዓለም ስም ስለያዙኝ አንድም አልሠረዝኩትም። መድኃኒ ዓለምን በጣም እፈራለሁና ነው። ወደርሶ ጉዳይ እንመለስ። በድሬዳዋ ለመድኃኒትም ረጅም ሴት ከሌለ ለመድኃኒትነቱ እርሶ ይበቃሉ። እርግጥ መጠንዎ ለሴት ቁመት ይረዝማል እንጂ አያሠጋዎትም።

“ሽንጧ የሚመስለው ዛፍ የራቀው ሐረግ” የሚባለው ግጥም ለእንደርሶ አይነቱ ነው።

በርዝማኔዎ የሴቶችን የርዝማኔ ሪኮርድ አልሰበሩም። 1889ዓ.ም በጀርመን ሀገር ቤንኬንዶርፍ በተባለ ከተማ የተወለደችው ጀርመናዊቷ ማሪኔ ወዴ የቁመቷ ርዝመት ሦስት ሜትር ይደርስ ነበር። ባለ ሪኮርዷ እሷ ናት። እርሶ የሷ ግማሽ ኖት አይስጉ። ታኮ ጫማ አያድርጉ። (አዲስ ዘመን ግንቦት 24 ቀን 1958ዓ.ም)

፠ከእጮኛዬ ጋር የጋብቻችን ጊዜ በመቃረቡ የቤታችንን እቃ ለመግዛት በአሳሰብ ትርዳኛለች ብዬ ሳማክራት የራስህ ጉዳይ ነው እያለች የግልዋን ብቻ ታሳስበኛለች፡፡ እስካሁን የልጅነት ጸባይ ነው በማለት ቆይቻለሁ፡፡ ወደፊትስ በዚህ ብትቀጥል ምን ይበጀኝ ይመስልዎታል?

አንተነህ ኃይል

– ለወደፊትማ አይሆንም፡፡ አሁን በሰው ሃብት እንዴት እንደልቤ ልናገርበት ብላ ነው፡፡ ሳይሆን ይቀራል ብለው? (አዲሰ ዘመን ሰኔ 10 ቀን 1958ዓ.ም)

፠ሁሉም በልጅነቱ ያምራል፡፡ ነገር ግን እንጀራ በልጅነቱ አያምርም የሚል ትችት አለ፡፡ የእንጀራ ልጅ እንጎቻ፣ ወይም ብጥሌ ነው፡፡ ታዲያ ይህ አነጋገር ቅዝምዝም ወዲህ፣ ፍየል፣ ወዲያ አልሆነም ወይ? ያንተስ አስተያየት እንዴት ነው?

አክባሪህ አየለች ወርዶፍ( ከአርባ ምንጭ

-እሜትዬ የሚሉት ለኔ አልገባኝም፡፡

(አዲስ ዘመን የካቲት 19 ቀን 1958ዓ.ም)

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 9/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *