አዲስ አበባ፡- ሀገር አቀፍ የታክስ ገቢ ማነቃቂያና ማሳደጊያ ዘመቻ በይፋ መጀመሩን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ዘመቻው የመገናኛ ብዙሃንን በማሳተፍ ግብር የመክፈል ባህልን ለማሳደግ ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡
‹‹ሚዲያና ገቢ›› በሚል ርዕስ ከመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ለተውጣጡ ጋዜጠኞች ትናንት በካፒታል ሆቴል በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደገለፁት፣ ግብርን የሁሉም አጀንዳ ለማድረግና በተለይም ከመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት በማጎልበት የግብር ሥርዓቱን ማጠናከር ወሳኝ ነው፡፡ለዚህም አገር አቀፍ የታክስ ገቢ ማነቃቂያና ማሳደጊያ ዘመቻን ማስጀመር አስፈልጓል፡፡
ዘመቻው ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ዘላቂ ገቢን እውን ለማድረግ፣ የትራንስፎርሜሽን ሥራው በህዝቡ ዘንድ በቂ ግንዛቤ እንዲሰርጽ ለማስቻል፣ የተሻለ የህግ ተገዢነት እንዲኖር በማድረግና ግብርን በመክፈል ሊገኝ የሚችለውን የጋራ ጠቀሜታ ሁሉም እንዲገነዘበው ለማድረግ ትልቅ ሚና እንዳለውም ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ በግብር ገቢ ዙሪያ የመገናኛ ብዙሃን የዘመቻው ወሳኝ አጋርና መሪ ናቸው፡፡ በዘመቻው ዝግጅቶች ሙሉ ተሳታፊ በመሆን ሚናቸውን በሚገባ መወጣት አለባቸው፡፡ የግብር መክፈል ጠቀሜታዎችን ለህብረተሰቡ ማስተማር ይኖርባቸዋል፣ ደፋርና ከተፅዕኖ ነፃ በመሆን ህገ ወጥነትን መዋጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡
መገናኛ ብዙሃን በግብር ዙሪያ የበጎ ፍቃድ ሥራዎችን ማበረታታት እንደሚገባቸው ገልጸው፣ የፖለቲካ መረጋጋትና የማህበረሰብ ደህንነትን ለማምጣት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡
‹‹ሚዲያና ገቢ›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የምክክር መድረክ በዘመቻው ለማከናወን ተይዘው ከተከናወኑ ፕሮግራሞች ውስጥ አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ በቀጣይ ወራቶችም ልዩ ልዩ የጋራ መድረኮችና ዝግጅቶች የሚካሄዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በዚሁ መሰረትም በቀጣይ ሀገራዊ የታክስ ኮንፍረንሶች፣ የታክስ በጎ ፍቃድ አምባሳደር መርሀ ግብር ፣ የሚኒስትሮች የጋራ መድረኮች፣ ልዩ የታክስ ሎተሪ ፕሮግራሞች ፣ የታክስ ሳምንት፣ ታላቁ የታክስ ሩጫና ተንቀሳቃሽ የታክስ ትምህርት መርሀ ግብሮች እንደሚከናወኑ ሚኒስትሯ ገልፀዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ወቅት በተለይም የመገናኛ ብዙሃን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመሆን የግብር ሥርዓቱን ለማጠናከር በሚያስችሉ ነጥቦች ላይ የጋራ ውይይቶችን አካሂደዋል፡፡ በጋራ የሚሰሯቸውን ሥራዎችን በማቀድና ለቀጣይ የሚጫወቷቸውን ቁልፍ ሚናቸውን በመለየት ዘመቻውን ለመደገፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2011
በአስናቀ ፀጋዬ