
ክረምት በበሬ አርሰው በጭቃ ኮትኩተው ለሚያበሉን አርሶ አደሮች ልዩ ጊዜ ነው፡፡ አርሶ አደሮች ጎተራቸውን የሚሞሉበት፣ መሠረት የሚጥሉበትና ለሌሎች ተስፋ የሚሆኑበት ጊዜ በመሆኑም አጥብቀው ይወዱታል፤ ይናፍቁታልም፡፡ እናም እነዚህ ወራት ማንም እንዲነካባቸው አይፈልጉም፤ አይፈቅዱምም፡፡
ከዚያ ይልቅ የሚያስፈልጋቸውን የሚያቀርብላቸውና ብርቱ የሚላቸውን ይሻሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ፍላጎታቸው በተለይም ባለፈው ዓመት በአንዳንድ ክልሎች ሙሉ ሊሆን አልቻለም፡፡ አንዴ በግጭቱ ሌላ ጊዜ ደግሞ በግብዓት አቅርቦት ተፈትነዋል፡፡፡
ፈተናው ለእከሌ ተብሎ የመጣ ስላልሆነ ግን ችግሩን ተጋፍጠው ለመሥራት እየሞከሩ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ክልሎቹ አመራሮችም ቢሆኑ የሚያብራሩት ይህንኑ ነው፡፡ በተቻለ መጠን ነገሮች ለአርሶ አደሮች እየቀለሉላቸው እየሰራን ነው ሲሉም በ2015/16 ዓ.ም ያለውን የምርት ዘመን እንቅስቃሴ በሚመለከት ባቀረቡት ሪፖርታቸው ይገልጻሉ፡፡
በርግጥ ወሩ ሳይሰራበት ካለፈ ብዙ ነገሮች አስቸጋሪ ይሆናሉ፡፡ የመጀመሪያው ተጠቂ ደግሞ አርሶ አደሩ እንደሚሆን እሙን ነው፡፡ እናም በዚህ አይነት ፈተና ውስጥ ያሉ አርሶ አደሮች ችግሩን ተቋቁሞ መስራት የውዴታ ግዴታቸው እንደሆነ ያውቃሉና ማዳበሪያ ካልቀረበላቸው በተፈጥሮ ማዳበሪያ ትራክተር ካልቀረበላቸው ደግሞ እንደለመዱት በበሬያቸው እያረሱ የምርቱን ጊዜ በአግባቡ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። ለዚህም ማሳያው ደግሞ አመራሮቹ በአፈጻጸሙ ያቀረቡት ሪፖርት ነው፡፡
ለዛሬ በዚህ የከፋ ችግር ውስጥ እያለፉ ያሉትን የትግራይና አማራ ክልሎችን ነባራዊ ሁኔታ ልናስቃኛችሁ ወደናል፡፡ ቅኝታችን ደግሞ የግብርና ሚኒስቴር በአዘጋጀው መድረክ ላይ ሁለቱ ክልሎች ያቀረቡትን ሪፖርት መሰረት ያደረገ ነው፡፡
ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ስንነሳ ክልሉ ተለይቶ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት የምርት ዘመኑን ግብርና ዕቅድ አዘጋጅቶ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሆነ የቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው ተናግረዋል፡፡ እርሳቸው እንዳሉትም፤ በክልሉ በርካታ ችግሮች አጋጥመዋል፡፡ አርሶ አደሩም በተለያዩ ምክንያቶች ተፈትኗል፡፡ በሰላም እጦት እና በግብርና ግብዓት አቅርቦት የተፈተነበት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ክረምት ለአርሶ አደሩ ልዩ ወር በመሆኑ ይህንን ሁሉ ተግዳሮት ተጋፍጦ እንዲሰራ ሆኗል፡፡ በቢሮው በኩል አርሶ አደሩን ሊያግዙ የሚችሉ የተለያዩ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ከእነዚህ ሥራዎች መካከልም የ2015/16 የመኸር ምርት ዘመን ዝግጅትና ትግበራ ነው፡፡
‹‹በዚህ የመኸር የምርት ዘመን ከ5ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በማረስ ወደ 160 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዳል፡፡ ይህ ደግሞ ባለፈው ዓመት ካመረትነው ወደ 20 ሚሊዮን ኩንታል ተጨማሪ ያለው ነው፡፡ የዘር ሥራ ሲከናወን ከአርሶ አደር እስከ ቦታ ልየታ ድረስ ተሰርቶ በመሆኑ አሁን ላይ ከአራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ ማለትም ወደ 80 በመቶ የሚሆነው በዘር ተሸፍኗል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለፃ፣ አማራ ክልል ውስጥ 28እና 29 አይነት ሰብሎችን ማምረት ይቻላል፡፡ ይሁንና ሁሉም አይነት ሰብሎች በእኩል ደረጃ ርብርብ ሊደረግላቸው አይችልም፡፡ ከፍተኛ ርብርብ የሚያደርግባቸው በመሬትም ሆነ በምርት ከ80 በመቶ በላይ ሽፋን ያላቸው ሰብሎች ላይ ነው፡፡
ለዚህም እንደ ክልል አሥር የሚሆኑ የሰብል አይነቶች ተለይተዋል፡፡ አሥሩ ሰብሎች በጥቅል በመሬት ወደ 80 በመቶ፤ በምርት ደግሞ 86 በመቶ የሚሸፍኑ ናቸው፡፡ ይህ በመሆኑ ደግሞ ከዚህ በፊት በቆሎ፣ ማሽላና ሰሊጥና ሩዝን የመሳሰሉ ሰብሎች ላይ ጥብቅ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡ እንደየአካባቢው ወቅታቸውን ጠብቀው የሚከናወን ቢሆንም ሌሎች ሰብሎችም በዚህ ልክ ይሰራባቸዋል፡፡፡
‹‹አሁን ያለንበት ወቅት የዘር ሥራ የሚከናወንበት ነው፡፡ እንደ ክልል በዘር ራስ የመቻል እቅድ አቅደን ወደ ሥራ ገብተናል፡፡ የሚቀረው 20 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው›› የሚሉት ዶክተር ኃይለማርያም፣ይህም በዋናነት ጤፍና ስንዴን የሚይዝ እንደሆነም ያነሳሉ፡፡
በኩታ ገጠም እርሻ እንደ ክልል አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር አካባቢ ይታረሳል ተብሎ ታቅዷል። በዚህም አሁን 98 በመቶ የሚሆነውን መሬት ልየታ ተደርጓል፡፡ አንድ ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታርም ከልየታ አልፎ ተዘርቷል፡፡
‹‹እንደ ክልል አሁን ያለንበት የክረምት ወቅት ዝናብ ወጣ ገባ የሆነበት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለተባይ መፈጠር ምቹ ሁኔታን ይሰጣል፡፡ እናም እንደ ክልል የሰብል ጥበቃን በተመለከተ ብዙ ሥራዎች ማከናወን እንዳለብን ያስጠነቀቀን ነው›› ይላሉ፡፡

በምስራቅ አማራ በኩል ያሉ አካባቢዎች ለዚህ ተጋላጭ መሆናቸውንና የተምችና የአንበጣ ወረርሽኝ በተከታታይ እንዳጋጠማቸው የሚጠቁሙት ዶክተር ኃይለማርያም፤ የፌደራል መንግሥት በተለይ የኬሚካል አቅርቦቱን ትኩረት አድርጎ ሲከታተለው ስለነበር እንደ ወረዳና ክልል ከፍተኛ ርብርብ ተደርጎ የተምች ወረርሽኙን ጉዳት ሳያደርስ መከላከል መቻሉንም ይገልፃሉ፡፡
ይሁንና በአካባቢ የተከሰተውን የአንበጣ ወረርሽ ግን ገና የመቆጣጠር ሥራ እየተከናወነና አሁን ባለው ሁኔታ ሦስተኛ ዙር ጭምር ወረርሽኙ ሊከሰት እንደሚችል ስጋት መኖሩን የሚያመለክቱት ኃላፊው፣ ‹‹በእኛ በኩል ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን፣ ሕዝቡና የሚመለከታቸው አካላትም ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል ››ሲሉም ያሳስባሉ፡፡
ክልሉ የክረምት አትክልትና ቅመማ ቅመም ዘርፍን ራሱን ችሎ እንዲሰራበት እየተደረገ መሆኑን የሚጠቁሙት ኃላፊው፤ በዚህም ወደ 272 ሺህ ሄክታር አካባቢ ለማልማት መታቀዱንና እስካሁን 164 ሺህ አካባቢ ማለትም 60 በመቶውን በዘር መሸፈን እንደተቻለም ያነሳሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ጎንደር አካባቢና የምስራቅ አማራው አካባቢ በእጅጉ የተመቹና የተለዩ አካባቢዎች መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡
የግብዓት አቅርቦትና ስርጭትን በተመለከተ ዶክተር ኃይለማርያም ሲገልፁም፤ ለክልሉ የአደረውን ጨምሮ ከተመደበለት 5ነጥብ3 ሚሊዮን ኩንታል እስከ ሐምሌ 26 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ 4ነጥብ6 ሚሊዮን ለስርጭት ቀርቧል፡፡ ከዚህ ውስጥም ለአርሶ አደሩ የደረሰው 4ነጥብ235 ሚሊዮን ነው፡፡ በስርጭት ሂደቱ በርካታ ችግሮች ገጥመዋል፡፡ ሆኖም ለመፍታት ተችሏል፡፡
በተለይም ሕገወጦችን በመከላከል በኩል የአርሶ አደሩ ጥቆማና የፖሊስና የፍትህ አካላት በእጅጉ እግዛ አድርገዋል፡፡ በተሰራው ሥራም በ13 ዞኖች፣ በ46 ወረዳዎች በሕገ ወጥ ዝውውር ከተሳተፉ 327 ግለሰቦች 7ሺ129 ኩንታል ተወርሶ 5ሺ 132 ኩንታል ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል፡፡
ዶክተር ኃይለማሪያም በሰጡት ማጠቃለያም በርካታ ችግሮች የገጠሙ ቢሆንም ቢሮው በጽናት በጥንካሬ እንዲሁም በግብርና ቤተሰቦች በተፈጠረው ጠንካራ አንድነት በሁሉም መስክ ችግሩን በድል መወጣት ተችሏል፡፡ የቀጣይ ወራት ሥራዎችንም ብዙ ነገርን ይፈልጋሉና በመመካከር እና ያለእንቅልፍ በትጋት በመስራት በድል መወጣት ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ፡፡
በትግራይ ክልል ያለው የእርሻ ሥራን በተመለከተ ደግሞ የክልሉ የእርሻ ተፈጥሮ ሃብትና የአፈር ልማት ማሻሻል ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ በክልሉ ያለውን የ2015/ 16 የመኸር ወቅት ትግበራና እቅድ አስመልክቶ አቶ ሰለሞን እንደገለጹትም፣ በክልሉ ከ6 መቶ 25 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ታርሷል፡፡ 4 መቶ 82 ሺህ ሄክታሩ አሁን ላይ በዘር ተሸፍኗል፡፡
አቶ ሰለሞን እንደሚሉት፤ የማዳበሪያ አቅርቦቱና ፍላጎቱ እንደክልል የተመጣጠነ አይደለም፡፡ ለአብነት ለዘንድሮው የምርት ዘመን የተጠየቀው አጠቃላይ የማዳበሪያ ብዛት 800 ሺህ ኩንታል ሲሆን፤ በወቅቱ ደርሶ ለገበሬው 196 ሺህ ኩንታል ብቻ ነው፡፡ ዩሪያን ብቻ ብናነሳ የተጠየቀው 400ሺህ ኩንታል ሲሆን፤ እስከ ሐምሌ 15 ቀን 2015ዓ.ም የገባው ግን 151 ሺህ ኩንታል ገደማ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሥራዎችን እንዲጓተቱ አድርጓል፡፡ ምክንያቱም እስከ ሰኔ 15 አጋማሽ ድረስ በአብዛኛው ምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ትግራይ የስንዴ ዘር የሚዘራበት ወቅት ነው፡፡
ለዘር የሚሆነው ማዳበሪያ ከመዘግየቱ በተጨማሪ በመጠንም አነስተኛ እንደሆነ ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ በክልሉ ሌላ እንደ ትልቅ ችግር የነበረው በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ የዝናብ እጥረት ማጋጠሙን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ ዘር እንዳይዘራ ሆኖ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ክልል የመፍትሔ አቅጣጫ ተቀምጦ የግብርና ቢሮ ከገበሬው ጋር በመሆን ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ መሬቱ በወቅቱ እንዲታረስና ለሥራው አስቸጋሪ የሆነበት ጉዳዮች እየተለዩ መፍትሄ እንዲበጅላቸው የማድረግ ለአብነት እርጥበት የመያዝ ሥራም ተጀምሯል፡፡
‹‹አሁን የእርሻ ሥራ ለማከናወን በሬ ያጡ ገበሬዎች ቢኖሩም ችግሮቹን በመቋቋምና ሌሎች እንስሶችን እንደ አማራጭ በመጠቀም ሁሉም በደቦ እየሰሩ ይገኛሉ›› የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ቢሮው የክልሉ አርሶ አደሮች ከዚህ በላይ እንዳይቸገሩ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ያነሳሉ፡፡ አንዱ በማዳበሪያ፣ በዘር መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ዘር እንዳያጡ ለማድረግ ከተለያዩ በጎ አድራጊዎችና ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን 44 ሺህ ኩንታል ገደማ አሰባስበው የተገኘውን ዘር ለሁሉም ስለማይበቃ ቅድሚያ ለሚዘሩ አካባቢዎች ማድረስ እንደቻሉ ያስረዳሉ፡፡
ማዳበሪያን በሚመለከት ደግሞ እንደ አማራጭ የተጠቀሙት 100ሺህ ኩንታል ገደማ ከሌሎች ክልሎች ለቀጣይ የሚመለስ በመውሰድ ወደ ቆላማውና ወይና ደጋ አካባቢ እንዲሰራጭ በማድረግ መሆኑን ያነሳሉ። በተጨማሪም በአግሮ ኬሚካል ጠቃሚ መረጃዎችን መስጠት ሌላኛው ተግባራቸው እንደነበር ያስረዳሉ፡፡
እንደ አቶ ሰለሞን ማብራሪያ፤ በክልሉ ከሚያዝያ አጋማሽ ጀምሮ ማሽላ፣ በቆሎ፣ ዳጉሳ የተዘራ ሲሆን፤ ከሰኔ 15 ወዲህ ደግሞ በዋናነት የተዘሩትና እየተዘሩ የሚገኙት ስንዴ፣ ጤፍ፣ ገብስና ጥራጥሬ ናቸው፡፡ በመሆኑም ዘር ተዘርቶ ከተገባደደ ወዲህ አነስተኛ ቁጥር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ቢገባም ዩሪያ የተሰኘው ማዳበሪያ ዘር ከበቀለ ከ30 እስከ 40 ቀናት ቢቆይ ችግር አይፈጥርም፡፡ በዚህ ወቅት ችግር ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚታሰበው የፀረ ተባይ መድኃኒት ነው፡፡ ይህም ቢሆን አብዛኛው ጊዜ በመንግሥት የሚከናወን በመሆኑ ከተመደበው በጀት ላይ ለመግዛት በዝግጅት ላይ እንደሆነና ወደ ገበሬው የሚዳረስበት መንገድ እየተመቻቸ ይገኛል፡፡
በክልሉ ምስራቃዊና ደቡብ ምስራቅ አካባቢ እስከ አሁን ከአንድ ወር በላይ ዝናብ ባለማግኘቱ ስጋት እንደሆነ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ በእነዚህ አካባቢዎች ላይ እርጥበት ከመያዝ ባለፈ በፍጥነት የሚደርሱ አዝርዕት ለመዝራት መረጃዎች እየተሰጡ እንደሚገኝ ይናገራሉ። በጥቂት ውሃ ሊበቅሉ የሚችሉ እንደ አተርና ሽምብራ የመሳሰሉት ላይ ገበሬው ትኩረቱን እንዲያደርግም የማስተባበር ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡
በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የአንበጣ ምልክት እየታየ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ይህን ከወዲሁ ግብረ ኃይል በማዘጋጀት ሁሉም አመራርና ሕዝብ በትኩረት በመሥራት መቆጣጠር ይገባዋል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8/2015