እንዴት ናችሁ ልጆች? ይህንን ክረምት በሚገባ እየተጠቀማችሁበት እንደሆነ ጥርጥር የለኝም፡፡ መደበኛ ትምህርታችሁን እስከምትጀምሩ ድረስ ጊዜያችሁን በሚገባ እየጠቀማችሁበት እንደሆነም አምናለሁ፡፡ ዛሬ ስለንባብ ጥቅምና ወላጆቻችሁም እናንተ እንድታነቡ እንዴት ማገዝ እንዳለባቸው እንመለከታለን፡፡
ልጆች እረፍት ስትሆኑ ምን ማድረግ ያስደስታችኋል? ቴሌቪዥን ማየት፣ ከጓደኞቻቸሁ ጋር መጫወት፣ ሞባይል መነካካት፣ ስዕል መሳል ወይስ ምን ያስደስታችኋል? እነዚህ ሁሉ እንዳሉ ሆነው ማንበብ ብላችሁ የመለሳችሁ ምርጫችሁ ላቅ ያለ እውቀትን የሚያስገኝ እንደሆነ ልነግራችሁ እወዳለሁ፡፡
ልጆች መጽሐፍትን ማንበብ በአንድ ጉዳይ ላይ ጠለቅ ያለ እውቀት እንዲኖር ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም በምታነቡበት ወቅት በአእምሯችሁ እየሳላችሁ እንድትመዘግቡት እንዲሁም እንድትመራመሩ ስለሚረዳችሁ፤ የተለያዩ ቦታዎችን፣ አካባቢዎችን፣ ታሪኮችን፣ ክስተተቶችን እንዲሁም ክንውኖችን በቀላሉ እንድታውቁት እንድትገነዘቡት ይረዳችኋል፡፡
ሌላው የማንበብ ጥቅም ነገሮችን በጥልቅ የማሳብ ችሎታችሁ እንዲዳብር ያደርጋል፡፡ በትምህርት ቤታችሁ የተለያዩ ክበባቶች እንዳሉ እገምታለሁ፤ ስለዚህም ልጆች የንባብ ባህላችሁ እንዲዳብር የሚረዷችሁ ክበባት ውስጥ አባል መሆን በንቃት መሳተፍ ይኖርባችኋል፡፡ እንዲሁም በመኖሪያ አካባቢዎቻችሁ ወደ ሚገኙ ቤተ መጽሐፍት በማቅናት መጽሐፍትን በማንበብ እየተዝናናችሁ ብዙ እውቀትን መገብየት ትችላላችሁ፡፡
ልጆች ‹የኢትዮጵያ ልጆች› ቴሌቪዥንን ትመለከታላችሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ በቴሌቪዥኑ ከሚተላለፉ መዝሙሮች መካከል ‹ማንበብ እወዳለሁ› የሚለውን የምታውቁት ይመስለኛል፡፡ ታዲያ በዚህ መዝሙር ላይ፡-
ማንበብ እወዳለሁ
ሁልጊዜ አነባለሁ
ባነበብኩኝ ቁጥር
ይገባኛል ምስጢር
የጥበብን ምስጢር
የእውቀትን ምስጢር
እኔ ልንገራችሁ
ከየመጸሐፍቱ ታገኙታላቸሁ
የሚል የግጥም ስንኝ ይገኛል፡፡
እናም ልጆች መጽሐፍት ብዙ ምስጢሮችን፣ ጥበብ እና እወቀት እንደያዙ ከመዝሙሩ እንደተረዳችሁ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ስለዚህም የእንቆቅልሽ መጽሐፍትን በማንበብ እና ከጓደኞቻችሁ ጋር በመጠያየቅ አእምሯችሁን በሚገባ እንድትጠቀሙበት ይረዳችኋል፡፡ የተረት መጽሐፍትን ስታነቡ ደግሞ ከመዝናናታችሁ በተጨማሪ መልካም ባህሪ፣ ጥሩ ሥነ ምግባር ያለው እና ጎበዝ ልጆች እንድትሆኑ ያግዟችኋል፡፡ ሌላው ደግሞ የተረት እና ምሳሌ መጽሐፍትን በማንበብ የሀገራችንን አባባሎችን በቀላሉ ለመረዳት ያስችላችኋል፡፡ ሀገራችን የበርካታ ታሪክ ባለቤት መሆኗን ለመረዳት የተለያዩ የታሪክ መጽሐፍትን በማንበብ ስለ ሀገራችሁ በቂ ግንዘቤ እንዲኖራችሁ ያስችላችኋል፡፡
አሁን አሁን ደግሞ በጣም የሚበረታታ ነገር እያየን ነው፡፡ እሱም ምን መሰላችሁ? ልጆች የማንበብ ልምዳቸውን እንዲያዳብሩ የሚያግዙ የተለያዩ የመጸሀፍት ኤግዚቢሽኖችና ፕሮግራሞች እየተዘጋጁ ሲሆን፤ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በጋራ ሆነው የሚያነቡባቸው አጋጣሚ እየተፈጠረ ይገኛል፡፡ እናም ልጆች እንደዚህ ያሉ ዝግጅቶች ላይ በመታደም የንባብ ክህሎታችሁን ማዳበር ነገ የምታስቡት ደረጃ ላይ ለመድረስ ያግዛችኋል፡ ፡ ዛሬ ላይ ያሉ ታዋቂ ደራሲዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ዶክተሮች፣ ተመራማሪዎች እና ሌሎች ባለሙያዎች ራሳቸውን ለዚህ ያበቁት በማበብ ነው፡፡ እናም ልጆች ለወላጆች ምን ማንበብ እንደሚያስደስታችሁ በመንገር ብዙ እውቀትን እንድታገኙ ይረዷችኋል፡፡
እንዲሁም ትምህርት ቤት ሲከፈት ደግሞ ከጓደኞቻችሁ ጋር ስላነበባችኋቸው መጽሐፍት በመነጋገር እንዲሁም ማን ብዙ አነበበ ተባብላችሁ በቀናነት በመጠያየቅ በመወዳደር እና በቀናነት በመፎካከር ብትወዳደሩ እና ብታነቡ በርካታ እውቀትን እንታገኙ ያደርጋችኋል፡፡
ልጆች እናተን መጽሐፍትን አንብቡ ስንል ወላጆች ምንም ድርሻ የላቸውም እያልን አይደለም፡፡ እንደውም ወላጆች የልጆቻችሁን ዝንባሌዎች በመለየት እንዲያነቡ ብታደርጉ የልጆቻችሁን የማንበብ፣ የቃላት አጠቃቀም እና በትምህርታቸውም ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ይረዳቸዋል፡፡
ሌላው ወላጆች ገና ማንበብ ያልጀመሩ ወይም የማይችሉ ልጆቻችሁን ተረት በማንበብ የንባብ ልምድ እንዲኖራቸው ከማለማመድ ባሻገር ከልጆች ጋር ደስተኛ ጊዜ እንዲያሳልፉ አጋጣሚውን ይፈጥርላቸዋል፡፡ ስለሆነም ወላጆች ልጆቻችሁ እንዲያነቡ አመቺ ሁኔታዎችን በማስተካከል ለምሳሌ በመኝታ ክፍላቸውም ይሁን በሚመቻቸው ቦታዎች ልጆቻችሁ የሚወዱት አይነት መጽሐፍት በመግዛት እንዲያነቡ ማድረግ ይገባል፡፡
ብዙ ወላጆች ልጆች እንዳያስቸግሯቸው በማሰብ ቴሌቭዥን፣ ታብሌት፣ ኮምፒውተር እና የሞባይል ስልክ እንዲመለከቱ እና ጌሞችንም እንዲጫወቱ ያደርጋሉ፡፡ ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ድርጊት የልጆችን የንባብ ባህል ዝቅ እንዲል ከማድረግ ባሻገር በማህበራዊ መስተጋብር ወይም ተግባቦት ላይ ችግር እንደሚፈጥር በመረዳት ከዚህ ድርጊት ወላጆች ራሳችሁን ማራቅ ይኖርባችኋል፡፡
ሕብረተሰቡ የንባብ ቀንን በማስመልከት የሚከበሩ ቀናት ልጆች መጽሐፍት በማንበብ አቅማቸውን የሚያሳድጉበትን ልዩ ልዩ ጨዋታዎችን በማዘጋጀት፣ የመጽሐፍ ሽልማቶችን በማበርከትና ማህበረሰቡ የንባብ ባህልን እንዲያዳብር የማነቃቃት ሥራ እየሠሩ ያሉትን ማበረታታት ይገባል።
በተጨማሪም የንባብ ልምድ ለማዳበር ልዩ ፍላጎት ላላቸው ህፃናትና ታዳጊዎች የእውቀት አድማሳቸውን ለማስፋት፣ የማስታወስ እና የማተኮር ችሎታቸውን ለመጨመር፣ እንዲሁም ከሰዎች ጋር ለመግባባት እና ሰፋ ያለ ርዕሰ ጉዳዮችን እንዲያውቁ ከሌሎች ልጆች በተለየ መልኩ የወላጅ፣ የአሳዳጊዎችና የተከንባካቢ ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ ያስፈልጋል።
ሌላው ወላጆች መረዳት ያለባቸው ነገር ቢኖር ልጆች ለማንበብ እንዲችሉ ጸጥ ያሉ አካባቢዎች መፍጠር ይጠበቅባችኋል፡፡ ልጆቻችሁ ኢንተርኔት ወይም መሰል ነገሮችን የግድ መጠቀም ያለባቸው ሁኔታዎች ከተፈጠሩም የጊዜ ገደብ በማበጀት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ከወላጆች የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው፡፡
መላው ቤተሰብ በማንበብ እንዲሳተፍ በማድረግ፤ ከንባብ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጨዋታዎች በመጫወት፣ ልጆች ስላነበቡት መጸሐፍ ምን እንደተገነዘቡ በመጠየቅ፣ ልጆች ትኩረታቸውን የሚስቡ ነገሮችን በመጠየቅ፣ በየዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው መጽሐፍትን እንዲያነቡ በማድረግ ንባብን እንዲወዱት እና እንዲለማመዱት ማደረግ ይገባል፡፡
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 7/2015