ያልቀለለ ሸክም

ቅድመ -ታሪክ

አዲሱ ጎጆ በአዲስ ትዳር ከተሟሸ ሰንብቷል። ጥንዶቹ ባተሌዎች ናቸው። ሁለቱም ቤታቸውን ለመምራት ፣ ጓዳቸውን ለመሙላት ሲሮጡ ይውላሉ። አባወራው ብርቱ አናጺ ነው። ማለዳ ወጥቶ ምሽቱን ሲመለስ ቤተሰቡን ያስባል። ወይዘሮዋ ስለቤቷ አትሆነው የለም። ያገኘችውን ሰርታ ለማደር ሁሌም ጉልበቷን ትሰጣለች።

ባልና ሚስት ዛሬን የሚኖሩት ነገን በማሰብ እንደሆነ ያውቃሉ ። አሁን ካሉበት ኑሮ በተሻለ የወደፊቱ ያጓጓቸዋል። ከቤት ኪራይ መውጣት፣ ገቢ ባለው ሥራ መኖር ምኞታቸው ነው። ይህ ይሆን ዘንድ እንቅልፍ ይሉት የላቸውም። ጧት ማታ በሥራ ይተጋሉ፣ ይለፋሉ።

አሁን የባልና ሚስቱ ጎጆ በህጻን ልጅ ለቅሶና ሳቅ መድመቅ ይዟል። የመጀመሪያ ልጃቸው ሶስተኛው ቤተሰብ መሆን ከጀመረ ወራት እየተቆጠሩ ነው ። ከዚህ በኋላ ኑሮ እንደበፊቱ አይሆንም። ለቤቱ ተጨማሪ ገቢ ያሻል ። በቂ ገንዘብ ያስፈልጋል።

ጥንዶቹ ዛሬም ስለቤታቸው ይለፋሉ ። አሁንም ኑሮ ፈቅ አላለም ። የእለት ወጪ ፣ የቤት ኪራይ፣ የልጅ ፍላጎትና ሌላም እየፈተናቸው ነው። ባልና ሚስት ትጋታቸው ቀጥሏል። ወጥተው በገቡ ቁጥር ስለ ጎጇቸው ሙላት፣ ስለነገው መልካም ሕይወት ያወጋሉ።

አባወራው በቀን ስራው ከድንጋይ፣ ከብረቱ፣ ከእንጨት ከሲሚኒቶው ሲታገል ይውላል። እንጀራ የሚበላበት ሙያው የልፋቱን አያሳጣውም። ቤት ሲደርስ ባለቤቱ በፍቅር ተቀብላ ቤት ካፈራው፣ ትቆርስለታለች። ህጻን ልጁን ሲያይ፣ሚስቱን ሲያወጋ የቀን ድካሙን ይረሳል ።

የጥንዶቹ ቤተሰብ እየሰፋ ነው። ሁለተኛው ልጅ ቁጥር ጨምሮ ወንድሙን ተቀላቅሏል። ባልና ሚስት አሁን ከቀድሞው በላቀ መስራት መልፋት አለባቸው። የልጆች መጨመር የፍላጎት ማየል ህይወታቸውን እያከበደ፣ ኑሯቸውን እያዛባ ነው ።

ሁለት ህጻናት ያሉበት ቤት ብዙ ይፈልጋል። ስለነገው ለውጥ የሚሮጡት ጥንዶች ስለጎጇቸው ዝም አላሉም። ወይዘሮዋ ከጉልት ትውላለች። ጎመን፣ ቃሪያውን፣ ሽንኩርት ድንቹን ለመሸጥ ጉልበት ያሻታል። ልጆች ወልዶ በማሳደግ ድካም ያላት እማወራ ሌት ተቀን እየለፋች ነው። ለገበያዋ ራቅ ብላ የምታመጣው ዕቃ የጉልበት ዋጋ ያስከፍላል ። መርጦ መግዛቱ፣ ተሸክሞ ፣ አሸክሞ ማምጣቱ፣ የየዕለት ድካም አለው።

ወይዘሮ መሰሉ ልጆች ለማሳደግ ፣ ጎጆን ለመሙላት መተማመኛዋ ሥራዋ ነው። በጉልት እሷን ከመሰሉ ሴቶች ጋር ተቀምጣ ስትውል ተስፋዎቿ ደንበኞቿ ናቸው። ተመሳሳይ ነገር ፣ በአንድ አይነት ዋጋ ሸጦ መዋል ብልሀትን ይጠይቃል። አሁን አሁን ውሎው በውድድር ነው ‹‹እትዬ እህቴ ፣ እቺን ግዙ ፣ እቺን ውሰዱ ማለቱ ተለምዷል። ለዚህ ደግሞ ግንባርና ድፍረት ያሻል።

አንዳንዴ ገበያው እንደታሰበው አይሆንም። ሻጭ ከገዢ፣ ሳይገናኝ፣ የተዘረጋው ሳይቀነስ፣ ሳይጠየቅ ይውላል። አጋጣሚው ሲደጋገም አትክልት ቲማቲሙ ይበላሻል። ጎመን ቃሪያው ይባክናል። እንዲህ መሆኑ ለዕለት ጉርሱ ለሚሮጠው ባተሌ ኪሳራ ነው ።

መሰሉና ጓደኞቿ ከአትክልት ተራ ሄደው ማምጣታቸው ጥቂት ለማትረፍ ነው። አንዳንዴ ግን ገበያው ከታሰበው በላይ ያሻቅባል። እንዲህ ሲሆን በውድ የገዙትን ጨምረው ለመሸጥ ይቸገራሉ። እውነታውን የማይረዱ ደንበኞቻቸው በዋጋው ተማረው ጥለዋቸው ይሄዳሉ። አንዳንዶች ተመልሰው አይመጡም።እነሱን ትተው ሌሎች ደንበኞች ያፈራሉ።

ወይዘሮ መሰሉ ይህ አይነቱ እውነት የየዕለት አጋጣሚዋ ነው። እሷ ሁሌም ከእጇ ያለውን ሸጣ የነገውን ለማምጣት ታቅዳለች። ማልዳ የምትወጣበት የአትክልት ተራ ውሎ የአቅሟን ያህል ያስገዛታል። መርጣ፣ተከራክራ፣ ከጸሀይ ውላ ፣ ከዝናቡ ታግላ ለጎጇዋ ትደርሳለች። ለሆድ ብቻ የደረሱት ህጻናት ሲያገኝዋት ርሀባቸው ይጠፋል። በእናታቸው መምጣት ፊታቸው ይበራል።

ሌላ ሆድ..

አሁን የቤተሰቡ ቁጥር ስድስት ደርሷል። ሁለት ህጻናት ታክለው ልጆቹ አራት ሆነዋል። ዛሬም ከቤት ኪራይ ያልተላቀቁት ባልና ሚስት ኑሮ ህይወታቸው እየከበደ፣ጉልበት አቅማቸው እየደከመ ነው። ሁለቱም ስለአራቱ ልጆቻው መኖር ከልፋት ግዴታ ገብተዋል። በእነሱ ጫንቃ የወደቀው ኃላፊነት በእኩል እያሮጠ ያውላቸዋል።

አናጺው አባወራ ለልጆቹ ፣ ለራሱና ለባለቤቱ መድከም መልፋቱ አያስከፋውም። ከአድካሚ ስራው መልስ ከቤቱ ሲገባ በልጆቹ ሳቅ ጨዋታ ይደሰታል። በእነሱ እስትንፋስ የእሱ ዓለም ይደምቃል ።በእነሱ መኖር ተስፋው ይለመልማል።

የስድስቱ ቤተሰብ ህይወት እንደትናንቱ ነው። ህጻናት በወላጆቻው እጅ ያድጋሉ፣ እማወራዋ ከጉልት ትውላለች። አባወራው በአናጺነት ሙያው ይደክማል። የቤት ኪራይ ወር ጠብቆ ይከፈላል። ቀን እየመሸ ይነጋል፣ ክረምት እያለፈ በጋው ይተካል። ህይወት መክበዱን ፣ኑሮ መናሩን ቀጥሏል።

አዲስ ምክር

ውሎ አድሮ አባወራው መፍትሄ ባለው ሀሳብ ከሚስቱ መከረ። ከአዲስአበባ ወጣ ብሎ መስራት መፈለጉን አዋያት። በጉዳዩ ሚስት አምናበት ተስማማች። ራቅ ብሎ መሄዱ ለቤት ለልጆቹ እንደሚሻል ደጋግመው ተነጋገሩ። ሀሳቡ በእኩል ጸደቀ። ካለበት

 ሆኖ የሚልከው ገንዘብ ለቤት መደጎሚያ፣ ለልጆቹ ማስተማሪያ ይሆናል። ሁለቱም ይህ እንዲሆን ከውሳኔ ደርሰዋል። ከቀናት በኋላ ባል ሚስቱንና ልጆቹን ተሰናበተ። ሁሉም ቸር እንዲያገባው ተመኝተው በምርቃት ተለዩት።

አባወራው ጓዙን ይዞ ጅማ ላይ ከተመ። የአናጺ እጆቹ ስፍራው ሲደርሱ ይበልጥ በረቱ። ካለበት ቤተሰቡን እያሰበ ፣ ሚስት ልጆቹን እየናፈቀ ሥራውን ጀመረ። ከውስጥ ከውጭ የሚደጎመው ጎጆ አራት ልጆች ይዞ ህይወት እንደትናንቱ ቀጠለ። እንጀራ ያራቀው አባት አሁንም ስለነገው ያስባል። ርቆ መሄዱ፣ ዛሬን መልፋቱ ስለ ወደፊቱ የልጆቹ ህይወት መሆኑን አሳምሮ ያውቃል። አናፂው አባት ይህን ባሰበ ጊዜ ብሩህ ቀን ይናፍቀዋል።የላብ፣ የድካም ፍሬው ይታየዋል።

የቀን ሥብራት…

ከቀናት በአንዱ የቤተሰቡን የህይወት አቅጣጫ የሚያናጋ ክፉ አጋጣሚ ሆነ። ማልዶ ለሥራ የወጣው ባተሌ አባወራ እንደቀድሞው በሰላም አልተመለሰም። ያላሰበው ገጠመው። ጆሮ የገባው ድንገቴ ወሬ መልካም ዜና አልያዘም። አናጺው ጎልማሳ በሥራ ላይ ሳለ ከፎቅ መውደቁ ተሰማ ። ይህ ክፉ ወሬ በናፍቆት የከረመውን መላ ቤተሰብ አንገት አስደፋ። ስብራት ህመሙ፣ቁስል ፣ሥቃዩ ለሁሉም ደረሰ ።

ወይዘሮዋ የአባወራዋን ከፎቅ ላይ መውደቅ እንደሰማች ልቧን ደግፋ ፣ራሷን ይዛ፣ ደረቷን እየደቃች፣ በጩኸት፣ በለቅሶ ካለበት ደረሰች። የተባለው ሁሉ እውነት ሆኖ አገኘችው ። ግማሽ አካሏ፣ የትዳር አጋሯ፣ የአራት ልጆቿ አባት፣ እንዳይሆን ሆኗል።

ሁኔታዋን ያዩ እጆቿን ይዘው ባሏ በህይወት ስለመኖሩ ነገሯት ። ጥቂት መለስ አለች። ከዓይኗ ጆሮዋን አላመነችም። ቀረብ ብላ ትንፋሹን አደመጠች። ጥቂት ሙቀት ያለው አንዳች ድምጽ ‹‹ሽው›› ሲል ተሰማት። በህይወት ስለመትረፉ ደጋግማ ፈጣሪዋን አመሰገነች።

ፈታኙ የህይወት ጉዞ ቀጥሏል። እናት መሰሉ ከታላቅ ጭንቅ ወድቃለች። ትናንት ጎጆ ትዳሩን ይመራ፣ ልጆቹን በወግ ያሳድግ የነበረው ባለቤቷ ዛሬ ከሰው እጅ ወድቋል። ዛሬን እንደ ትናንት ማልዶ ሥራ አይሄድም። ለልጆች ፣ ለሚስቱ የኪሱን አይሰጥም ። ወይዘሮዋ አባወራውን ማስታመም ይዛለች፣ ልጆች ለሥራ አልደረሱም ።ቤቱ የችግርና የሥቃይ ድምጽ እያስተናገደ ነው።

የጎደለ ጎጆ

በሁለት ሰው ትከሻ የቆመው ቤት አሁን ከአንዱም መሆን አልቻለም ።ይሀ እውነት ለዚህ ቤተሰብ አዳጋች ሆኗል። አባወራው አልጋ መያዙ ሚስትን ስራ አልባ አድርጎ ጎጆውን አጉድሏል። አሁን ቤት ቤተሰቡ አጋዥ ረዳት አጥቷል። ወራት የቆጠረው የጎልማሳው ስቃይ መፍትሄ አላገኘም።ጉዳቱ በመሞት፣ መኖር መሀል እያሰቃየው ነው።

ወይዘሮ መሰሉ አቅሟ ተፈትኗል። ባለቤቷ አገግሞ መነሳት፣ መዳን አልቻለም። ጉዳት ያገኘው አካሉ አልላወስ ብሎ እያሰቃየው ነው። ወይዘሮዋ ጨንቋታል።የሚያሰራው ድርጅት ለስድስት ወራት ህክምናውን ችሏል። ከዚህ በኋላ ያለው ጊዜ በዋዛ የሚገፋ አልሆነም።እናት መሰሉ ጉልት በምትውልበት ገበያ እርዳታ መጠየቅ ይዛለች። የሚያውቋት ሁሉ እጃቸውን ዘርግተዋል። የባሏን አሳዛኝ ታሪክ የሰሙ የአቅማቸውን አድርገዋል።

ስድስት የጭንቅ ወራት ካለፉ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ የሆነው ሁሉ ሆነ። በአደጋው የህመም ስቃይ ሲከፍል የቆየው አባወራ ህይወቱ አለፈ።ይህ ጊዜ ለወይዘሮ መሰሉና ልጆቿ ከባድ ነበር። የእሱን መሞት ተከትሎ ቤተሰቡ በችግር ተፈተነ።

የአባወራው አሰሪ ድርጅት አስታሞ ከቀበረ በኋላ ዞር ብሎ አላያቸውም። ወይዘሮዋ ልጆቿን ለማሳደግ በጥረት ልፋቷ ቀጠለች።አሁን ከጎኗ የሚቆም ‹‹አለሁሽ ››የሚል አጋር የላትም። የአራቱ ልጆች ኃላፊነት በእሷ ወድቋል።ጥርሷን ነክሳ በብርታቷ ገፋች። የጉልት ሥራዋ ቋሚ መተዳደሪያ ሆኗታል። ቀድሞ የነበረችበት ስፍራ በህጋዊነት ተቀብላ አጠንክረዋለች። ልጆቿ እያደጉ ፣እሷ እየበረታች ነው።

ከዓመታት በኋላ

እነሆ! ይህ ታሪክ ካለፈ ድፍን አስራአምስት ዓመታት ተቆጠሩ። ዛሬ እሷና ልጆቿ በዕድሜ ገፍተዋል። የአንድ እጅ ኑሮዋ ባይሞላም ጓዳዋ አልጎደለም። ሮጣ ታድራለች፣ ሰርታ ትገባለች። ቋሚ የጉልት ስራዋ የቤት ኪራይ ይችልላታል። ኑሮዋን ደጉሞ ከሰው ያውላታል። ዛሬ ላይ መሰሉ ለቤት ኪራይ የምትጠየቀው ገንዘብ እንደበፊቱ አይደለም።ዋጋው በእጥፍ ጨምሯል።

የኑሮው ውድነት፣ የዕለት ወጪው ጣጣ በዋዛ አይቀምስም። ይህ ሁሉ ለእናት መሰሉ የየዕለት እውነታ ነው። ካንዱ ወስዳ ለአንዱ መሙላት፣ግድ ይላታል።ለዚህ ሁሉ ጎዶሎ ተስፋ የሆናት የጉልት ሥራዋ ብቻ ነው። ጉልቱ ለልጆቿ መኖር ዋስትና ሆኗል። በእሱ መኖር ቆማለች። ሁሌም እሷን ያሉ ደንበኞቿ ፈልገው አያጧትም።

መሰሉና የጉልት ጓዶቿ ዛሬም በስፍራቸው ተገኝተዋል። ድንች ሽንኩርቱን ጎመን ቲማቲሙን አስቀድመው ሊያወርዱ የዕለት ሥራቸውን ይዘዋል። አብዛኞቹ ዓይናቸውን ከመንገዱ ተክለው ጠያቂ ይጠብቃሉ። የእጃቸውን ጨርሰው ሌላ ለመተካት የያዙት ማለቅ አለበት። አንዳንዶቹ ደንበኞቻቸው የሚፈልጉትን እየጠየቁ ይገዟቸዋል።

ድንገቴው ክስተት

ከቀናት በአንዱ በድንገት የተነሳው ግርግርና ሁካታ አካባቢውን ማደፍረስ ያዘ።ከላይ ታች የሚራወጡት ሰዎች ተደናግጠዋል። አረንጓዴ ለባሾቹ ደንብ አስከባሪዎች ቆመጥ ዱላ እንደያዙ በፖሊሶች ታጅበው ሥራቸውን ቀጥለዋል። በአፍታ ቆይታ የነመሰሉ ጉልትና አካባቢው እንዳልነበረ ሆነ።

ሸራ የለበሱ የንግድ ቤቶች ጣራ ግድግዳቸው እየፈረሰ ፣ማገራቸው ተቆለለ። ጩኸት፣ለቅሶና ሁካታ ስፍራውን በአንዴ ለወጠው። ንብረታቸው አብሮ የባከነባቸው እነመሰሉ በተማጽኖ ደጅ ጠኑ። በጉልታቸው በቅርቡ ለሽያጭ ያስገቡት አትክልት ይመለስላቸው ዘንድ አብዝተው ለመኑ፣ተማጸኑ። ሙከራቸው አልተሳካም። ዓይናቸው እያየ ያስገቡት ሽንኩርት ድንች በመኪና ታጭቆ መሄዱን አረጋገጡ።

መሰሉ ለጉልት ስራዋ ከመኪና ያወረደችው ሰባት ሳጥን ቲማቲም ፣ ሽንኩርትና ድንች በአይሱዙ ተጭኖ ሲሄድ በመሪር ሀዘን ሸኘችው። ጉልቱ ማለት ለእሷና ለቤተሰቦቿ የእንጀራ ሞሰባቸው፣ የመኖር እስትንፋሳቸው ነበር። ለዓመታት ችግር መከራን አልፈውበታል፣ደግ ክፉ አይተውበታል።

መሰሉና የሥራ አጋሮቿ እንደሚሉት የጉልቱን ቦታ ያገኙት በህጋዊ መንገድ ነው። የግብር መክፈያ ቁጥር /ቲን ነምበር / ተሰጥቷቸውም በአግባቡ ሲገብሩ ቆይተዋል። ድንገቴው ጉዳይ ያልጠበቁትና ፈጽሞ ያልተዘጋጁበት ዱብዕዳ ሆኖባቸዋል።

ሁሉም ሴቶች ጉዳዩን በአግባቡ ለማስረዳትና መፍትሄ ለመሻት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ሲማጸኑ ከርመዋል። እነሱን ከመስማት ይልቅ ስድብና ማመናጨቅን የመረጡ አካላት ግን በአካባቢው ድርሽ እንዳይሉ አባረዋቸዋል።

ከሰሞኑ ጥቂት የጉልት ሴቶች በአካባቢያቸው አስኮ አዲሱ ሰፈር ከሚገኝ የመንገድ ዳርቻ ጥቂት ዕቃዎችን ይዘው ተቀምጠዋል።ሁሉም ‹‹አዩኝ አላዩኝ›› በሚል መሳቀቅ ቀኑን ይገፉታል። ስፍራው አንዳች ከለላና ተገን የለውምና ለእይታ ተጋላጭ ናቸው።እነሱን ያለ የአቅሙን እየገዛ፣ እየጎበኛቸው ያልፋል።

የደንቦች ኮቴና ጥላ የሚያስደነብራቸው የጉልት እናቶች በሥፍራው የመገኘታቸው እውነት በርካታ ነው። አብዛኞቹ የዕለት ጉርሳቸውን ለመሙላት ሌላ ምርጫ የላቸውም። የቤት ኪራይ ፣ የልጆች ማሳደግና የኑሮውን ውድነት በእነሱ አቅም የሚጋፈጡት አይደለም።

ዛሬን በጥያቄ

መሰሉ ድንገት በሆነባት ጉዳይ ግራ እንደተጋባች ነው።አሁን የቱን ይዛ የቱን እንደምትለቅ ጨንቋታል።እሷና መሰል ሴቶች ከሚመለከተው ክፍል ምላሽን ይሻሉ። ዛሬ በጓዳቸው በእነሱ አቅም የማይሸፈኑ በርካታ ችግሮች ከፊታቸው ቆመዋል። የህይወት ስንክሳሮችን ተቋቁመው ኑሮን ከሞላ ጎደል ለመምራት የነበረቻቸው አንድ ዓይን ጠፍታባቸዋለች።አሁን ጥያቄ አላቸው። መልስ ይጠብቃሉ። ዛሬ ብርሀን የሚያሳያቸው ሸክማቸውን የሚያቀልላቸው እጆችን ይናፍቃሉ።ለፍቶ አዳሪዎቹ የጉልት እናቶች።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ነሃሴ 6/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *