ዳያስፖራው የሀገር ክንድና መከታ እንጂ የግጭት ነጋዴዎች መጠቀሚያ አይደለም!

በውጪ የሚኖሩ አብዛኞቹ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን (ዳያስፖራ) ሀገር ችግር ላይ በወደቀችባቸው በየትኞቹም ጊዜያት ፈጥነው በመንቀሳቀስ፤ ለሀገራቸው እና ለወገናቸው ያላቸውን ከፍ ያለ ፍቅር በተግባር አሳይተዋል። በዚህም በመላው ሕዝብ እና በመንግሥት ሰፊ እውቅና አግኝተዋል፤ በታሪክም ውስጥ ደምቆ የመታየት እድላቸው ሰፊ እንደሚሆን ይታመናል።

በተለይም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በሀገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ በመደገፍ ያሳዩት ሁለንተናዊ ንቅናቄ፤ በርግጥም ለወገኖቻቸውና ለሀገራቸው ብሩህ ነገዎች ያላቸውን ቀና እሳቤና በጎ ህሊና በተጨባጭ ያሳየ ነው ። ለተግባራዊነቱም ያላቸውን ዝግጁነት እና ቁርጠኝነት በአደባባይ ማስመስከር ያስቻለ፤ የአዲስ ምዕራፍ ጅምር ተደርጎ የተወሰደ ነው።

ይህ ከዘረኝነት ፣ ከመንደርተኝነት እና ከጽንፈኝነት ያልተጋባው፤ ሀገርና ሕዝብን ብቻ ታሳቢ ያደረገው ንቅናቄ ከሀገር አልፎ ዓለምን ያስገረመ፤ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ስላላቸው የላቀ ፍቅር ቀደም ሲል ሲነገር የነበረን እውነታ በዓለም አቀፍ አደባባዮች በተጨባጭ ያስመሰከረ ክስተት ነው።

ሀገር ከሃይማኖትና ከማንነት፤ የሀገር እና የሕዝብ ተስፋዎች ከዛሬ ተግዳሮቶች በላይ መሆናቸውን ከመረዳት የመነጨው ይህ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን (ዳያስፖራ) ንቅናቄ፤ ሀገርን ተፈጥሮ ከነበረው የህልውና ስጋት ለመታደግ በተደረገው መራራ ተጋድሎ ትልቅ አቅም ሆኖ አልፏል። አሁን ላለው ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት አስተዋጽኦው ከፍ ያለ ነው።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገራዊ ንቅናቄ ገና ከጅምሩ ብዙም ያልተዋጠላቸው ጥቂት የግጭት ነጋዴዎች፤ ንቅናቄውን በመንደር እና መንደርተኝነት ሊፈጥራቸው በሚችሉ ጽንፈኛ አስተሳሰቦች ለመከፋፈል ሰፊ ዘመቻዎችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል። “ከበሬ ወለደ” ትርክት ጀምሮ በአግባቡ ስለማያውቋቸው ብሄር ፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የመብት ተሟጋች ሆነው ሰልፍ ለማሳመር ሞክረዋል።

በመንደርተኝነትና ጽንፈኛ አስተሳሰቦች ፤ ለእውነት መቼም ቢሆን ላይነቁ ተኝተው እያንኮራፉ፤ በማንኮራፋታቸው ብዙዎችን ሰላም እየነሱ ፤እራሳቸውን “የማህበረሰብ አንቂ” በሚል ዘመነኛ ስያሜ በሕዝባችን ዛሬዎች እና ከዛሬ በሚወለዱ ነገዎች ላይ ሲያላግጡ፤ በዚህም ሲፈነድቁ ውለው ማደር ከጀመሩ ሰንብተዋል።

እነዚህ በሕዝብ ደም የሚገበያዩ የግጭት ነጋዴዎች፤ ጥላቻ እንጂ ፍቅር የማያውቁ፤ ለአትራፊነት ሞት እንጂ ህይወትን የማይመርጡ ፤ ከጥፋት ውጪ ልማት የማይታያቸው፤ አዕምሯቸው በመንደርተኝነት እሣቤ ታጥሮ ለዚሁ እና ለዚሁ ብቻ የተገዛ፤ የድብቅብቆሽ ዓለም እየፈጠሩ የጠራውን ከደፈረሰው፣ የፀዳውን ካደፈው የሚያደበላልቁ ፤ ፍርሃትንና ስጋትን በማሰራጨት ሕዝብን ምቾትና እንቅልፍ ማሳጣት የገበያ አማራጭ አድርገው የወሰዱ ናቸው።

በዚህ ማንነታቸው በሀገር ውስጥ ያለውን ዜጋ ሕይወት ስጋት ውስጥ ከመጨመር ጀምሮ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ስለሀገራቸው እና በሀገራቸው እየተካሄዱ ስላሉ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ፣ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ተገቢና ትክክለኛ መረጃ እንዳይደርሳቸው በማድረግ የግጭትና የሁከት ዓላማቸው ሰለባ እንዲሆኑ እየሰሩ ነው።

በተለይም ከሀገር ውጪ ያለውን ኢትዮጵያዊ እና ትውልደ ኢትዮጵያዊ በመንደርተኝነት እና በጽንፈኛ አስተሳሰቦች በመመረዝ ስለሀገር ያለውንና የነበረውን ፍቅርና ተቆርቋሪነት ወደ መንደር ለማውረድ የሄዱበትና እየሄዱበት ያለው የጥፋት መንገድ አደገኝነቱ የከፋ ነው።

አደገኝነቱ አንድም ስለ ሀገሩና ወገኑ የነበረውን ተስፋ እንዲጥልና ወደ ቀደመው የቁዘማ ሕይወት እንዲመለስ የሚያደርገው ሲሆን፤ ከዚህም ባለፈ ባለው አቅሙ ሀገሩንና ወገኑን እንዳይደግፍ፤ በዚህም ሊያገኝ የሚችለውን ርካታ እንዲያጣ የሚያደርግ፤ ከተስፋውና ከእርካታው የሚያፋታ ነው።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን (ዳያስፖራ) የግጭት ነጋዴዎች የገበያ አማራጭ አድርገው የወሰዱት ሀገርን በግጭት አዙሪት የመክተት ተልእኮ በሰከነ መንፈስ ፣ በአግባቡ ተረድተው ራሳቸውን ከመንደርተኛ አስተሳሰቦች ሊጠብቁ፤ ስለ ሀገራቸው ሲሉ ከመንደርተኝነት እና ከጽንፈኝነት ርቀውና ሀገርንና ሕዝብን ብቻ ታሳቢ ባደረገ ቀናና በጎ አስተሳሰብ ሊንቀሳቀሱ ይገባል!

አዲስ ዘመን ነሃሴ 6/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *