የከተማዋን የውሃ ችግር ለማቃለል የሚያግዙ ፕሮጀክቶች

አዲስ አበባ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገች ትገኛለች። የከተማዋን ዕድገት ተከትሎ በተለይ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና ፍላጎት መመጣጠን አልቻለም። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዛ የመጣው የነዋሪዎቿ ቁጥርም የውሃ ፍላጎቷ ከዓመት ዓመት እንዲጨምር ካደረጉ ምክንያቶች መካከል በዋነኝነት ይጠቀሳል።

በመዲናዋ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይኖርባታል ተብሎ የሚገመት ሲሆን፣ መረጃዎች እንደሚያመላክቱትም፣ ከተማዋ በቀን እስከ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ያስፈልጋታል። በከተማዋ ያለው የውሃ አቅርቦትና ምርት ግን በቀን ከ725 ሺህ ሜትር ኪዩብ የሚበልጥ አይደለም። ይህን ተከትሎም የመዲናዋ ነዋሪዎች በንፁሕ የመጠጥ ውኃ ችግር በተለያዩ ጊዜያት ምሬታቸውን ሲገልፁ ማዳመጥ የተለመደ ነው።

በመዲናዋ የውሃ ጥያቄ ያልነካው ሰፈር፣ ያልዳሰሰው ሕብረተሰብ፣ ያላሳሰበው የለም። በመሀል አዲስ አበባ ሳይቀር ውሃ በተከታታይ ከሳምንቱ ቀናት ከግማሽ በላይ ወይንም ለሶስትና ለአራት ቀናት መጥፋት ተለምዷል። በከተማዋ በስፋት የውሃ እጥረት የሚስተዋልባቸው አካባቢዎችና በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ውሃ የሚያገኙ ሰፈሮች መኖራቸውም ይነገራል።

አብዛኞቹ ነዋሪዎችም የዝናብ ውሃን ለማጠራቀም ሲሯሯጡ መመልከትና በታንከርና በተለያዩ ማጠራቀሚያ እያጠራቀሙ መገልገልን ልምድ ማድረግ ከጀመሩ ውለው አድረዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች የመጠጥ ውሃ በተደጋጋሚ በመጥፋቱ ነዋሪዎች መደበኛ ሥራዎቻቸውን ጭምር በመተው ጀሪካን ይዘው ውሃ ፍለጋ ከቦታ ቦታ የሚንከራተቱበትን ትይዕንት ማስተዋልም ተለምዷል።

ለመዲናዋ የውሃ ፍላጎት መጨመርም የተለያዩ ምክንያቶች ይዘረዘራሉ። ከፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም በተጨማሪ የኢንቨስትመንት መስፋፋት፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የሕዝቡ አኗኗር ዘይቤ መለወጥ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። የኤሌክትሪክ መቆራረጥና ለመንገድ ግንባታ የሚቆፈሩ ቧንቧዎች እንዲሁም በከንቱ የሚባክን ውሃ መብዛቱ የውሃ እጥረቱን እንዳባባሱትም ይገለፃል።

የአንድ ሀገር ንፁህ ውሃ የማምረት አቅም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትርጉሙ ከፍተኛ እንደሆነ ምሁራን ያስረዳሉ። ለአብነትም በአንድ ሀገር የሚከሰት የውሃ አቅርቦት ችግር ኢኮኖሚን ይጎዳል። የውሃ አለመኖር ብዙ ሕዝብ የሚተዳደርበትንና ውሃን አሟጦ በሚጠቀም የሚታወቀውን የአገልግሎት ዘርፍ (Service Sector) ያሽመደምደዋል። የውሃ እጥረት ለበርካቶች የሥራ እድል ፈጣሪ ነው የሚባለው የኮንስትራክሽን ዘርፍ ወደፊት እንዳይራመድ ትልቅ መሰናክል ይሆናል።

የውሃ አቅርቦት ከኢንቨትመንት ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው። የውጭ ባለሃብቶች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ሲያስቡ ከሰላም ባሻገር ቀጥሎ የሚያሳስባቸው የኢንተርኔት፣ የውሃ እና የኤሌክትሪክ ኃይልን የመሰሉ የመሠረተ ልማቶች አቅርቦት ነው። ስለ አዲስ አበባ የውሃ አቅርቦት አቅም የተካሄዱ ጥናቶችም የከተማዋ የውሃ እጥረት እየተባባሰ እንጂ እየቀነሰ የሚሄድ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ አመላክተዋል።

ብዙ ስመጥር የሃይድሮሎጂ ምሁራንም ይህን ፍላጎት ለማሟላት ከከርሰ ምድር ውሃ በተጨማሪ ለገጸ ምድር ውሃ ልማት ትኩረት መስጠት እንደሚገባ በተደጋጋሚ መክረዋል። የመዲናዋ የውሃ ፍላጎት አቅርቦቱን እየቀደመ መገኘቱን ተከትሎ ይህን አለመጣጣም ለማስተካከል የተለያዩ አማራጮችን ለመተግበር ተሞክሯል። በተለይ ከፍተኛ የውሃ እጥረት በስፋት በሚከሰትባቸው የከተማዋ አካባቢዎች ውሃ በፈረቃ የማቅረብ ተግባር ጊዜያዊ የመፍትሄ አማራጭ ተደርጎ ሲሰራበት ቆይቷል።

ይሁን እንጂ መሰል የመፍትሄ አማራጮች አስተማማኝና ዘላቂ ውጤት ማምጣት የማይችሉ በመሆናቸው የከተማዋ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ችግሩን ሊፈቱ የሚችሉ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ፕሮጀክቶች በመንደፍ ለተግባራዊነታቸው መትጋት ከጀመረ ቆይቷል። በተለይ የገፀ-ምድርና የከርሰ ምድር የውሃ ምንጮችን መሠረት ያደረጉ አማራጮችን በማዘጋጀት የተለያዩ ፕሮጀክቶች ለመተግበር እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቆይተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በየጊዜው የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር የውሃ ልማት ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ እያስገባ ይገኛል። ከቀናት በፊትም የከተማዋን እለታዊ የውሃ ምርትና ሥርጭት እንዲሁም የፍሳሽ ማስወገድ አቅም ከፍ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ለምርቃት በቅተዋል። የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከቀናት በፊት ከአንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸውን ፕሮጀክቶች መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።

ፕሮጀክቶቹን መርቀው ሥራ ያስጀመሩት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ‹‹ውሃ ለከተማችን እጅግ ወሳኝ እና አንገብጋቢ ጉዳይ በመሆኑ ዛሬ ያስጀመርናቸው ፕሮጀክቶች በእጅጉ ወሳኝ ናቸው፣ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን የንጹሕ መጠጥ ውሃ ችግር በተጨባጭ ሊያቃልሉ ይችላሉ›› ብለዋል።

ከ2011 ዓ.ም ወዲህ ያለው ውሃ የማምረት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የሚገኝ ሲሆን፣ እስከ 2011 ዓ.ም በቀን ይመረት የነበረው የከተማዋ የውሃ አቅርቦት ከ525 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ አልነበረም። በአሁኑ ወቅት የውሃ አቅርቦቱን ከ800 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ ማድረስ ተችሏል።

የከተማዋን የውሃ አቅርቦት አቅም ለመጨመር የከተማ አስተዳደሩ የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ሥራዎችን እያሻሻለ ይገኛል። ውሃ ከማምረትና ከማሰራጨት ባሻገር ለሕብረተሰቡ የሚሰራጨውን ውሃ ደህንነት የሚያረጋግጥ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ዘመናዊ የውሃ እና ፍሳሽ ላብራቶሪ ተቋቁሞ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል።

አጠቃላይ እየተሰራ ያለው ሥራ የመጠጥ ውሃ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን የከተማዋን ፍሳሽ ማጣራት ደግሞም መልሶ መጠቀም እንደሆነ የተናገሩት ከንቲባዋ፣ ‹‹ከዚህ አንፃር ከተማችን አዲስ አበባ ፍሳሽ ማጣራት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ የነበራት ፍሳሽ የማጣራት አቅም ከ84 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ አልነበረም። በአሁኑ ወቅት ይህን አቅም ከእጥፍ በላይ መጨመር ችለናል። ከለውጡ ወዲህ ብቻ 93ሺህ ሜትር ኪዩብ ‹አዲስ ፍሳሽ የማጣራት አቅም መጨመር ችለናል›› ሲሉ አስረድተዋል።

እንደ ከንቲባዋ ገለፃ፣ የከተማ አስተዳደሩ የሕዝቡን ጥያቄ የሚመልሱና ተጠቃሚነቱን የሚያረጋጋጡ ፕሮጀክቶችን በጥናት በመለየት በቅደም ተከተል በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ እያስገባ ይገኛል። ይህም ‹‹ከተማዋን እንገነባለን፣ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንችላለን›› ለተባለው ተጨባጭ ማስረጃ ነው። በተለይም በ2015 ዓ.ም በከተማ አስተዳደሩ የተገነቡና በአንድ ዓመት ውስጥ የተጠናቀቁ ከአምስት ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች እንዲሁም ማህበረሰቡን በማሳተፍ፣ መኖሪያ ቤትን ጨምሮ፣ የተገነቡ ከስድስት ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚቻል አፍ ሞልቶ ለመናገር የሚያስችሉ ናቸው።

የተመረቁት የውሃ ፕሮጀክቶች በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ተጀምረው የተጠናቀቁ መሆናቸውን ያመላከቱት ከንቲባዋ፣ ‹‹ከተማችን ፕሮጀክት ጀምራ በተያዘለት ጊዜና በጀት የማጠናቀቅ ባህሏን ጠብቃ የነዋሪውን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥና የከተማችንን ገጽታ በመገንባት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን ከፍ ለማድረግ በትጋት ማገልገላችንን እንቀጥላለን›› ነው ያሉት።

‹‹በአሁኑ ወቅም ፕሮጀክቶችን ጀምሮ መጨረስ ብቻ ሳይሆን የትኛው ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል? የማህበረሰቡን ጫና ሊያቃልል የሚችለው እንዴት ነው? እንዴት ቢሰራስ ነው በፍጥነትም በጥራትም ማጠናቀቅ የሚቻለው? የሚለውን እውቀት ጭምር በማዳበር እየተሰራ ነው›› ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ የከተማ አስተዳደሩ የመዲናዋን የውሃ ችግር ለማቃለል የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ለአገልግሎት ቢያበቃም ህብረተሰቡ የውሃ ብክነትን በማስቀረትና ፕሮጀክቶቹን በመንከባከብ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንደሚኖርበትም አሳስበዋል።

በመዲናዋ ውሃ በእጅጉ እንደሚባክን ያመላከቱት ከንቲባዋ፣ መሰል የውሃ ፕሮጀክቶችን ገንብተን ውሃ እያቀረብን እንዲሁም በበርካቶች ዘንድ ከፍተኛ የውሃ ፍላጎት እያለ የመጠጥ ውሃን ለተሽከርካሪ እጥበት በተለያዩ መንገድ ለተለያዩ የንፅህና መጠበቂያዎች ጥቅም ላይ ማዋል ይስተዋላል። ከዚህ አልፎ የጎላ የውሃ አጠቃቀም ችግርም ይታያልም›› ይላሉ። ያለን ሃብት በትክክል እንዲሁም በእውቀት መጠቀም እስካልተቻለ ድረስ መሰል ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ ዋጋ አይኖረውም። ስለዚህም አግባብ የሆነ የውሃ አጠቃቀም ባህልን ማዳበር እንደሚገባም አፅእኖት ሰጥተው አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዘሪሁን አባተ፣ የውሃ ፕሮጀክቶቹ የከተማዋን እለታዊ የውሃ ምርትና ሥርጭት የሚለውጡ እንደሆኑ ጠቁመው፣ በቀን 67ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ መስጠት የሚችሉና የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱን ውሃ የማምረት አቅም በቀን ከ725 ሺ ወደ 792 ሺህ ሜትር ኪዩብ የሚያሳድጉ ስለመሆናቸውም ይናገራሉ።

ሥራ አስኪያጁ እንደሚገልጹት፣ ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ከ670 ሺህ በላይ ለሚሆኑት የንፁህ ውሃ አገልግሎት የሚሰጡት የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክቶች በ2015 ዓ.ም በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች የተቆፈሩና ከ300 እስከ 500 ሜትር ጥልቀት ያላቸው 25 የውሃ ጉድጓዶች ናቸው። የኤሌክትሮ-ሜካኒካል እና ሲቪል ሥራዎች እንዲሁም የተለያየ ስፋት ያላቸው የ31 ኪሎ ሜትር የውሃ መስመር ዝርጋታ፣ ከ200 እስከ አንድ ሺህ 500 ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም ያላቸው ማጠራቀሚያ ጋኖች፣ የመቆጣጠሪያ ክፍልና ሌሎች መሠረተ ልማትና ግብዓቶች ተሟልተውላቸዋል።

አዲስ የውሃና ፍሳሽ ፕሮጀክቶች ከመሥራት ጎን ለጎን በከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰሩ ያሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የውሃና ፍሳሽ መስመር መዘርጋት መኖሩን የጠቀሱት ኃላፊው፤ ጉዳዩ ጊዜ የማይሰጠው መሆኑን በመረዳት በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች በሚገኙ የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የተለያየ መጠን ያላቸው 40 ኪሎ ሜትር የውሃ ማስተላለፊያ መስመሮች እንዲሁም 138 ኪሎ ሜትር የፍሳሽ መስመር በመዘርጋት ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን ያነሳሉ።

ውሃ ለመጠጥ የሚያገለግል መሆን/አለመሆኑን፣ ለህብረተሰቡ ከተለቀቀ በኋላም ደረጃውን መጠበቁን ለማረጋገጥ እንዲሁም ፍሳሽ ቆሻሻን ሳያጣሩ ወደ ታችኛው ተፋሰስ መልቀቅ በአካባቢ ጥበቃ ሕግ የተከለከለ ነው። እናም የተሰበሰበ ፍሳሽ በአግባቡ ስለ መጣራቱ ለማረጋገጥ የተደራጀ ላብራቶሪ መገንባት ግዴታ ነው። ይህን መሠረት በማድረግ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ከዓለም ባንክ በተገኘ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር ብድር የውሃና ፍሳሽ ላብራቶሪ ተቋቁሟል።

ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በሁለት መቶ ሚሊዮን ብር ወጪ 150 ሺህ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የማድረግ አቅም ያላቸው ስድስት የውሃ ፕሮጀክቶችን በበረካ እና በሰበታ ወረዳ ለመገንባት የርክክብ ሂደት ላይ ይገኛል። የገፀ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ፋይናንስ ከማፈላለግ ጎን ለጎን በሁለት ዓመት ውስጥ ወደ ሥርጭት የሚገባ በቀን ከ80 እስከ 100 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ መስጠት የሚችል ፕሮጀክትም እያለማ ይገኛል።

መዲናዋን የሚመጥን ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያ ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ ነው። በዚህም በ241 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በቀን 104 ሺህ ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ ማጣራት የሚችል የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ እና ከከባድ እስከ ቀላል የፍሳሽ ማሰባሰቢያ መስመር ዝርጋታ ሥራ ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቀዋል ተብሏልም።

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ነሃሴ 6/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *