የትውልድ ቦታቸው ባህርዳር ከተማ ፤ እድገታቸው ደብረማርቆስ ነውⵆ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያው በደብረ ማርቆስ ተምረዋል። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪነግ ተምረው አጠናቀዋል። ለሁለት ዓመት ያህል በሥራ ዓለም ካገለገሉ በኋላ ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ ነጻ የትምህርት እድል የሁለተኛ ዲግሪ(ማስተርስ) ትምህርታቸውን በኤሮ እስፔስ (Aerospace) ኢንጂነሪንግ በጀርመንና ሲዊድን ለስድስት ወራት፤ በፊላንድ ለአንድ አመት በመማር እ.ኤ.አ 2009 አጠናቀዋል።
ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በጀርመን ስፔስ ኤጀንሲ (Space Agency of Germen) ውስጥም ለአምስት አመታት እየሰሩ በመማር የሶስተኛ ዲግሪ (ፒኤችዲ) ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። እ.ኤ.እ እስከ 2014 እዚያው በጀርመን ስፔስ ኤጀንሲ ቆይታዋል። በጃፓን ቶሆኩ ዩኒቨርሲቲም ለሁለት ወራት ያህል ሠርተዋል።
እኤአ ከ2014 በኋላ ከስፔስ ሳይንስ ፕሮግራም በመውጣት በሚዲካል ሮቦቲክስ (medical robotics) ለአንድ ዓመት ፖስት ዶክ በተሰኘ ፕሮግራም ተቀጥረው ሰርተዋል። መጀመሪያ ጀርመን እያሉ ሥራዎቻቸውን አሜሪካ ለኮንፍረንስ አቅርበው ስለነበረ በአሜሪካ ናሳ ምርምር ማዕከል የሚሰሩ ባለሙያዎች ሥራቸውን አይተው በምርምር ማዕከሉ ሴሜናር እንዲያቀርቡ እድሉን እንደከፈቱላቸው ያስታወሳሉ። ሴሜናሩን ሲያቀርብ በማስተባበር የረዳቸው ከሳቸው ቀደም ብሎ አሜሪካ ናሳ የምርምር ማዕከል ይሰራ የነበረው ኢትዮጵያዊው ሲኒየር ዶክተር ብሩክ ላቀው እንደነበር አጫውተውናል።
በቀጣይም በናሳ የምርምር ማዕከል የሚሰሩት ባለሙያዎች ለምን እኛ ጋ መጥተህ አትሰራም በሚል ጥሪ ስላቀረቡላቸው ወደ ምርምር ማዕከሉ በመግባት ፤ በፖስት ዶክ ፕሮግራም በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ እየሰሩ ይገኛሉ።
ሀገራቸውን በሙያቸው ለመርዳት ካላቸው ከፍያለ ፍላጎት የተነሳም ሲስተም ኢንጂነሪንግ ‹‹SSGI SYSTEM ENGINEERING HANDBOOK›› የተሰኘ መጽሐፍ ለሕትመት አብቅተዋል። መጽሐፉ በናሳ ቆይታቸው ያገኙትን ተሞክሮ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጆኦስፖሻል ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው። የዛሬ እንግዳችን ዶክተር መላክ ዘበናይ ይባላሉ። ከእሳቸው ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ሳይንስ ትምህርት እንዴት ገቡ?
ዶክተር መላክ፡– በልጅነቴ በትምህርት ቤት ቆይታዬ የሂሳብ ትምህርትን በጣም እወድ ነበር። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስገባም እንደዚሁም ሂሳብ ፣ኬሚስትሪ እና ፊዚክስ በጣም የምወዳቸው የትምህርት አይነቶች ነበሩ። ብዙ እውቀት ሳይኖረኝ ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ መማር እንዳለብኝ ዝም ብዬ አስብ ነበር ። እንዲያውም ወላጆቼ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴ በሰባት ትምህርት አራት ነጥብ (ስትሬት 7A ) ያመጣሁ ስለነበር፤ እንደዚህ አይነት ውጤት ያመጡ ልጆች ብዙ ጊዜ የሕክምና (ሜዲስን) ትምህርት ይመርጡ ስለነበር ወላጆቼም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ወደ ሕክምና (ሜዲስን) ትምህርት እንድገባ ብዙ ግፊቶች ያደርጉብኝ ነበር። እኔ ግን ፍላጎቴ ኢንጂነር የመሆን ነበርና ወደ ኢንጂነሪንግ ትምህርት ገባሁ።
በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪነግ ተምሬ ተመርቄ ወደ ሥራ ዓለም ከገባሁ ጀምሮ፤ ለቴክኖሎጂ ያለኝ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለመጣ በቴክኖሎጂ ላቀ ያለ እውቀት ለማግኘትና በጥልቀት ለማወቅ ደግሞ ትምህርት መማር ስለነበረብኝ ሥራዬን አቋርጬ ትምህርቴን ቀጠልኩ። የጀመርኩት መንገድም በራሱ እየተስተካከለ አሁን የደረሰኩበት ደረጃ ልደርስ ችያለሁ። እስካሁንም በሳይንስ ትምህርት መስክ እንደቀጠልኩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የናሳ ምርምር ማዕከልን የተቀላቀሉበት ሂደት ምን ይመስላል ?
ዶክተር መላክ፡- በጀርመን ሀገር ስፔስ ኤጀንሲ እየሰራሁ የሶስተኛ (ፒኤችዲ) ዲግሪ ትምህርቴን እየተማርኩም በነበርኩበት ጊዜ ሥራዬን አሜሪካ ኮንፍረንስ አቀርብ ነበር። በዚያን ጊዜ በናሳ ምርምር ማዕከል የሚሰሩ ባለሙያዎች ሥራዎቼን ስላዩ በማእከሉ ሴሜናር እንዳቀርብ እድሉን ሰጡኝ። ከዚያም ናሳ በሚሰሩ ሥራዎች ግፊት ከጀርመን ስፔስ ሳይንስ ወደ ናሳ ምርምር ማዕከል ልገባ ቻልኩ። አሁንም እዚያው በምርምር ማዕከሉ እየሰራሁ እገኛለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በናሳ ምርምር ማዕከል የእርስዎ የሥራ ድርሻ ምንድነው?
ዶክተር መላክ፡- የሥራ ድርሻዬ የተለያየ ነው። በተለያዩ ተልዕኮዎች ላይ ተሳትፌያለሁ። ለምሳሌ ባለፈው በናሳ ምርምር ማዕከል አስትሮይዲዶ /Asteroidido/ የተሰኘ ያልተሳካ ተልዕኮ ተደርጎ ነበር። እዚያ ሥራ ላይ መቆጣጠሪያ (controller) ዲዛይን ሲደረግ መነሻ ሀሳቡን (concepts) ዲዛይን በማድረግ ተሳትፎ አለኝ ፤እንዲያውም ጥናታዊ ጽሁፍ የመጻፍ እድልም አጋጥሞኝ ነበር። ከዚህ በፊት መቆጣጠሪያ /ኮንትሮለር/ ዲዛይን በማድረግ ሥራ ላይ ለሁለት ዓመት ሰርቻለሁ።
ለምሳሌ አሁን ላይ በጣም ውድ የሆነ ሳተላይትን ከመጣል /ሪፊውል/ በማድረግ መጠቀም በሚለው ሀሳብ ከሶስተኛ (ፒኤችዲ) ዲግሪ ትምህርቴ ጋርም የተገናኘ በመሆኑ እዚሁ ተልእኮ ላይ በሲስተም ኢንጂነሪንግ እየተሳተፍኩ ነው፤ ፐሪንሲፖል አናሊስት/ Principal annalistic/ ነኝ። ያ ማለት ለዚያ ተልዕኮ መሆን ያለባቸውን ነገሮች በማስመሰል (simulate) በማድረግ የሚያስፈልጉ ነገሮች (reqerument) በትክክል መተግበራቸውን የምናረጋግጠበት፤ ዲዛይኖች በትክክል መስራታቸውን መረጃዎችን /ዳታዎች የመተንተን ሥራ ላይ እየሰራሁ ነው።
ከዚያ በፊት መቆጣጠሪያ /ኮንትሮለር ዲዛይን/ በሚል የሥራ ክፍል ውስጥ ሳተላይትን መቆጣጠር የሚያስችል ዲዛይን ያስፈልገው ነበር። በዚህ ሥራ ላይ ለሁለት ዓመታት ያህል ሰርቻለሁ።አሁን ላይ ሲስተም ኢንጂነሪን ቲም ወይም ሚሽን ሲስተም የሚባል የሥራ ክፍል ውስጥ ነው የምሰራው። በዚህም አጠቃላይ ተልዕኮውን በመተንተን የተሰሩት የተለያዩ ዲዛይኖች በትክክል መስራታቸውን በማረጋገጥ ችግር ካለ ዲዛይን ላደረጉት ኢንጂነሮች ሪፖርት የማድረግ ሥራ እየሰራሁ እገኛለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ሲስተም ኢንጅነሪንግ የተሰኘውን መጽሐፎ በምን ላይ ያተኮረ ነው?
ዶክተር መላክ፡– በምሳሌ ለማስረዳት ያህል በናሳ ነባራዊ ሁኔታ ፕሬዚዳንቱ ጨረቃ ላይ መሄድ አለብን ብሎ ከፍተኛ ደረጃ ያለው ሃሳብ / የሃይ ሌቨር ኮንሴፕት/ ተናገረ ብንል።ፕሬዚዳንት ስለሆነ ከዚህ በላይ ምንም አይልም፤ የእሱ ሥራ ምናልባት ለዚያ የሚያስፈልገውን በጀት ሲነገረው መፍቀድ ብቻ ነው። ፕሬዚዳንቱ አንድ ሰው ጨረቃ ላይ መሄድ አለበት ካለ ኢንጂነሮች ደግሞ አንድን ሰው ጨረቃ ላይ ለመውሰድ የሚያስፈልጉ ነገሮች ምንድናቸው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት አለባቸው።
ለዚህ ሰው የሚያስፈልገው ነገር ከዜሮ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ ያለውን ተቀብለው ለመስራት የሚያስችል ሂደት ( process) መስራት ይጠበቅባቸዋል። በመጀመሪያ ምንድነው የተፈለገው? የሚለውን ከተለየ በኋላ ቁጭ ተብሎ የተልዕኮ ሀሳብ( mission concept) ይሰራል። ይህንን ለማድረግ ከ<ሀ> ጀምሮ የሚያስፈልገውን ነገር የምንሰራበት መንገድ እያንዳንዱ ሂደት ቅደም ተከተል (procedure ) አለው። መቼ ነው የሚከለሰው (review) የሚደረገው? የበጀቱ የጊዜ ገደብ እስከመቼ ነው? ሲስተሙስ ምን አይነት መሆን ነው ያለበት ? የሚለውን እና የመሳሰሉትን ሁሉንም ነገር የሚሰራበት ይሆናል።
ጨረቃ ላይ የሚሄድ ነገር ይሰራ ሲባል ቃሉ ቀላል ነው።ነገር ግን እዚያ ለመሄድ (ለመላክ )ያለው ሂደትና መንገድ ረጅም ነው። ይህ ሲስተም ኢንጂነሪንግ መጽሐፍ ያንን ሁሉ ረጅም መንገድ እንዴት መሄድ እንዳለብን እያንዳንዱን ሂደት ቀምሮ የሚያሳይ ነው። ማንኪያ መስራት ብዙም ላይከብድ ይችላል፤ በአንድ ሰው ሊሰራ ይችላል። መኪና መስራት ግን ብዙ ነገሮች ያስፈልጉታል። መኪናን ለመስራት የሚያስችል ሁሉንም ሂደቶች በሰው ጭንቅላት መዝግቦ ለመያዝና ለማስታወስ አይታሰብምⵆ
ይህ መጽሐፍ ግን እያንዳንዱ ነገር እንዴት ነው መረጃ ሆኖ የሚቀመጠው? ውሳጣዊ ነገሩንስ እንዴት ነው የሚረጋገጠው? የሚለውን ሁሉ የሚሰራበትን መንገድ የሚያሳይ ነው። ስለዚህ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኢንስቲትዩቶች የሚሰሯቸውን ፕሮጀክቶች ግድብ ሊሆን ይችላል፤ የባቡር አሠራር ወይም ደግሞ ሌላ ትልቅ ፕሮጀክት ሲሰራ በምን መልኩ ነው መስራት ያለበት የሚለውን በሚገባ የሚያስረዳና የሚያሳይ ነው። ይህ አሠራር (ሲስተም) ደግሞ ለማኔጀመንቱ ሥራዎችን ለመከታተልና ለመቆጣጠር በእጅጉ የሚያግዝ ነው።
ከታች ያለው ኢንጂነር ደግሞ ለማን ሪፖርት ማድረግ እንዳለበት፣ ምን አይነት ነገሮች ማረጋገጥ እንደሚያስፈልገው የሚያሳይ እና ሁሉን የሚያቀናጅ አሠራር (ሲስተም) ነው። እንደዚህ አይነት ሲስተም ከሌለ ብዙ ጊዜ ማኔጀመንት ላይ ያሉ ሰዎች አሠራሩን ስለሚያውቁ የሚጠብቁት ውጤቱን ብቻ ነው። መሀል ላይ ያለውን ሂደት በአይናቸው የሚታይ ነገር እስካላዩ ድረስ ለማመን ይቸገራሉ። ይህ የሲሰተም ኢንጂነሪንግ መጽሐፍ ግን ሥራዎች ከመስራታቸው በፊት የተሰራው ሥራ የት ደረጃ እንደደረሰ በትክክል መረጃው እየተያዘ (ዶክሜንት) እየተደረገ፤ ዲዛይኑ የት ደረጃ እንዳለ ፤ ምንያህል በጀት እንደሚያስፈልገው እና ምን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅ ሁሉንም አንድ በአንድ የሚያስረዳ አሠራር (ሲስተም) ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህን መጽሐፍ ለመጻፍስ ምን አነሳሳዎት? መጽሐፉ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ያለው ጥቅም እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር መላክ፡- ይህ ሲስተም ለኢትዮጵያ ያስፈልጋል የሚል ሀሳብ ይዤ ነው የተነሳሁት። ለወደፊት በኢትዮጵያ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ስኬታማ ሆነው እንዲቀጥሉ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ። ይህንንም እውን ለማድረግ ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ና ጆኦስፖሻል ኢንስቲትዩት ማኔጀመንት አካላት ጋር በመነጋገር ሥራውን አብረውኝ የሚሰሩ ባለሙያዎች ተመድበውልኝ ሰርተነዋል። በኢትዮጵያ የሚሰሩት
ፕሮጀክቶች ስኬታማ ሆነው እንዲቀጥሉ ሲስተም ኢንጂነሪንግ ያስፈልጋል። መጽሐፉም ይህንን ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት አስገብቶ የተሰራ ነው።
ይህ አሠራር (ሲስተም) በመጽሐፍ መልኩ ታትሞ የቀረበ ፤ አዲስ ኢንጂነር እዚያ መስሪያ ቤት ሲቀጠር ምን ማድረግ እንዳለበት የሚያሳውቅና እያንዳንዱ ፕሮጀክት የሚሰራበትን መንገድ የሚያሳይ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው መኪና ሥራ ቢባል ከየት ፣ከምንና እንዴት እንደሚጀመር፣ የትኛውን ማስቀደም እንዳለበት ግራ ሊገባው ይችላል። ሰውዬው ኢንጂነር እንኳን ቢሆን መጀመሪያ የትኛውን ነው የማስቀደመው ጎማውን ወይስ የትኛው ክፍሉን ሊል ይችላል፤ ይህንንስ ለመስራት ምንድነው የማደርገው የሚለው ነገር ግልጽ አይሆንለትም። እኛ የሰራነው ሥራ ይህንን ሁሉ ለመስራት የሚያስችል ግልጽ የሆነ አሠራር (ሲስተም) መዘርጋት የሚያስችል ነው ።
አዲስ ዘመን፡- የናሳ የምርምር ማዕከል ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የእርስ በእርስ ግንኙነት ምን ይመስላል?
ዶክተር መላክ፡- የናሳ የምርምር ማዕከል በተለያየ ስቴቶች የሚገኝ ነው። እኔ ያለሁበት ቦታ ሜሪላንድ አካባቢ ያለው ምርምር ማዕከል ሲሆን ወደ 10ሺ የሚጠጉ ሠራተኞችን ይዟል፤ ከእነዚህ ውስጥ እኔ የማውቃቸው ኢትዮጵያውያን አንድ ሁለት ሦስት አሉ። ጓደኞቼ ሁለቱ ናቸው። ላስቪጋስም ያለው ምርምር ማዕከል ውስጥ አንድ የማውቀው ኢትዮጵያው አለ። እኔ የሲስተም ሚሽን ዲፓርትመንት/ sysystem mission department/ ውስጥ ነው የምሰራው።
ኢትዮጵያም መጥቼ የተገነዘብኩትን ሀሳብ እዚያ ላሉ ሁለቱም ጓደኞቼ ነግሬያቸው እነሱም ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ፣ በሀሳብ በማገዝና በማበረታታት እንረዳሃለን ብለው በገቡት ቃል መሠረት እየተረዳሁ ነው። በተወሰነ መልኩ ቢሆን በቪርችዋል ውይይት እናደርጋለን። በብዙ ነገሮችም ተሳትፈዋል። በተለይ ዶክተር ብሩክ እና ዶክተር ብረሃኑ በተለያዩ ችሎታና አቅም ይሄ መጽሐፍ ስኬታማ እንዲሆን ተሳትፈዋል።
ይህ ሲስተም ኢንጀነሪንግ መጽሐፍ ለአንድ ሥራ ብቻ የሚያገለግል አይደለም ለብዙ ነገሮች የሚሆን ሲስተም ለመዘርጋት ይጠቅማል። መጽሐፉ ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ ያለውን የአንድን ነገር የአሠራር ሂደት በሙሉ ያሳያል።
ከሁለቱ ጓደኞቼ ጋር በተገኛኘን ቁጥር በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት እናደርግ ነበር፤ እንመካከራለን የደረሰበትን ደረጃ እንገመግማለን። መጽሐፉ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ እስኪመረቅ ድረስ ጓደኞቼ አጋሮቼ ነበሩ። መጽሐፉ ተመርቆ እዚህ ደረጃ በመድረሱ እነሱ ከኔ በላይ ደስተኛ ናቸው። በተለይ በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ላይ ምን እናድርግ የሚለውን ስንገኛኝ ሁሌም እናወራለን።
አዲስ ዘመን፡- ሀገራችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለችበትን የእድገት ደረጃ በእርስዎ ምልከታ ምን ይመስላል?
ዶክተር መላክ፡- በኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ጥሩ ጅማሮ አለ። ለአብነት መጽሐፉ ምርቃት ላይ በናሳ የምርምር ማዕከል ሞክረው ያልተሳካለትን ተልዕኮዎች ለማሳየት ሙከራ አድርገን ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ የተሰሩ አንዳንድ ፕሮጀክቶች የዓባይ ግድብ ብንመለከት ፣ የባቡር ፕሮጀክቱ እና ሌሎችም የፈጁትን ጊዜዎች አንስተን ነበር። በናሳም ቢሆን ሲስተም ኢንጂነሪንግ በደንብ ተግባራዊ መሆን ባልቻለበት ዘመን ያልተሳኩ ተልዕኮዎች አሉ።
በናሳ ተሞክሮ ያልተሳካውን ተልዕኮ ወደ እኛ ሀገር እንዳይመጣ ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህም ደግሞ የኢትዮጵያን ስፔስ ሳይንስና ጆኦስፖሻል ኢንስቲትዩት ሲስተማቲክ ሆኖ ያለውን በጀት በአግባብ ተጠቅሞ ስኬታማ እንዲሆን ዋስትና የሚሰጥ አሠራር ነው። ምክንያቱም ሥራው በግምት አይደለም የሚሰራው። የአሠራር ሂደት (ሲስተሙን) ተከትሎ ነው የሚሰራው። ትልቅ ውጤት ማምጣት የሚቻለውም እንደዚያ ሲሆን ነው። እኛም ያደረግነው ይህንን ነው። ይህንን መጽሐፍ ለመስራት ስድስት የሚሆኑ የኢትዮጵያን ስፔስ ሳይንስና ጆኦስፖሻል ኢንስቲትዩት ውስጥ የሚሰሩ ኢንጂነሮች ተሳትፈዋል።ይህ አሠራር በመጽሐፍ ከተጻፈው ባሻገር ለሰዎች የተላለፈ እውቀት እንዳለ ማሳያ ነው።
እኔም በናሳ ውስጥ ያገኘሁትን ልምድና ተሞክሮ ይዤ ጓደኞቼ እንዲሁ ያላቸውን ልምድ ለማካፈል ኢትዮጵያ መጥተን ስልጠና ሰጥተናል። በተለይ ዶክተር ብሩክ ከእኔ ጋር በመሆን ስልጠና ሰጥቷል። ይህንን ሁሉ ለማድረግ ያነሳሳን አሠራር(ሲስተም) እንደሚቀድም ለማሳየት ነው። የሚሰራው ሥራ በግምት እንዳይሰራ የአሠራር ሂደትን ( ሲስተምን) ተከትሎ እንዲሰራ ለማድረግ ነው። ሌሎች ሀገሮች በሚሄዱበት መንገድ የሚያስችል ሥራ እንዲሰራ ለማድረግ በማሰብ ነው።
ወደፊት መንግሥት የሆነ ነገር ስሩ ብሎ ሲሰጥ የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፖሻል ኢንስቲትዩት ይህንን ሲስተም ተጠቅሞ ስኬታማ ተልዕኮውን እንዲወጣ ለማድረግ ችለናል ። አሁን ላይ ያለው ሁኔታ ጥሩ ጀማሮ ነው። ጅማሮው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ግን የበለጠ ሲስተማቲክ መሆን ስላለበት ይህንን አሠራር (ሲስተም)መጠቀም ያስፈልጋል።
ሌሎች ሀገራት ሞክረውት ሳይሳካላቸው ቀርተው ከውድቀታቸው ተምረው የሞከሩት ሲስተም በመሆኑ እነሱን ለስኬት ያበቃቸውን መንገድ ተጠቅመን ሳይሳካልን ቀርቶ ከራሳችን ውድቀት ከምንማር በዚህ መንገድ ተጉዘው የተሳካላቸው ካሉ ከእነሱ መማር ትልቅነት ነው። አንድ ሰው ከወደቀ በኋላ ከውድቀቱ ሊማር የሚችልበትን ምክር ሲመከር ይሰማል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ውደቀት ደረጃ ሳይደርስ የሚሰጠውን ምክር መስማት ደግሞ ብልህነት ነው።
የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፖሻል ኢንስቲትዩት የጀመራቸው ሥራዎች ለውድቀት ሳይዳርጉት የኛን ምክር ሰምተው ይህንን ሲስተም እንዲዘረጋ መፍቀዳቸው እኔ እንደትልቅ ነገር አየዋለሁ። አሁን ላይ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በኢትዮጵያ ያለው እድገት ጥሩ ጅምር ላይ ነው። ይበልጥ ደግሞ ሲስተማቲክ በመሆን ሥራዎች ሲሰሩ ጥሩ ደረጃ ይደረሳል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ስለ ኢትዮጵያ ምን ያስባሉ? ምክረ ሃሳብ ካለዎ?
ዶክተር መላክ፡- ይህንን ሲስተማቲክ ኢንጂነሪንግ “ሀንድ ቡክ” ለስፔስ ሳይንስና ጂኦስፖሻል ኢንስቲትዩት ይጠቅመዋልⵆ ሌሎችም የመከላከያ ፕሮጀክት ፣ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና ትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ የሚሰሩ የመንግሥትም ይሁኑ የግል ካምፓኒዎች ትኩረት ሰጥተው ሊያዩት ይገባል። የናሳ የምርምር ማዕከል ብንመለከት የሚሰራቸው ፕሮጀክቶች ስኬታማነት 94 በመቶ በላይ ነው።
ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት በፖሊሲ ደረጃ የወጣ የሲስተም ኢንጂነሪንግ “ሃንድ ቡክ” በመከተላቸው ነው። ይህ መጽሐፍ ኢንስቲትዩቶችም ሆነ ሌሎች በቴክኖሎጂ ላይ የሚሰሩና ለማይሰሩ ተቋማት ለሁሉም ይጠቅማል። ይህ መጽሐፍ የያዘው ኢንጂነሪንግን ብቻ አይደለም። ብዙ አይነት ሲስተሞች ያሉት በመሆኑ ሁሉም ሊጠቀምበት ይገባል።
የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፖሻል ኢንስቲትዩትም የመጽሐፉን የመጀመሪያ እትም ወስደው ለራሳቸው በሚመጥን መልኩ አስተካክለው እንዲጠቀሙበት እመክራለሁ። ይህ ሲሆን የሀገርን ሀብት መቆጠብ߹ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ማጠናቀቅ ይቻላል። ማኔጅመንቱም ሥራዎችን በቀላሉ መከታተልና መቆጣጠር ይችላል።
ይህ አሰራር የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮ የስፔስ ኢንስቲትዩቶች እና ካምፓኒዎች ትላልቅ ፕሮጀክት ሲስተማቲክስ አሠራር መጠቀም ያስፈልጋል። ይሄ ደግሞ ማንም የሚፈልገው ሀሳብ ነው ብዬ አምናለሁ። ሁሉም ተጠቅሞበት ውጤታማ እንዲሆን እመክራለሁ ።
አዲስ ዘመን፡- የሲስተም ኢንጂነሪንግ “ሃንድ ቡክ” ቀጣይ ክፍል ይኖረዋል? በቀጣይ ምን እንጠብቅ?
ዶክተር መላክ፡- አሁን ይህ መጽሐፍ ተዘጋጅቶ የመጀመሪያ ሕትም ተሰራጭቷል። ነገር ግን መጽሐፉ ሲነበብ ግልጽ ያልሆነ ነገር ካለው፤ ብዙዎች ይሄ ነገር ግልጽ አይደለም የሚሉ ከሆነ፤ ሁለተኛ እትም የማይወጣበት ምክንያት አይኖርም። ይሁን እንጂ የመጀመሪያ እትም ሙሉ ነው። አንድ ፕሮጀክት ተጀምሮ እስኪቋጭ ድረስ ያለውን የአሠራር ሥርዓት የያዘ ነው።
ይህ ማለት አንድ መኪና ለመስራት በሀሳብ ተጠንስሶ ተሰርቶ ፤ ተጠቅመንበት ጨርሰን እቃውን የትነው የምንጥለው እስከሚለው ድረስ ያለውን እያንዳንዱን የአሠራር ሂደት በግልጽ ቁልጭ አድርጎ ይዟል። ነገር ግን ይሄ አገላለጽ በአጭር የተቀመጠ ነው ሰፋ እናድርገው የሚል ከመጣ ሁለተኛ እትም ተሻሽሎ የማይወጣበት ምክንየት አይታየኝም።
እኛ መጽሐፉን ስንጽፍ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ከግንዛቤ ለማስገባት ጥረት አድርገናል። ነገር ግን የጎደሉ ነገሮች አሉ፤ እነዚህ መካተት ነበረባቸው፤ በዚህ መልኩ መስተካከል አለበት የሚሉ ባለሙያዎች ከመጡ ሁለተኛ እትም የሚወጣበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል እጠብቃለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ወደፊት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ተባብራችሁ ሀገራችሁን በምን መልኩ ለመርዳት አስባችኋል?
ዶክተር መላክ፡- እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ በምንችለውና አቅማችን በፈቀደ መጠን ሀገራችንን እንረዳለን። አሁንም ሌሎች ፍቃደኛ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር ብዙ ሥራዎች እየሰራን ነው። የተማርኩበት ዩኒቨርሲቲም አልሙናይ ሴክሪቴሪ ስለሆንኩ በዚያ በኩል ብዙ ሥራዎችን እንሰራለን። ለአንድ ወር ኢትዮጵያ በመጣሁበት ጊዜ አልሙናይ ጋር በመተባበር እና ገንዘብ በማወጣት 160 የሚሆኑ ሃይ ኮንፒቲንግ ማሽኖች ለዩኒቨርሲቲዎች (40 ለአዲስ አበባ ፣40 ለጅማ ፣ 40 ለውሎ እና 40 ለባህርዳር ) ሰጥተናል። እነዚህ ማሽኖች ጥናታዊ ጹሑፎች( Research) እና በተመሳሳይ የዳታ ማዕከል ለሚሰሩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያገለግሉ ናቸው።
ብዙ የሚያግዙ ልጆችም አሉ። ይህንንም በማስቀጠል በምችለው አቅም ለመርዳት እፈልጋለሁ። አሁን የጀመርኩትም የሲስተም ኢንጂነሪንግ ሃንድ ቡክ ታትሞ ተሰራጭቷል። ፕሮጀክት እየሰሩ ይሄ ነገር ከብዶናል ምን ማድረግ አለብን ለሚሉት አካላት በሙሉ በማንኛውም አጋጣሚ ለመርዳት ዝግጁ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ጊዜ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመስግናለሁ።
ዶክተር መላክ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ነሃሴ 6/2015