በሀገራችን የከበሩ ማዕድናት አይነትና የክምችት መጠን በሚፈለገው ልክ በጥናትና በምርምር ተለይተው ባለመታወቃቸው ምክንያት ከዘርፉ ሊገኝ የሚገባው ጥቅምን ማስጠበቅ እንዳልተቻለ የዘርፉ ምሁራን በተለያየ ጊዜ ሲያነሱ ይደመጣል። በገበያ ውስጥም ከውስን ማዕድናት ውጪ ጥቅም ላይ ሲውሉ አለመታየቱና በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆኑ የማዕድን ሀብቶችን ወደ ውጪ በአግባቡ ልኮ ተጠቃሚ ለመሆን አልተቻለም።
የግንዛቤ እጥረቱ ደግሞ ተጨማሪ ችግርም ሆኗል። ይህም በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የከበሩ ማዕድናት የህገወጥ ነጋዴዎች ኪስ ማደለቢያ እንዲሆኑ አድርጓል። በእርግጥ የግንዛቤ ችግር ብቻ ሳይሆን ለሃብቶቹ ከተሰጠው አነስተኛ ትኩረትም አንጻር እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ። ሃብቶቹ የጌጣጌጥ ገበያ ውስጥ ካለመታየታቸውም ባሻገር በአነስተኛ ዋጋ በህገወጦች በኮንትሮባንድ መውጣታቸው የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በእጅጉ እየጎዳው ይገኛል።
ከሰሞኑ ከላይ ያነሳናቸውን ቁልፍ ችግሮች ይፈታል ተብሎ የታመነበት አንድ ማህበር መቋቋሙ ይፋ ተደርጓል። ይህ ማህበር ለመፍትሄው የሚሰራ ሲሆን፤ በጋራ መስራትን የሚያበረታታ እንደሆነ ተነግሮለታል። በተለይም ማህበረሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ከማድረግ አኳያ የራሱን ሚና ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል። እንደ ሀገር በማዕድን ዘርፉ በተለይም በከበሩ ማዕድናት ላይ የሚታየውን የሀብት አጠቃቀም ችግር መፍትሄ እንደሚቸረው ታምኖበታል። ማህበረሰቡ በማዕድናቱ ላይ እሴት በመጨመር ተጠቃሚ የሚሆንበትን እድል ፈጥራልም ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።
ማህበሩን የመሰረቱት የኢትዮጵያ የከበሩ ማዕድናትና ጌጣጌጦች አቅራቢ፣ አምራቾችና ላኪዎች ናቸው። ማህበሩ በማዕድን ልማት ዘርፍ ከምርቱ ጀምሮ ተሳስሮ መሥራትን፤ የተሻለ ገቢ ማግኘትን የትኩረት አቅጣጫው አድርጎ በቅንጅት ለመስራት የሚያግዝ እንደሆነ መስራቾቹ ይፋ አድርገዋል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የማዕድን ዘርፍ ልማት የሚጀምረው ከመሬት ጥናት ነው። ማምረትና ለገበያ ማቅረብ የሚሉት ቀጣይ ተግባራት ናቸው። ከመሰረቱ መጀመሩ ደግሞ በተለይም ሕገ ወጦችን ከመታደግ አኳያ ሰፊ ሚና ይኖረዋል። ማህበሩም ይህንን ነው የሚያደርገው። ምክንያቱም ማህበሩ ከማዕድን ማውጣቱ እስከ ውጪ መላኩ ድረስ የሚሳተፉት አካላትን ያቀፈ ነው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ በማህበሩ ምስረታ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያዊያን ሀብት ተሸክመን ድሃ መሆናችን ሁለጊዜ ሊያስቆጨን ይገባል። ከከበሩ ማዕድናት ዘርፍ ብቻ ብዙ ገንዘብና ዶላር ማግኘት ስንችል በ10ሺህ ኪሎ ግራም አውጥተን 10 ሚሊዮን የማይሞላ የውጪ ምንዛሬ ነው የምናገኘው። ለዚህ የዳረገን ደግሞ በአግባቡ ቁጥጥር አለመደረጉ፤ ድጋፉ ጥብቅ አለመሆኑ፤ እሴት ጨምሮ መስራትና የመሳሰሉት ተግባራት ባለመከወናቸው ነው። ዛሬ ግን ተስፋ አግኝተናል ብሎ መውሰድ ይቻላል። ምክንያቱም ማህበሩ ይህንን ችግር በብዙ መልኩ ይፈታል ተብሎ ይታሰባል።
የማዕድን ሀብት አላቂ ነው። ያለጥቅም እየወጣም በመመናመን ላይ ይገኛል። እናም በተገቢው መልኩ ጥቅም ላይ ለማዋል ከምንም በላይ ዛሬ መስራት ያስፈልጋል። በተለይም እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ ላይ ሰፊ ርብርብ ማድረግ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ማህበሩ በጋራ ለመስራት መነሳቱ ይበል ያሰኛል። ምክንያቱም የግብይት ሰንሰለቱን ከማሳለጥ ባለፈ የሥራ እድል መፍጠርና የሀገርን ጥቅም ማስከበር ያስችላል። ይህንን ደግሞ አስተሳስሮ መስራት ያለበት ማህበሩ ሊሆን ይገባል ይላሉ።
ኢትዮጵያ በማዕድኑ ዘርፍ ሁሉም ተዳምሮ ግማሽ ቢሊዮን እንኳን ገቢ ማግኘት እንዳልቻለች የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ይህ ገቢ በአንዱ የማዕድን አይነት ብቻ መግባት የሚችል ነበር። ሆኖም ዘርፉ በብዙ መልኩ የተፈተነ በመሆኑ ይህንን ማድረግ አልተቻለም። ስለዚህም ማህበሩ የተለዩ ችግሮችን እንኳን ለመፍታት ቢሞክር መንግሥትም አግዞ ጥልቅ ሥራዎችን ማከናወን ይቻላል። ይህ ደግሞ ለዓለም ገበያ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ውስጥ ገበያ ጭምር የምናቀርባቸውን የማዕድን ውጤቶች ያሰፋዋል ባይ ናቸው።
‹‹ማህበሩ ማህበር ብቻ ሳይሆን ትልቅ ኮርፖሬሽን፤ ፋብሪካ መሆን ይገባዋል። ዝም ብሎ የተሰባሰቡበት ማህበር ሳይሆን የሚያመርትና ሀገር የሚለውጥ ማህበር መሆን ይኖርበታል። በየጊዜው አዳዲስ ነገሮችን ለሀገር የሚያመጣ ማህበርም ሊሆን ያስፈልጋል›› ሲሉ ለማሕበሩ አባላት መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ኢንጅነር ሀብታሙ፤ ይህንን ለማጠናከር ደግሞ ሚኒስቴሩ አብሮ እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል።
የኢትዮጵያ የጌጣጌጥ አቅራቢዎች፣ የማኑፋክቸሪንግ እና ላኪ ማኅበራት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ስንታየው በበኩላቸው ስለ ማህበራቸው ምንነትና አስፈላጊነት የተለያዩ ሀሳቦችን ያነሳሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የማዕድን ዘርፉ ለዝርፊያና ለህገ ወጥ ንግድ የተጋለጠ በመሆኑ ከማዕድን ሀብት የሚገባውን ገቢ አላገኘም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ህገ-ወጥ ማዕድን ማውጣት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ ተግዳሮቶችን እየፈጠረ ነው። በእርግጥ ሕገወጥነት የኢትዮጵያ ችግር ብቻ አይደለም። በውጪው ዓለምም ተንሰራፍቶ ያለ ነው። ነገሩ ገኖም ሀገራትን እየፈተነ ነው። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በተፈጥሮ ሃብታቸው የሚታወቁ ሀገራት በዚህ ችግር ከፍተኛ ጉዳት ይደርስባቸዋል።
ኢትዮጵያ እንደ ወርቅ፣ታንታለም እና የከበሩ ድንጋዮች ያሉ ማዕድናት ያሉባት ሀገር ናት። በዚህም ህጋዊ የሆኑትንም ሆነ ህገወጥ የማዕድን አውጪዎችን ወደ ራሷ የመሳብ አቅም ፈጥራለች። ይህ ግን በተለይም ለሕገ-ወጡ ብዙ እድል እንደሚሰጥ እሙን ነው። ምክንያቱም ማዕድን ማውጣት በራሱ ፈታኝ ነው። ተገቢውን ፈቃድ ሳያገኙ ወይም የቁጥጥር ማዕቀፎችን ሳይከተሉ የሚከናወኑ የማዕድን ሥራዎች በስፋት ስለሚኖሩ። እናም የማህበሩ አስፈላጊነት የሚመጣው ይህንን ከማስቆም አኳያ ነው ይላሉ።
በኢትዮጵያ ለሕገ-ወጥ ማዕድን ማውጣት ምክንያት ሆነው የሚነሱ በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ የሚጠቅሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከእነዚህ መካከል ድህነት፣ የመተዳደሪያ ዕድሎች ውስንነት፣ የሕግ አስከባሪ አካላት ደካማነት እና ሙስና መሆናቸውን ያብራራሉ። እነዚህ ምክንያቶች ግለሰቦች እና ቡድኖች ከህግ ወሰን ውጪ በማዕድን ስራዎች ላይ የሚሳተፉበትን ሁኔታ የሚፈጠሩ ሲሆን፤ ይህም በማህበረሰቡ ላይ ከፍ ሲልም እንደ አጠቃላይ በሀገሪቱ ላይ መጥፎ የሚባል ተፅእኖዎችን እያሳረፈ ነው። እናም ማህበሩ ይህንን በመከላከል በኩልም ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ሲሉ ይናገራሉ።
የከበሩ ማእድናት እንደ ሀገር የማይታወቁ በመሆናቸው ሀብቱ በህጋዊ መንገድ ሳይዘጋጅ ወደ ሌሎች ሀገራት ይላካል። ይህ ደግሞ እንደሀገር ያለውን ገቢ ይጎዳዋል። እናም ማህበሩ ይህንን ከመፍታት አኳያ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ለዚህ ደግሞ ከአጋር አካላት ጋር የሚሰራ ይሆናልም ነው ያሉት።
አቶ ቴዎድሮስ እንደሚሉት፣ ማዕድኖቹን በተገቢው መንገድ ተጠቅመን ወደ ውጭ ብንልክ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የሥራ ዕድል እንፈጥራለን። የውጭ ምንዛሪ ችግርንም እንቀንሳለን። እንዲሁም ፈጣን ለውጥ ለማምጣት ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከግል ባለሀብቶች ጋር እንድንተባበር እድል ይሰጠናል። ህገ ወጥ ማዕድን አውጪዎችን፣ ላኪዎችን በመዋጋት ረገድም ከፍተኛ ሚና እንዲኖረን ያደርጋል።
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶቿን እንድትጠብቅ፣ አካባቢዋን እንድታስጠብቅ፣ የተጎዱ ማህበረሰቦችን እንድታክምና የኑሮ ሁኔታቸውን እንድታሻሻልም ያግዛታል። ሆኖም ይህ እውን የሚሆነው የማህበሩን አባላትና ሌሎች በዘርፉ የተሰማሩ አካላት በማስተማርና በህገ ወጥ መንገድ የሚደክሙ ግለሰቦችን በማስቆም መስራት ሲችሉ እንደሆነም ያነሳሉ።
ማህበሩ ለሴክተሩ ሰራተኞች የተለያዩ የክህሎትና የእውቀት ስልጠናዎችን በመስጠት በዘርፉ ያለውን የባለሙያዎች እጥረት መቅረፍ የሚችል እንደሆነ ያነሱት አቶ ቴዎድሮስ፤ ማህበሩ የተለያዩ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን በመጠቀም ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምርቶች እንዲመረቱ የማድረግ ሥራን ይሰራል። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ሀገር አስፈላጊውን ገቢ እንዲያገኝ ያግዛል። ስለዚህም በሥራው ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚንቀሳቀስም አስረድተዋል።
‹‹ኢትዮጵያ ህገወጥ ማዕድን ማውጣትን ለመዋጋት ወሳኝ እርምጃ በመውሰድ የተፈጥሮ ሀብቷን መጠበቅ፣ አካባቢን መጠበቅ እና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ማረጋገጥ ትችላለች። መንግሥት፣ የአካባቢ ማህበረሰቦች እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ እስካደረገች ድረስ ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበት የማዕድን ዘርፍ ለመፍጠርም የሚያቅታት ነገር አይኖርም። ለዚህ ደግሞ የማህበሩ መመስረት አንዱ ማሳያ ነው›› የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያ የከበሩ ማዕድናትና ጌጣጌጦች አቅራቢ፣አምራቾችና ላኪዎች ማህበራት ቦርድ አባልና የማህበሩን የስልጠና ክፍል ኃላፊ አቶ ቁምላቸው ተስፋዬ ናቸው።
አቶ ቁምላቸው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ የማዕድን ሀብቷን በዘላቂነት ለመጠቀም፣ የልማት ገቢ ለመፍጠር እና የዜጎችን ደህንነት ለማሻሻልና ህገ-ወጥ የማዕድን ስራዎችን ለመግታት ውጤታማ ስልቶችን መቀየስ ይኖርባታል። ለዚህ ደግሞ ዓለም አቀፍ ትብብር እና ድጋፍ ያስፈልጋታል። ስለዚህም ማህበሩ ይህንን ከማድረግ አንፃር የራሱ ሚና ይኖረዋል። የከበሩ ድንጋዮችን አይደለም ማህበረሰቡ በኢትዮጵያ ጌጣጌጥ ላይ ለረጅም ዓመታት የሰሩት እንኳን እየጠቀሙበት አይደለም። እሴት ከመጨመር ይልቅ በጥሬው መላክ ይቀናቸዋል። ይህን ችግር ከመፍታት አኳያ የማህበሩ መመስረት ከአባላት የጀመረ ለውጥ ያመጣል። በዘርፉ የተሻለ ሥራ ለማከናወንም ያስችላል።
አቶ ቁምላቸው እንደሚሉት፤ የማህበሩ አባል የሆነው እርሳቸው የሚሰሩበት የዘሚካኤል ጌጣጌጥ ካምፓኒ ድርጅት ሥራዎችን የሚያከናውነው ከብሔራዊ ባንክ ወርቅ በመግዛት ነው። የከበሩ ድንጋዮችን ደግሞ በቀጥታ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ከሚገኙ አምራቾች ይረከባሉ። ከማህበሩ መመስረት በኋላ ግን ሁሉም በቅንጅት የሚሰራ በመሆኑ መቀባበልና መረዳዳት ይኖራል። ከመንግሥት ጋር በመሆን የገቢ ሁኔታውን እንደሚያሳድጉበት እምነት አሳድረዋል። በተለይም የምርት ጥራት ፣ጥገና አለማድረግ፣ በዓለም አቀፍ ንግድ ለመሳተፍ የተለያዩ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች አለመኖራቸው፣ የፋይናንሺያል አቅም ማነስ እና የዘርፉ በባለሙያዎች አለመመራቱ እንደማይፈትናቸውም እምነታቸው ነው።
አቶ ቁምላቸው፤ በኢትዮጵያ ህገ-ወጥ የማዕድን ማውጣትን ጉዳይን ለመፍታት የቁጥጥር ማዕቀፎችን ማጠናከር፣ የህግ ማስከበር አቅምን ማሳደግ፣ ኃላፊነት የሚሰማው የማዕድን ማውጣት ስራዎችን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ። አያይዘውም የህገ-ወጥ ማዕድን ማውጣት መንስኤ የሆኑትን እንደ ድህነት እና ውስን የኑሮ እድሎች መፍታትን የሚያካትት አጠቃላይ አካሄድን መከተል ያስፈልጋል የሚል ምክረ ሃሳብ ይሰጣሉ።
የሎሊት የከበሩ ማእድናት እና ጌጣጌጥ ንግድና ላኪ ካምፓኒ ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ኪያ ሞይሳም የማህበሩን መመስረት አስመልክቶ በሰጡት ሃሳብ በርካታ ችግሮቻቸው እንደሚፈታላቸው ገልፀዋል። አንዱ የመሥሪያ ቦታ እጥረታቸው ነው። በሌላ በኩል ለሥራ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ ጉዳይ ፈተና አይሆንባቸውም።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ህገ-ወጥ የማዕድን ቁፋሮ ተጽእኖ ከፍተኛ የአካባቢ አደጋዎችን ያስከትላል። ህገ-ወጥ ማዕድን ማውጣት ብዙውን ጊዜ እንደ ሜርኩሪ ውህደት ያሉ መሰረታዊ እና አካባቢያዊ ጎጂ ዘዴዎችን መጠቀምን ያካትታል። እናም ይህ አይነት አሰራር ወደ ወንዞች እና አፈር ውስጥ መርዛማ ኬሚካሎች እንዲለቀቁ ያደርጋል። በተጨማሪም ቁጥጥር ያልተደረገበት የማዕድን ማውጣት ተግባራት የደን መጨፍጨፍ፣ የአፈር መሸርሸር እና የመኖሪያ አካባቢዎች ውድመትን ያስከትላል። ይህም ቀድሞውንም ደካማ የሆነውን የስነ ምህዳር ሚዛን የበለጠ ያባብሰዋል።
ህገ-ወጥ ማዕድን ማውጣት በተለይ ለአካባቢው ማህበረሰቦች ከፍተኛ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መዘዝ አለው። በህገ ወጥ መንገድ የማዕድን ቁፋሮ የተሰማሩ ብዙ ግለሰቦች በድህነት እና ፍላጎት ጫና ስር ያሉ በመሆናቸው እንቅስቃሴዎቻቸው ብዙውን ጊዜ የድህነት እና የብዝበዛ ሂደት የተከተለ ያደርግባቸዋል። ተገቢው የቁጥጥር ሥርዓት ባለመኖሩም ሠራተኞች ብዙውን ጊዜ ለአደገኛ የሥራ ሁኔታዎች፣ ለደመወዝ ማነስ እና ፍትሃዊ ካሳ ሳይሰጡ በጉልበት በሚጠቀሙ ደላሎች እጅ ይወድቃሉ። እነዚህ ሁሉ ችግሮች በማህበሩ መመስረት የሚፈታ ይሆናልም ተብሏል። የማእድን ልማት በሚካሄድበት አካባቢ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት መተዳደሪያ ደንብ እንደሚኖረውም ነው የተገለፀው። ለዚህ ደግሞ ማህበሩ ገና ከጅምሩ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄ የሚሆን ስምምነትን አድርጓል። በተለይም ኢንዱስትሪው ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር ለመስማማት ችሏል።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 5/2015