ድርና ማግ

ተፈጥሮዋ እንደ ጀምበር ነው። ዝም ብላ የምትደምቅ። የምትፋጅ። ቀይ ናት፤ እንደ ጀምበር። ቀና ያለን ሁሉ የሚረመርም እሳታማ ውበት አላት። ሳያት የጀምበር መሀሉን፤ ከዋክብቶች ያደመቁትን ብራ ሰማይ ትመስለኛለች። ሳያት ክረምት ያለመለመው ጠልና ጤዛ ያልጣለ ማለዳ ትመስለኛለች። ሳያት በወናፍ እንደፋመ የባለ’ጅ ማንደጃ ትመስለኛለች። ጣይ የምትወጣበት የምስራቅ አድማስ እንኳን የእሷን ውበት ያክል መድመቁን እጠራጠራለሁ።

ሁሌ የማያት ዝም ብላ ነው። ጉዳይ ያለው መስዬ ስታወራ ላያት ለሁለት አመታት ወዳለችበት ተመላልሻለሁ። በሰባት መቶ ሰላሳ ቀን ውስጥ፣ በመቶ አራት ሳምንታት ውስጥ፣ በሀያ አራት ወራት ውስጥ በእልፍ ደቂቃና ሰከንዶች ውስጥ ያወራችው ቃል ቢቆጠር አስር አይሞላም።

ነፍሴ ለዝምታዋ ተረታች። ዝም ያለች ነፍሷ ትናፍቀኝ ጀመር።

በልጅነቴ ያጣኋት በምናቤ ውልብ የምትል የሰፈራችን የህጻንነት ጓደኛ አለችኝ። ሰንያ እና ውዳሴ የምትባል። ሁለት ስም ነው ያላት። ከክርስቲያን እናቷ እና ከሙስሊም አባቷ ጋር ነው የምትኖረው። አባቷ ሰኒያ ሲላት እናቷ ደግሞ ውዳሴ ይሏታል። አብረን መስኪድ እና ቤተክርስቲያን ሄደን እናውቃለን። አንገቷ ላይ መስቀል እያለ ሂጃብ የሚታሰርላት ጓደኛዬ ነበረች። ማርያምንና ወላሂን ብላ ነው የምትምለው። በልጅነቴ አላህና እግዚአብሄር እነሱ ቤት አብረው ያሉ ይመስለኝ ነበር። በዘመኔ ሰውነት ጣይ ሲመስል የእሷን ገላ ነው የማውቀው። ቀይ ናት … ሰኔን ታኮ በሰማይ ርቃን ላይ እንደሚታይ የመብረቅ ብልጭታ። የገላዋ ማማር፣ የሰውነቷ ጽዳት ብርሀን እንዳረፈበት መስታዋት ብርሀን አስተላላፊ አይነት ነበር። እውቀት ባልዘለቀው የልጅነት ሀሳቤ ዓለም ከእሷ ውበት በሚነሳ ጨረር የደመቀች ይመስለኝ ነበር። ጸሀይ ወጣች ሲባል ሰኒያ ከእንቅልፏ የምትነቃ፤ ጸሀይ ገባች ሲባል ደግሞ የተኛች ይመስለኝ ነበር።

በልጅነቴ ውስጥ ከተቀረጹ ጸሀያማ ወሬዎች ውስጥ አንዱ የዛች የሰፈሬ ልጅ ፊትና መልክ ነው። ያያት ሁሉ ጉንጭዋን ሳይስምና ‹ጸሀይ የመሰለች ልጅ› ሳይላት አልፏት አያውቅም። ያኔ እኔን ከመጤፍ የሚቆጥረኝ የለም። አብረን ተወልደን፣ አብረን ልደታችንን እያከበርን ጸሀያማ እየተባለ በወጪ ወራጁ የሚሳመው የእሷ ጉንጭ ነበር። ግን አይከፋኝም፤ ከስሬ ስለማትጠፋና ከስሯ ስለማልጠፋ እሷ ስትሳም እኔ የተሳምኩ ያህል ነበር የምቆጥረው። አንዳንድ ሰዎች ከእኔ ነጥለው ብስኩትና ከረሜላ ሲገዙላት ያኔ ብቻ እከፋ ነበር። ግን የተገዛላትን ብስኩትና ከረሜላ ሳታካፍለኝ ብቻዋን በልታ አታውቅም። አንዳንድ ጊዜ ትገርመኛለች፤ ትናንት እኔ ትልቅ ስለወሰድኩ ዛሬ አንተ ትልቁን ውሰድ ብላ በለጥ ያለውን ትሰጠኛለች። ግን እኮ አንድም ቀን ትልቅ ወስዳ አታውቅም። ትልቅ የመሰላትን እንኳን ምራቋ እስኪንጠባጠብ አፏ ውስጥ አስገብታ ሸርፋና ፈረካክሳ ነው የምታካፍለኝ። ፍትህ እሷ ጋ ነበረች እላለሁ። ያን መሳይ የልጅነት ፍትህ አድጌ በማንም ልብ ውስጥ አላየሁትም። ፡ ሰኒያ የነፍሴ ጣይ ነበረች እላለሁ፤ በልጅነቴ ምስራቅ ላይ ፍንትው ብላ የጠፋች። እንዴት እንደሞተች ዛሬም ድረስ አላውቅም። አሁን በማላስታውሰው አንድ ማለዳ ላይ ከእንቅልፌ ስነቃ እማዬና አባዬ አጠገቤ የሉም። አራስነቱን ያልጨረሰ ታናሽ ወንድሜ ብቻ በቢጫ ካካ ሱሪዬን ኩሎ ጎኔ ተኝቷል። ከርቀት የለቅሶ ድምጽ ይሰማኛል። ብዙም ሳይነጋ እናቴ በእንባ በራሰ ጉንጭና በሞጨሞጩ አይኖች ነጠላዋን አዘቅዝቃ ቤት መጣች። ለህጻን ወንድሜ ጡት እየሰጠች “ጓደኛህ አረፈች” አለችኝ። ማረፍ ምን እንደሆነ አላውቅም ነበር። ማረፍ መሞት እንደሆነ ያወኩት ለበርካታ ጊዜያት ሰኒያን ከጎኔ ሳጣት ነበር። ቆይቶ ስሰማ ቡዳ በልቷት ነው፤ ተለክፋ ነው የሚባል የመንደር ወሬ ሰማሁ። ግን ያን ውበት እንዴት ቡዳ፣ እንዴት ሰይጣን ደፈረው? የሁል ጊዜም ጥያቄዬ ነው።

እናም የልጅነት ጓደኛዬን በዚች ዝምተኛ ሴት ነፍስ ውስጥ አየኋት። አሁን ላይ ሰኒያን ብዙም አላስታውሳትም። ባስታውሳትም ጸሀያማ ውበቷንና ማንም የሚስመውን ጉንጭዋን ነው። እና ደግሞ ለትንሽ ለትልቁ የሚስቅ ፍልቅልቅ ልጅነቷን። ሰፈር ውስጥ እኛ የማያስቀን ሰኒያን ያስቃት ነበር። ዛፍ ላይ ጎጆዋ ውስጥ ሆና ባየቻት እርግብ ትስቅ ነበር። መሬት ላይ ቀለብ ጭኖ በሚንደፋደፍ ምስጥ ትፍለቀለቅ ነበር። በቃ ሁሉ ነገር ያስቃታል። እኛ የምንስቀው ባልገባን በእሷ ሳቅ ነበር። ይቺን ሴት እንዴት ሞት ደፍሮ ወሰዳት? እላለሁ።

ትንሽዋ ሰኒያ ስሟን ከማላውቀው ትልቋ ሴት የምትለየው በሳቋ እና በወሬዋ ነበር። በብዙ ምክንያት ነፍሴ ይቺን ሴት ከጀለቻት። የመጀመሪያውና የመጨረሻ ምክንያቴ ልጅነቴን የማስታውስባትን ሴት ስለምትመስል ነበር። አጠገቧ ስቆም በዝምታ ነው ሰላም የምትለኝ። በዝምታ እንዴት ሰላም እንደሚባል ከእሷ ነው የለመድኩት። ፊቷ ስቆም እጅ የምትነሳኝ በትልቅ ዝምታ ውስጥ ብልጭ ባለች ትንሽዬ ፈገግታ ነው። ለአቅመ ፈገግታ ባልደረሰች ትንሽዬ ንቅናቄ። እየቆየ ዝምታዋን አጋባችብኝ። ራሴን ትቼ እሷን መምሰል ጀመርኩ። በተጋባብኝ የዝምታዋ ጠኔ ስለፈልፍ መጥቼ በዝምታ ፊቷ እቆማለሁ። ጥላዬ ሲያርፍባት እንዳማልላት የተነሰነስኩት ሽቶ በአፍንጫዋ ሲማገድ እጆቿን ከምትጠበጥበው የላፕቶፕ ቁልፍ ላይ ሳትነቅል ቀና ትላለች። ከዛም ለሁለት አመት ተለማምጄ ባልቻልኩት ከእሷ ሌላ ማንም በማይችለው ዝምታዋ ሰላም ትለኛለች። በዝምታ ውስጥ ፈገግታ በፈገግታ ውስጥ ዝምታ ልዩ ተሰጥኦዋ ነው።

እጆቿ ኮምፒውተሩ ቁልፍ ላይ ቦታ ሳይስቱ ቀና ትላለች። የአይኖቿን ቆቦች ወደ ላይ ገልባ እጅግ ላነሱ ስብርባሪ ሰኮንዶች ታስተውለኛለች። ከዛ በዝምታዋ ውስጥ ወዳለው ጽልመተ ፈገግታዋ ትመለሳለች። እኔ ብቻ የማውቀው ፈገግታዋ ይታየኛል። እነዛ አፍታ ጊዜዎች በሴት ፊት በኩራት የቆምኩባቸው ሆነው ሁሌም ይታወሱኛል። በነፍሱ ላይ ድሮና ዘንድሮን ሁለት ነፍስ ላቆነጎለ ሰውነት ያቺ አፍታ የክብር ጌጡ ብትሆን ምን ይገርማል? ስታየኝ የረሳኋቸው የሰኒያ አይኖች ይታወሱኛል …።

አንድ ከሰአት ጸሀይ በሌለችበት አመዳማ ቅዳሜ ውበቷ አጥበርብሮኝ በግድ የቀረብኳት ሴት ናት . . ። ሰውን በግድ መቅረብ ቅጣቱ ምን ያክል እንደሆነ እኔ ማስተማሪያ ነኝ። በእሷና በውበቷ በኩል የረሳኋትን የልጅነት ነፍሴን አስታወስኳት።

ዝምታዋን አፈቀርኩት…

ዝምታዋን ባፈቀርኩበት ሰሞን በሌለ ድፍረት ወዳለችበት ሄጂ … ‹እልፍ ጸጋ እባላለሁ› አልኳት።

ሰኒያ ስትል ከኮምፒውተሩ ላይ ለአፍታ ቀና ብላ በዝግታ መለሰችልኝ። ተፈረካከስኩ። በዝምታም ፊቷ ቆምኩ። አታይኝም … ኮምፒውተሩ ላይ አቀርቅራለች።

ሰኒያ ሞታ የለ? ውዳሴ የታለች? ያን ቀን እናቴ “ጓደኛህ አረፈች” ብላኝ የለ? ከዛ በኋላ ከሰኒያ ጋር መች ተገናኘን? ብቻዬን አይደል ያደኩት? ብዙ አሰብኩ። ለሀሳቤ ጭንቅላቴ ጠበበው።

ከኋላዬ ‹ሰናይ! የሚል አንድ ድምጽ ሰማሁ። እውነት ነው፣ ሰምቼ ነበር። አንድ ሰው ወዳለንበት መጥቶ ሲጨብጣት ከሞትኩበት ነቃሁ። ለካ በወጉ ሳልሰማት ቀርቼ ነው … ያለችኝ ሰናይ ነበር።

ሰናይ … ሰኒያ።

ጸሀይና ጨረቃ

ሰማይና ኮከብ

ጉምና ደመና …

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 5/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *