
የኢትዮጵያ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ዛሬ በድሬዳዋ ይጀመራል። ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮናው ለ13ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን ከ18 ዓመት በታች ቻምፒዮናው ደግሞ ለ4ኛ ጊዜ ነው የሚከናወነው። ቻምፒዮ ናውን በድምቀት ለማካሄድም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዘጠኝ ሚሊዮን ብር በጀት ቅድመ ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ በሰጠው መግለጫ ተቁሟል።
ከግንቦት 18-24/2017 ዓ.ም በሚካሄደው ቻምፒዮና ላይ 8 ክልሎች ፣ 2 ከተማ አስተዳደሮች እና 35 ክለቦች እና ተቋማት ተሳታፊ ናቸው።
ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮናው ላይ 359 ሴቶች፣ 463 ወንዶች በድምሩ 825 አትሌቶች ተፎካካሪ ናቸው። ከ18 ዓመት በታች ቻምፒዮናው ላይ ደግሞ 178 ሴቶች፣ 192 ወንዶች በድምር 370 ወጣት አትሌቶች ተሳታፊ ሲሆኑ፤ በሁለቱም የእድሜ ምድብ በአጠቃላይ 1ሺ195 አትሌቶች እንደሚወዳደሩ በጋዜጣዊ መግለጫው ተጠቁሟል።
የቻምፒዮናው አላማም እ.ኤ.አ ከጁላይ 16- 20/2025 በናይጄሪያ አቡኩታ ከተማ ለሚካሄደው የአፍሪካ ከ18 ዓመት እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን ለመምረጥ እንደሆነ ተነስቷል ።
ቻምፒዮናውን በማስመልከት በአጠቃላይ ዝግጅት ዙሪያ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን፣ አስተዳደራዊ ይዘት ያላቸውን የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ እንግዳ፣ በውድድሩና በቴክኒክ ጉዳዮች ዙሪያ የፌዴሬሽኑ ውድድር እና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ ፣በሚዲያ ሽፋንና አጠቃላይ የሚዲያ ዝግጅት ዙሪያ የኮሚኒኬሽን ከፍተኛ ባለሙያ መሐሪ ነጋሽ እና በዕድሜ ተገቢነትና ተያያዥ የሕክምና ጉዳዮች ዙሪያ የፌዴሬሽኑ ከፍተኛ የሕክምና ባለሙያ ዕጩ ዶክተር ቅድስት ታደሰ በጋራ በመሆን መግለጫውን ሰጥተዋል።
እ.ኤ.አ ከጁላይ 16-20/2025 በናይጄሪያ አቡካታ ከተማ ለሚካሄደው 3ኛው የአፍሪካ ከ18 ዓመት እና ከ20 ዓመት በታች ጥምር የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን ለመምረጥ ታስቦ የሚካሄድ ውድድር መሆኑን የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህንና የፌዴሬሽኑ ውድድር እና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ በመግለጫው ላይ ተናግረዋል።
ናይጄሪያ በምታስተናግደው ቻምፒዮና ከመላው አህጉሪቱ የተውጣጡ ከ500 በላይ ወጣት አትሌቶች ለሜዳልያ ይፎካከራሉ። የቀጣዩ ዘመን የአፍሪካ ከዋክብት አትሌቶች የሚፋለሙበት 3ኛው የአፍሪካ የወጣቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ቀደም ሲል በአልጄሪያ ኦራን እንዲካሄድ መርሃ ግብር ተይዞለት የነበረ ቢሆንም፣ በይፋ ባልተገለጸ ምክንያት ወደ ናይጄሪያ አቡካታ መዛወሩን አወዳዳሪው አካል የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን አስታውቋል።
ቻምፒዮናው ከናይጄሪያ ዋና ከተማ ሌጎስ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘውና 10ሺ ተመልካቾችን በሚያስተናግደው ኤም ኬ ኦ ኢንተርናሽናል ስቴድየም እንደሚካሄድ መረጃዎች ይጠቁማል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም