ረዥሙ ጉዞ ከወሎ እስከ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

ህልም፣ ተስፋ እና ትጋት በአንድ መንፈስ ከሄዱ መጨረሻቸው ድልና ስኬት ነው የሚባለው እንዲሁ አይደለም። ህልማቸውን ሰንቀው በትጋት የተራመዱ እና የስኬት ማማ ላይ የተቀመጡ ብዙዎች ስላሉ ነው። ወጣት ጋሻው ምሳየ ይባላል፤ ውልደትና እድገቱ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን አማራ ሳይንት ወረዳ ውስጥ በምትገኝ የገጠር ቀበሌ ነው።

ወጣት ጋሻው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ሶመት በተባለ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለውን ደግሞ አምባፋሪት በተሰኘ ትምህርት ቤት ተከታትሎ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በሳይንት ሁለተኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተምሯል።

በትምህርቱ ጎበዝ ከሚባሉት ከደረጃ ተማሪዎች መካከል የነበረው ጋሻው፤ በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና 515 ነጥብ በማስመዝገብ በጥሩ ውጤት ለከፍተኛ ትምህርት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅሏል። በትውልድ አካባቢው የአንደኛ ክፍል ትምህርት ሲጀምር፤ ይማር የነበረው እንደ ማንኛውም የአካባቢው ተማሪ በድንጋይ ላይ ቁጭ ብሎ ነበር።

ወጣት ጋሻው እንደሚገልጸው፤ ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል በአካባቢያቸው ትምህርት ቤት አልነበረም። ስለዚህ የግድ ትምህርቱን መከታተል ስላለበት ደርሶ መልስ በቀን አራት ሰዓት እየተመላለሰ በአምባፋሪት ትምህርት ቤት በብቃት ትምህርቱን መከታተል ችሏል።

በወቅቱ ትምህርቱ የሚሰጠው በፈረቃ ስለነበር፤ ስድስት ሰዓት ለሚጀምር ትምህርት እርሱ እና ጓደኞቹ ከአራት ሰዓት በፊት ጉዞ በመጀመር በቦታው እንደሚደርሱ ከትምህርት በኋላ ደግሞ ከሰዓት አስራ አንድ ሰዓት በመውጣት ምሽት ሁለት ሰዓት ወደ መኖሪያ ቤት እንደሚደርሱ የልጅነት የትምህርት ጊዜውን ወጣት ጋሻው ወደኋላ ተመልሶ በማስታወስ ይናገራል።

ለሚያጋጥሙ ፈተናዎች እጅ ሰጥቶ እንደማያውቅ የሚናገረው ወጣት ጋሻው፤ የሁለተኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርቱን ለመከታተል ደግሞ የወረዳቸው ዋና ከተማ ወደሆነችው አጁሀር ወደምትባል ከተማ አቀና። በግብርና ከሚተዳደሩ ቤተሰቦቹ ጋር በመነጋገር የኪራይ ቤት በመያዝ ትምህርቱን ተከታትሎ ዛሬ ላለበት ደረጃ መድረስ ቻለ።

በትምህርት ጊዜው ትልቁ ፈተና ምን እንደነበር ወጣት ጋሻው ሲናገር፣ የፋይናንስ ችግር የመጀመሪያው እና ትልቁ ፈተናው ነበር። ‹‹የተገኘሁት በግብርና ከሚተዳደሩ አርሶ አደር ቤተሰብ ነው። መሬትም ብዙ አልነበረንም። ስለዚህ ቤተሰቦቼ የሚኖሩት ከእጅ ወደ አፍ በሚባል ኑሮ ነው። ስለዚህ እኔም ችግር ውስጥ ነበርኩ» ይላል።

ሌላው የአመለካከት ችግር እንደሆነ ይገልጻል። በትውልድ አካባቢው 16 እና 17 ዓመት ለፍቶ ጥሩ ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚያስብ ሰው እንዳልነበረ ይናገራል። ከእርሱ ጋር ትምህርት አብረው ከጀመሩ ተማሪዎች መካከል አብዛኛዎቹ አቋርጠዋል። እርሱና አንድ ሌላ ጓደኛው ብቻ ትምህርታቸውን እስከ መጨረሻው ተከታትለው ሲጨርሱ፤ ሌሎች ጓደኞቹ ትምህርታቸውን በተለያየ ጊዜ በማቋረጥ ዛሬ ላይ በአብዛኛው በቀን የጉልበት ሥራና በግብርና እየተዳደሩ ነው። ሴቶች ጓደኞቹ ደግሞ ልጅ ወልደው በትምህርታቸው ብዙ መዝለቅ ሳይችሉ በአጭሩ ለማቋረጥ ተገደዋል።

‹‹ወላጅ እናቴ እኔን ጨምሮ ሌሎች ልጆቿ በትምህርት ቀጥለው ውጤታማ እንዲሆኑ ከመጀመሪያው ጀምሮ ህልም ነበራት። » የሚለው ወጣት ጋሻው፤ በእርሷ ጠንካራ ድጋፍ ትምህርቱን ለ16 ዓመት በሚገባ ተከታትሎ በዲግሪ በማጠናቀቅ ለአካባቢው ልጆች፣ ወጣቶች ምሳሌ መሆን እንደቻለና በዚህም ደስተኛ እንደሆነ ይገልፃል።

የነበረበትን የገንዘብ ችግር ለማቃለል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን መማር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፤ በትርፍ ሰዓቱ እቃ መሸከምን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ እራሱን ለመደገፍ እና ገቢ ለማግኘት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመረጠበት አንዱ ምክንያት ከግቢ ውጭ እራሱን ለመደጎም የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት ስለሚያመችና በሌላ በኩል ደግሞ የትምህርት አቅሙ ስላለው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እራሱን ለመፈተን እና ብቁ ሆኖ ለመውጣት ትክክለኛው ቦታ ነው ብሎ በማሰብ ስለመቀላቀሉ ይናገራል።

ወጣት ጋሻው፤ በግቢ ቆይታው ያለፉትን ሶስት አመታት በተለይም ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ የተለያዩ ተማሪዎችን በቁጥር ወደ አምስት የሚጠጉ ተማሪዎችን በማስጠናት ጊዜውን ያሳልፍ ነበር። በዚህ ምክንያት የገንዘብ ችግሩ ተቃልሎለት እራሱን ችሎ ትምህርቱንም እየተከታተለ የማስጠናት ሥራውን ጎን ለጎን እየሰራ ጥሩ ጊዜ ያሳለፈበት ወቅት እንደነበረ ይናገራል።

ወጣት ጋሻው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስለነበረው ቆይታ ሲናገር፣ የኮቪድ ወረርሽኝ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ መጨናነቅን ፈጥሮ ነበር፣ በመጀመሪያ ዓመት በወረርሽኙ ምክንያት ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ተደርጎ ነበር። ይህ የፈጠረው ጫና ቀላል እንዳልነበር ይናገራል።

ከኮቪድ መልስ የነበሩ የትምህርት ፕሮግራሞች ደግሞ አጫጭር ሲሆኑ፤ በሁለት ወር ተምሮ መጨረስ ግድ ነበር። በየግማሽ መንፈቅ ዓመቱ በሁሉም የትምህርት አይነቶች አራት ነጥብ ሰርቶ ለማለፍ ለሚፈልግ ተማሪ ጊዜው አጭር መሆኑ ከባድ ነበር። ነገር ግን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከክፍል ትምህርት ባለፈ የተለያዩ አማራጮች ማለትም የኢንተርኔት አገልግሎት ምቹ በመሆኑ፤ የፀጥታ ችግር እና ሌሎችም በብሔር የሚነሱ ግጭቶች ስላልነበር እና አሳሳቢ የፀጥታ ችግር ሁኔታ ባለመፈጠሩ ለትምህርት ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ ውጤታማ መሆን እንዲችል እንደረዳው ይናገራል።

በተጨማሪም ወደ ዩኒቨርሲቲ ግቢው ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የመጡ የራሳቸው ባህል፣ ቋንቋ ያላቸው የተለያዩ ጓደኞች እንደነበሩት የሚናገረው ወጣት ጋሻው፣ በግቢ ቆይታው ከእነዚህ ጓደኞቹ ጋር ያለውን ነገር በመጋራት በወንድማማችነት እንዳሳለፉ ይናገራል።

ወጣት ጋሻው እንደሚናገረው፤ እራሱን በገቢ ለመደገፍ ከትምህርቱ ጎን ለጎን በሚሰራቸው ሥራዎች ጓደኞቹ በጥሩ ዕይታ ተቀብለው ከማጣጣል ይልቅ በማበረታታት ይደግፉ እንደነበር ይገልፃል። ከእርሱ በተጨማሪ ሌሎች ጓደኞቹም ከትምህርት ጎን ለጎን ሥራ እንዲሰሩ ከማሰብ የተነሳ ህብረት በመፍጠር ከቤተሰብ የሚላክ ገንዘብ የሌላቸው እራሳቸውን መደገፍ እንዲችሉና ከግቢ ውጭ ያለውን ሕይወት እንዲያውቁ ጥረት ማድረጋቸውን ይገልፃል።

ይህንን ተግባር ብዙዎቹ በመጥፎ መንገድ የሚረዱ አልነበሩም። እንደውም ጥያቄያቸው ‹‹ይህን ያህል ጊዜ ከግቢ ውጭ እያሳለፍክ በትምህርትም ጠንካራ ሆነህ መቀጠል የቻልከው እንዴት ነው? ›› የሚል የመገረም ጥያቄ ነበራቸው ይላል።

‹‹ይህን ተከትሎ አብዛኛዎቹ ጓደኞቼ እኔ የተሻለ ውጤት እንደመጣ ያግዙኝ ነበር። እኔም በተለያየ መንገድ እነርሱን በመደገፍ በትምህርታቸው ውጤታማ መሆን እንዲችሉ የተቻለኝን ሁሉ አደርግ ነበር። » የሚለው ወጣት ጋሻው፤ እርስ በእርስ በመተጋገዝ ያሳለፏቸው ጊዜያት እጅግ መልካም እንደነበር ይገልፃል።

36 A+ እና 16 A CGPA አጠቃላይ በትምህርት አመታቱ፤ አራት ነጥብ በመምጣት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ የትምህርት ክፍል በኢኮኖሚክስ ትምህርት በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀው ወጣት ጋሻው፤ ‹‹እዚህ ድረስ መምጣቱ ብቻውን ዋጋ የለውም ለብዙ ጊዜ የለፋሁበት ነገር የተሻለ ቦታ ደርሶ ማየት እፈልጋለሁ» ይላል። ከዚህ አንፃር የመጀመሪያ እቅዱ በመጀመሪያ ጥሩ ሥራ አግኝቶ ወደ ሥራ መሰማራት ነው።

ከሥራ ባለፈ በመጀመሪያ ዲግሪ ብቻ መቆም በቂ ስላይደለ፤ በመጀመሪያ ዲግሪ ለተከታተለው የትምህርት መስክ ልዩ ፍቅር ስላለው ለእራሱ፣ ለቤተሰቦቹ ከፍ ሲልም ሀገሩን ለመጥቀም እና የተሻለ ነገር ለመምጣት ትምህርቱን መቀጠል እንደምፈልግ ያናገራል። እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ብሎ እስከ 3ተኛ ዲግሪ፤ ማለትም የዶክትሬት ዲግሪ ድረስ መማርን በረዥም ጊዜ እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ተነግሯል። ይህንንም ለማሳካት የተለያዩ የውጭ የትምህርት ዕድሎች ለማግኘት ጥረት እያደረገ እንደሆነ ተናግሮ፤ ያካበተውን እውቀት ሀገር በሚጠቅም ደረጃ ደርሶ የማየት ዕቅድ እንዳለው ገልጿል።

እርሱ እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ወላጅ እናቱ የከፈለችው መስዋዕትነት ከፍተኛ መሆኑን የሚገልፀው ወጣት ጋሻው፤ የትምህርትን ፋይዳ ብዙ ባልተረዳ ማህበረሰብ ውስጥ ሆነው ለእርሱን የነገ ሕይወት ለማቃናት ብዙ መልፋታቸውን ይገልፃል። የአካባቢው ህብረተሰብ ለልጆቹ የሕይወት ስኬት ከለፋው አስር እጥፍ በላይ ለእርሱ እና ለወንድም እህቶቹ እናቱ መድከማቸውን ይገልፃል።

ሌላው የሚገርመው እና እናቱን ለዘላለም ለማመስገን የሚያስገድደው ምክንያት ወጣት ጋሻው ሲናገር፣ የአካባቢው ማህበረሰብ አመለካከቱ ትምህርት ያን ያህል ጠቃሚ አይደለም የሚል ነው። ከሚወስደው ረዥም ጊዜ አንፃር አታካች በመሆኑ ፋይዳው አይታየንም የሚሉ ናቸው።

እንደወጣት ጋሻው ገለፃ፤ በአካባቢው ልጆች የሚወለዱት እንደ ኢንቨስትመንት ታስበው ነው። ይወለዳሉ፤ አምስት እና ስድስት ዓመት ሲሆናቸው ቀጥታ ከብቶችን ይጠብቃሉ። በመቀጠል ወደ እርሻ ይሰማራሉ። በአካባቢው ያለው ባህል ይህ ነው።

‹‹ወላጅ እናቴ ግን ነፍስ ማወቅ ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ እቅዷ የነበረው እኛ ተምረን የተሻለ ቦታ እንድንደርስ ነው። ይህንን ሀሳብ በአካባቢው ማንም በማያስብበት ጊዜ በማስተዋል ዛሬ እኔ እዚህ እንድደርስ ለከፈለችው መስዋዕትነት ምስጋናዬ በቃላት የሚገለፅ አይደለም» ይላል። በተጨማሪም ታላቅ ወንድሙ በተቻለው ሁሉ ከጎኑ በመሆን እዚህ እንዲደርስ እንደረዳው ገልጾ፤ ዛሬ ለደረሰበት ስኬት ከፈጣሪ በታች ለእነርሱ ያለው ምስጋና ከፍተኛ እንደሆነ ተናግሯል።

‹‹እኔ እንደ እቅድ በሕይወቴ ይዤ የነበረውን ዓላማ በ16 ዓመት ያለመታከት ተጉዤ በውጤታማነት ግቤን አሳክቻለሁ›› የሚለው ወጣት ጋሻው፤ ሰው በሕይወቱ የተለያየ እቅድ ይኖረዋል። አንድን ነገር ከግብ አድርሶ ለማሳካት ‹‹ከእኔ ተሞክሮ አንፃር መናገር የምችለው ሰዎች የሚያቅዱትን ነገር መውደድ እና ሙሉ ጊዜ በመስጠት መትጋት አለባቸው የሚል ነው። ›› ይላል።

በየጊዜው መሰናክሎች ይገጥማሉ። ፈተናዎቹ ደግሞ ከገጠር አካባቢ ለሚመጡ ለእርሱ መሰል ልጆች በአንፃራዊነት እጥፍ ናቸው። የ16 ዓመት ትምህርቱን ተከታትሎ ስኬታማ ለመሆን በሚያደርገው ጥረት ያጋጠሙት ፈተናዎች ብዙ ነበሩ። የገንዘብ፣ በአቅራቢያ ትምህርት ቤት አለመኖር፤ ተስፋ አስቆራጭ በነበረ የአራት ሰዓት መንገድ ሲመላለስ ጫማ እስከማለቅ ደርሷል። ሆኖም ይህም እንደሚያልፍ በማሰብ ተስፋ ባለመቁረጥ ትምህርቱን ተከታትሎ ውጤታማ መሆን መቻሉን ይናገራል።

ከዚህ ሌላ ግን ትምህርት ቤት በነበረበት ጊዜ የመምህራንን፣ የግብርና ባለሙያዎች የነበሩ ሰዎችንና የእርሱን ሕይወት እንዲሁም እርሱ በተወለደበት አካባቢ ካሉ ገበሬዎች ጋር ያነፃፅር እንደነበር የሚናገረው ወጣት ጋሻው፤ ከዚህ አንፃር መማር ወሳኝ እንደሆነ በደንብ ተረድቶ 16 ዓመታትን በትጋት ተጉዞ ውጤታማ መሆን መቻሉን ይገልፃል።

‹‹የሆነ ነገር ለማሳከት እራስን መስጠት እና ለሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ሰይበገሩ ለማለፍ ቁርጠኛ መሆን ወሳኝ ነው›› የሚለው ወጣት ጋሻው፤ ‹‹እንዴ እኔ ያሉ ወጣቶች ጊዜያቸውን በአግባቡ ቢጠቀሙ መልካም ነው» ይላል። ለአብነት ወጣት ጋሻው ሲናገር፤ በአራት አመት የግቢ ቆይታው አቅሙ እያላቸው ትምህርታቸውን በሥነ ሥርዓት መከታተል አቅቷቸው እና ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላቸው ማውጫ ፈተና ላይ ወድቀው የቀሩ ጓደኞች እንዳሉት ተናግሮ፤ እነርሱ ለትምህርታቸው ጊዜ አጥተው ሳይሆን በአጠቃቀም ችግር መዝናናት በማብዛት ቤተ መጻሕፍት ገብቶ ከማንበብ ይልቅ ለሌላ ነገር ሰፊ ጊዚያቸውን በመስጠት እስከ መጨረሻው ተጉዘው ውጤታማ መሆን እንዳልቻሉ ይናገራል።

በሁሉም መስክ የጊዜ አጠቃቀም ብዙ ነገሮችን እንደሚወስን የሚናገረው ወጣት ጋሻው፤ የእርሱ መርህም ጊዜን በተጠቀሙበት ልክ መልሶ ይከፍላል የሚል እንደሆነ ይገልፃል። ለማንኛውም ማሳካት ለምንፈልገው ነገር ከምንም በላይ ትልቁና ወሳኙ ነገር ጊዜ እንደሆነ አፅኖት ሰጥቶ ይናገራል።

በመጨረሻም የዝግጅት ክፍሉ አራት ነጥብ አምጥተህ እንደመመረቅህ እንዴት ነፃ የትምህርት ዕድል አልተሰጠህም? የሚሉ ጥያቄ ያቀረበለት ሲሆን፤ ወጣት ጋሻው እንደመለሰው፤ ሌሎችም ሰዎች ይህን ጥያቄ ያቀርባሉ። ነገር ግን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኃላፊነት ደረጃ ላይ ካሉ ሰዎች ለእርሱ የደረሰው መረጃ በላቀ ውጤት በመመረቁ ያገኘው የዕውቀትና ሰርተፊኬት በማንኛውም ቦታ ለተለያየ ነገር ይጠቀማል የሚል ነው። ከዛ ውጭ ነፃ የትምህርት ዕድል አልተሰጠውም።

‹‹ማንም ትምህርቴን መቀጠል እንድችል መንገዱን አለመቻቸልኝም። ይህ የዩኒቨርሲቲው አሰራር ነው። ነገር ግን በዲግሪ የሚገኝ እውቀት ብቻ በቂ ስለማይሆን ለሀገር እና ለሕዝብ የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት፤ በትምህርት መግፋት የግድ ስለሆነ ከዚህ አንፃር በአሰራር ደረጃ የላቀ ውጤት ወይም ሙሉ አራት ነጥብ ላላቸው ተማሪዎች ሥራ እየሰሩ የሚማሩበት ዕድል ቢመቻች መልካም ነው። ›› ሲል መልዕክቱን ለሚመለከታቸው አካለት አስተላልፏል።

 ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 5/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *