‹‹ቶራ›› – የሕፃናት መጠጊያ፤ የእናቶች ደጋፊ

የተራበን ማብላት፣ የታረዘን ማልበስ፣ ያዘነን ማፅናናት፣ የተቸገረን መርዳት… ኢትዮጵያውያን የሚታወቁበት ባህርያቸው ነውና፣ ወይዘሮ ገነት ገብረማርያምና 12 ጓደኞቻቸው ለ10 ዓመታት ያህል ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 10 ልጆች ልዩ ልዩ እርዳታዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። በየዓመቱ መጀመሪያ ለልጆቹ ለትምህርት የሚስፈልጓቸውን ቁሳቁሶች ገዝቶ ከመስጠት በተጨማሪ በአራት ዓመታዊ ዐበይት በዓላት ወቅት ደግሞ የምግብ ድጋፍ (ጤፍ፣ ዱቄት ዘይት…) ያደርጉ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ የእርዳታ ተግባራቸው ለልጆቹ የሚያስፈልገውን ክትትል ያካተተ አልነበረም። የትምህርት ቁሳቁስና የምግብ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር ልጆቹ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙና ዕለታዊ እንቅስቃሴያቸው ምን እንደሚመስል አስፈላጊው መረጃ አልነበራቸውም።

ወይዘሮ ገነትና ጓደኞቻቸው በ10 ዓመታት የእርዳታ ተግባራቸው ምን እንዳሳኩ ሥራቸውን ሲገመግሙ፣ እርዳታ ሲያደርጉላቸው የቆዩት ልጆች ያሉበት የትምህርትና የሥነ ምግባር ደረጃ እነ ወይዘሮ ገነትም ሆኑ ማኅበረሰቡ ባሰቡትና በተመኙት ደረጃ አልነበረም። ይህም የ10 ዓመታት የእርዳታ ተግባራቸው ውጤታማ እንዳልሆነ አስገነዘባቸው። ልጆችን ማብላት፣ ማጠጣትና የትምህርት ቁሳቁሶችን ገዝቶ መስጠት በአስፈላጊ ክትትል ካልታጀበ ትርፉ ድካም ብቻ እንደሚሆንም አመኑ። ስለሆነም ለሕፃናት ከመጀመሪያው ጀምሮ ክትትል እያደረጉ ማሳደግ የተሻለውና ውጤታማው አማራጭ እንደሆነ ተስማሙ።

በየቦታው ተጥለው የሚገኙ ሕፃናት ጉዳይ የማኅበራዊ ቀውስ ምንጭ እንደሆነና ጨቅላ ሕፃናትን ከወደቁበት አንስቶ ማሳደግ ለክትትል አመቺ እንደሆነም እነ ወይዘሮ ገነት ያውቃሉ። ከዚህ በተጨማሪ ጉዳዩ በተናጠል ከሚደረግ ድካምና እርዳታ በመስጠት ላይ ብቻ ከተወሰነ ሥራ ይልቅ የተደራጀና ክትትል የሚፈልግ ጥረት እንደሚያስፈልገው በማመን ወይዘሮ ገነትና ጓደኞቻቸው ራሳቸውን ‹‹ቶራ የበጎ አድራጎት ድርጅት›› በተሰኘ ምግባረ-ሰናይ ተቋም ጥላ ስር አሰባሰቡ።

‹‹ቶራ›› የበጎ አድራጎት ድርጅት የተመሰረተው መጋቢት 2012 ዓ.ም ነው። የድርጅቱ መቋቋም ምክንያት ደግሞ በበርካታ አካባቢዎች ብዙ ሕፃናት ተጥለው የመገኘታቸው ድርጊት በየጊዜው እየተባባሰ መምጣቱ ነው። ወይዘሮ ገነት የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ‹‹ብዙ ሕፃናት ተጥለው መገኘታቸውን ስንሰማና ስንመለከት፣ አቅማችን በፈቀደው መጠን ጥቂት ሕፃናትን ማሳደግ ብንችል ጥሩ መሆኑን ተረዳን። ጥናት በማድረግ የድርጅቱ 13 መስራች አባላት (ሰባት የቦርድና አምስት የሥራ አስፈፃሚ አባላት) የተጣሉ ሕፃናትን የመታደግ ሥራ ጀመርን›› በማለት የድርጅቱን ሥራ አጀማመር ያስታውሳሉ። ‹‹እንደ አቅማችን አምስትም ሆነ አስር ልጆችን ይዘን ማሳደግ ይገባል ብለን በመመካከር፣ ጥናት አዘጋጅተን ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ጥያቄውን አቀረብን። ለሕፃናቱ ከመጀመሪያው ጀምሮ ክትትል ለማድረግ እንዲመቸን በማሰብ እንዲሰጡን የጠየቅነው ጨቅላ ሕፃናትን ነበር። በጊዜው ሞራልና መልካም ሃሳብ እንጂ ገንዘብ አልነበረንም። መጀመሪያ ቤቱን ማደራጀት እንዳለብን ተነገረን፤ ፈቃድ የምናገኘውም ቤት ተከራይተን ለልጆቹ የሚስፈልጋቸውን ነገር ማሟላታችን ከተረጋጋጠ በኋላ እንደሆነ ተገልፀልን። 200ሺህ ብር ከግለሰብ ብድር ወስደን ቤት ተከራየን። ለሰባት ልጆች የሚሆን አልጋ፣ ፍሪጅ፣ ልብስ ማጠቢያና ሌሎች የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ተሟሉ።

ቤቱ የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባለሙያዎች ከታየ በኋላ፣ ‹ከአምስት ዓመት በላይ የሆናቸውን ሕፃናትን ነው የምንሰጣችሁ› ተባልን። እኛ ደግሞ ከመጀመሪያው ጀምሮ ክትትል እያደረግን ለማሳደግ የሚመቹን ጨቅላ ሕፃናት እንደሆኑ ስለምናምን በሃሳባቸው ለመስማማት ተቸገርን። ‹እስኪ እናስብበት› ብለን ነገርናቸው። ጨቅላ ሕፃናትን እንዲሰጡን በተደጋጋሚ ማሳሰባችንን ግን ቀጠልንበት። ይህን ሁሉ ለፍተንና ከስረን ከምንተወው ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት እድሜ ያላቸውን ልጆች እንዲሰጡን ጥያቄ አቀረብን። ቤት ተከራይተን ኪራይ መክፈል ከጀመርን ከስድስት ወራት በኋላ፣ ከስድስት ወር እስከ ሁለት ዓመት ተኩል እድሜ ያላቸው ሰባት ሕፃናትን ከ‹ክበበ ፀሐይ የጨቅላ ሕፃናት ጊዜያዊ ማቆያና እንክብካቤ ማዕከል› ሰጡን። ከዓመት በኋላ ከሦስት እስከ 11 ዓመት እድሜ ያላቸው አምስት ልጆች ተጨመሩልን። ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ ከአንድ እናትና አባት የሚወለዱና ወላጆቻቸው ሞተውባቸው ጎዳና የወጡ ሦስት መንታ ልጆችን ተቀበልን። አሁን በአጠቃላይ 15 ልጆችን እያሳደግን ነው›› ይላሉ።

የድርጅቱ ዋና ዋና ተግባራት ሕፃናትን ማሳደግ እና እናቶችን ማብቃት እንደሆነ የሚናገሩት ወይዘሮ ገነት፤ ‹‹ዓላማችን የወደቁ ሕፃናትን መታደግ እና እናቶች ሥራ ሰርተው ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ነው። ሕፃናትን ከማሳደግ በተጨማሪ እናቶች ልጆቻቸውን እንዳይጥሉ እንዲሁም ገቢ ሳይኖራቸው ልጅ እንዳይወልዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን እንሰጣለን። ምንም ዓይነት መተዳደሪያ ለሌላቸው እናቶችም ወርሃዊ ድጋፍ እናደርጋለን። ልጆችን ማሳደግ ሲባል ማብላትና ማጠጣት ብቻ አይደለም። ትምህርታቸውን ጨርሰው ራሳቸውን እስከሚችሉ ድረስ መከታተልና መደገፍን ይጨምራል። እናቶችም በዘላቂነት ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ስለሚገባ ሥራ ለማስያዝ እንጥራለን›› በማለት ስለድርጅቱ ተግባራት ያስረዳሉ።

‹‹ቶራ›› የበጎ አድራጎት ድርጅት በአሁኑ ወቅት 46 ልጆች ላሏቸው፣ የድሃ ድሃ ለሆኑ 30 እናቶች በየወሩ መሰረታዊ የምግብ አቅርቦት ድጋፍ እያደረገ ነው። የፅዳት እቃዎችንም ይሰጣል፤ አቅም ሲፈቅድ የትራንስፖርት ወጪ ድጋፍም ያደርጋል። ወይዘሮ ገነት ‹‹ለአንድ እናት በወር ሁለት ሺህ ብር ይመደባል። በአጠቃላይ ለእናቶች በወር 60ሺህ ብር እናወጣለን። ድጋፉ የሚሰጠው በዓይነት ነው። በበዓላት ወቅት ደግሞ ተጨማሪ የጥሬ ገንዘብ እርዳታ ይደረግላቸዋል። ይሁን እንጂ እናቶች ተረጂ ሆነው እንዲቀጥሉ አንፈልግም። ሥራ ሰርተው፣ ራሳቸውን ችለው ልጆቻቸውን እንዲያሳድጉ እንሻለን። ልጆች ወደ ጎዳና ሳይወጡ ከወላጆቻቸው ጋር እንዲያድጉ ከተደረገ ጎዳና ላይ የሚወድቁ ሕፃናት ቁጥር ይቀንሳል ብለን እናምናለን። ስለዚህ ዓላማችን እናቶች እየሰሩ ልጆቻቸውን እንዲያሳድጉ ነው›› ይላሉ። ለዚህ ይረዳ ዘንድ በሚቀጥለው ኅዳር 2015 ዓ.ም የሚጀመር ፕሮጀክት እንዳለም ወይዘሮ ገነት ይናገራሉ።

ፕሮጀክቱ እንጀራ የማከፋፈል ተግባር ሲሆን፣ እናቶች ስልጠና ወስደው ተቀጥረው እንዲሰሩ የሚደረግበት ነው። ከተረጂነትና ጥገኛነት ወጥተው፣ ተቀጣሪ ሆነው፣ ራሳቸውን እንዲረዱና እንዲያስተዳድሩ ትልቅ እገዛ ያደርጋል። ይህን ለማሳካት ድርጅቱ እያንዳንዳቸው 20 ብር የሚሸጡ አንድ ሚሊዮን ትኬቶችን አዘጋጅቶ ለሽያጭ አቅርቧል። እናቶቹ ሥራቸውን ሲያከናውኑ ልጆቻቸውን የሚያቆዩበት ማቆያ (Day Care) ያስፈልጋቸዋል። ስለሆነም ከእንጀራ ማከፋፈያ ፕሮጀክቱ በተጨማሪ የሕፃናት ማቆያ ስፍራውን የማደራጀት ተግባርም እንደሚከናወን ሥራ አስኪያጇ ነግረውናል።

‹‹ቶራ›› እነዚህን ሁለት ትልልቅ ተግባራት እስከ ቀጣዩ ኅዳር ድረስ ለመጀመር አቅዷል። እናቶችን ሥራ የማስያዙ ተግባር በአንድ ዙር ብቻ የሚጠናቀቅ እንዳልሆነ የሚገልፁት ወይዘሮ ገነት፣ በመጀመሪያው ዙር ሥራ እንዲይዙ ከሚደረጉት 30 እናቶች በተጨማሪ በተከታታይ ዙሮች ተጨማሪ እናቶችን ሥራ በማስያዝ ለልመና የሚዳረጉ ሴቶችን ቁጥር ለመቀነስ ጥረት እንደሚደረግም ነው ያነሱት።

‹‹ቶራ›› የበጎ አድራት ድርጅት ለሕፃናት ምግብና አልባሳት ከማቅረብ ባሻገር ሥነ-ምግባር የሚማሩበትም ምግባረ ሰናይ ተቋም ነው። በዚህ ረገድ ወይዘሮ ገነት ‹‹ከማብላትና ከማጠጣት በተጨማሪ ሕፃናቱ በሥነ-ምግባር ታንፀው እንዲያድጉ እንፈልጋለን፤ እንጥራለንም። እንደ የሃይማኖታቸው የግብረ ገብ/የሥነ-ምግባር ትምህርት እንዲማሩ እናደርጋለን። ከጎዳና ላይ የመጡ ልጆቻችን የሥነ-ልቦና አማካሪ ተመድቦላቸው ድጋፍ እየተደረገላቸውም ነው›› በማለት ሥራቸው በምን መልኩ እየተከናወነ እንዳለም ያብራራሉ።

ድርጅቱ የውጭ እርዳታ እንደሌለው የሚናገሩት ወይዘሮ ገነት፣ የገቢ ምንጩ በየወሩ ከ200 እስከ ስምንት ሺህ ብር ድጋፍ ከሚያደርጉለት ቋሚ አባላት የሚገኝ ገንዘብ ነው። በተጨማሪ ከበጎ ፈቃደኞች የሚገኝና የልጆቹን የትምህርት ወጪ የሚሸፍነው የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ እንደሆነ ያስረዳሉ። 12 ልጆች በ2015 ዓ.ም ትምህርታቸውን በግል ትምህርት ቤት እንደተከታተሉና ለ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመንም እንደተመዘገቡ ይገልፃሉ።

‹‹የድርጅቱ አባላት 150 ናቸው። ከአባላት የሚገኘው ገንዘብ የማሳደጊያውን ወጪ ይሸፍናል። የትምህርት ቤት ወጪን በተመለከተ የ12 ልጆችን የ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የትምህርት ቤት ወጪ 12 ሰዎች ስፖንሰር አድርገዋቸው ተምረው ጨርሰዋል። በ2016 ዓ.ም ትምህርት ቤት የሚገቡት 13 ልጆች ናቸው። የጥቂቶቹን ወጪ የሚሸፍኑልን የተወሰኑ ሰዎችን አግኝተናል። እስከ መስከረም ድረስ ለሁሉም እናገኛለን ብለን እናስባለን›› በማለት አሁን ያለውን የድርጅታቸውን ችግርም ያነሳሉ።

ድርጅቱ ሦስት ሞግዚቶች፣ አንድ ምግብ አብሳይ፣ አንድ የፅዳት ሠራተኛ፣ አንድ የአስተዳደር ሠራተኛ እንዲሁም አንድ አካውንታት በአጠቃላይ ሰባት ሠራተኞች አሉት። ከ13 መስራች አባላት አንድ ሰው ብቻ ተቀጣሪ ሆኖ ሌሎቹ በበጎ ፈቃደኝነት እያገለገሉ ይገኛሉ። በየጊዜው የሚጨምረው የቤት ኪራይ ዋጋ የድርጅቱ ትልቅ ፈተና ሆኗል።

የ‹‹ቶራ›› የበጎ አድራጊት ድርጅት ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች እናቶችን በማብቃት ችግሮቻቸውን የመቅረፍ ተግባራት ናቸው። ወይዘሮ ገነት ‹‹ከዚህ በኋላ ሌሎች ልጆችን የመቀበል እቅድ የለንም። አሁን ላሉት 15 ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ነገር በማሟላት በመልካም ሥነ-ምግባር ማሳደግ እንፈልጋለን። ከዚህ በኋላ መሥራት የምንፈልገው እናቶች ላይ ነው። አሁን ድጋፍ ከሚደረግላቸው 30 እናቶች በተጨማሪ ሌሎች እናቶችም ሥራ ይዘው ራሳቸውን እንዲችሉ የማድረግ እቅድ አለን። የሥራ መስኮችን እየፈጠርን ሥራ የሚይዙበትን መንገድ በማመቻቸት ልመናን ለመቀነስና ልጆች ወደ ጎዳና እንዳይወጡ አስቀድሞ የመከላከል ሥራ እንሰራለን። ለእናቶች የሥነ-ልቦና ድጋፍና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና የሚሰጥ አካል ማግኘትም እንፈልጋለን›› በማለት ስለድርጅቱ ቀጣይ እቅዶች ያስረዳሉ።

የመንግሥት አካላት የሚያደርጉት ትብብር አመርቂና በሚፈለገው ልክ እንዳልሆነ የሚገልጹት ወይዘሮ ገነት፣ ሕፃናትን የመታደግ ተግባር መንግሥትን ጨምሮ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚመለከት ተግባር በመሆኑ፣ የመንግሥት አካላት በመሰል የበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ ለተሰማሩ ምግባረ ሰናይ ተቋማት አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንዳለባቸውም ይመክራሉ።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 5/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *