የሴት ልጅ ግርዛት በአፋር

በአፋር ክልል ከ15 እስከ 49 የእድሜ ክልል የሚገኙ ሴቶች ይገረዛሉ፡፡ የሴት ልጅ ግርዛት ምጣኔ 91 በመቶ እንደነበር እ.አ.አ በ2016 በኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብና ጤና መረጃ ያመላክታል፡፡

በክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ተሳትፎና ንቅናቄ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ፋጡማ ሀምፈሬ እንደሚሉት በአፋር ክልል ከሴት ልጅ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች፤ የሴት ልጅ ግርዛት፣ ያለ እድሜ ጋብቻ እና ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች አሉ።

ይህን ከሃይማኖት አባቶች፣ ከፍትህ አካላት እና ከተለያዩ የሴቶች አደረጃጀቶች ጋር በመሆን የሴት ልጅ ግርዛት ለመከላከል የግንዛቤ እና የንቅናቄ ሥራ እንደሚሰራ ወይዘሮ ፋጡማ ያስረዳሉ፡፡ በአፋር ክልል ሴት ልጅን የሚገርዙ አካላት ከዚህ በፊት በነበራቸው ግንዛቤ ሴት ልጅን መግረዝ እንደ ባሕልም፤ እንደ ሃይማኖትም ግዴታቸው አድርገው ነበር የሚያስቡት። በዛ ላይ ደግሞ ገቢ የሚያገኙበት ሥራም ጭምር ነው፡፡ በሴቶች ግርዛት በሚገኝ ገቢ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ ይህም ችግሩን ቶሎ ለመቅረፍ እንቅፋት ሆኗል፡፡

ገራዥ ሴቶችን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ለማድረግ እንደ ቢሮ የተሰራው የመጀመሪያው ሥራ፤ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን መስጠት ነው፡፡ ሌላው ገራዧ የምትተዳደረው በዚሁ ሥራ እንደመሆኑ በሌላ ሥራ እንድትሳተፍ የሥራ እድሎችን በማመቻቸት ረገድ ሥራ መሰራቱን ያስረዳሉ፡፡

ገራዦቹ ለረጅም ዓመታት በሥራው ገቢ ሲያገኙበት እንደ መቆየታቸው ከዚህ ሥራ ለመውጣት ያላቸው ፈቃደኝነት በመጀመሪያ ፈታኝ ነበር፡፡ ገራዦቹ ይህንን ሕገ ወጥ ተግባር እንዲተው በሁለት ዓይነት መልኩ ነበር የተሰራው፡፡ የመጀመሪያው ከዚህ ሥራ ካልወጡ በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ማስጠንቀቂያዎች የተሰጡ ሲሆን፤ ሌላኛው ተደራጅተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡

በአፋር ክልሉ ከ40 በላይ ወረዳዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ወረዳዎች ከ25 በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች ቀደም ሲል በገርዝና ሥራ ይተዳደሩ ነበሩ እናቶች በሌላ ሙያ ተደራጅተው መሥራት መጀመራቸውን ወ/ሮ ፋጡማ ያስረዳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከ43 በላይ ቀበሌዎች ከሴት ልጅ ግርዛት እና ያለ እድሜ ጋብቻ ነፃ ሆነዋል፡፡ ነፃ መሆኑን የሚረጋገጠው በመጀመሪያ ደረጃ የወረዳው እና የቀበሌው አመራሮች ቃል የገቡበት ሁኔታ አለ፡፡ ቃል ከመግባትም በላይ የማህበረሰብን መመሪያ አውጥተው የሚዳኙበት መንገድ ተዘጋጅቶ መመሪያውን ሳይፈጽሙ ሲቀር ተጠያቂ የሚሆኑበት ስምምነት ላይ መደረሱን ያነሳሉ፡፡

ወይዘሮ ፋጡማ እንደሚሉት፤ ወረዳዎቹ ከእነዚህ ተግባራት ነፃ መሆናቸውን ለማረጋገጥ፤ እንደ መንግሥት በቀጣይነት የሚከተል አካል አለ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ያለ እድሜ ጋብቻም ከበፊቱ አሁን ላይ የቀነሰበት ሁኔታ አለ፡፡ ምክንያቱም ከግርዛት በተለየ የሃይማኖት አባቶች ጋር አንድ ሴት ልጅ ያለ እድሜዋ ስላገባች፤ ቤተሰብ በሕግ ተጠያቂ አይሆኑም የሚል እምነት አላቸው፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት ደግሞ የሃይማኖት ትዕዛዝ ነው የሚል ሽፋን ነው፡፡ ሆኖም ይህ ከሃይማኖት አባቶች ጋር በተደረገ ምክክር ችግሩ እየተፈታ ሄዷል፡፡

ለሃይማኖት አባቶች በተሰጠው ግንዛቤ መሠረት፤ አሁን ላይ በክልሉ ካለው የኑሮ ዘይቤ አንጻር በሌሎች አካባቢዎች እና በአፋር ክልል ያሉ ሴቶች አስተዳደግ እኩል አለመሆኑን ከስምምነት በመድረስ በአፋር ያለውን ያለ ዕድሜ ጋብቻ ማስቆም እንደሚገባ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ የአካባቢው ሴት ልጆች አስተዳደጋቸው ደካማ የሚባል ነው፡፡ ሴት ልጆች ትምህርታቸውን ማቋረጥ እንደሌለባቸው እና በዛ ላይ ግርዛትም ስላለ ያለ እድሜ ሲያገቡ ወሊድ ላይ የሚያደርሰውም ጫና ከፍተኛ በመሆኑ ችግሩ ቶሎ መቅረፍ እንደሚገባው ሁሉም መረዳት መጀመሩን ወ/ሮ ፋጡማ ይናገራሉ፡፡

ዳይሬክተሯ እንደሚናገሩት፤ ሴቶች ትምህርታቸ ውን እንዳያቋርጡ እና ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ የሴቶች የልማት ህብረት የሚባል አደረጃጀት አለ። የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ክትትል ያደርጋል። ያቋረጡና በትምህርት ገበታቸው ያሉ ሴቶችን ለይተው ለቢሮ ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ ከቢሮው በኩል ደግሞ በየዓመቱ መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ቅስቀሳ ይደረጋል፡፡

እናም አሁን አፋር ክልል ላይ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የሚያጠናቅቁ ሴቶች ቁጥር ጨምሯል። ከዚህ በፊት ከነበረው በገጠር አካባቢዎች ጭምር እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለው ተሳትፎ ከፍተኛ ነው፡፡ ትንሽ ችግር ያለው በሁለተኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ በዛም ላይ እየተሰራ ነው ይላሉ፡፡

በክልሉ የሴቶች ጥቃትን ለመከላከል የሚሰሩ ሥራዎችን ከኢኮኖሚ ጋር በማስተሳሰር እየተሰራ መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ፋጡማ፤ ምክንያቱም፤ ሴት ልጅ በኢኮኖሚ ጠንካራ ስትሆን ነው ጥቃት እንዳይደርስባት መከላከል የምትችለው፡፡ ‹‹እኔ ላይ የደረሰ ጥቃት ልጄ ላይ መድረስ የለበትም›› ‹‹ልጄን ብቻዬን ማሳደግ እችላለሁ›› የምትልበት አቅም ስለሚኖራት ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ ማንኛውንም ሥራ ሲሰራ ከገቢ ማስገኛ ሥራዎች ጋር አስተሳስሮ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በክልሉ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተሳትፎ በማጠናከር ረገድ በተደረገው እንቅስቃሴ በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ፣ በሻይ ቡና ንግድ እና በግብርና ሥራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች አሉ፡፡ በሌማት ትሩፋት ተጠቃሚ ሆነው፤ ዶሮ እርባታና ሌሎች ሥራዎችን ሰርተው በኢኮኖሚ እራሳቸውን ከመቻል ባለፈ፤ አንድ ዓይነት ምግብ ሲበሉ የነበሩ፤ ዛሬ ላይ የተመጣጠነ የአመጋገብ ሥርዓት የሚከተሉ ቀበሌዎች መኖራቸውን ማስተዋል መቻሉን ይጠቁማሉ፡፡

ዳይሬክተሯ እንደሚናገሩት፤ ከጦርነቱ በኋላ አፋር ክልል ከዚህ በፊት ባልነበረ እና በማይታወቅ ሁኔታ የሴቶች ጾታዊ ጥቃት በክልሉ በጣም የጨመረበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እነዚህ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እንዲያገኙ የአንድ መስኮት አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላት አሉ፡፡ በእነዚህ ማዕከላትም ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች የሥነ ልቦና ህክምና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ወ/ሮ ፋጡማ አስረድተዋል፡፡

ጥቃት የደረሰባት ሴት ወደ ማህበረሰቡ ለመቀላቀል ያሳለፈችውን ጠባሳ በመፍራት ወደ ቀዩዋ ላትመለስ ትችላለች፡፡ እናም ብዙዎች ወደ ከተማ ይሰደዳሉ፡፡ ከዚያም መልሰው ለኢኮኖሚ ጥገኝነትና ለጥቃት ይጋለጣሉ፡፡ ይህንን ችግር በመረዳትም ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ስልቶች ተነድፈው ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ ከሥራና ክህሎት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በመሆን፤ የሥራ እድል እየተፈጠረላቸው፣ የብድር አገልግሎት እየተመቻቸላቸው መሆኑን ወ/ሮ ፋጡማ ያስረዳሉ፡፡

ሌላው ተጎጂዋ ሴት ከማዕከሉ ወጥታ ችግሯ በፍትህ አካላት እንዲታይላት ወደ ፍትህ አካላት ስትመላለስ፤ ምስክሮችን የማሸሸ፣ ጉዳዩን በሽምግልና የመጨረስ ሂደት በስፋት ይታይ ነበር፡፡ ሆኖም ጉዳት ፈጻሚ አካላት ትክክለኛውን የፍርድ ብያኔ እንዲያገኙ ጥቃት የደረሰባት ሴት ብቻዋን የክስ ሂደት ከምትመሰርት ይልቅ ወደ አንድ ማዕከል አገልግሎት ተቋም በመምጣት በማዕከሉ በኩል ክስ እንድትመሰርት የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ጥቃት የደረሰባት ሴት አንዴ ወደ ማዕከሉ ከገባች እዛው ፖሊስ ቃሏን ይቀበላል፣ ጉዳዩ ለፍትህ አካላት እንዲቀርብ ይደረጋል፡፡ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ እርግዝና እንዳይፈጠር፤ ተላላፊ በሆኑ በሽታዎች እንዳትያዝ አፋጣኝ ህክምና ይሰጣታል፡፡ ማዕከሉ ከዚህ በፊት ሶስት የነበረ ሲሆን ሁለት ተጨምሮ አሁን በክልሉ አምስት የአንድ መስኮት አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላት እንዳሉ ወ/ሮ ፋጡማ ይናገራሉ፡፡

ማዕከላቱ በአምስቱም የዞን ማዕከላት አሉ፡፡ አሁን ሁለት ሆስፒታሎች በተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች አማካኝነት በመገንባት ላይ ናቸው፡፡ እሱ ሲጠናቀቅ ማዕከላቱ ወደ ሰባት ያድጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እንደ ክልል የተገነባ የማገገሚያ ማዕከል አለ፡፡ የአንድ መስኮት አገልግሎት ማዕከሉን ከማገገሚያ ማዕከሉ ጋር የማስተሳሰር ሥራ ይሰራል ይላሉ፡፡

ጥቃት የደረሰባት ሴት በአንድ መስኮት አገልግሎት ማዕከሉ ለ72 ሰዓት በምታገኘው አገልግሎት ላታገግም ትችላለች፡፡ ወደ ማህበረሰቡ ስትመለስ ማህበረሰቡ የሚሰጣት ስም ስላለ ለማገገም ይከብዳታል፡፡ ስለዚህ ወደ ማገገሚያው ገብታ ሶስት ወርም ይሁን አራት ወር ቆይታ የተለያዩ የሙያ ስልጠናዎችን ወስዳ እራሷን ችላ የምትወጣበት መንገድ ለመፍጠር እንደ ክልል አንድ ማዕከል ተገንብቷል፡፡ በቀጣይ ተጨማሪ የማስገንባት እቅድ እንዳለም ይጠቁማሉ፡፡

ከዚህ በፊት ሴቶች ጥቃት ሲደርስባቸው ወጥተው ለመናገር ይፈራሉ፡፡ ጉዳዩም በሽምግልና ይያዝና ተለባብሶ ይቀራል፡፡ አሁን ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ወጥተው የደረሰባቸውን ጥቃት መግለጽ ጀምረዋል፡፡ በዚህ ረገድ በዙሪያቸው ያሉ ወንዶች አጎት፣ ወንድም ሆነ አባት እያደፋፈሯቸውና ወጥተው እንዲናገሩ እየረዷቸው ነው ይላሉ፡፡

ወይዘሮ ፋጡማ እንደሚናገሩት፤ አሁን ላይ እስከ መጨረሻው ድረስ በፍርድ ቤት ተከታትለው ፍርድ የሚያገኙ እና ብይን ከተሰጠ በኋላም፤ የተሰጠው ብይን ትንሽ ነው ብሎ ይግባኝ የሚጠይቅ ማህበረሰብ ተፈጥሯል፡፡

ጥቃትን በመከላከል ረገድ ተግዳሮት የሆነባቸውን ጉዳይ ዳይሬክተሯ ሲናገሩ፤ በክልሉ የሚኖረው ማህበረሰብ ጎሳን መሠረት አድርጎ የሚኖር ስለሆነ፤ በሁለቱ ጎሳዎች ግጭት እንዳይፈጠር በሚል ችግሩን በሽምግልና ይዞ የማስቀረት ሁኔታ አለ ይላሉ፡፡

ጾታዊ ጥቃት ደግሞ ከመገደል ያነሰ አይደለም፡፡ ሴቷ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ካለመገንዘብ፣ ግጭት ይፈጠራል በሚል በሽምግልና ይያዛል፡፡ አፋር ክልል ከሌላው ክልል የሚለየው ግጭት እንዳይፈጠር ተብሎ ፖሊስ በቀጥታ ገብቶ ወንጀለኛውን አያወጣም በማለት ይገልጻሉ፡፡

ይህን ችግር ለመፍታት ከጎሳ መሪዎች እና ከሃይማኖት መሪዎች ጋር በቅንጀት የጀመርነው ነገር አለ፡፡ በጋራ ስንሰራ ወንጀለኛው ወጥቶ ቅጣቱን የሚያገኝበት ሂደት እና ጥምረቱን ለማጠናከር በ2016 ዓ.ም ሥራዎች ተጀምረዋል በማለት ይናገራሉ፡፡

አፋር ላይ ሴት ልጅ ሌሊት እንኳን ብቻዋን ብትሄድ ጥቃት አይደርስባትም ነበር፡፡ ከጦርነቱ በኋላ የተለያዩ ባሕሎች የመወራረስ ነገር መጥቷል፡፡ ከዚህ በፊት እንደ ክልል አንድ ጥቃት በዓመት ልንሰማ የምችለው አሁን፤ በአንድ ቀን ከአምስት ወረዳ የጥቃት መረጃ የሚደርሰን ጊዜ አለ ይላሉ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ምንድነው መነሻው፣ ጥቃት የደረሰባቸው ምን ያህል ነው የሚለውን ለማወቅ እና መፍትሔ ለማስቀመጥ ጥናት ተጀምሯል የሚሉት ዳይሬክተሯ፤ በመጨረሻም ሴቶች ጥቃት ሲደርስባቸው ተስፋ ሳይቆርጡ ለመብታቸው እንዲከራከሩ እና ወንዶችም እንደ እራሳቸው እህት በማየት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀርባሉ፡፡

በአጠቃላይ በአፋር ክልል የሴት ልጅ ግርዛት በተመለከተ አበረታች ውጤቶች የተመዘገቡትን ያህል እንደ አዲስ በክልሉ እየተስፋፋ የመጣውን አስገድዶ መድፈር በጋራ ንቅናቄ ማምከን ያስፈልጋል፡፡

ሆኖም ለረጅም ዘመናት ያህል ችግር ሆኖ የኖረው የሴት ልጅ ግርዛት ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያስገኘ ነው። ይህን ተከትሎ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደ ሀገር ለክልሎች ሽልማት የሰጠበት ሁኔታ አለ፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ሽልማት አግኝታለች፡፡ በዚህ ዕውቅናም የአፋር ክልል እውቅና አግኝቷል፡፡ ይህን እውቅና ያመጣው ቢሮ ብቻውን በሰራው ሥራ ሳይሆን ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሴት አደረጃጀቶች፣ ከሌሎች አካላት ጋር በተሰራው ሥራ ነው፡፡ ለዚህ ለተገኘው ውጤት ላበረከቱ አስተዋጽኦ ለሀገር ሽማግሌዎች፣ ቀደም ሲል በገራዢነት ሲሳተፉ ለነበሩትና አሁን በተለያዩ ሙያዎች ለተሰማሩ ሴቶች እና ግንዛቤ በመፍጠር ሥራ ለተሳተፉ ሴቶች እውቅና እንሰጣለን በማለት ምስጋና አስተላልፈዋል፡፡

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን መስከረም 7/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You