በበርካታ የዓለም አገራት የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ውስጥ ገዝፎ የሚታየው ‹‹የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት›› (Public Private Partnership – PPP) ነው። አሰራሩ በየጊዜው እያደገ የመጣና ሚናው ከፍተኛ ሲሆን፤ በብዙ አገራት መንግሥታዊ አገልግሎቶችን በግሉ ዘርፍ በኩል እንዲያቀርቡ እድል የፈጠረ እንደሆነም ይነገርለታል። ይህ አጋርነት መንግሥት በራሱ ማቅረብ የሚገባውን አገልግሎት ከግሉ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት የሚያቀርብበትም ነው።
የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት ሁሉንም የምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ ጥናት ባለሙያዎች የሚያስማማ ትርጓሜ አልተገኘለትም። የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት እንዲጠናከር ድጋፍ ከሚያደርጉ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የዓለም ባንክ (World Bank)፣ የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት ‹‹መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በረጅም ጊዜ የውል ስምምነት አገልግሎቶችን ለማቅረብ በትብብር የሚተገብሩት አሠራር›› እንደሆነ ይገልፃል።
የዓለም የገንዘብ ድርጅት (International Monetary Fund – IMF) በበኩሉ፣ የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነትን፣ ‹‹በተለምዶ መንግሥት ያቀርባቸው የነበሩ አገልግሎቶች በግሉ ዘርፍ በኩል እንዲቀርቡ የሚያስችል አሰራር›› ብሎ ይተረጉመዋል። በድርጅቱ ትርጓሜ መሠረት በመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት አሰራር ሥርዓት፣ መንግሥት የሚያቀርባቸው አገልግሎቶች በግሉ ዘርፍ ሲቀርቡ የግሉ ዘርፍ የአገልግሎቶቹን የፋይናንስ፣ የግንባታና የአስተዳደር/አመራር ኃላፊነቶችን ይረከባል።
የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት ‹‹የአገልግሎት አቅርቦትንና ተደራሽነትን ዓላማቸው ባደረጉ የመንግሥት ተቋማት እና ትርፍን ታሳቢ ባደረጉ የግል ዘርፍ ተዋንያን መካከል የሚደረግ የአገልግሎት አቅርቦትና አስተዳደር ስምምነት ነው›› የሚል ብያኔ የሚሰጠው ደግሞ የምጣኔ ሀብት ትብብርና ልማት ድርጅት (Organization for Economic Co-Operation and Development – OECD) የተሰኘው በይነ-መንግሥታዊ ተቋም ነው።
አገራት ለመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት የሚሰጡት ብያኔ እንደየአገራቱ ነባራዊ ሁኔታዎች የተለያየ ነው። አገራት የሚከተሏቸው የምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሞች በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት በሚደረጉ ስምምነቶችም ሆኑ በአጠቃላይ አስፈላጊነታቸው ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ይገመታል። ርዕዮተ ዓለሞቹ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በገበያ ውስጥ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ስለሚወስኑ፣ በሁለቱ አካላት አጋርነት የሚከናወኑ ተግባራት ዓይነትና ወሰን የርዕዮተ ዓለሞቹ ጫና ሰለባ መሆናቸው አይቀርም።
በአጠቃላይ ‹‹የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት›› በአገር ልማትና እድገት ውስጥ ዋነኛ ተዋንያን በሆኑት በመንግሥትና በግል ዘርፎች መካከል የሚደረግ የአገልግሎት አቅርቦትና የልማት ትብብር እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት መገለጫ ከሆኑት ባህርያት አንዱ የግሉ ዘርፍ መንግሥት ለሕዝብ አገልግሎት ማቅረብ በሚገባው ዘርፍ ውስጥ መሳተፉ ነው። ቀጣይ ጊዜን ታሳቢ ያደረጉ የረጅም ጊዜ ስምምነቶች እና የሀብት፣ የክህሎትና የኪሳራ ክፍፍሎችም የአጋርነቱ ሌሎች መገለጫዎች ናቸው። አንዳንድ አገራት የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት የውል ጊዜ እስከ 25 ዓመታት ድረስ መዝለቅ እንዳለበት ደንግገዋል። የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን ኪሳራ ለሁለቱ ወገን ያከፋፍላል፤ ሁለቱ ተዋንያን ከኪሳራ በተጨማሪ ሀብትና ክህሎትንም ይጋራሉ።
በርካታ የጥናት ውጤቶች እንደሚሳዩት፣ የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት ለኢንቨስትመንት ዘርፍ እድገት ትልቅ ሚና አለው። የባባሳሄብ አምቤድካር ዩኒቨርሲቲ (ሕንድ) መምህራኑ ጓራቭ ሲንግ እና መሐመድ ካሃን የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት በማኅበረሰብ ግንባታና በአገር እድገት ላይ የሚኖረውን ሚና በዳሰሱበት ‹‹The Role of Public Private Partnership (PPP) in Building Society›› በተሰኘው ጥናታቸው፣ ብዙ የዓለም አገራት፣ በተለይም ታዳጊዎቹ፣ በመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት በኩል የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት በርካታ ተግባራትን እንደሚያከናውኑ ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪም የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት የመልካም አስተዳደር ሥርዓትን ለማስፈን ሁነኛ ግብዓት ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
ይህ አሠራር በተለይም የማኅበራዊ አገልግሎቶችን ተደራሽነት ለማስፋት ለሚያስፈልገው ፋይናንስ ተጨማሪ ምንጭ በመሆን ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ማደግ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የባለሙያዎቹ ጥናት ያስረዳል። በአጠቃላይ የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት የአገልግሎቶችን ተደራሽነትና ጥራት በማሳደግ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ እድገት ምቹ መደላድሎችን የሚፈጥር ግብዓት ነው።
የዓለም ባንክ፣ አገራት የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነትን እንዲተገብሩና አሰራሩ እንዲጠናከር ድጋፍ ከሚያደርጉ ተቋማት መካከል በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል። የባንኩ የጥናት መረጃዎች እንደሚያሳየውም፣ ከ 134 በላይ የዓለም አገራት የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት አሠራርን በተግባር ላይ አውለዋል። ከ 15 እስከ 20 በመቶ የሚሆነው የእነዚህ አገራት የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት (Infrastructure Investment) የተገነባውም በዚሁ አጋርነት አማካኝነት ነው። ባንኩም ይህን የአሰራር ሥርዓት ለሚተገብሩ አገራት በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (International Finance Corporation – IFC) እና በባለብዙ ወገን የኢንቨስትመንት ዋስትና ድርጅት (Multilateral Investment Guarantee Agency – MIGA) በኩል ከፍተኛ የፋይናንስ ድጋፍ ያደርጋል። ባንኩም በክትትልና ድጋፉ የአሠራሩ ትግበራው የየሀገራቱን የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ተደራሽነትና ጥራትን ለማሳደግ ላቅ ያለ አስተዋፅኦ እንዳበረከተ ምስክርነቱን ሰጥቷል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥትም በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ የግል ድርጅቶች ጋር በጥምረት የመሠረተ ልማት አውታሮችን የመገንባት ተግባራትን ሲያከናውን ይታወቃል። እንዲህ ዓይነቱ አሠራር በተለያዩ ጊዜያት በወጡት የኢንቨስትመንት አዋጆች ውስጥም እውቅና ያገኘና የተደነገገ ነው። የአጋርነቱን ትግበራ የተሻለ ውጤታማ ለማድረግና በትግበራው ሂደት የሚታዩ ክፍተቶችን ቅርፅ ለማስያዝ ያስችላል የተባለው ‹‹የመንግሥትና የግል አጋርነት አዋጅ›› (1076/2010) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁ ይታወሳል።
የመሠረተ ልማት ሥርዓቱን ጨምሮ የአገሪቱን የልማት ግቦች ከማሳካት አንጻር የግሉ ሴክተር ወሳኝ ስትራቴጂያዊ አጋር መሆኑ በአዋጁ ላይ የተመላከተ ሲሆን፤ አዋጁ ግልጽነትን፣ ፍትሐዊነትን እና ዘላቂነትን ለማስፈን እና በግሉ ዘርፍ የፋይናንስ አቅም የሚገነቡ የመሠረተ-ልማት ፕሮጀክቶችን ለማበረታታት የሚረዳ አመቺ የሕግ ማዕቀፍ እንደሆነም ተጠቁሟል።
የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት እንዲጠነክር ምቹ ሁኔታ ከሚፈጥሩ አሠራሮች መካከል አንዱ በሁለቱ ዘርፎች መካከል የሚደረግ የጋራ ምክክር (Public-Private Dialogue) ነው። የጋራ ምክክሩ የግሉ ዘርፍ ያሉበትን ችግሮች ለመንግሥት በማቅረብ የግሉ ዘርፍ ጠንካራና ተወዳዳሪ ሆኖ በመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት ፕሮጀክቶች ላይ እንዲሳተፍ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል።
በኢትዮጵያም የግሉ ዘርፍ ከመንግሥት አካላት ጋር ምክክር እንዲያደርግ እድል የፈጠረው ብሔራዊ የመንግሥትና የግል ዘርፍ የምክክር መድረክ (National Public-Private Dialogue)፣ የግሉ ዘርፍ ያሉበት ችግሮች በጥናት ተለይተው ለመንግሥት ሲቀርቡበት ቆይቷል።
የግሉ ዘርፍ ወኪል በሆነው የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የሚዘጋጀው ይህ የምክክር መድረክ፣ በወቅቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና በምክር ቤቱ መካከል በተደረገ ስምምነት፣ በ2002 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል ያለውን የልማት ግንኙነትና አጋርነት ለማጎልበት እንዲሁም ለንግድና ኢንቨስትመንት ማነቆ የሆኑ ችግሮች እልባት እንዲያገኙና ለአፈፃፀማቸው ክትትል የሚደረግበት ሥርዓት እንዲኖር ታስቦ የተቋቋመ መድረክ ነው።
ይህ መድረክ በ2007 ዓ.ም በዓለም አቀፍ ደረጃ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረኮችን በሚደግፈውና በየዓመቱም ክንውኖቻቸውን በሚገመግመው ዓለም አቀፉ የግልና የመንግሥት ምክክር መድረክ ኮሚቴ ‹‹ለረዥም ጊዜ ዘላቂ የሆነ የምክክር መድረክ በማካሄድ›› እውቅና እንደተሰጠውም ይታወሳል።
የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው፣ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ ስለንግዱ ማኅበረሰብ ችግሮች የሚወያዩበትና ቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጡበት መድረክ እንደሆነ ይገልጻሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፣ የምክክር መድረኩ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል ውይይትን፣ ትብብርንና ስትራቴጂካዊ አጋርነትን ለማጎልበት ወሳኝ መድረክ ሆኖ ቆይቷል። በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል በሰከነ መንፈስ የመመካከርንና ለችግሮች የጋራ መፍትሄ የመፈለግ ባህልን አሳድጓል። ‹‹ድህነትን ለማጥፋት የግሉ ዘርፍ ዋናው የትኩረት ማዕከል እየሆነ በመምጣቱ ጥራቱን የጠበቀ የጥሬ እቃ አቅርቦትንና የቴክኖሎጂ አቅምን ማሳደግ፣ የምርት እሴትን መጨመር፣ የጥራት መመዘኛ ማእቀፎችን ማዘጋጀት እና ለአገር ውስጥ ምርቶች ጥበቃ ማድረግ ያስፈልጋል›› የሚሉት ኢንጂነር መላኩ፤ አገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገቱን በግሉ ዘርፍ የሚመራ ማድረግ እንደሚገባ ያስረዳሉ።
‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ ይሄዳል፤ የግሉ ዘርፍ በምጣኔ ሀብቱ ውስጥ ተዋናይ ሆኖ የሥራ እድል እየተፈጠረ የውጭ ምንዛሪ ግኝት አስተማማኝ እንዲሆን እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በአገር ምርት እንዲተኩ ትኩረት መደረግ አለበት። ለዚህ ደግሞ የግሉ ማኅበረሰብ ያሉበትን በርካታ ችግሮች መፍታት ያስፈልጋል። ‹እድገት ተመዘገበ› ተብሎ ሲነገር እድገቱ የተመዘገበው በግሉ ዘርፍ በተሰራው ስራ ነው። በአገሪቱ ትልቁ የሥራ እድል ፈጣሪ የግሉ ዘርፍ ነው። ላለፉት 30 ዓመታት ኢትዮጵያ አስመዘገበችው በተባለው እድገት አብዛኛው አስተዋፅዖ የመንግሥት ኢንቨስትመንት ነው፤ የግሉ ዘርፍ ድርሻ አነስተኛ ነበር። የግሉ ዘርፍ መሪ የሆነበት የምጣኔ ሀብት እድገት እውን ሊሆን ይገባል›› ይላሉ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተሻለ በልሁ በበኩላቸው፣ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በርቀት ሆነው የሚተያዩበት ጊዜ ቀርቶ የግሉ ዘርፍ አገርን የማልማት ኃላፊነቱን እየተወጣ እንዲሁም መንግሥት ለንግድና ኢንቨስትመንት መስፋፋት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን በማስወገድ የግሉ ዘርፍ በምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ውስጥ ዋና ተዋናይ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ እንደሚገኝ ይናገራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፣ የመንግሥትና የግል ዘርፍ የምክክር መድረኮች የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢው እንዲሻሻል ያስቻሉ የመፍትሄ አማራጮች እንዲመላከቱ አስችለዋል።
ባለፉት አራት ዓመታት መንግሥት ዘርፈ ብዙ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሮችን ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል። ከእነዚህ መርሃ ግብሮች አንዱ፣ አገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብር (Homegrown Economic Reform Program) ነው። የመርሃ ግብሩ ዓላማ አምራች የሆነውን የሠው ኃይል የሚሸከም የሥራ እድል እና የተረጋጋ የማክሮ-ኢኮኖሚ ከባቢ በመፍጠር እንዲሁም የግል ዘርፍ መር (Private Sector-Led) የሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመገንባት ዘላቂና ፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት ማስመዝገብ ነው። የኢንቨስትመንት አዋጅና የንግድ ሕግ ማሻሻያዎች፣ ብሔራዊ የንግድና ቢዝነስ ሥራ አመቺነት ማሻሻያ መርሃ ግብር (National Ease of Doing Business Initiative) እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የግብይት ሥርዓት ጋር ዘመናዊ ትስስር ለመፍጠር የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆን ተወስኖ ውሳኔውን ለመተግበር እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶች የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሩ አካል ናቸው። እነዚህ ማሻሻያዎች የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖረውን ሚና ለማሳደግ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉ ይታመናል። የግሉ ዘርፍ በምጣኔ ሀብት ውስጥ የሚኖረው ሚና ሲያድግ ደግሞ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ማደግ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥረው የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት ይጠናከራል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 4/2015