የአማራ ህዝብ ለኢትዮጵያ የከፈለውን መስዋዕትነት የሚያሳንሱ ተግባራትን ሊታገል ይገባል !

የለውጥ ኃይሉ ወደ ስልጣን ከመጣ ማግስት ጀምሮ ሀገርን ከግጭት አዙሪት ለመታደግ ችግሮች በይቅርታ፤ በውይይትና በድርድር የሚፈቱበትን ሀገራዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ ባህል ለማድረግ በስፋት ተንቀሳቅሷል። ጥረቱ ከመጣንበት የሴራና የጡንቻ እንፈታተን የፖለቲካ ባህል የተነሳ የታሰበውን ያህል ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል። በዚህም ሀገርንና ህዝብን ብዙ ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል ተገድደዋል።

ለውይይትና ለድርድር እንግዳ የሆነው የፖለቲካ ባህላችን፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እንደ ሀገር ለተፈጠረው አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ ተግዳሮት በመሆን፤ ህዝባችን ተስፋ ያደረገውን፣ በተጨባጭም በተግባር ለማየት እድል ያገኘውን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ችግር ውስጥ በመጣል ሳይወድ ከፍቃዱ ውጪ ወደቀደመው የግጭት አዙሪት እንዲገባ ሆኗል።

በዚህም እንደ ሀገር መላው ህዝባችን በአንድም ይሁን በሌላ የግጭቱ ሰለባ ሆኗል። በግጭቶች ሞቷል፣ ቆስሏል፣ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል፤ ከፍያለ የስነ ልቦና ጫና እና የልብ ስብራት ደርሶበታል። ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ተስፋ ያደረጋቸው ብሩህ ነገዎቹ በሴራና በጡንቻ እንፈታተን ፖለቲካ ደብዝዘውበታል። ዘመናት የተሻገሩ እሴቶቹም ለከፋ ተግዳሮት ተጋልጠው ታይተዋል።

በተጣመሙ የታሪክ ትርክቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ አንገቱን አቅንቶ የሚራመድባቸው የነፃነት ተጋድሎ ታሪኮቹ ሳይቀሩ ያለመግባባት ምንጭ ሆነው ታይተዋል፤ የግጭት ምንጭ እንዲሆኑ በስፋት ተሰርቶባቸዋል። በዚህም የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት ችግር ውስጥ በመጣል የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት፤ የተደረጉ ጥረቶች መላው ህዝብ መከራን አምጦ እንዲወልድ አስገድዶታል።

በዚህም ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ለሀገሪቱ ፖለቲካ ምስቅልቅል ተጠያቂ የሆኑ ከሴራ ፖለቲካ ሊጠሩ ያልቻሉ የፖለቲካ ሊህቃን ፤ በ27 ዓመታት ውስጥ ሀገሪቱን ጥፋት ውስጥ የከተተው የጽንፍ ፖለቲካ አስተሳሰብ ውልዶች፤ የቀደመው ስርዓት ዋነኛ ተዋንያንና ዘመነኞቹ የግጭት አትራፊዎች /የፌስ ቡክና የዩቲውብ አርበኞች/ በስፋት እየተሳተፉ ነው።

በታሪካዊ ጠላቶቻችን፤ አንገት የሚያስቀናን ታሪካዊ ትርክቶቻችን ሰላም በሚነሳቸው ኃይሎች የሚደገፉት እነዚህ ለሀገርና ለህዝብ ፈተና የሆኑ ግለሰቦች እና ቡድኖች፤ ሀገርን የግጭት ማእከል በማድረግ ብሄራዊ ክብራችንን ለማሳነስ በሚደረገው የተቀናጀ ዓለም አቀፍ ጥረት ዋነኛ አቅም በመሆን የባንዳነት ተልእኮ ፈጻሚ ሆነው ተሰልፈዋል።

ይህ እውነታ ላለፉት አራት ዓመታት ሀገርን የህልውና ስጋት ውስጥ እስከመክተት ደርሶ የነበር ቢሆንም፤ መንግስትና ህዝብ ባደረጉት ርብርብና እንደ ሀገር በተከፈለ ከፍ ያለ መስዋእትነት ሊቀለበስ ችሏል። ሀገርም እንደ ሀገር ከህልውና ስጋት ወጥታ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር ወደሚያስችል አዲስ ታሪካዊ ምእራፍ መሸጋገር ችላለች።

ዛሬ ላይ በአማራ ክልል እየታየ ያለው እውነታ የዚህ የጥፋት ትርክት ቀጣይ ምእራፍ ስለመሆኑ በድፍረት ለመናገር ይቻላል። እነዚህ ኃይሎች ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ለሀገሪቱ ፖለቲካ ቀውስ ተጠያቂ የሆኑ ከሴራ ፖለቲካ ሊጠሩ ያልቻሉ የፖለቲካ ሊህቃን፤ በ27 ዓመታት ሀገሪቱን ጥፋት ውስጥ የከተተው የጽንፍ ፖለቲካ አስተሳሰብ ውልዶች፤ የቀደመው ስርአት ዋነኛ ተዋንያንና ዘመነኞቹ የግጭት አትራፊዎች /የፌዝ ቡክና የዩቲውብ አርበኞች/ ናቸው ።

አብዛኞቹ በክልሉ የሌሉ፣ ከክልሉ ውጪና በባህር ማዶ የሚኖሩ፤ በአብዛኛው ስለ ክልሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሕይወት ያላቸው እውቀት /መረጃ በሰሚ ሰሚ የሚደርሳቸው፤ ከተገነቡበት የማንነት ጡቦች አንጻር ነገሮችን በሰከነ አእምሮና በጠራ መንፈስ ለማየት ያልታደሉ፤ ሁሉን ነገር በጠላትነት በመፈረጅ ፈጥነው ለጥፋት የሚንቀሳቀሱ፤ ይህንንም የሊህቅነት ዋነኛ መመዘኛ አድርገው የሚወስዱ ያልነቁ አንቂዎች ነን ባዮች ናቸው።

እስከ ዛሬ ባለው ተጨባጭ እውነታ የአማራ ህዝብ ለሚወዳት ሀገሩ የከፈለውን መስዋእትነት የሚያሳንሱ፤ በዘመናት መለያው የሆነውን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በፍቅር ተቻችሎ የመኖር ማህበራዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ እሴቶቹን የሚያጎድፉ፤ በለውጡ ዋዜማ ብሩህ ነገዎችን ተስፋ አድርጎ የከፈለውን መስዋእትነት ትርጉም አልባ የሚያደርጉ ናቸው።

የአማራ ህዝብ በአሁኑ ወቅት በስሙ የሚነግዱ ፀረ ሰላም ኃይሎች በክልሉ እያካሄዱት ያለው የዘረፋ ተግባርም ሆነ ሰላም የማደፍረስ እንቅስቃሴና ተግባር ህዝቡ ለኢትዮጵያ ሃገረ መንግስት ግንባታ የከፈለውን መስዋዕትነት የሚያሳንስና ለክብሩም የማይመጥን በመሆኑ ሊታገላቸው ይገባል።

አዲስ ዘመን ነሃሴ 4/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *