ከፓርኩ የወጪ ንግድ ከ54 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

– ከ24 ሺህ በላይ ኦፕሬተሮች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል

አዲስ አበባ፡- በ2015 በጀት ዓመት ለውጪ ገበያ ከቀረቡ ምርቶች 54 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ አስታወቀ:: በፓርኩ ከ24 ሺህ በላይ ለሆኑ ኦፕሬተሮች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል::

የኢንዱስትሪ ፓርኩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቲዎስ አሸናፊ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የአጎዋ ጫናን በመቋቋም ከኢንዱስትሪ ፓርኩ ለውጪ ገበያ ከቀረቡ ምርቶች 54 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል::

እንደ አቶ ማቲዎስ ገለጻ፤ በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከሚመረቱ ከጨርቃጨርቅ ምርቶች ስምንት ሚሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፤ ቀሪው ገቢ ከተለያዩ ምርቶች የተገኘ ነው::

የፓርኩ ምርቶች በአፍሪካ ሀገራት፣አውሮፓና በአሜሪካ ለሚገኙ ገበያዎች ላይ ይቀርባሉ ያሉት አቶ ማቲዎስ፤ በተለይም አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ፈረንሳይ ለፓርኩ ምርቶች ዋነኛ መዳረሻ ሀገራት መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ሥራ አስኪያጁ እንዳመለከቱት፤ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ 52 ሼዶች አሉ። 44ቱ ሼዶች በሥራ ላይ ሲሆኑ፤ 22 ኢንቨስተሮች እየሰሩባቸው ይገኛል::

ደረጃቸውን የጠበቁና ለሥራ ዝግጁ የሆኑ ስምንት ሼዶች ነፃ መሆናቸውን የጠቆሙት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤በአጭር ጊዜ ውስጥ ስድስት ሼዶችን በኢንቨስተሮች ለማስያዝ የሚያስችል ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በፓርኩ ከሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ኢንቨስተሮች በዋናነት የቻይና፣ የባንግላዴሽ፣ የሕንድ፣ የሆንግኮንግን፤ የኢንዶኔዢያና የሲሪላንካ ኢንቨስተሮች መሰማራታቸውን አስታውቀው፤ በተጨማሪም ሦስት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በፓርኩ መሰማራታቸውን ጠቁመዋል።

በፓርኩ የሚገኙ ኢንቨስተሮች ከ24 ሺህ በላይ ለሆኑ ኦፕሬተሮች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን አመላክተዋል።

በፓርኩ የሚገኙ ሠራተኞች የክህሎት እና የቴክኖሎጂ ዕውቀት እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል::

በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኙ ሙሉ ሼዶች ወደ ሥራ ከገቡ ለ60 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ይችላል:: በዚህም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ወደ ውጭ በመላክ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማሳደግ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ፓርኩ ምርታማነቱን በማሳደግና የአጎዋ ማዕቀብን ጫና በመቋቋም የበለጠ ውጤት ለማምጣት እየሰራ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ላይ የአጎዋ ዕድል እገዳ ከመጣሉ በፊት ከፓርኩ ምርቶች ከ80 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ይገኝ እንደነበር አስታውቀው፤ ጫናውን ለመቋቋም ወደ አውሮፓና የአፍሪካ ገበያዎች መዳረሻዎችን የማስፋት ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ የአጎዋ ማዕቀብ የሚነሳበት ሁኔታ ቢፈጠር እንኳን የምርት መዳረሻ ሀገራትን ወደ አፍሪካ ለማስፋት የታሰበ መሆኑን ጠቁመው፤ የምርት ጥራትን በማሳደግ ለአውሮፓ ሀገራት ገበያ ማቅረብ የሚያስችል ሥራ በመሰራት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 3/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *