ኢትዮጵያ በታሪኳ የተለያዩ ወራሪ ሀይሎች ከሩቅም ከቅርብም በመሆን ቀኝ ሊገዟት፤ ድንበሯን ሊገፉና ድንበር ሊያሰምሩ፤ የተፈጥሮ ጸጋዋን ሊበዘብዙ በብዙ ደክመዋል። እነዚህ ሙከራዎች በተለያዩ ጊዜያትና የመሪዎች ለውጥ ይኑርባቸው እንጂ ሁሉም ማለት በምንችልበት ደረጃ የሀገሪቷ መሪዎች ለወራሪዎች ያላቸው አቋም አንድ ነበረ። “የተረከብናት ሀገር ነጻና የማትደፈር ነች፤ የምናስረክባትም በዛው መልኩ ነው “ የሚል ቀጥተኛ አቋም ነበራቸው።
በኢትዮጵያ ታሪክ ሀገርን ከነክብሯ ለማቆየት የህይወት መስዋዕትነት ከፍሎና ወራሪን ደምስሶ ለትውልድ ማስተላለፍ ከጥንት የነበረ አሁንም የቀጠለ የሀገር ወዳዶች ልምድ ነው። መሪ ሀገራችሁን ከመጣባት ክፉ ወራሪ ሀይል ልታደጋት እየሄድኩ ነውና ተከተሉኝ ሲል ለህይወታቸው ሳይሳሱ፤ ነገ ለልጆቻቸው የሚያወርሷትን ሀገር ከአደጋ የፀዳች ለማድረግ ሁሉም ሳያንገራግር “ሆ” ብሎ ወጥቶ፤ በየጦር ሜዳው ተነግሮ የማያልቅ ጀብዱ ሲሰራ ኖሯል። ኢትዮጵያም በዚህ መልኩ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዛሬ ደርሳለች።
በትውልዱ በሚገባው ልክ እውቅናና ትኩረት ካላገኘው የድል ታሪክ መካከል የኢትዮ ሱማሌን ጦርነት ወይም የካራማራውን ጦርነት ማንሳት እንችላለን። በካራማራው ጦርነት በዋርዜ፤ በሺላቮ፤ ቀብሪደሃር፤ በጅግጅጋ እንዲሁም በሌሎች የምስራቅ ኢትዮጵያ ክፍሎች መሽጎ የነበረውን የሱማሌ ወራሪ ሀይል የኢትዮጵያ ውድ ልጆች በህብረት አሳደው ከኢትዮጵያ ድንበር በማስወጣት የካቲት 26 ቀን 1969 በካራማራ ላይ ጀግኖች ሰንደቅ አላማቸውን የሰቀሉበት የድል ታሪክ ነው።
በወቅቱ ከጦርነቱ በህይወት ተርፈው የኢትዮጵያን ባንዲራ በኩራት እንዲውለበለብ ከተከሉት የሰራዊት አባላት መካከል መቶ አለቃ ታምራት ሞላ አንዱ ናቸውⵆ “ቅንጡ ኑሮ ያለ ሃገር ምንድነው? የተመቸ ኑሮስ ያለክብር ምን ያደርጋል? በማለት ከሚጠይቁትና በሀገራቸው ክብር ቀልድ ከማያውቁት የጦር ሜዳ ጀግና እና በአሁኑ ሰዓት በወላይታ ዞን የኢትዮጵያ የቀድሞ ሰራዊት ፕሬዚዳንት ከሆኑት መቶ አለቃ ታምራት ሞላ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አዘጋጅተን አቅርበነዋል።
ትውልድና እድገት
መቶ አለቃ ታምራት ሞላ ትውልድና እድገታቸው በወላይታ ዞን ነው። እስከ ስድስተኛ ክፍል በዚያው ወላይታ ዞን ሊጋባ በየነ ሰብስብ አንደኛ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆዩ። በ1964 ዓ.ም ግን ኑሮ እጅ እንዲሰጡ አደረጋቸው፤ ትምህርታቸውን መቀጠል ባለመቻላቸው የቀን ስራ እየሰሩ ራሳቸውን ለመደጎም በማሰብ ወላይታን ለቀው ወደ አባድር የእርሻ ልማት አራተኛ ካምፕ በመሄድ ተቀጥረው መስራት ጀመሩ።
በዚሁ የእርሻ ልማት ውስጥ በመስራት ላይ ሳሉ የኢትዮ-ሶማሌ ጦርነት በመታወጁ በቀረበው የሀገራዊ ጥሪ መሰረት በጦርነቱ ለሀገራቸው ለመፋለም ህዳር 21 ቀን 1968 ዓ.ም ተመዝግበው የነበልባል ክፍለጦርን ተቀላቀሉ። ስልጠናቸውን ጨርሰው ወደ ጦር ግንባር ለመሄድ ሲዘጋጁ በወቅቱ አገሪቱን የሚያስተዳድረው ደርግ ሊቀመንበር እንዲሁም የአገሪቱ መሪ የነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያም የነበልባል አርማ ትከሻቸው ላይ ካኖሩላቸው በኋላ ‘እንደዚህ አይነት ወታደር ለማፍራት ብዙ መስራት ይጠበቅብናል’ በማለት ንግግር ማድረጋቸውን ያስታውሳሉ መቶ አለቃ። ከሰራዊቱ መሃል ተመርጠውም ደብረዘይት ወደ ነበረው ለምለም ጣቢያ ለሰባተኛ ጅቦ እና ለስድስተኛ ነበልባል ክፍለ ጦር አሰልጣኝ ተደርገው ተመረጡ።
በወቅቱ በነበሩት የጦር አመራሮች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ስለነበራቸው የክፍለጦሩ ድርጅት መምሪያ ተጠሪ እንዲሆኑ ፈተና እንዲፈተኑ እድል ተሰጣቸው። መቶ አለቃ ታምራትም ከ27 ሰዎች አንደኛ በመሆን አልፈው የስድስተኛ ነበልባል ክፍለ ጦር ድርጅት መምሪያ ተጠሪ ሆኑ።
የኢትዮ-ሱማሌ ጦርነት
በ1969 ዓ.ም ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ኮሎኔል መንግስቱ ሀይለ ማሪያም፤ ‘እናት ሀገሬ ተወራለች፤ ባንዲራ ተረግጧል፤ ድንበር ተደፍሯል፤ ተነሱ ታጠቁ ዝመቱ እናት ሀገራችሁን ከአደጋ አድኑ’ በማለት ሚያዚያ 4 ቀን 1969 ዓ.ም ባወጁት አዋጅ መሰረት፤ 300 ሺህ ሚሊሻ ታጠቅ የጦር ሰፈር ገብቶ ስልጠና ከወሰደ በኋላ ሰኔ 10 ቀን ስልጠናውን በመጨረስ ተመርቆ ወደ ግንባር ዘመተ።
በወቅቱ የኢትዮጵያ ሰራዊት ከበትር ያልበለጠ መሳሪያ ታጥቆ፤ ከውጭ ሀይሎች በሚያገኘው ድጋፍ እስከ አፍንጫው የታጠቀውን የሶማሊያን ጦር ድል ማድረግ ችሏል። በኢትዮጵያ በኩል ወደ ጦር ሜዳው ከገቡት 300 ሺህ ሚሊሻዎች መካከል 76 ሺህ የሚሆኑት በዚህ ጦርነት መስዋዕት ሆነዋል።
በጦርነቱ ወቅት በርካታ ጀብድ የሰሩ የሰራዊቱ አባላት መኖራቸውን የሚጠቅሱት መቶ አለቃ ታምራት፤ ጀብዱ ከሰሩት የሰራዊት አባላት መካከል የአየር ሀይል አባል የነበረው በዛብህ ጴጥሮስ የተማረከ በመምሰል ወደ ሶማሊያ አየር ክልል በመግባት የክብሪት ፋብሪካቸውን በማቃጠል ከጥቅም ውጪ በማድረግ ትልቅ ጀብዱ ፈፅሞ እንደነበር ይተርካሉ።
የኢትዮ-ሶማሌ ጦርነት ሲነሳ ጀግናው ጀብደኛ አሊ በርኬ ሁሌ ስሙ አብሮ መነሳቱ የግድ ነው። ታዲያ መቶ አለቃ ታምራት ሞላ እና ጀግናው አሊ በርኬ ምንም እንኳን በጦር ሜዳ በአካል ባይተዋወቁም ለአንድ አላማ በተመሳሳይ የውጊያ ሜዳ ላይ ለሀገራቸው ለመፋለም ችለዋል። ከዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ የቀድሞ ሰራዊት ድጋፍና ልማት ማህበር ሲቋቋም የቀድሞ ሰራዊት አባላት ዳግም ለመሰብሰብ በመብቃታቸው በአካል ለመገናኘት ችለዋል።
“የጦር ሰራዊት ምንም እንኳን በጦር ሜዳ ላይ እየተዋጋ በአካል ባይገናኝም አይተዋወቅም አይባልም፤ በአራቱም ማዕዘን ለሀገሩ ሲዋጋ የነበረ ሰራዊት አላማው አንድ በመሆኑ በአካል ባይተዋወቅም የቆመለት አላማ እንዲተዋወቅ ያደርገዋል” ይላሉ መቶ አለቃ ታምራት።
በወቅቱ ሰራዊት ተመልምሎ ሲመደብ ከአንድ አካባቢ የሚመጡ አባላት በአንድ ቦታ እንደማይመደብ የሚናገሩት መቶ አለቃ ታምራት፤ ከተለያየ ቦታ የተሰባሰቡ አባላት ስለሚገናኙ አንዱ ከአንዱ ቋንቋ እየተማረ ልምድ እየተለዋወጠ በፍቅር ለአንድ አላማ ይዋጋ እንደነበር ያስታውሳሉ።
‘ናዝሬት ምሳ በልቼ አዲስ አበባ እራት እበላለው’ ያለውን የሶማሊያን ጦር ባለአምስት ኮከብ ዘመቻ፤ የዚያድባሬን ሰራዊት ጨርቁን አስጥሎ ሞቃዲሾ ያስገባው የኢትዮጵያ ሰራዊት፤ በምስራቅ የተገኘ ድል በሰሜን ይደገማል በማለት ወደ ሰሜን ዘመተ።
‘ተነሳ ተራመድ ክንድህን አበርታ
ለሀገር ብልፅግና ለወገን አለኝታ።’
‘እኔ ምኞቴ እኔ በህይወቴ
ከሁሉም በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ።’ እያለ የዘመተው ሚሊሻ ሰራዊት ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ ኢትዮጵያን አድኖ ለዚህ ትውልድ አስረክቧል። በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ኢትዮጵያ ተሸንፋ ቢሆን ኖሮ፤ አሁን ያለንባትን ሀገር አናገኛትም ነበር፤ ለትውልድም በኩራት የምናወርሰው ሀገር አይኖረንም ነበር ሲሉ በኩራት ይናገራሉ።
መቶ አለቃ ታምራት ወደ ሰሜን የጦር ግንባር ጉዞ ያደረጉት በወቀቱ የክፈለ ጦሩን ንብረት የመቆጣጠር ስራ እየሰሩ ነበር። መቀሌ ላይ የተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በኋላ 1970 ዓ.ም ሃምሌ አራት ቀን በትግራይና በኤርትራ መካከል ባለችው ጋውርሳርናይ በተባለች ቦታ የጦር ቀዳሚ መምሪያው ስለተመታ ለተወሰነ ጊዜ እዚያው ለመቆየት ተገደዱ።
ከቆይታ በኋላ ወደ ፆረና፤ ከፆረና ወደ መሆኒ በመጓዝ በ1970 ዓ.ም ሃምሌ መጨረሻ ቀማሪ ደረሱ። ከቀማሪ በመነሳት ቀይኩር አድ ሀበሻ የሚባል ቦታ በማቋረጥ አስመራ ገቡ። በአስመራ ቆይታቸው ግምጃ ቤት ተሰጥቷቸው የንብረት ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል። በወቅቱ ወደ ናቅፋ ዘምቶ የነበረው ክፍለ ጦር ጉዳት ደረሰበት። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ክፍለጦሩ በድጋሚ ሲቋቋም ለስድስተኛ ነበልባል ክፍለጦር ተወካይ እንደሆኑ አስመራ ቆዩ። በዛም በቀይ ባህር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ መከታተላቸውን ይናገራሉⵆ
ህዳር አንድ ቀን 1982 ዓ.ም በደቀመሀሪ ግንባር ቱርክ ምሽግ ላይ በተደረገ ውጊያ፤ በአንድ የጦር ሜዳ ውሎ የጀግና ማዕረግና የሜዳሊያ ሽልማት ከኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያም እጅ ለማግኘት ቻሉ። ይህንን ማዕረግና የሜዳሊያ ሽልማት እንዲያገኙ ያስቻላቸው፤ የወታደር ትጥቅ፣ ስንቅ እና ጥይት ጭነው ወደ ጦር ሜዳ በተጓዙበት ወቅት ጦርነቱ ተፋፍሞ ነበርና የ112ኛ ብርጌድ አዛዥ የነበረው ሺህ አለቃ ኃይሌ ገብረመድህን ‘የወታደር፣ የሴት እና የቄስ እንግዳ የለምና ወደ ጦር ሜዳ ግባ’ በማለታቸው መቶ አለቃ ታምራት ወደ ጦር ሜዳው ተቀላቅለው ሁለት መሳሪያ ከጠላት እጅ በመማረክ ለመውሰድ በመቻላቸው ነበር።
ከአስመራ መልስ
የመቶ አለቃ ታምራት፤ ሚያዚያ 8 ቀን 1983 ዓ.ም የቤተሰብ ችግር ስላጋጠማቸው ፍቃድ በመውሰድ ወደ ወላይታ ሶደ ተመለሱ። ወደ አስመራ ሳይመለሱ በወቅቱ የነበረው መንግስት ከስልጣን መውረዱን ተከትሎ ሰራዊቱ በመበተኑ ወላይታ ለመቆየት ተገደዱ።
ትውልዱ ስለ ካራማራው ጦርነት ምን ያህል ያውቃል?
ከአርባ ዓመት ወዲህ ያለው ትውልድ የካራማራውን ጦርነት ቀርቶ ሀገር ምን እንደሆነች ራሱ በአግባቡ የሚያውቅ መሆኑ ያጠራጥረኛል የሚሉት መቶ አለቃ ታምራት፤ የባንዲራ ምንነት የገባው ትውልድ እያጣን ነው፤ ዳር ድንበር ሲባል በዙሪያው ያለው አካባቢ ብቻ የሚመስለው ትውልድ እያፈራን ነው። ለዚህ ትልቁ ምክንያት ሀገሪቱ በጎሳና በዘር መከፋፈሏ ነው። ሰው ከቦታ ቦታ ካልተንቀሳቀሰና በሚመቸው ቦታ ካልኖረ ሁሉም በአካባቢው የሚገደብ ከሆነ፤ አንዱ ጎሳ ከሌላ ጎሳ ተጋብቶ መኖር ካልቻለ ትውልዱ የሚኖርበትን አካባቢ ብቻ የሚያውቅ ውስን ይሆናል በማለት ስጋታቸውን ይገልፃሉ።
“ቆዳ ዳር ዳሩ በአይጥ ሲበላ የቀረው የመሃሉ ክፍል ዳር ይሆናል። ሀገር ዳር ዳሩን በጦርነት ስትታመስ፤ እዚያ ነው እንጂ እኛ ጋር ሰላም ነው የሚል ትውልድ እየበረከተ ነው። አንድ ሰው እንቅፋት እግሩን ቢመታው ራሱን መታመሙ የማይቀር ነው። ይህንን እውነት ትውልዱ እንዲያውቅ ማድረግ ይኖርብናል” ይላሉⵆ
ትውልዱ ያላየውን የካራማራ ጦርነት ታሪክ ሊያውቅ ይቅርና አሁን የሚኖርባትን ኢትዮጵያን በአግባቡ አያውቃትም። ለዚህ መፍትሄው ትውልዱ ታሪኩን በሚገባ የሚማርበትን መንገድ ማመቻቸት ነው። የትምህርት ስርዓታችን ዜጋው ስለሀገሩ ጠንቅቆ የሚያውቅበትን የማስተማር ስርዓት ሊከተል ይገባዋል። ማህበረሰቡም ልጆቹ ስለሀገራቸው እንዲያውቁ ማድረግ አለበት። የተለያዩ የሚዲያ ተቋማትም ትውልዱ ስለሀገር ፍቅር እንዲያውቅ እና ሀገሩን የሚወድ እንዲሆን ዘወትር በትጋት መስራት ይኖርባቸዋል ይላሉ።
“እድሜዬ ሄዷል አሁን የምወዳትን ሀገሬን ለተረካቢው ትውልድ በማስረከብ ላይ ነኝ። የሚረከበው ትውልድ ሀገራቸው እንዴት በአያቶቻቸው ደም እና አጥንት ያለ ወራሪ እንደቆየላቸው መረዳት አለባቸው። ታሪክን የሚያራክሱ አሉ፤ ነገር ግን ይህ ታሪክ በህይወት የተለወጠ በደም የተጻፈ ነው። ታሪክ በሸቀጥ አይቀየርም፤ ህይወት ተከፍሎበታል። ይሄንን ሚረዳ ትውልድ ለኢትዮጵያ ያስፈልጋታል። አትዮጲያዊነት የሚባለው ስሜት ከእራስ ወዳድነት ጋር አብሮ አይሄድም።” ይላሉ።
የኢትዮጵያ የቀድሞ ሰራዊት አባላት
በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ የቀድሞ ሰራዊት አባላትን በሚገባቸው ቦታ አስቀምጠናቸው ቢሆን፤ ለሰላም ማስከበሩ አስተማሪና መሪ በሆኑ ነበር ሲሉ ቁጭታቸውን የሚገልፁት መቶ አለቃ ታምራት፤ የቀድሞ ሰራዊት አባላት ጉልበታቸው ተራራ ባይወጣ፤ እውቀቱ ከጉልበት ባሻገር ያለውን ተዋግቶ ይመልሳል በማለት ያስረዳሉ።
መቶ አለቃ ታምራት በወላይታ የሚገኙ አቅማቸው የደከሙ የቀድሞ ሰራዊት አባላት እና ቤተሰቦቻቸውን ለሀገር ትልቅ ዋጋ ቢከፍሉም በኑሮዋቸው ድጎማ የሚያስፈልጋቸውን ከተለያዩ አካላት እና ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን የዓመት በዓል መዋያ የሚሆናቸውን የገንዘብ ድጋፍ ያሰባስባሉ።
ሀገርና ባንዲራ ለመቶ አለቃ ታምራት
መቶ አለቃ ታምራት ሀገርን ሲገልጿት፤ “በህይወት የምኖርባት ስሞት የምቀበርባት፤ የማልደራደርባትና የምሞትላት እናቴ ናት” ይላሉ። ከዚህ በፊት የነበሩ ነገስታት የሞቱላት ወደፊትም ትውልዱ የማይደራደርባትና ለማንም አሳልፎ የማይሰጣት ሀገር መሆኗንም ያስረዳሉ።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የቀድሞ ሰራዊት አባላት የነበሩ 825 አባላትን እየመሩ ሲሆን ጥቅምት 4 ቀን 2015 ዓ.ም ወደ ጦላይ የጦር ማሰልጠኛ እንዲሄዱ በማድረግ በማሰልጠኛው ውስጥ ላለው ሰራዊት ስልጠና እንዲሰጡ አድርገዋል። በወቅቱ ከማሰልጠን ባሻገር የቀድሞ ሰራዊት አባላቱን ወደ ጦር ሜዳ በመላክ ለሀገር በተደረገ ውጊያ የቆሰለው ቆስሎ የሞተው ሞቶ ድጋሚ ታሪክ ሰርተው በክብር ተመልሰዋል።
መንግስትም ላደረጉት ተጋድሎ የጀግና ሽኝት አድርጎላቸው ወደ መኖሪያ ቦታቸው ሲመለሱ ክብራቸው እንዲጠበቅ ጡረታቸው እንዲከበርላቸው እንዲሁም የቤት መስሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው ሲል ለዞኑ መልዕክት አስተላልፏል። መቶ አለቃ ታምራትም 6000 የቀድሞ ሰራዊት አባላትን በፕሬዚዳንትነት እየመሩ ሲሆን፤ በውጊያ ተሳትፈው ሽኝት የተደረገላቸውን አባላት ሞቅ ባለ የአቀባበል ስነ ስርዓት ለማስተናገድ ሽርጉድ በማለት ላይ ይገኛሉ።
የመቶ አለቃ ታምራት አደራ፡- ለልጆቻቸው
መቶ አለቃ ታምራት በአሁን ሰዓት የሚተዳደሩት በግብርና ስራ ሲሆኑ የ15 ልጆች አባትም ናቸው። ከልጆቻቸው መካከልም የእርሳቸውን ፈለግ በመከተል የሀገር ክብርን ለማስጠበቅ ወደ ውትድርናው ዓለም የገባ ልጅ አላቸው። መቶ አለቃ ታምራት በልጃቸው የስራ መስክ እጅጉን ደስተኛ ናቸው።
ከመቶ አለቃ ታምራት ልጃቸውን ዘወትር እንዲህ ሲሉ ይመክሩታል፤ “ልጄ ወታደር በመሆንህ እድለኛ ነህ፤ እናት ሃገርህን ለመጠበቅ የታደልክ ነክ። ጦር ሜዳ የምትሄደው ሃገርህን ለመጠበቅ ነው። የአቅምህን ያህል ለአገርህ አድርግ፤ የበላይ አለቆችህን አክብር፤ የበታቾችህን ሳትንቅ አስተባብር። ከአቅምህ በላይ ችግር ከገጠመክ እጅህን ለጠላት እንዳትሰጥ፤ እንደ አፄ ቴዎድሮስ ሁን።”
እጅ መስጠት ለጠላት ባሪያ መሆን ማለት ነው የሚሉት መቶ አለቃ፤ በርካታ የኢትዮጵያ ወታደሮች በተደረጉ የተለያዩ ጦርነቶች እጅ አንሰጥም ብለው መስዋዕት ሆነዋል።
ማየት የሚፈልጓት ኢትዮጵያ
ሀገራቸው መከበሪያቸው መሆኗን በኩራት የሚናገሩት መቶ አለቃ፤ ዜጎቿ በህብረት እና በመተባበር የሚኖሩባት ጠንካራ የሆነ አንድነት የተገነባባት ኢትዮጵያን ማየት እንደሚናፍቁ ይናገራሉ። ሙስና የሌለባት በተለያዩ የስልጣን ደረጃዎች ላይ ያሉ ዜጎች በታማኝነት ሀገራቸውን የሚያገለግሉባት፤ በዘር፣ በሃይማኖት እና በብሄር ያልተከፋፈለች አንድ የሆነች እንዲሁም ታታሪ ሰራተኞች ያሉባት ኢትዮጵያን ማየት የዘወትር ምኞትና ተስፋቸው ነው።
በለጥሻቸው ልዑልሰገድ እና መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ነሃሴ 3/2015