የአማራ ሕዝብ ከግጭት ነጋዴዎች እራሱን ሊጠብቅ ይገባል!

 የአንድን አገር ህልውና ፣ የህዝቦችን ሰላም እና መረጋጋት ዘላቂ ለማድረግ በአንድም ይሁን በሌላ ሕግና ሥርዓት የሚከበርበት አገራዊ አውድ መፍጠር ወሳኝ ነው። ይህንንም እውን ለማድረግ አገራት የተለያዩ የጸጥታ ተቋማትን ጨምሮ ጠንካራ የመከላከያ ሠራዊት በመገንባት ላይ ትኩረት ሰጥተው ይሰራሉ። በዚህም የሚያስመዘግቡት ስኬት የአገራዊ ህልውናቸው መተማመኛቸው መሠረት ነው።

ዓለም አቀፍ እውነታው ውስብስብ በሆኑ ፍላጎቶች በተሞሉበት ፣ እነዚህን ፍላጎቶች ለማሟላት አገራት ከመኖር ወደ አለመኖር ፤ ሕዝቦች ከሰላማዊ ሕይወታቸው በግጭት ነጋዴ ግለሰቦች፣ ቡድኖች ተፈናቅለው ለስደት ፣ ለከፋ መከራና ስቃይ በሚዳረጉበት ሁኔታ ውስጥ አገራዊ ሕግና ሥርዓት ማስከበር የሚያስችል ጠንካራ የጸጥታ ተቋማትና የመከላከያ ኃይል የመገንባቱ እውነታ ወሳኝ ነው።

ይህንን እውነታ ታሳቢ በማድረግ በአገራችን በጸጥታ እና በመከላከያ ተቋማት ላይ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች ተሰርተዋል፣ በዚህም ዛሬ ላይ ከትናንት በተሻለ ሁኔታ ሕግና ሥርዓትን ማስከበር የሚችል አቅም የተላበሰ የጸጥታ እና የመከላከያ ኃይል መገንባት ተችሏል። ይህ ኃይል በተግባር በተፈተኑ ግዳጆች አገርን ከህልውና ስጋት ፣ ሕዝብን ከመበተን አደጋ መታደግ ችሏል።

ይህ ኃይል በተለይም አገር እንደ አገር ከመጣችበት የግጭት አዙሪት ተመልሳ እንዳትገባ ፤ ችግሮች በውይይትና በድርድር በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን መንገድ ቅድሚያ በመስጠት ተንቀሳቅሷል ፤ የኃይል ርምጃ በራሱ ዘላቂ የችግር መፍቻ አማራጭ እንዳልሆነ በተጨባጭ አሳይቷል። እየተተኮሰበት መልሶ ላለመተኮስ እረጅም እርቀት በመጓዝ አላስፈላጊ ዋጋ ከፍሏል።

ያለበትን የአገር ህልውና፣ የህዝቦችን ሰላም እና መረጋጋት የመጠበቅ ሕገ- መንግሥታዊ ኃላፊነት ለመወጣት ፤ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ፤ በግጭት አካባቢ ከሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ፤ ከአገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር ተከታታይ ውይይቶችን አድርጓል። በየትኛውም ሁኔታ ህዝብ ከግጭት አትራፊ ሊሆን እንደማይችል ለማስገንዘብ ሰፊ ሥራዎችን ሰርቷል ።

ከቀደሙት ወቅቶች በመማር ህዝባዊነቱን ከዛም ባለፈ ሃይል አምላኪ አለመሆንን በአደባባይ አሳይቷል። በተለይም በተለያዩ ምክንያቶች ፤ በግልጽም ይሁን በስውር የአገሪቱን ሰላም እና መረጋጋት ችግር ውስጥ በመክተት ፤ የችግሩ አትራፊ መሆን የሚፈልጉ በአገር ውስጥ ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳሱ የግጭት ነጋዴዎች ለዓላማቸው ቀዳዳ እንዳያገኙ ስለ ሰላም ሀዋሪያ ሆኖ ተንቀሳቅሷል።

በዚህም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ነፍጥ አንስተው በነጻ አውጪ ስም ይንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት ተመልሰው ለአገራዊ ሰላምና መረጋጋት አቅም የሆኑበት እድል እንዲፈጠር አስችሏል። በዚህም የአካባቢው ነዋሪዎች አንጻራዊ ሰላም አግኝተው ወደ ልማት እንዲመለሱ የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር ችሏል። ከግጭት ለማትረፍ ሌት ተቀን የሚተጉ ኃይሎች ህልምም ከንቱ እንዲሆን አድርጓል።

ይህ ችግሮችን በሰላም እና በውይይት ለመፍታት ቅድሚያ የሚሰጠው የአገሪቱ የጸጥታ እና መከላከያ ኃይል በአማራ ክልል የተፈጠሩ አለመግባባቶች ወደ ግጭት እንዳያመሩ ፤ አሉ የሚባሉ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ በውይይት እንዲፈቱ ከመንግሥት ጋር በመሆን ያሉትን አማራጮች ሁሉ ተጠቅሟል። ከህዝቡ ፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር መክሯል። ከትናንት ተጨባጭ ተሞክሮ በመነሳትም የክልሉ ህዝብ ከየትኛውም ግጭት አትራፊ ሊሆን እንደማይችል ለማስገንዘብ ጥሯል።

ለክልሉ ህዝብ የሚያስፈልገው በቀደመው ጦርነት የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ፤ የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን መልሶ መገንባት ፤ የተሰበሩ ልቦችን መጠገን እንደሆነ አምኖ በማሳመን ባለው አቅም በመንቀሳቀስ ለአማራ ህዝብ ያለውን በጎ ሕሊና በተጨባጭ አሳይቷል። በዚህም ከህዝቡ ያገኘው ከበሬታ ከፍ ያለ እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው።

ዛሬም በክልሉ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ሕገመንግሥታዊ ሃላፊነቱን ከመወጣት ባለፈ ለአማራ ህዝብ ካለው በጎ ህሊና የሚመነጭ ፤ አገርን በተለይም የክልሉ ህዝብ ከግጭት ነጋዴዎች በመታደግ ፤ በልማት ነጋዴዎቹን ብሩህ ለማድረግ የጀመረውን የለውጥ ጎዳና ለማስቀጠል እና ስኬታማ እንዲሆን ለማስቻል ነው።

ይህንን ተጨባጭ እውነታ ታሳቢ በማድረግ ህዝቡ ከግጭት ነጋዴዎች ተራ ፕሮፓጋንዳ እንዲሁም ከግጭት አባባሽ የፈጠራና የውሸት ትርክቶቻቸው እራሱን በመጠበቅ ፤ የጸጥታ እና የመከላከካያ ኃይሉ ለሚያደርገው ሕግና ሥርዓት የማስከበር ግዳጅ አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ ፤ በዚህም ለራሱ ሰላም እና ደህንነት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ሊያሳይ ይገባል።

አዲስ ዘመን ነሃሴ 3/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *