ለአንድ ሀገር ህልውና ወሳኝ ከሆኑ ተቋማት መካከል አንዱ የመከላከያ ሰራዊት ነው። ይህንን ዓለም አቀፋዊ እውነታ ታሳቢ በማድረግም መንግስት ላለፉት አምስት ዓመታት የሀገሪቱን የመከላከያ ሰራዊት በሁለንተናዊ መልኩ ለተጣለበት ሀገራዊና ህዝባዊ ኃላፊነት ብቁ ለማድረግ ሰፊ የሪፎርም ስራዎች ሲሰራ ቆይቷል፤ በቀጣይም ሊሰራቸው የሚገቡ ብዙ ስራዎች እንደሚኖሩ ይታመናል።
የሰራዊቱን ሀገራዊ ተልእኮ በማያሻማ መንገድ ግልጽ ከማድረግ ጀምሮ፤ ተልእኮውን የማስፈጸም አቅሙን በመገንባት ላይ የተመሰረተው የመንግስት ሪፎርም፤ መከላካያ ሰራዊቱ በአንድ ወቅት ተፈጥሮ ሊከስም የሚችል የየትኛውም ቡድን/የፖለቲካ ድርጅት አጀንዳ አስፈጻሚ እንዳይሆን፤ ከዛ ይልቅ ትውልድ ተሻጋሪ ተቋም እንዲሆን ትኩረት የሰጠ ነው።
መከላከያ ሰራዊቱ ምንም አይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ ተሸካሚ እንዳይሆን፤ ከዛ ይልቅ ለሀገር ህልውና እና ሉአላዊነት፤ ለህዝቦች ሰላም እና ደህንነት መተማመኛ የሚሆን ሁለንተናዊ ቁመና በመፍጠር፤ ለዘመናት በብዙ መስዋእትነት የተጠበቀውን የሀገሪቱን ሉአላዊነት እና የሕዝቦችን ነጻነት በአስተማማኝ መሰረት ላይ ማዋቀር ነው።
ከትናንት ሀገራዊ ተሞክሯችን በመነሳት ተግባራዊ እየሆነ ያለው የመከላከያ ሪፎርም፣ አንድም አሁን ባለው ዓለም የሀገር ሉአላዊነትን ሆነ የህዝቦችን ነጻነት አስጠብቆ ለመጭዎቹ ትውልዶች ለማስተላለፍ፣ ከዛም ጎን ለጎን ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የጀመርነው ሀገራዊ መነቃቃት ስኬታማ ሆኖ ወደ ተመኘነው ብልጽግና ለመድረስ ወሳኝ ነው።
እንደ ሀገር በጉዟችን ጥላ ሆነው የሚከተሉን ታሪካዊ ጠላቶቻችን በየትኛውም ወቅት፣ በየትኛውም መልኩ ሊሰነዘሩ የሚችሉትን ጥቃት ሆነ፤ የሚደግሷቸውን የጥፋት ድግሶችን አስተማማኝ በሆነ መንገድ ለመቀልበስ በመከላከያው ላይ የተጀመረው ሪፎርም ከፍ ያለ ሀገራዊ አቅም ግንባታ አካል እንደሆነ ይታመናል። በዚህም ባለፉት አራት ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶች ተጨባጭ ማሳያ ናቸው።
ሀገር በውስጥ እና በውጪ ኃይሎች የህልውና ስጋት ውስጥ በነበረችበት፤ መላው ሕዝባችን እንደ ህዝብ ከፍ ባለ የመበተን ስጋትና ሟርት ውስጥ በነበረበት በነዚህ ዓመታት፤ ሰራዊቱ እራሱን በጦርነት አውድማ እያበቃ በብዙ መስዋእትነት፣ ሀገርን ከህልውና ስጋት፤ ህዝባችንን ከመበተን ሟርት በመታደግ ደማቅ ታሪክ ፅፏል፡፡ የህዝብ ባለውለታ መሆን ችሏል።
ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያ ፍቅር ውጪ ሊገዛው የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ በተጨባጭ ስለ ሀገሩ በሚከፍለው መስዋእትነት በየእለቱ እያስመሰከረ ያለው ይህ ሰራዊት፤ ዛሬም በሚወስዳቸው ሀገርና ህዝብን ከጥፋት የመታደግ ግዳጆች በተጨባጭ የሚታየውም ይኸው ነው፤ ለሀገርና ህዝባዊ ተልእኮው ያለውን ታማኝነትና ቁርጠኝነት የሚያስመሰክር ነው።
ሰራዊቱ በየትኛውም ሁኔታ፤ የግዳጅ ውስብስብነት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን በላቀ ወታደራዊ ሙያና የመንፈስ ፅናት መሻገር እንደሚችል ባለፉት አራት ዓመታት ያስመዘገባቸው ስኬቶች የአደባባይ ሚስጥሮች ናቸው። ስኬቶቹ ለመላው ህዝባችን ያስገኙት እፎይታ ሆነ፤ ለወዳጅም ለጠላቶቻችንም ያስተላለፉት መልእክት ትርጉሙ ከፍ ያለ ነው።
ይህ ሰራዊት ዛሬም ቢሆን ከተላበሰው ህዝባዊነት የተነሳ በተሰማራባቸው የግዳጅ ወረዳዎች የሀገርን ሰላምና የህዝቦችን ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማስከበር ስለመቻሉ፤ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ብቃት ስለመላበሱ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። ይህንን በተጨባጭ በቅርቡ የምናየው፤ በማየት የምናረጋግጠው ይሆናል።
በርግጥ ከሰራዊቱ ህዝባዊነት በሚመነጭ ሆደ ሰፊነት ብዙ ያልተገቡ ዋጋዎችን ለመክፈል ቢገደድም፤ በዚህም አንዳንዶች አሳንሰው እንዲያዩት እና ” እንሞካከር” ወደ ሚል ያልተገባ ድፍረት ቢወስዳቸውም፤ ለሁሉም ነገር ጅማሬና ፍጻሜ ልክ እንዳለው ሁሉ አሁን ያለው የሰራዊቱ የግዳጅ እንቅስቃሴና አፈፃፀም ለነገሮች ፍጻሜ በማበጀት ከዚህ በፊትም በተግባር የተፈተነና ውጤታማ የሆነ ብቃቱን የሚያስመሰክርበት እንደሆነ ለማንም ግልፅ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ነሐሴ 2 ቀን 2015 ዓ.ም