የዋሊያዎቹ የወዳጅነት ጨዋታዎች ሚና

የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማድረግ ወደ ሰሜን አሜሪካ ያቀናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) የአስር ቀናት ቆይታውን ነገ የሚያጠናቅቅ ይሆናል። ብሔራዊ ቡድኖች እና ክለቦች መሰል የወዳጅነትና የአቋም መለያ ጨዋታዎችን የሚያደርጉ ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን እምብዛም ያልተለመደ ጉዳይ ነው። ኑሯቸውን በአሜሪካ ባደረጉ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም አጋር ተቋማት ከተሰናዳው ከዚህ የወዳጅነት ጨዋታ መርሃ ግብርም ቡድኑ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚያገኝ አያጠያይቅም።

ብሔራዊ ቡድኖች ከሀገራቸው ወጥተው ከአቻዎቻቸው ጋር መጫወታቸው የውድድርና የፉክክር ልምድን እንዲሁም በራስ መተማመንን እንዲያጎለብቱ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አብዛኛውን ጊዜ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሲኖሩበት በፊፋ እና ካፍ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ከማድረግ አኳያ መቸገሩ ተደጋግሞ የተነገረ ጉዳይ ነው። ከመደበኛ ውድድሮች በተጨማሪ በርካታ የመዘጋጃ ጨዋታዎችን የሚያደርግ ብሔራዊ ቡድን ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ደረጃው እንዲያድግና ተፎካካሪ እንዲሆንም ያስችለዋል።

ለማሳያ ያህል ዋሊያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ በነበራቸው ተሳትፎ በጊዜ ለመሰናበታቸው የሚነሱ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም እንደ ቡድን የነበራቸው በራስ መተማመን መውረድ እና ቀድሞ መሸነፍ ዋነኛው ነው። ከመከላከል ድክመት እስከ የግብ ዕድልን ፈጥሮ ወደ ጎልነት የመቀየር ሥራ የሚሠራው ደግሞ ጊዜውን በጠበቀና ብዙ የወዳጅነት ጨዋታዎችን በማድረግ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) በዓለም አቀፍ የፊፋ የሀገራት እግር ኳስ ደረጃ ከዓለም 143 ከአፍሪካ ሀገራት ደግሞ

 42 ደረጃን ይዞ ይገኛሉ። የሀገራት እግር ኳስ ደረጃ የሚለካው በሚያደርጉት የነጥብ ጨዋታዎችና የወዳጅነት ጨዋታዎች ብዛት በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው በብዙ ሀገራት ይካሄዳሉ። በዚህም መሠረት ሀገራት ባካሄዱት የጨዋታ ብዛት እና በሚያስመዘግቡት ነጥብ ልክ ተሰልቶ የእግር ኳስ ደረጃቸው ይቀመጣል። ዋሊያዎቹ ዓለም አቀፍ የጊዜ ሰሌዳዎችን ጠብቆ ተደጋጋሚ ጨዋታዎች መድረግ አለመቻላቸው በውድድሮች ላይ ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርጓል፤ በመሆኑም መሰል ጨዋታዎች ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል።

ዋሊያዎቹ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከጉያና ብሔራዊ ቡድን ጋር በማድረግ በአሸናፊነት መደምደማቸው የሚታወስ ነው። ቀድሞ የተያዘው ሁለተኛው ጨዋታ መሰረዙን ተከትሎም በምትኩ መቀመጫውን በሊዝበርግ (ቨርጂንያ) ካደረገው ሎዶን ዩናይትድ ጋር ማድረግ ችሏል። ይህም ከፊቱ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ለሚጠብቀው ቡድን የሚኖረው ድርሻ አያጠያይቅም። ለ2026 የዓለም ዋንጫ በምድብ አንድ ከግብጽ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ጊኒቢሳው፣ ሴራሊዮን እና ከጂቡቲ ጋር የተደለደለው ቡድኑ በመጪው ጥቅምት የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን የሚያደርግም ይሆናል።

ከዚህ ባለፈ ተጫዋቾች በመልማዮች የመታየት ዕድላቸውም የሚሰፋ ይሆናል። በዚህም መሠረት በሜጀር ሊግ ሶከር የሚሳተፉት የዲሲ ዩናይትድ እና አትላንታ ዩናይትድ መልማዮች የቡድኑን ስም ዝርዝር ቀድመው የጠየቁ ሲሆን፤ በጨዋታው ላይም ተገኝተው የተጫዋቾችን እንቅስቃሴ ተመልክተዋል። ፌዴሬሽኑም ቢሆን አጋጣሚውን ተጠቅሞ ስፖንሰሮችን በማፈላለግ እንዲሁም ሌሎች ምንጮችን በመጠቀም ገቢ ለማግኘት ያስችለዋል።

ጨዋታዎቹ በተካሄዱበት ወቅት የብሔራዊ ቡድኑን መለያ ልብስ መሸጥ ከእነዚህ መካከል አንዱ ነው። የመጀመሪያው ጨዋታ 5ሺህ ተመልካች በሚይዘው ሴግራ ፊልድ የተካሄደ ሲሆን፤ 2ሺህ 640 ተመልካች ትኬት ቆርጦ በመግባት ጨዋታውን ተመልክቷል። በዚህም 260ሺህ ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል።

መሰል ስፖርታዊ ሁነቶች ሲዘጋጁ ኑሯቸውን ከሀገራቸው ውጪ ያደረጉ ዜጎችን ለማሰባሰብ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር የታወቀ ነው። በዚህም ነዋሪነታቸውን በአሜሪካ ያደረጉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ቡድናቸውን የመመልከትና የማበረታታት ዕድል አግኝተዋል። በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ እና የመስሪያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች፣ የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋቾች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ጨምሮ ባለሀብቶች ተገኝተዋል። በዚህም ቡድኑ የነበረው የቀናት ቆይታ የሚያስፈልገውን ወጪ በመሸፈን እንዲሁም የጨዋታና የጉብኝት መርሃ-ግብሮችን በማዘጋጀት ስኬታማ እንዲሆን አድርገዋል።

አለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *