ተፈጥሮን ማሳነስ ማዳበሪያን ማተለቅ ያመጣው መዘዝ

የኢትዮጵያ ግብርናን ስናነሳ ብዙ ለውጦች የታዩበት ቢሆንም ብዙ ችግሮችን ማስተናገድም እንደቻለ በማዳበሪያ ዙሪያ እየሆነ ያለውን ብቻ ማንሳት በቂ ነው። ግብርናው ተፈጥሯዊ ማዳበሪያዎችን መጠቀም ትቶ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአፈር ማዳበሪያ ላይ ጥገኛ ሆኗል። የአፈር ማዳበሪያ ተጠቃሚ አርሶ አደሮችም ከማዳበሪያ ውጪ ዘር መዝራትን አሻፈረኝ ካሉ ሰነባብተዋል። ይህ ደግሞ ዛሬ ላይ የአፈር ማዳበሪያ ችግር ሲያጋጥም ወገቤን እንዲሉ አስገድዷቸዋል። አርሶ አደሩ በሰብል ልማት ሥራው የማይፈልገው ወጪ ውስጥ እንዲገባም አድርጎታል።

ኢትዮጵያም ይህንን ተከትሎ ከጊዜ ወደ ጊዜ አርሶ አደሩ ማዳበሪያ ተጠቃሚ እንዲሆን የምታስገባው የአፈር ማዳበሪያ መጠን እንዲጨምር ከፍተኛ ወጪ እያወጣች ትገኛለች። ልዩነቱን ብናነሳ እንኳን የኢትዮጵያ አፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም በ1960ዎቹ ውስጥ 35 ሺህ ኩንታል ነበር። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ሚሊዮኖችን አስቆጥሯል። ለአብነት በ2008/2009 የምርት ዘመን የኢትዮጵያ አፈር ማዳበሪያ ዓመታዊ ፍጆታ አምስት ሚሊዮን 800 ሺህ ኩንታል ሲሆን፣ በ2015/16 የምርት ዘመን 15 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለመስኖ፤ ለበልግና ለመኸር አገልግሎት ላይ እንዲውል መደረጉ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ ፍጆታ ከዓመት ዓመት እያደገ መምጣቱ ደግሞ የቀጣይ ገበያ ዋጋን በእጅጉ እንደሚያንረው አጠያያቂ አይደለም። ምርት በኋላ ደግሞ በገዛበትና ባመረተበት ልክ ሊሸጠው አይችልም። ስለዚህም የገበያው ዋጋ የማዳበሪያውን ወጪም የሚጨምር ይሆናል። በዚህ ጊዜ ደግሞ ሸማቹ የሚይዘው የሚጨብጠው ማጣቱ አያጠያይቅም።

በእርግጥ ይህ ችግር የኢትዮጵያ ብቻ ይሆናል ብሎ ማሰብ ተገቢነት የለውም። ምክንያቱም አርሶአደሩ የተቸገረው ያለምክንያት አይደለም። ዓለም አንድ መንደር በመሆኗ ሳቢያ ለዓለም ገበያ ከፍተኛውን የአፈር ማዳበሪያ የምታቀርበው ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ በመግባቷ የዓለም የአፈር ማዳበሪያ መሸጫ ዋጋን እንዲያሻቅብ አድርጓል። በየዓመቱ የአፈር ማዳበሪያ ፍጆታዋ እየጨመረ ለመጣችው ኢትዮጵያ ደግሞ ይህ ፈተና በብዙ መልኩ መከራን ያበዛባት ሆኗል።

አንዱ በተፈጥሮ ማዳበሪያ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋንና የአቅርቦት ችግሩን እንዳታክም ሀገራዊ ችግሯ ይህንን የሚያሠራበት ሁኔታ ላይ አይደለም። በጦርነት ምክንያት ተረጋግቶ መሥራት የሚችለው አካል እንዳይኖር አድርጎት ከርሟል። አሁን ተነስቼ የተፈጥሮ ማዳበሪያን ላዘጋጅ ቢል ደግሞ አይሆንለትም።

በእርግጥ እንደመንግሥት ዝም እንዳልተባለ የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ አብራርተዋል። አርሶአደሩ ማዳበሪያው ባይደርሰው እንኳን በሚል የተፈጥሮ ማዳበሪያን እንዲጠቀም ቀድሞ የማዘጋጀት ሥራ ተሠርቷል። በዚህም በዚህ ዓመት ብቻ የማዳበሪያ እጥረቱ ቢኖርም የተፈጥሮ ማዳበሪያ አርሶአደሮች እንዲያዘጋጁ በመበረታታቱ 153 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲዘጋጅ ሆኗል። ይህ ግን ሁሉም ላይ የተከናወነ ባለመሆኑ የአርሶአደሩ ምርጫ ዋጋውን ተጋፍጦ ማዳበሪያ ማግኘት ነው።

የማዳበሪያ ፍላጎትና ፈተናው

የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያውያን አርሶአደሮች በአብዛኛው በሚባል ደረጃ ዛሬ ላይ የአፈር ማዳበሪያ ተጠቃሚ ናቸው። መሬታቸው አዘውትሮ ማዳበሪያውን መጠቀም ለምዷል። ማዳበሪያ መጠቀምን ማቆም የሚሉበት ደረጃ ላይ አይደሉም። እንደውም አሳንሶ እንኳን መጠቀም አይችሉም። አፈሩ በለመደው ልክ ካልሰጠው ምርቱን እርሱም መልሶ እንደማይሰጠው ያውቃል። ስለዚህም ተበድሮም ቢሆን ያለውን መግዛት ግዴታው ሆኖበታል። በአጠቃላይ የማዳበሪያ ጉዳይ እንደመንግሥትም እንደ አርሶአደርም ውስብስብ ነው።

እንደ መንግሥት ችግሩ እልባት እንዲያገኝ መሥራት ግድ ነውና ከባለፈው ዓመት በተለየ መልኩ ዋጋ ጨምሮ ማዳበሪያ ለማቅረብ ተችሏል። ለአብነት ላለፈው የምርት ዘመን ለማዳበሪያ ወጪ የተደረገው ገንዘብ 650 ሚሊዮን ዶላር ነበር። ለዘንድሮ የምርት ዘመን ግን የ350 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ወጪ ተደርጎ አንድ ቢሊዮን ዶላር ማውጣት ግዴታ ሆኗል። ይህም ሆኖ የሕገወጦች ጉዳይ ነገሩን አሳሳቢ አድርጎታል። ከጂቡቲ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ ጀምሮ በስርቆት ሲጠመድ ታይቷል። አርሶአደሩ ጋርም እስከሚደርስ ድረስ ያለው ስርቆት ሀገርንም አርሶአደሩንም ፈተና ውስጥ እየከተተ ነው። እናም ይህንን ለማስቀረት ሌላ ሥራ መሥራት እንዳለብንም አሳስቦናል። ለዚህም የግብርና ሚኒስቴር አንድ ዘዴ መዘየድ እንዳለበት አምኗል ይላሉ።

እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ ለጊዜውም ቢሆን በብዙ መልኩ አሠራሮችን በማስተካከል ማዳበሪያው ለአርሶአደሩ እንዲደርስ እየተሠራ ነው። ሆኖም በዚህ መልኩ መቀጠል ግን አያስችልም። ስለዚህም ልክ እንደ ነዳጁ ሁሉ በኩፖን መልክ የሚሠራበት አሠራር ይዘረጋል። ማን አወጣ፤ ለማን ደረሰና መሰል ነገሮችን ባማከለ መልኩ በቴክኖሎጂ ዘምኖ የሚሠራም ነው። አርሶአደሩ እንዳይቸገርም ብዙ አማራጮች ይተገበራሉ። ለዚህም የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው።

የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ፤ ‹‹የ2015/16 የምርት ዘመን ፍላጎት ወደ 20 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ሲሆን፤ ፍላጎት የሚቀርበው ሰፋ ተደርጎ በመሆኑ መግዛት የተቻለው 13 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ነው። ይህ ደግሞ ለትግራይ ክልል የተገዛውን 800 ሺህ ኩንታል ጨምሮ ነው። ከዚያም ይህም የሚበቃ እንዳልሆነ ሲታይ ካለፈው ዓመት የተረፈውን ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጨምሮ በድምሩ 15 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ለመስኖ፤ ለበልግና ለመኸር ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ እየተሞከረ ነው ›› ይላሉ።

የማዳበሪያ ተደራሽነት

ዶክተር ግርማ እንደሚገልፁት፣ የተገዛውን ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ገቢ አድርጎ ለአርሶአደሩ ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ እርብርብ እንደተደረገ የሚያነሱት ዶክተር ግርማ፤ ከተገዛው 13 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ውስጥ 11 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል (87 በመቶ) የሚሆነው እስከ ሐምሌ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ጅቡቲ ደርሷል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 10 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታሉ (89 ነጥብ ሰባት በመቶው) ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ሆኗል። አሁን የሚቀረው አንድ ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ነው።

ይህንን ደግሞ በርካታ አካላት ተረባርበው ያደረጉት ነው። እንዲያውም በአንድ ቀን እስከ 20 ሺህ ሜትሪክ ቶን እንዲጓዝ የማድረግ ሥራ ተሠርቶ ነበር። አንድ መርከብ በሦስት ቀን እንደመጫን ማለት ነው። ቁም ነገሩ ማዳበሪያ መግዛትና ማጓጓዝ ብቻ እንዳልሆነ የሚናገሩት ሚኒስትሩ፤ እንደመንግሥት ይህንን በመረዳት 12 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶአደሩ እንዲደርስ ሆኗል። ይህ ማለትም ካለው ማዳበሪያ ውስጥ 68 በመቶ ለአገልግሎት ዝግጁ ተደርጓል። ለዚህም ከፍተኛ ርብርብ ተደርጓል።

ዶክተር ግርማ ማብራሪያ፤ ‹‹ማዳበሪያ ስንገዛና ስንጭን ቅደም ተከተል እናስይዛለን። አርሶአደሩ የትኛውን ማዳበሪያ በትኛው ወቅት ያስፈልገዋል የሚለውን መረጃ መሠረት በማድረግ ግዢው እንዲፈጸም እናደርጋለን። በዚህ ወቅት የሚያስፈልገው ኤንፒኤስ (NPS) እና ኤንፒኤ ቦሮን (NPA) የሚባሉት ከዘር ጋር አብሮ የሚጠቀማቸው የማዳበሪያ አይነቶች ናቸውና እነርሱን በተቻለ መጠን ገዝቶ ወደሀገር ውስጥ አስገብቶ ለአርሶአደሩ ለማድረስ ተችሏል። ቀሪዎቹ ጥቂት አስፈላጊ ማዳበሪያና ዩሪያ ናቸው። ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ዩሪያው ደግሞ ለአሁን የሚያገለግሉ ሳይሆኑ ሰብሉ ከበቀለ በኋላ ጥቅም ላይ የሚውል ነው። ሆኖም ሀገር ውስጥ ገብቶ በሚፈለገው ጊዜ ለአርሶአደሩ መድረስ ስላለበት በአራት መርከቦች በቅርቡ ጅቡቲ ይደርሳሉ፤ ለክልሎች ይከፋፈላል›› ይላሉ።

የተጫኑ ማዳበሪያዎች የት እንደደረሱና ቀሪዎቹን በመጋዘን ያሉ ማዳበሪያዎችን እንዴት ለአርሶአደሩ ይድረሱ በሚል ጉዳይ ላይ ከክልሎች ጋር በቪዲዮ ኮንፍረንስ ውይይት እንደሚያደርጉ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ይህ ቢሆንም ሕገወጥነቱ በተለየ ዘዴ እየተከወነ ከአቅም በላይ እየሆነ መጥቷል። ምክንያቱ ደግሞ የተፈጠረውን የማዳበሪያ እጥረት በመጠቀም የግል ፍላጎትን ማርካት ነው። ስለዚህም እንደመንግሥት አዲስ አሠራር መዘርጋት ግድ እንደሆነ ታምኖበታል ሲሉ አስረድተዋል።

‹‹የማዳበሪያ ግዢው በየዓመቱ ስለሚጨምር ዘራፊውም በዚያው ልክ ፍላጎቱን ያሰፋል። የስርቆት መርሑንም ይቀያይራል። ስለዚህም ይህንን በተቀናጀ መልኩ መመከት ካልተቻለ አደጋው ከባድ ነው።›› የሚሉት ዶክተር ግርማ፤ እንደመንግሥት ከዚህ በኋላ ማዳበሪያን በተለመደው መንገድ ማሰራጨት ይቀራል። እንደከዚህ ቀደሙ የተለየ ሥራ የሚከናወንም ይሆናል። ለአብነት ያህል ከዚህ ቀደም የማዳበሪያ ስርቆትን ለማስቀረት ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ዩኒየኖች ከብድርና ቁጠባ ተቋማት ኩፖን ወስደው በኩፖኑ መሠረት ማዳበሪያውን እንዲረከቡ ተደርገዋል። ይህ በመሆኑም ከገንዘብ ንክኪ እንዲርቁ ማድረግ ተችሏል። ሆኖም ሥራው ግን በቂ አልነበረም። አንዳንድ ክፍተቶች ነበሩበት›› ሲሉ እስከዛሬ የወሰዷቸውን እርምጃዎች ያብራራሉ።

በቀጣይ ስለተያዘው እቅድ ሲናገሩም ‹‹አዲስ የሪፎርም ሥራ ማከናወን አንዱ ተግባር ነው። ይህም የግዢ ሂደቱ ላይ ማሻሻሎችን ማምጣት ሲሆን፤ ለአብነትም በጨረታ ብቻ የመግዛት ሁኔታን ማሻሻል ተጠቃሽ ነው። በሁሉም የግዢ አማራጮች ማዳበሪያ የመግዛትና ለአርሶአደሩ ተደራሽ የማድረግ አሠራርን ለመተግበር ታቅዷል። ይህ ሲሆን ደግሞ ልክ እንደ ውጪ ሀገራት ሁሉ መንግሥት የማዳበሪያ አቅርቦቱን ሲያመቻች በመንግሥት በኩል ግዢውን መፈጸም ነው። ይህም መንግሥት ከመንግሥት ጋር ግብይት የሚያደርግበትን እድል መፍጠር ነው›› ብለዋል። በሌላ በኩል የተያዘው እቅድ የረጅም ዓመት ግዢ በመፈጸም ችግሮችን መፍታት ላይ ማተኮር ሲሆን፤ ይህንን አሠራር እውን ሊያደርግ የሚችል የግዢና አሠራር ሁኔታ የሚጠቁም መመሪያ እየተዘጋጀ እንደሆነም አስረድተዋል።

የመኸርና የበልግ ወቅቶች ሥራ

ዶክተር ግርማ እንደሚገልፁት፣ የዘንድሮው የበልግ ወቅት ከቀደሙት ዓመታት በብዙ መልኩ የተለየ ነው። ጥሩ በሚባል ደረጃ አልፏልም። ለአብነት የዝናብ ሁኔታው በጥሩ መልኩ ለሁሉም የደረሰበት ሁኔታ ነበር። ከዚህ አንጻርም በበልግ እርሻ ወደ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማረስ ታቅዶ ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር አርሶ በዘር በመሸፈን ከእቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል። ከዚህ እርሻ 65 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል። እስከአሁንም ከ800 ሺህ ሄክታር መሬት ምርት ተሰብስቧል። ከበልግ በኋላ ደግሞ ቀጣዩ የእርሻ ወቅት መኸር በመሆኑ ወደ መኸር ሥራ የሚገቡ አካባቢዎች መኖራቸውንም ያስረዳሉ።

የመኸር እርሻን በተመለከተ ከባለፈው ዓመት በበለጠ እንደታቀደ የሚገልጹት ሚኒስትሩ.፤ 17 ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር ለማረስ ታስቧል። ይህ እቅድ በልግ ላይ ምርታቸውን ሰብስበው ወደ መኸር እርሻ የሚሻገሩትን የሚጨምር ሲሆን፤ ከባለፈው ዓመት አንጻር ሲታይም የሁለት ሚሊዮን ሄክታር ልዩነት አለው። ስለዚህም እስካሁን ድረስ 15 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር (88 በመቶ) መሬት ታርሷል። ይህ ደግሞ አምና ታርሶ ከተዘራው በላይ መሬት እንደተዘጋጀ የሚያሳይ ነው። ከዚህ ውስጥ በዘር የተሸፈነው ደግሞ 10 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ሲሆን፤ ይህም አምና ታርሶ ከተዘራው በአንድ ሚሊዮን ሄክታር ብልጫ አለው።

እንደሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ አምና ዓመቱን ሙሉ በትራክተር የታረሰው መሬት ሁለት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር ሲሆን፤ ዘንድሮ ይህ መጠን ወደ ሦስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር አድጓል። ይህ ደግሞ የሜካናይዜሽን ሥራው ምን ያህል ትኩረት እንዳገኘ የሚያሳይ ነው። በተመሳሳይ የኩታ ገጠም እርሻን በተመለከተ ባለው መረጃ ባለፈው ዓመት ስድስት ነጥብ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም የታረሰ ሲሆን፤ ዘንድሮ ስምንት ሚሊዮን ለማድረስ ታቅዷል። እስካሁን ባለው መረጃም በዘር ከተሸፈነው 10 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር ውስጥ ገና የስንዴውና የጤፉ ሳይጨምር አምስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር በኩታገጠም መታረስ ችሏል።

የሰብል ጥበቃ ሁኔታ

የዘንድሮ የምርት ዘመንን በተሻለ መልኩ ምርታማ ለማድረግ ፀረ-ተባይ ኬሚካል አቅርቦቱ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት ዶክተር ግርማ፤ ባለፈው ዓመት ዘንድሮ ከሚቀርበው ውስጥ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሊትር አግሮ ኬሚካልስ የተባይና የአረም ማጥፊያ እናቀርባለን ብለን አቅደን ነበር። እስካሁን አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሊትር አግሮ ኬሚካልስ ቀርቧል። በ83 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ፀረ-ሰብል ተምችና ተባይ አጋጥሟል። ከዚህ ውስጥ 16 ሺህ ሄክታሩን በባሕላዊ፣ 50 ሺህ ሄክታሩን ደግሞ ኬሚካል በመርጨት በአጠቃላይ በ66ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሰብል ጥበቃ ሥራዎች መከናወናቸውንም አብራርተዋል።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *