በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የሚገኙ ሕዝቦች ዛሬ ላይ ለሚገኙበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሕይወታቸው ከሁሉም በላይ የራሳቸው አስተዋፅዖ ከፍ ያለ ነው። በተለይም ያደጉ ሀገራት ሕዝቦች ትናንቶቻቸውን በአግባቡ ተረድተው እና ከትናንቶቻቸው ተምረው ዛሬዎቻቸውን የተሻሉ ስለማድረጋቸው የታሪክ መዛግብት በስፋት ይተርካሉ።
በእርግጥ እያንዳንዱ ትውልድ እራሱን ዘመኑን በሚዋጅ እውቀትና እውቀት በሚፈጥረው መነቃቃት እየበቃ፣ ዛሬዎቹ ከትናንት የሚሻሉበትን፣ ነገዎቹ ደግሞ ከትናንት የሚልቁበትን፣ በታሪክ ፊት ከፍ ብሎ የሚታሰብበትንና የሚዘከርበትን ተጨባጭ እውነት ለመፍጠር መትጋት፤ በዚህም ስኬታማ መሆን ይጠበቅበታል።
ያደጉ የሚባሉ ሀገራትም ቢሆኑ አሁን ያሉበት የእድገት ደረጃ በመድረስ የዓለምን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሕይወት ለመዘወር የቻሉት፤ የዓለም ፖሊስ አድርገው ራሳቸውን እስከ ማየት የደረሱት ይህንኑ ሂደት በተገቢው መንገድ እና ስኬታማ በሆነ መልኩ ማለፍ፤ ከዛም በላይ ሂደቱን ማስቀጠል የሚያስችል ሥርዓት መገንባት በመቻላቸው ነው።
እኛም እንደ ሀገር የጀመርነው ድህነትን ታሪክ የማድረግ ሀገራዊ ንቅናቄ ስኬታማ የሚሆነው ይህንኑ እውነት ታሳቢ ባደረገ መንገድ ትናንቶቻችን በአግባቡ ተረድተን፤ ስለትናንቶቻችን ትክክለኛ የጋራ አመለካከት መፍጠር ስንችል ነው ። ትናንቶቻችን ላይ ቆመን ከመወቃቀስ ወጥተን፤ ትናንቶችን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ መረዳት የሚያስችል የአእምሮ ክፍተት እና ልበ ሰፊነት ስንፈጥር ነው ።
ትናንቶችን ፈጥሮ ያለፈው ትውልድ የተገዛባቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እሳቤዎች የመቶና ከዚያም በላይ ዓመታት ልዩነቶችን ያስተናገደ፤ ይህንኑ ታሳቢ ላደረገ የአእምሮ ውቅር የተገዛ ነው። ያንን የአእምሮ ውቅር የፈጠረ መረጃ /እውቀት ያን ያህል ዘመናትን ወደኋላ መለስ ብለን እንድናስብ የሚስገድደን ነው።
ለዚህ ደግሞ ስለ ታሪክ ያለንን መረዳት መልሰን አግባብ ባለው መንገድ ልናጤነው ይገባል። ትናንቶቻችንን በዛሬ አእምሯዊ ውቅር እና ውቅሩ በፈጠረው አስተሳሰብ፤ አስተሳሰቡ በወለደው ድርጊት እየኮነንን፤ በነሱ ዛሬዎቻችንን ትርጉም ማሳጣት፤ ነገዎቻችንን ተስፋ አልባ ማድረግ አይገባንም።
ትናንቶች /ታሪክ/ ለዛሬ ሆነ ለነገዎቻችን ያላቸው ትልቁ አበርክቶ፤ ከትናንቶች ተምረን ስህተቶችን እንዳንደግም፤ ከተንሰላሰለ የስህተት አዙሪት ወጥተን ዛሬዎቻችን ቢያንስ ቢያንስ የትናንት ስህተቶቻችን ሰለባ እንዳይሆኑ ለማድረግ ነው ። ይህን ማድረግ ደግሞ በየዘመኑ ያለ ትውልድ የመጀመሪያ ሥራው ነው።
ይህንን ሥራ በጠራ እውቀት እና ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ መወጣት የማይችል ትውልድ፤ ስህተትን ከመድገም ባለፈ የራሱን ታሪክ መሥራት የሚያስችል ቁመና ሊኖረው አይችልም። ከዚህ ይልቅ ሀገርን የሁከት እና የትርምስ ማዕከል በማድረግ በትውልዶች መካከል ሊፈጠር የሚችለውን ተናቦ የማደግ እድል ሊያመክነው ይችላል።
ይህ ደግሞ እንደ ሀገር ሀገርን የሕልውና አደጋ ውስጥ ሊከት፤ በትውልዶች መካከል ሊኖር የሚችለውን ማኅበራዊ መስተጋብር በማጥፋት፤ የማንነት ግራ መጋባት ሊፈጥር የሚችል ትልቅ ስጋት ነው። በአንድ ሀገር ውስጥ ያሉ ሕዝቦችን የጋራ ብሔራዊ እሴቶችን ሊያቀጭጭ የሚችል ነው ።
ችግሩ እንደኛ ላሉ ለሀገራቸው ከፍ ያለ ፍቅር ላላቸው፤ ለዚህም በየዘመኑ ብዙ የሕይወት ዋጋ/ መስዋዕትነት በመክፈል፤ ብሔራዊ ክብራቸው ዋንኛ የማንነታቸው መገለጫ ለሆኑ ሕዝቦች ትልቅ ስብራት ነው። ይዞት የሚመጣው አደጋም አሁን ላይ ሆነን በአግባቡ ሊታሰብ የሚቻል እንዳልሆነ ይታመናል።
ከዚህ አሁነኛ ሀገራዊ ስጋት ወጥተን ወዳሰብነው የብልጽግና ጎዳና ለመግባትና በመንገዳችን ስኬታማ ለመሆን ፤ ከሁሉም ቀድመን ስለ ትናንቶቻችን በአግባቡ እና በተገቢው መንገድ ልንነጋገርና መግባባት ላይ ልንደርስ ይገባል። ትናንቶችን ከመውቀስ ወጥተን ከነሱ መማር የሚገባንን ተምረን፤ ዛሬዎቻችን የተሻሉ፣ ነገዎቻችን ባለተስፋ ልናደርጋቸው ይገባል።
ለዚህ ደግሞ አሁን ላይ በእጃችን ያለውን ፤ ብሄራዊ የምክክር መድረክ በአግባቡ ልንጠቀምበት፤ ለዚህም እራሳችን በሁለንተናዊ መንገድ ማዘጋጀት ይጠበቅብናል ። ከሁሉም በላይ መድረኩ በአእምሯችን ውስጥ ያሉ የተበላሹ ትናንቶችን በማከም ለዛሬ ችግሮቻችን ፈውስ እንዲሆን ሁሉም ዜጋ ለታሪክ ያለውን ግንዛቤ ሊያስተካክል ይገባል !።
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም