አዲስ አበባ፦ የግዥ ፍላጎታቸውን ዝርዝር በወቅቱ ያላቀረቡ የመንግሥት ተቋማት ግዥ እንደማይፈፀምላቸው ተገለጸ።
የፌዴራል የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ በግዥና ንብረት ማስወገድ ባሉ ችግሮች ዙሪያ ትናንት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ሲደረግ እንደገለጹት፣ ተቋሙ ሁሉም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የሚጠቀሙበትን ማንኛውም ንብረት በማዕቀፍ ግዥ የሚፈጽም ቢሆንም አብዛኞቹ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በወቅቱ የግዥ ፍላጎታቸውን ባለማሳወቃቸው ግዥ አይፈጸምላቸውም።
የመንግሥት ግዥ ረጅም ሂደትን የሚከተል መሆኑን ገልጸው የመንግሥት ተቋማት በወቅቱ ፍላጎታቸውን ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ በግዥ ማዕቀፍ ውስጥ መካተት ከሚገባቸው 142 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ 82ቱ ብቻ የግዥ ፍላጎታቸውን ያሳወቁ ሲሆን፣ ከ45 ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ደግሞ የግዥ ፍላጎታቸውን ያሳወቁት 22 ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ተቋሙ ለእነዚህ መስሪያ ቤቶች ፍላጎታቸውን መሰረት በማድረግ የንብረት ግዥ ፈፅሞ ተደራሽ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ይገኛል።
በተለይም በማዕቀፍ ግዥ ሥርዓት ውስጥ ገብተው ፍላጎታቸውን ላሳወቁ 22 ዩኒቨርሲቲዎች ንብረቱን ግቢያቸው ድረስ እንደሚያቀርብላቸው ገልጸዋል።
እስካሁን ድረስ የግዥ ፍላጎታቸውን ያላሳወቁ መሥሪያ ቤቶች በህገወጥ መንገድ ግዥ የሚፈጽሙ ከሆነ በቀጣይ በህግ የሚጠየቁበት ሥርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ከ2011 እስከ 2013ዓ.ም ድረስ የማዕቀፍ ስምምነት ግዥ ለመፈጸም 402 ዓይነት ዕቃዎች ተለይተዋል፡፡ ተቋሙም የዕቃዎቹን የግዥ ሂደትና አቅርቦት ለማፋጠን ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ ነው።
ይሁን እንጂ ከተጠቃሚ መስሪያ ቤቶች የግዥ ፍላጎት መሰብሰብና ማደራጀት፣ የጥራትና ናሙና ፍተሻ ማስደረግ፣ እንዲሁም ጨረታ መገምገምና በግምገማ ውጤቱ ላይ ተጫራቾች የሚያቀርቡትን ቅሬታ መፍታት የግዥ ሂደቱ የተንዛዛ እንዲሆን አድርጎታል።
የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ህዳር 25 ቀን 2011 ዓ∙ም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ባደረገው ውይይት የተለያዩ አቅራቢ ድርጅቶችና ተጠቃሚ የሆኑ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ተሳትፈዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2011
በፍሬህይወት አወቀ