የዓለምን አትሌቲክስ የሚመራው ማህበር ከኦሊምፒክ ባለፈ የአትሌቲክስ ውድድሮች ብቻ የሚካሄዱበት ቻምፒዮና ለማካሄድ ማቀዱን ተከትሎ የዛሬ 40 ዓመት የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በፊንላንድ፣ ሄልሲንኪ ተጀመረ፡፡ በወቅቱ በኦሊምፒክ ድል ስሟ የገነነው ኢትዮጵያም በቻምፒዮናው በአምስት ርቀቶች ማለትም በ5000፣ 10ሺህ እና 3ሺህ ሜትር መሰናክል፣ ማራቶን እንዲሁም በ20 ኪሎ ሜትር እርምጃ በወንዶች ብቻ የተዋቀረ ቡድንን ይዛ ቀረበች፡፡
በዚህ ቻምፒዮናም ብቸኛውን የብር ሜዳሊያ በማግኘት ከዓለም ሃገራት 15ኛ ደረጃን በመያዝ ልታጠናቅቅ ችላለች፡፡ ታሪካዊውን ሜዳሊያ በማግኘት ሃገሩን ያስጠራው የወቅቱ አትሌትም ሻለቃ ከበደ ባልቻ ሲሆን፤ ሜዳሊያው በአፍሪካም ብቸኛው በመሆኑ የአህጉሪቷ ኩራት ሊሆንም ችሏል፡፡ በመሆኑም የዛሬው የስፖርት ማህደር አምድ ያልተነገረለትን ድንቅ የማራቶን አትሌት ታሪክ ያወሳል፡፡
በ1943 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል፣ ሰበታ ከተማ፣ አጠበላ ቀበሌ የተወለደው ሻለቃ አትሌት ከበደ ባልቻ ከትምህርት ዓለም በኋላ የፖሊስ ሰራዊት አባል በመሆን ነበር ከስፖርቱ ጋር የተዋወቀው፡፡ ወቅቱ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ስፖርት በመላው ዓለም የታወቀችበት መሆኑን ተከትሎ የወጣቱ አትሌት ከበደ ብቃት ይህንኑ የሚመጥን በመሆኑ በ1967 ዓ.ም በኦሜድላ ስፖርት ክለብ ውስጥ በመታቀፍ በአትሌቲክስ የረጅም ርቀት ሩጫ ቡድን አባል ለመሆን በቃ፡፡ በማራቶንም ከአህጉር አቀፍ ቻምፒዮናዎች እስከ ኦሊምፒክ ሃገሩን በመወከል ለሃገሩ እጅግ በርካታ የወርቅ፣ የብርና የነሃስ ሜዳሊያዎችን፤ እንዲሁም ዲፕሎማዎችን አስገኝቷል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በአቴንስ ማራቶን የተሳተፈው አትሌቱ በቀዳሚነት ያጠናቀቀ ሲሆን፤ እአአ በ1979 በሴኔጋል፣ ዳካር በተካሄደው የአፍሪካ ቻምፒዮና ላይ የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ ማስገኘት ችሏል፡፡ በዚያው ዓመት በርካታ ድሎችን ባጣጣመበት የሞንትሪያል ማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፎ በማድረግ ዳግም የበላይነቱን ለመቀዳጀት ችሏል፡፡ ይኸው አቋሙም በቀጣዩ ዓመት ሞስኮ ላይ ለሚካሄደው ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን የሚወክለው ብሄራዊ ቡድን አባል እንዲሆን አብቅቶታል፡፡ አራት ሜዳሊያዎች በተመዘገቡበት ውድድርም በማራቶን ተጠባቂ የሆነው ከበደ ውድድሩን አቋርጦ ነበር የወጣው፡፡
በቀጣዩ ዓመትም ወደ ካናዳ በማቅናት የሞንትሪያል ማራቶንን በመሮጥ ቀድሞ የገባበትን ሰዓት አሻሽሎ በድጋሚ አሸናፊ በመሆን አጠናቋል፡፡ ስኬታማው የረጅም ርቀት አትሌት ከዓመት ቆይታ በኋላ በድጋሚ እአአ 1983 በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ታየ፡፡ ቀድሞ የታወቀበትንና ዝናውም በናኘበት የሞንትሪያል ማራቶን ለሶስተኛ ጊዜ ተሳትፎ በማድረግም ሶስተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ለማጥለቅ ቻለ፡፡ ነገር ግን ይህንን ውድድር ካለፉት ጊዜያት ለየት የሚያደርገው ያስመዘገበው 2:10:03 በሆነ ሰዓት በመሆኑ ለዘመናት በሌላ አትሌት ሳይደፈር የቦታው ክብረወሰን እንደሆነ ኖሯል፡፡
በዚያው ዓመት የመጀመሪያው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በመካሄዱ አትሌቱ ኢትዮጵያን በመወከል፤ ለራሱ፣ ለኢትዮጵያ እንዲሁም ለአፍሪካ ብቸኛዋን ድል በማስገኘት ደማቅ ታሪክ ሊያጽፍ ችሏል፡፡ በወቅቱ ካለው ልምድ የተነሳ በውድድሩ ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረው አትሌቱ አውስትራሊያዊውን አትሌት ተከትሎ ሲገባ እንደ ማራቶን ባሉ ውድድሮች ባልተለመደ መልኩ በመካከላቸው የነበረው የሰከንዶች ልዩነት ብቻ ነው፡፡ በወቅቱ ርቀቱን የሸፈነው 2:10:27 በሆነ ሰዓት ሲሆን፤ ይኸውም በሞንትሪያል ካስመዘገበው ፈጣን ሰዓት በሰከንዶች ብቻ የዘገየ ነው፡፡ የአትሌቱን ብቃት ለየት የሚያደርገውም በአንድ ዓመት (1983) ብቻ በርካታ ውድድሮች ላይ መሳተፍ መቻሉ ሲሆን፤ የለንደን እና ቶኪዮ ማራቶኖችን ጨምሮ አራት ማራቶኖችን ሮጧል፡፡
በቀጣዩ ቻምፒዮና ኢትዮጵያ በመድረኩ ባትሳተፍም አንጋፋው አትሌት ከበደ ግን በግል የማራቶን ውድድሮችን አካሏል፡፡ በፍራንክፈርት፣ በቶኪዮ፣ በሮተርዳም እና በፎኮካ ማራቶኖች ከመሮጥ ባለፈ በሞንትሪያልም አራተኛውን ድሉን ሊያስመዘግብ ችሏል፡፡ በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች እና የአፍሪካ ቻምፒዮና ላይም ኢትዮጵያን ወክሎ ተካፋይ ሆኗል፡፡ በዚህም የሃገሩን ስም በተደጋጋሚ በዓለም አደባባይ በጀግንነት እንዲነሳ አድርጓል፡፡
ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት የነበረው አትሌቱ ተደጋጋሚ ድልን ባጣጣመባት ካናዳ ኑሮውን አድርጎ ሳለ በገጠመው የጤና እክል በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በ67 ዓመቱ ህይወቱ አልፏል፡፡ የቀብር ስነስርዓቱም በክብር ሲያስጠራት በቆየላት ሃገሩ ሃምሌ 3/2010 ዓ.ም አዲስ አበባ፣ ዊንጌት አካባቢ በሚገኘው በብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ወገብርኤል ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡ ህያው የሆነው የአትሌቲክስ ታሪኩ ግን ከዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና እኩል ሲወሳ የሚኖር ነው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2015