በኢትዮጵያ ለቱሪስት መስዕብነት የሚሆኑ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ ስፍራዎች በእጅጉ በርካታ ናቸው። አገሪቱ ምድረ ቀደምትና የሰው ዘር መገኛ ምድር ከመሆኗ አንፃር በእጅጉ ሲበዛ አስደናቂ ሃብቶች ባለቤት ነች። ይሁን እንጂ ዓለማችን ላይ በጎብኚዎች መዳረሻነት ከሚታወቁት አገራት ተርታ በቀዳሚነት ለመሰለፍ አልቻለችም። በባህላዊ፤ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ እሴቶቿ በብዙ እጥፍ የምታስከነዳቸው አገራት ሃብቶቻቸውን የመጠበቅ፣ የማስተዋወቅና ምቹ መሰረተ ልማት የመገንባትና የመንከባከብ ተግባር በመስራታቸው ብቻ ቱሪዝም የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ኃይል እንዲሆን አስችለዋል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት የቱሪዝም ዘርፉ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ማድረግ እንደሚቻል አምኖ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራ ይገኛል። በተግባርም የገበታ ለአገር፣ የገበታ ለሸገርና የገበታ ለትውልድ እያለ ሰፋፊ ልማቶችን፣ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ።
መንግሥት በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የመዳረሻ ስፍራዎች በማልማት፣ በማስተዋወቅ፣ ጎብኚዎችን በመሳብና አዳዲስ መዳረሻዎችን በመፍጠር ከሃያላኑ ተርታ የሚያሰልፍ ጠንካራ ኢኮኖሚ መፍጠር እንደሚቻል አምኗል። ከ110 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያላት ኢትዮጵያ አዳዲስ ከገነባቻቸው የሳይንስ ሙዚየም፣ የእንጦጦ ፓርክ፣ የገበታ ለአገር ፕሮጀክቶችና ሌሎችም የቱሪዝም መዳረሻ ልማት በአግባቡ ከተጠቀመችና ወደ ምርትነት ከቀየረች ከዓለም አቀፍ ቱሪስቱ በላይ በአገር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ብቻ ተጠቅውሞ የቱሪዝም ገቢን መጨመር፣ ማነቃቃትና የሚፈለገው ደረጃ ማድረስ እንደሚቻል የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።
ከአዳዲሶቹ የመዳረሻ መስዕብ ስፍራዎች ባሻገርም ነባር ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓምድራዊ ሃብቶችን በሚገባ አስተዋውቆና ጠብቆ የአገርንና የዜጎችን ገቢ ማሳደግ እንደሚያስፈልግም እነዚሁ ምሁራን ያነሳሉ።
የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚሰጡት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፍ የምታገኘው ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ነው። በተለይ ቱሪዝም ከአምስቱ ዋና ዋና የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ምሰሶዎች እንደ አንዱ ተወስዶ ሰፊ ስራዎች መሰራት መጀመራቸው የገቢ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል። የዝግጅት ክፍላችንም ይህንን መረጃ መሰረት በማድረግ ክልሎች የከተማ አስተዳደሮችና የቱሪዝም መስዕብ አስጎብኚ ተቋማት “ከውጪና አገር ውስጥ ጎብኚዎች በ2015 በጀት ዓመት ምን ያህል ገቢ አስገቡ” የሚለውን መረጃ ወደእናንተ ለማድረስ ወድዷል።
የሲዳማ ክልል
የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ የውጪና የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ መልክዓ ምድሮች፣ ባህል ታሪክና ሀይቆች ባለቤት ነው። በተለይ በሃዋሳ ከተማ ዙሪያ የሚገኘው ሀይቅና ተወዳጅ ገፅታ የበርካታ ጎብኚዎችን ቀልብ ይስባል። ከጊዜ ወደ ጊዜም የጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረና በኢትዮጵያ ተመራጭ የመዳረሻ አካባቢ እየሆነ ነው። በዚህ ምክንያት ከዘርፉ የሚገኘው ገቢም እንዲሁ እያደገና ብዙሃን በተፈጠረው የስራ እድል ምክንያት በኢኮኖሚው ተጠቃሚ እየሆኑ ነው።
ክልሉ በ2015 በጀት ዓመት ብቻ ከቱሪዝም ዘርፍ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ይፋ አድርጓል። የሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ አበበ ማሪሞ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት፤ የቱሪዝም ሀብቱን በአግባቡ አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ ይናገራሉ። በዚህም በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት ከቱሪዝም ዘርፉ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል።
የሲዳማ ክልል ካለው ውብ መልክዓ ምድር፣ የአየር ፀባይ፣ ተፈጥሯዊና ባሕላዊ ሀብቶች አኳያ ከፍተኛ የቱሪዝም መስዕብ ያለው መሆኑን አንስተው፤ ይህን ሀብት ወደ ቱሪዝም ኢንዱስትሪና ኢኮኖሚ ገቢ ለመቀየር የመዳረሻ ልማት እየተካሄደ እንደሚገኝ ይገልፃሉ።
“በ2015 በጀት ዓመት 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ የውጭና የአገር ውስጥ ቱሪስቶች ሲዳማ ክልል ጎብኝተዋል” የሚሉት ኃላፊው፤ ወደ ኢትዮጵያ ከሚገቡት የውጭ ቱሪስቶች መካከል ወደ ሲዳማ ክልል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቱሪስት የገባ መሆኑን አንስተዋል። በተጨማሪም የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን ጠቅሰው፤ የቱሪስት ፍሰቱ ለገቢው ማደጉ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ነው ያስረዱት።
ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ በቱሪስት መስዕብ ስፍራነታቸው ከሚጠቀሱ ቦታዎች መካከል አንዱ የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል ነው። አካባቢውን በርካታ የአገር ውስጥና የውጪ አገራት ጎብኚዎች ያስተናግዳል። በክልሉ እንደ ጨበራ ጩርጩራ እና ኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ያሉ የተለያዩ የቱሪስት መስዕቦች ይገኛሉ። በዳውሮ ዞን እና ኮንታ ልዩ ወረዳ መካከል የሚገኘው እና ከ29 የሚበልጥ አጥቢ የዱር እንስሳትን በውስጡ የያዘም ነው።
የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ዝርያው እየተመናመነ የመጣው የአፍሪካ ዝሆን፣ ጎሽ፣ ዲፋርሳ፣ ከርከሮ፣ ሳላ እና እንደ አጋዘን ያሉ የዱር እንስሳት እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በዚሁ ክልል ከሚገኙ የተፈጥሮ መስዕቦች መካከል አንዱ የንጉሥ ሃላላ የድንጋይ ካብ አንዱ ሲሆን፤ በገበታ ለአገር ፕሮጀክት ውስጥ የተካተተው ሃላላ ኬላ ሎጅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጎብኚዎች የአይን ማረፊያ መሆኑ ይታወቃል።
በገበታ ለአገር ከሚለሙ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው ኮይሻ ፕሮጀክት የሚገኘው በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሲሆን በተጨማሪም በሸካ ዞን የሚገኘው ጥብቅ ደን፣ የከፋ የጫካ ቡና እንዲሁም ሰፊ ሽፋን ያለው ደን ከመስዕብ ስፍራዎቹ መካከል ናቸው። የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ በዚሁ ክልል የሚገኝ ሲሆን፤ በውስጡም ልዩ ልዩ የዱር እንሰሳትና ዕፅዋት ይገኙበታል። ክልሉ በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመትም ከላይ የጠቀስናቸውን የመስዕብ ስፍራዎች በማስጎብኘት አንድ ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ገቢ ማስገባቱን ለዝግጅት ክፍላችን ይፋ አድርጓል።
የክልሉ የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ “የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን በማበረታታት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ በመሰራቱ አንድ ነጥብ 3 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ወደ ክልሉ ገብተዋል” ብለዋል። በተጨማሪ 1ሺ600 የውጭ ሀገር ጎብኚዎች የመስዕብ ስፍራዎቹን መጎብኘታቸውን አስታውቀዋል።
ኦሮሚያ- ቢሾፍቱ ከተማ
ከኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ በቱሪዝም ዘርፍ በርካታ የአገር ውስጥና የውጪ አገር ጎብኚዎችን ከሚስቡ መካከል ነች። በውስጧ በርካታ ሃይቆችን የመዝናኛ ስፍራዎች፣ ሎጆች እና ለኮንፍረንስ ቱሪዝም የሚሆን የመሰብሰቢያ አዳራሾችን በመያዟ ምክንያት ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ነች። ከአዲስ አበባ በ45 ኪሎ ሜትር ርቀት የምትገኘውና በአዳማ የፍጥነት መንገድ በቀላሉ የምትገናኘው ይህችው ከተማ ከሁሉም አቅጣጫ ለመዝናናት እና ለስብሰባ በሚል እንግዶች በየቀኑ ገብተው ይወጡባታል።
የውጪ ጎብኚዎችም ከዋና መዲናዋ በቅርብ ርቀት የምትገኘውን ቢሾፍቱን በስፋት ምርጫቸው እንደሚያደርጓት መረጃዎች ያሳያሉ። ይህንን ተከትሎ በ2015 በጀት ዓመት 3ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል።
የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አለማየሁ አሰፋ ይፋ እንዳደረጉት፤ በከተማዋ ከተሰበሰበው ገቢ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ከሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የተገኘ ነው። የቢሾፍቱ ከተማ በተለይ በሃይቆቿ ዙሪያ በሚገኙ 18 የሚደርሱ ሎጆች በከተማዋ ባሉ መዝናኛ ስፍራዎች እና ለዋና ከተማው ቅርብ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ጎብኚዎች ተመራጭ ያደርጓታል።
አዲስ አበባ
በኢትዮጵያ በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ ከፍተኛ ገቢ ከሚያስገኙት መካከል በቀዳሚነት ትጠቀሳለች። የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እና የልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መገኛ የሆነችው የአዲስ አበባ ከተማ የጎብኚዎችን ቀልብ ትስባለች። በተለየ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት ተገንብተው በተጀመሩ ገበታ ለሸገር፣ የእንጦጦ ፓርክ እና መሰል የቱሪዝም መዳረሻዎች ተመራጭ እየሆኑ ነው። በከተማዋ የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት የሚያስመሰክሩ ቅሪተ አካላት የሚገኙበት ብሄራዊ ሙዚየምን ጨምሮ 18 የሚደርሱ ሙዚየሞች የአዲስ አበባ ድምቀቶችና የጎብኚዎች ምርጫ እንደሆኑ ይታወቃል። በተለይ የሆቴልና ሆስፒታሊቲ (ኮንፍረንስ) ቱሪዝምን ጨምሮ ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን ታስተናግዳለች።
የኢትዮጵያ አየር መንገድን የያዘችው አዲስ አበባ ከውጪ ልዩ ልዩ የአገሪቱን ክፍሎች ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶች በቅድሚያ አርፈውና ዙሪያ ገባዋን ተመልክተው የሚሄዱባት ነች። ከዚህ የተነሳ በቱሪዝም ከሚገኝ ገቢ ከፍተኛውን ድርሻ ትወስዳለች። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የ2015 የበጀት ዓመት አስመልክቶ እንዳስታወቀው፤ ከውጭ ቱሪስቶች 30 ነጥብ 56 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ 39 ነጥብ 12 ቢሊዮን ብር ገቢ ተደርጓል። ይህ የተገኘው 622 ሺህ 702 ከሚሆኑ የውጭ ጎብኚዎች መሆኑንም የቱሪዝም መዳረሻ ልማትና የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ማስፋፋት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ዓይናቸው ተናግረዋል።
አማራ ክልል
በኢትዮጵያ በቱሪስት መዳረሻነታቸው ከሚጠቀሱት መካከል ቀዳሚው የአማራ ክልል ነው። በተለይ በተፈጥሮ፣ በቅርስ በባህልና ሃይማኖታዊ በዓላት ምክንያት በርካታ ቱሪስቶች የክልሉን ደጃፍ ያንኳኳሉ። በጎንደር ፋሲለደስ (ጥምቀትና ልዩ ልዩ በዓላትን ጨምሮ)፣ በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ፣ በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት (ጥምቀትን በላሊበላ ጨምሮ)፣ በጮቄ ተራራ በጣና ዙሪያና ገዳማት እና ሌሎችም እጅግ በርካታ በሆኑ የክልሉ የመስዕብ ስፍራዎች የውጪና የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ይገኛሉ። በዚህም ከስራ እድል ፈጠራና ከገቢ አንፃር ቱሪዝም በክልሉ ትልቅ ድርሻን ይወስዳል።
ክልሉ በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት ብቻ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል። የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዓባይ መንግሥቴ ለዝግጅት ክፍላችን እንዳስታወቁት፤ በክልሉ በ2015 በጀት ዓመት በተፈጠረው አንፃራዊ ሰላምና ፀጥታ በርካታ ጎብኚዎች ወደ ክልሉ በመምጣታቸው ከቱሪዝም ዘርፍ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል። በገቢው ረገድም የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ድርሻ ከፍተኛ ነው።
እንደ መውጫ
የኢትዮጵያ መንግሥት የቱሪዝም ዘርፍ በኢትዮጵያ በገቢና ስራ ፈጠራ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው በማመን ትኩረት ሰጥቶት ልዩ ልዩ የልማት ስራዎችንና ታላላቅ ፕሮጀክቶችን እየገነባ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል የወንጪ ደንዲ፣ በአማራ ክልል የጎርጎራ፣ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ የኮይሻ እንዲሁም በአዲስ አበባ ገበታ ለሀገር፣ ለሸገር እና የመሳሰሉት ይገኙበታል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ለዜጎች የስራ እድል ከመፍጠራቸው ባሻገር ከፍተኛ ገቢ እንደሚያስገኙ ታምኖባቸዋል።
ቀድመው ከተጠናቀቁት ውስጥም ከፍተኛ ገቢ በማስገባት ላይ የሚገኙ የእንጦጦ፣ የአንድነት ፓርክ እና ሌሎች ቦታዎችንም መጥቀስ ይቻላል። ከእነዚህ አዳዲስ የመስዕብ ስፍራዎች ውጪ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ፣ በቅርስ፣ በቀደምት የህንፃ ጥበብና ስልጣኔ፣ በውብ መልክዓምድር እንዲሁም በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ 13 የሚደርሱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ይገኛሉ።
የመዳረሻ ሃብቶች ለውጪና ለአገር ውስጥ ጎብኚዎች አስተዋውቆ የገቢ ምንጭ ለማድረግ እየተሰራ ያለው በጎ ጅምር መኖሩን በምሳሌነት ተነስቷል። ይሁን እንጂ የሙሉ አቅም ተጠቃሚነትን ከማሳደግ አኳያ ቀሪ ስራዎች እንዳሉ መገንዘብ ያሻል። የዘርፉ ምሁራንም ኢትዮጵያ በቱሪዝም ያላትን ሀብት ብቻ በአግባቡ ብትጠቀም የኢኮኖሚ አቅማቸው ፈርጣማ ከሆኑ አገራት ተርታ እንደሚያስመድባት በማንሳት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ይወተውታሉ።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2015