ዶክተር ሰለሞን ቡሣ በዓይን ህክምና በስፔሻሊስት ደረጃ ሰልጥነው፤ ከ1958 ዓ.ም አንስቶ ለ46 ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ ተቋማት ሕዝብን አገልግለዋል፡፡ የአለርት ሆስፒታልን ከሶስት ዓመታት በላይ በሜዲካል ዳይሬክተርነት የመሩ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም በሆስፒታሉ የአይን ህክምና ክፍል ኃላፊ ሆነው በመስራት ላይ ይገኛሉ።
ዶክተር ሰለሞን በሆስፒታሉ ቆይታቸው ቁጥራቸው በርከት ያሉ ሀኪሞች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ስፔሻላይዜሽን ፕሮግራም እንዲያመሩ የሚያግዙ ስለመሆናቸው ይነገራል፡፡ ከጤና ሚኒስቴር ባገኙት ድጋፍና መመሪያ በአለርት ሆስፒታል የድንገተኛ ህክምና ማዕከል እንዲቋቋም ከመስራት በተጨማሪ፤ ከውጪ አጋር አካላትን በማስተባበር ከፍተኛ የዋጋ ግምት ያላቸውን የዓይን ህክምና መሣሪያዎች በማስገባት ተገልጋዮች መፍትሄ እንዲያገኙ በማድረግ በኩል የመሪነት ሚናቸውን ተወጥተዋል፡፡
ዶክተር ሰለሞን የዓይን ህክምና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እንዲስፋፋ ብዙ ጥረት አድርገዋል። በተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ፣ የግል የጤና ኮሌጆችና ማሰልጠኛዎች፣ እንዲሁም በሚያገለግሉበት የአለርት ሆስፒታል የዓይን ህክምና ባለሙያዎች የተሻለ ስልጠና አግኝተው አይነ ስውርነትን እንዲከላከሉ ዕውቀታቸውን ለብዙዎች አጋርተዋል፡፡
በደብረብርሃን፣ በአምቦ፣ በወረኢሉ፣ በዶዶላ፣ በግንደበረትና በአጣጥ ሆስፒታሎች በዓይን ሞራ የሚሰቃዩ ዜጎች ህክምና እንዲያገኙ በማድረግና ሥራውም ዘለቄታ እንዲኖረው ከፍተኛዉን ሚና ተጫውተዋል፡፡ ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ የአለርት ሆስፒታል የዓይን ህክምና ክፍል ኃላፊ ሆነው እያገለገሉ ያሉት ዶክተር ሰለሞን፤ በቅርቡ በጦርነት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት የተለያዩ ድጋፎች እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴርም የህይወት ዘመን የላቀ የሙያ አገልግሎት ተሸላሚ እንዲሆኑ መርጧቸው ሽልማት አግኝተዋል፡፡ እኛም እኝህን አንጋፋና ከፍ ያለ አበርክቶ ያላቸውን የህክምና ባለሙያ የህይወት ገጽታ የአምዳችን እንግዳ አድርገናቸዋል።ዶክተር ሰለሞን ቡሳ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የጀመሩት ከአምቦ 10 ኪሎ ሜትር ያህል በሚርቀው ጉደር በሚባል አካባቢ ደጃዝማች በሻህ አቡዬ ትምህርት ቤት ነው፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከፍ ባለ ትጋትና የትምህርት ፍቅር ካጠናቀቁ በኋላ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል ያመሩት ወደ አምቦ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው።
ዶክተር ሰለሞን በተለይም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከጀመሩ በኋላ የህክምና ሙያ። የአውሮፕላን አብራሪነት (ፓይለት) መሆን እንዲሁም የኢንጂነሪንግ የትምህርት ክፍሎች በህብረተሰቡ ዘንድም ጥሩ ተቀባይነት ያላቸው ጎበዝ ተማሪዎችም የሚያገኟቸው እድሎች መሆናቸው እየተገነዘቡ ሲመጡ ከህክምና ሙያው ይልቅ ወደ አብራሪነት (ፓይለት) የመሆን ፍላጎታቸው በውስጣቸው አደገ።
በዚህም ፓይለት ለመሆን የሚያስችላቸውን ፈተና ተፈትነው በሚገባ አለፉ፤ ነገር ግን ህልማቸውን እውን የማያደርጉበት ሌላ ተግዳሮት ገጠማቸው። ወደቤተሰብም ሃሳቡ ደርሶ ስለነበር በቀላሉ ማለፍን ሳይችሉ ቀሩ።
“ ….በወቅቱ እኔ ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚቻል ሁኔታ ፓይለት የመሆን ፍላጎት ነበረኝ። ነገር ግን አጎቴ ለአባቴ ልጅህ በምንም ዓይነት ፓይለት መሆን የለበትም፤ ፓይለት ከሆነ ቢሞት እንኳን ልትቀብረው አትችልም፤ በማለት አባቴን አሳመኗቸው፤ በዚህም አባቴ በእኔ ፓይለትነት ሳይስማሙ ቀሩ “ በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ።
ወቅቱ የወላጆች ቃል ፍጹም የሚሰማበት ቤተሰብ ካስቀመጠው መስመርም ወጥቶ መገኘት ብዙ ዋጋን የሚያስከፍል፤ በጠቅላላው ለመውጣትም የማይደፈር ነበር። ዶክተር ሰለሞንም ምንም እንኳን ህልማቸው ፓይለት መሆን ቢሆንም፤ ሀሳባቸው ተቀባይነት ባለማግኘቱ እያዘኑ የሚመርጡትን የሙያ ዘርፍ ወደ ማሻሻሉ ሄዱ።
በሌላ በኩል “ … እናቴ በዘውዲቱ ሆስፒታል የጤና ረዳትነት ሙያ ተመርቃ ነበር፤ ግን አልሰራችበትም። ቤት ውስጥ ልጆቿ ጉሮሯችንን ሲያመን እንጥላችን ሲወርድ መርፌ ትወጋን ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር ለህክምናው ቀረብ ያለ ፍቅርና ፍላጎት ነበረኝ ማለት ይቻላል፤ ይህም ቢሆን ግን በልጅነቴ ሀኪም እሆናለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር” ይላሉ።
ፓይለት አለመሆናቸው ከልብ ቢያሳዝናቸውም፤ የተሻለ በሚባለው የጤናው መስክ ላይ ለመሰማራት የሚረዳቸውን የከፍተኛ ትምህርት ለመማር ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አቀኑ። ጎንደር ዩኒቨርሲቲም በጤና መኮንንነት ተመድበው ትምህርታቸውን ቀጠሉ።
“…. በወቅቱ ፓይለት የመሆን ህልሜ ሲሰናከል በጣም ቅር ከመሰኘቴም በላይ በአባቴና አጎቴም በጣም አዝኜ ነበር። ለዚህ ምክንያቴ ደግሞ በተለይም አጎቴ ልጃቸው የበረራ አስተናጋጅ (ሆስተስ) ነበረች፡፡ ስራው ይህን ያህል አደጋ አለው መጥፎ ነው ብለው የሚያስቡ ከሆነ ለምን ለልጃቸው ፈቀዱ? እኔ እንዳልገባ ተከለከልኩ፤ ይህ በጣም አሳዝኖኝ ነበር። ያም ቢሆን ግን የኔ መንገድ ሌላ ነበርና ወደ ህክምናው መጣሁ “ በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ።
በወቅቱ እሳቸው ከተማሩበት የአምቦ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ይሁን ከሌሎች ትምህርት ቤቶች ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከ 40 እስከ 50 የሚሆኑ ተማሪዎች ፈተና ይወስዱና ዩኒቨርሲቲን የመቀላቀል እድል የሚያገኙት ሁለት በዛ ከተባለ ሶሰት ተማሪዎች ብቻ ነበሩ። እንደ አጋጣሚ ግን ዶክተር ሰለሞን 12ኛ ክፍል ሲደርሱ አሰራርን የሚቀይሩ ርዕሰ መምህር መጡላቸውና ከ ዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ያለውን ትምህርት በፈተናው እንዲካተት አደረጉ፤ በዚህም እሳቸውን ጨምሮ ቁጥራቸው ከፍ ያሉ ልጆች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የሚቀላቀሉበትን እድል ስለማግኘታቸው ያስታውሳሉ።“ ……እንግዲህ አሁን ፓይለትነቱን ተከልክያለሁ መሆን የምችለው የጤና ባለሙያ ነው፤ ስለዚህ ምርጫዬን አስተካክዬ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ገባሁ። በሚገርም ሁኔታ ግን ዩኒቨርሲቲውን ከተቀላቀልኩ በኋላ የማደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ደስ ብሎኝ የማደርጋቸው ሆኑልኝ። አንደኛ ትምህርቴ ህክምና መሆኑ ጆሮዬ ላይ ማዳመጫ አድርጌ መታየቴ በጣም ያስደስተኝ ነበር። ሌላው ደግሞ የታመመን ሰው አክሞ አድኖ ማየት ልዩ ስሜት ይፈጥርብኝ ጀመር፡፡ “ በማለት ከአጀማመሩ የወደዱትን የህክምና ትምህርት ይገልጹታል።
የህክምና ትምህርትን በመማር ላይም ሆነ ከዛ በኋላ ተመርቀው በሥራ ላይ ሲገቡ፤ ሙያው ትልቅ ኃላፊነት የሚጠይቅ ኋላ ላይ ደግሞ የታከመው ሰው ድኖ ሲሄድ፤ እርካታው እጥፍ ድርብ የሆነ የሙያ ዘርፍ ስለመሆኑ መመስከር እንደሚችሉ ይገልፃሉ።
ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በጤና መኮንንነት ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ በቀጥታ ስራን የጀመሩት ባሌ ጎባ ሆስፒታል ነበር።”…….በወቅቱ አብረን የተመረቅን ተማሪዎች የተመደብነው አንድ ላይ ነበር፡፡ በስራችንም እርስ በእርሳችን በጣም መልካም የሚባል ፉክክር እናደርግ ነበር፤ እንተራረባለንም፡፡ ከዚህ አንጻር ሥራ እና ትምህርቱ ለእኔ በጣም አስደሳች ሙያውንም ከልቤ እንድወደው አስገደደኝ “ ይላሉ።
እርሳቸውና ጓደኞቻቸው በዚህ መልክ ለታካሚዎቻቸው ልዩ ትኩረትን እየሰጡ በጣም በኃላፊነት ስሜት ሙሉ ጊዜያቸውን ተጠቅመው የሚሰሩ መሆናቸው ደግሞ በተለይም ዶክተር ሰለሞንን ከፍ ላለ ኃላፊነት አሳጫቸው። በዚህም ዶዶላ ገናሌ አውራጃ ውስጥ የአውራጃው የጤና ስራ አስኪያጅ በመሆንም እንዲሠሩ ተላኩ።
ዶዶላ ውስጥ ዶክተር ሰለሞን ከጤና መኮንንነት ስራቸው ባሻገር በዛ ያሉ ህብረተሰብን ሊጠቅሙ የሚችሉ ኃላፊነቶችን ሲወጡ ቆይተዋል። መንግስት ህብረተሰቡ ተበታትኖ ከሚኖር ይልቅ፤ በሰፈራ ሊሰባሰብ ይገባል ማለቱን ተከትሎ በመንደር የማሰባሰብ ስራ ሲሰራ እርሳቸው ደግሞ ሌላውን በማስተባበር ለህብረተሰቡ መጸዳጃ ቤት። መንገድ። ማብሰያ ቤቶች እንዲሰሩ በማስተማርና ሰርቶ በማሳየት በኩል ላቅ ያለ ሚናንም የተጫወቱ ነበሩ።
በሌላ በኩልም ዶዶላ ላይ የባህል መድሃኒት አዋቂዎችን በማደራጀትና መድሃኒቶቻቸውን ወደፓስተር ኢንስቲትዩት ልከው መድሃኒቶቻቸው ተቀምመው ውጤት የሚያመጡበት ነገር እንዲፈጠር ለማድረግ እየሰሩ ነበር፡፡ ሆኖም የአካባቢው የፖለቲካ ሁኔታ ምቾት ስላልሰጣቸው ለመልቀቅ መገደዳቸውን ያብራራሉ።
አካባቢውን ለቀው አዋሽ ሸለቆ ወደሚባለው ቦታ በመሄድ ሥራቸውን መጀመራቸውን የሚናገሩት ዶክተር ሰለሞን፤ በዛም ለጥቂት ጊዜያት ካገለገሉ በኋላ ለተሻለ ስራና እድገት ወደአዲስ አበባ መጡ፡፡ “…… በ1977 ዓ.ም አለርት ሆስፒታል የጤና መኮንን እንፈልጋለን የሚል የስራ ማስታወቂያ አውጥቶ ተመለከትኩ፡፡ ጊዜ ሳላጠፋ ተመዘገብኩ፤ የጽሁፍና የቃልም ፈተና ተፈትኜ በማለፌ ሆስፒታሉን ተቀላቀልኩ” ይላሉ።
ዶክተር ሰለሞን ሥራቸውን በአለርት ሆስፒታል ከጀመሩ በኋላ፤ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ከመወጣታቸው በላይ ተጨማሪ ወይም የማያውቁትን ነገር ለማወቅ በመፈለግ ውሏቸውን በግቢው ውስጥ በሚገኘው የአይን ሀክምና ክፍል ስለማድረጋቸው ይናገራሉ።“…
ምን ጊዜም ሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ እስካለሁ ድረስ የተሰጠኝን ስራ በሚገባ ካጠናቀቅሁ በኋላ የአይን ክፍል ውስጥ በመሄድ ምን እንደሚሰራ እመለከት ነበር፡፡ በተደጋጋሚ ማየቴ ደግሞ የአይን ህክምና የመፈለግ ደረጃ ላይ አደረሰኝ፡፡ ይህ ፍላጎቴ ከክፍሉ ባለሙያዎች ጋር በመሆን አንዳንድ ስራዎች ላይ ወደመሳተፍ ወሰደኝ፤” በማለት የአይን ህክምናን የተቀላቀሉበትን ሁኔታ ያስታውሳሉ።
ዶክተር ሰለሞን በዓይን ህክምናው ዘርፍ ለመሰማራት ያደረባቸውን ፍላጎት ዝም ብለው አላዩትም፡፡ ይልቁንም የተለያዩ የውጭ አገር ነጻ የትምህርት እድሎችን ማፈላለግ ጀመሩ፡፡ ወትሮውንም ቢሆን እንጀራቸው ይኸው ነበርና ፍለጋቸው ተሳክቶ ታንዛኒያ “ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዳሬሰላም” በመሄድ በዓይን ህክምና ሙያ ለሁለት አመት ሰለጠኑ።“…..ዳሬሰላም የህክምና ትምህርት የምንማረው ከተለያየ አገር የመጣን ሰባት ልጆች ነበርን፡፡ በሚገርም ሁኔታ ደግሞ ሁሉም በስራው ላይ ያሉ ዶክተሮች ናቸው። እኔ ደግሞ የጤና መኮንን ነኝ፡፡ ግን በፈጣሪ እርዳታ ትምህርቴን ለማጠናቀቅ የቻልኩት፤ ከሁሉም አንደኛ ሆኜ ነው “ ይላሉ።
የመጀመሪያውን የትምህርት ዓመት ጨርሰው ሁለተኛው ዓመት ላይ ሲደርሱ ከሁለም የበለጡ ስለነበር አንደኛ ዓመቶችን “አናቶሚ “የሚባል ትምህርት (ኮርስ) እንዲያስተምሩ ተደርጎ በዛም ገንዘብ ይከፈላቸው እንደነበር በማስታወስ፤ የትምህርት ቤት ቆይታቸውን ያብራራሉ።
የውጭ አገር ትምህርታችውን አጠናቀው ሲመጡ፤ ሥራቸውን የቀጠሉት አለርት ሆስፒታል የአይን ህክምና ክፍል ውስጥ ነበር። ዶክተር ሰለሞን ስራቸውን በትጋትና በኃላፊነት ስሜት እየተወጡ ጎን ለጎን ደግሞ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን የመማር ሀሳብ ወጠኑ፡፡ እሱንም ‹‹በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሌጎስ›› በመማር አጠናቀቁ።
የ37 ዓመት የአለርት ሆስፒታል ቆይታ
አለርት ሆስፒታልን በሥራ ባልደረባነት ሲቀላቀሉ የሚሰጠው አገልግሎት ውስን ነበር የሚሉት ዶክተር ሰለሞን፤ በተለይም ሆስፒታሉ ለስጋ ደዌ ህሙማን የተቋቋመ ከመሆኑ አንጻር ትኩረቱን ያደረገው የአጥንት ህክምና ላይ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሽታው ሌሎች የሰውነት ከፍሎችንም በአለርጂ መልክ የሚነካ በመሆኑ የሞቱት ጀርሞች በሰውነታቸው ላይ ሲሄዱ ሰውነታቸው በመቆጣት በጣም ስለሚታመሙ ይህንን ለማከም የሕክምና እርዳታ ይሰጥ እንደነበር እንደሚያስታውሱ ይገልፃሉ።
የቆዳ ህክምናን በመስጠት በኩል አለርት የአገሪቱ ሪፈራል ማዕከል (ሴንተር) ነበር። የአይን ህክምናን በተመለከተ የተጀማመሩ ነገሮች ቢኖሩም፤ ያን ያህል ጠንከር ብሎ የወጣ እንዳልነበር የሚያስታውሱት ዶክተር ሰለሞን፤ አይናችንን እንድንከፍትና እንድንዘጋ የሚያግዙንን ነርቮች አሉ፡፡ የስጋ ደዌ ታማሚዎች እነዚህ ነርቮቻቸው ስለሚዳከሙ አይናቸውን ከጉዳት ለመከላከል ይቸገራሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ አይናቸው በተለያየ ምክንያት እንዲቆስል ቁስሉ ጠባሳ ሆኖ አይናቸው እንዲጠፋ እንደሚያደርግ ይናገራሉ።
ይህንን ታሳቢ በማድረግም “ክርስቲያን ብላይንድ ሚሽን” የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት በሆስፒታሉ ውስጥ የአይን ህክምን ክፍል በተጠናከረ ሁኔታ መቋቋም አለበት ብሎ የአይን ህክምና ክፍሉ እንዲቋቋም ስለማድረጉ ይናገራሉ።
“……በወቅቱ በአገሪቱ ያሉ የዓይን ሀኪሞች ቁጥር ከ10 በታች ነበር። ነገር ግን ክፍሉ የግድ አስፈላጊ ስለነበር ከጀርመን አገር ባለሙያ መጥተው ስራው እንዲጀመር ሆነ። ህክምናው የሚሰጠውም ለስጋ ደዌ ህሙማኑ ብቻ ነበር። ነገር ግን ህክምና ተቋሙ በየክፍለ ሀገሩ እየተዘዋወረ አገልግሎት ሲሰጥ በህዝቡም ዘንድ ስራው እየታወቀ ሲመጣና ተፈላጊነቱ ሲበዛ ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል አገልግሎቱን እንዲያገኝ ተመቻቸ፡፡ “ ይላሉ።
ሆኖም በአንዲት ክፍል ውስጥ ይሰጥ የነበረው ህክምና በቂ ስላልነበርና ቦታም ስለጠበበ በአገሪቱ የመጀመሪያው የአይን ሀኪም የሆኑት ዶክተር ፍቃደ መንግስቱ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ በመጠየቅና ኬንያ ሄደው “የኩኩዩ” የአይን ሆስፒታልን በመጎብኘት የአለርት ሆስፒታልን ሙሉ ገጽታውን ስለመቀየራቸውም ይናገራሉ።
“ የማየው አለርትን እንደ ራሴ ቤት ነው፤ ብዙ ነገሮችን አውቄበታለሁ፡፡ ለሚሰራ ሰውም ጥሩ የስራ አካባቢ ነው “ የሚሉት ዶክተር ሰለሞን፤ አንድ ሰው አለርት ሆኖ ስራውን በአግባቡ ከሰራ የተቸገሩ ሰዎችን ሙያውና አቅሙ በፈቀደ መጠን ማገልገል ከቻለ ከእንቅፋት የፀዳ የስራ አካባቢ ስለመሆኑ ይመሰክራሉ።
ዶክተር ሰለሞን የተቸገረን መርዳት፣ ህብረተሰብን ማገልገል በጎ ምግባራቸው ነው፡፡ ይህንን ሲያደርጉም ለመለካት የሚከበድ እርካታ እንደሚሰማቸው ይገልጻሉ። አንዳንድ ጊዜ ይላሉ ዶክተር ሰለሞን፤ ሰዎች አገልግሎት ፈልገው መጥተው አገልግሎቱን ቢያገኙም የሚታዘዝላቸውን መድሃኒት ለመግዛት አቅም ያጣሉ። እንዲህ ያሉ ብዙ አጋጣሚዎችን ዶክተር ሰለሞን አያልፉም፡፡ የመድኃኒት መግዣ በመስጠት ችግራቸውን ይካፈላሉ፡፡ ይሄ አንዱ የበጎ ምግባራቸው ማሳያ ነው፡፡
ዶክተር ሰለሞን የህክምና አገልግሎት የሰጡበትን ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተርነት ሆነው ለአራት ዓመታት መርተዋል። በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ሆስፒታሉ አንድ እርምጃ የሚራመድበትን ተገልጋዩም ሁሉን አቀፍ አገልግሎትን በአንድ ቦታ የሚያገኝበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚችሉትን ያህል ጥረት አድርገዋል፡፡
ዶክተር ሰለሞን ለሙያውም ለአለርት ሆስፒታልም ልዩ ቦታ ስላላቸው ለስራው ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። ሆስፒታሉም እኝህን ታታሪ ባለሙያ ሊያጣቸው ባለመፈለጉ ጡረታ ወጥተው እንኳን ሊለቃቸው አልፈለገም። እሳቸውም ከአለርት የተሻለ ክፍያን የሚከፍሉ ሌሎች የግል የህክምና ተቋማት ሊወስዷቸው ጥሩ ደመወዝን ቢያቀርቡላቸውም ያገለገሉበት ሆስፒታል ያቀረበላቸውን ጥያቄ ገፍተው የሌሎቹን ጥሪ በፍጹም አልፈቀዱም። ደመወዙ አጥጋቢ ባይሆንም ህዝቤን ማገልገል ይበልጥብኛል ብለው በሆስፒታሉ ማገልገልን መርጠው አሁንም በሥራ ላይ ይገኛሉ።
የዓይን ህክምና ክፍሉን ለማጠናከር የሚያደርጉት ጥረት
ዶክተር ሰለሞን ለስራቸው ቀናይ ከመሆናቸው በላይ በተለይም የአይን ህክምና ክፍሉ ተጠናክሮ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት የሚሰጥ እንዲሆን የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። ለዚህ ማሳያው ደግሞ ከአይን ህክምና ክፍሉ በቅርብ ርቀት ላይ እየተሰራ ያለው የመነጽር ማምረቻ ፋብሪካ ነው። አሁን ላይ የፋብሪካ ግንባታ ተጠናቅቆ አስፈላጊው የመስሪያ ግብዓቶች ግዢም ተፈጽሞ ወደአገር ውስጥ በመጓጓዝ ላይ ሲሆን አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የመነጽር ማምረት ስራውን እንደሚጀምር በደስታ ስሜት ይናገራሉ።
“…..ይህ ፋብሪካ ህብረተሰቡ በመነጽር ግዢ ከፍ ያለ ወጪን ለማውጣት እንዳይዳረግ ከማድረጉም በላይ በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝተው መጠቀምንም የሚያስችል ነው” ይላሉ።
ዶክተር ሰለሞን “ክርስቲያን ብላይንድ ሚሽን” የተባለው ግብረ ሰናይ ደርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የዓይን ህክምና አገልግሎት እጅግ በጣም ድጋፍ ያደርጋል ያሉ ሲሆን፤ አሁን ላይ 12 ሆስፒታሎችን ከደመወዝ በስተቀር የሚያስፈልጋቸውን የመድሃኒት የህክምን መሳሪያና ሌሎችንም በማሟላት ብዙ አበርክቶ እያደረገ ስለመሆኑ ይናገራሉ። የአለርት የአይን ህክምና ክፍልም የዚህ እድል ተጠቃሚ ነው።
በሌላ በኩልም በአገሪቱ ያሉ 12 የዓይን ህክምና የሚሰጡ የመንግስት ሆስፒታሎች ጥምረት እንዲፈጥሩ ሆኗል፤ የጥምረቱ ፕሬዚዳንት ደግሞ ዶክተር ሰለሞን ናቸው፤ በዚህም አስፈላጊ መሳሪያዎችን በማሰባሰብ በማንቀሳቀስና ተደራሽ በማድረግ በኩል የበኩላቸውን እየተወጡም ስለመሆኑ ያብራራሉ።
በዚህ ተግባርም በመላው አገሪቱ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በዓይን ህመም ምክንያት ለከፋ ስቃይ እንዳይዳረጉ ከሙያ አጋሮቻቸው ጋር በመቀናጀት ዶክተር ሰለሞን የበኩላቸውን እየተወጡም ይገኛሉ።
የመጀመሪያው የህጻናት የአይን ህክምና ማዕከል
ዶክተር ሰለሞን ለሙያው ባላቸው ፍቅርና ሰውን ለመርዳት ባላቸው ጉጉት ለጋሽ አካላትን በማስተባበር ከሚሰሩት ስራ መካከል አንዱና ብቸኛው የሆነው የህጻናት የአይን ህክምና ማዕከል በቅርብ ቀን ውስጥ እውን ይሆናል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።
“…..የህጻናት የአይን ህክምና ማዕከል በአገሪቱ ውስጥ የለም፤ ይህን መስሪያ ድጋፉም መጀመሪያ ለሚኒሊክ ሆስፒታል ነበር የተሰጠው ነገር ግን እነሱ በወቅቱ ሊጠቀሙበት ስላልቻሉ በጎ አድራጊው ተቋም እድሉን ለታንዛንያ ሊሰጥ መሆኑን በሰማሁ ጊዜ የመቀስቀስ (ሎቢ) የማድረግ ስራዎችን በመስራት እድሉ ለአለርት እንዲሰጥ ሆነ። በአሁኑ ወቅትም አስፈላጊው ዝግጅት ሁሉ ተጠናቆ የግንባታ ስራውን የሚያከናውነውን ድርጅት ለመምረጥ ጨረታ ሊወጣ ነው”ሲሉ አጫውተውናል።ህንጻው ተገንብቶ ሲጠናቀቅም የራሱ የመመርመሪያ። የቀዶ ህክምና። የመኝታ ክፍል። ስለሚኖረው ህጻናትን በተሻለ ሁኔታ ለማከም የሚያግዝ ስለመሆኑም ይናጋራሉ።
ሙያን ሳይሰስቱ ለሌሎች መስጠት
ኢትዮጵያ ውስጥ ለ120 ሚሊየን ህዝብ 206 የአይን ህከምና ስፔሻሊስቶች። 54 ካተራክት ሰርጅኖች። 315 ኦፍታልሚልክ ነርሶች ብቻ ናቸው ያሉት። የህክምን ተቋማቱም በተለይም በመንግስት የሚተዳደሩት 47 ሲሆኑ 5 ስፔሻሊቲና ሰብ ስፔሻሊቲ አገልግሎቶችን የሚሰጡ አሉ። ይህ ቁጥር በቂ አይደለም። በመሆኑም እኔና ጓደኞቼ በፍቃደኝነት በተለያዩ የክልል ከተሞች ላይ እየተዘዋወርን የህክምና አገልግሎት እንሰጣለን በዚህ የሚጠቀመው ሰው ቁጥር ቀላል አይደለም።
“….እውነት ለመናገር ከትምህርት ቤት ተመርቄ ከወጣሁባት እለት ጀምሮ በሙያዬ ከእኔ የሚጠበቀውን ሁሉ ለሌሎች ለማድረግ ወደኋላ ብዬ አላውቅም። ለዚህም አቅምን ያበዛልኝ ፈጣሪ ነው። ይህንን ፈጣሪ የሰጠኝን እውቀት ደግሞ ለሌሎች መትረፍ እንዳለብኝ ይሰማኛል። በመሆኑም አቅሜ እስከፈቀደ ድረስ አምላክ የሰጠኝን እውቀት ለህዝቤ ለአገሬ ከማበርከት ወደኋላ የምል አይደለሁም” ይላሉ።
የጤና ሚኒስቴር የህይወት ዘመን ተሸላሚ
ዶክተር ሰለሞን ከወጣትነት እስከ አሁን ድረስ በህክምና ሙያ ላበረከቱት መልካም አስተዋጽኦ ብሎም በአለርት ሆስፒታል ላይ ባኖሯቸው ትልልቅ አሻራዎች ምክንያት የጤና ሚኒስቴር ጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም የዓመቱ የላቀ አስተዋጽኦና የረጅም ዓመት አገልግሎት በማለት ሽልማትን አበርክቶላቸዋል።
“…….ሽልማት ጥሩ ነው፤ በእኔም ላይ ሁለት ነገሮችን ፈጥሮብኛል። በመጀመሪያ ደረጃ ከወጣትነቴ አንስቶ ስራዬን በፍጹም ፍቅርና አክብሮት እንዲሁም ህብረተሰብን በላቀ ደረጃ በማገልገል ስሜት ስሰራ የኖርኩት እሸለማለሁ ብዬ አልነበረም፤ እውነት ለመናገር እሸለማለሁ ብዬም ገምቼ አላውቅም ነበር። ነገር ግን ሁልጊዜ አለርት እንዲያድግ በተለይም የዓይን ህክምና ክፍሉ ከላይ እንዳነሳነው እንዲሰፋና እንዲያድግ ከአጋር ደርጅቶች ጋርም ያለው ቀርቤታ መቆራረጥ ሳይኖረው ተጠናክሮ እንዲሄድ ጥረት አድርጌያለሁ “ ይላሉ።
በመሆኑም በዚህ ልክ እውቅና ማግኘቴ በጣም አስደስቶኛል፤ ነገር ግን ህይወቴ እስካለ ድረስ በስራዬ ላይ ትጋትን እንድጨምር ድርብ ኃላፊነት ነው የጣለብኝ በማለት ሁኔታውን ይገልጻሉ።
በህክምናው ዘርፍ ማየት የሚመኙት
አገሬ አድጋ በህክምናው ዘርፍም እየመጡ ያሉ ወጣት ባለሙያዎች እውቀታቸውን አውጥተው አገርና ወገናቸውን የሚጠቅሙበት አስቻይ ሁኔታ ተመቻችቶ ማየት እፈልጋለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ የህክምና መሳሪያዎች በአገራችን ባለመኖሩ ምክንያት ሰዎች ውጭ ሀገር ሄዳችሁ ታከሙ የሚባለው ነገር ቀርቶ በተቻለ መጠን ዋና ዋናዎቹን እንኳን አሟልተን ለወገናችን መድረስ ብንችልብዬ አስባለሁ።
የህክምና ባለሙያውም ሙያዊ ስነምግባሩን ጠብቆ መስራት አለበት፡፡ ገንዘብን ከማምለክ የሰውን ልጅ በሙያ ለማገዝ ተነሳሽነቱ ሰፍቶ ባይ ምኞቴ ነው።
የቤተሰብ ሁኔታ
ዶክተር ሰለሞን ነርስ ከሆኑትና ከዛሬ ሁለት ወር በፊት በሞት ካጧቸው ባለቤታቸው ሶስት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን የመጀመሪያ ልጃቸው ሶስት ማስተርስ ያላት ሲሆን አንዱ በህብረተሰብ ጤና ዘርፍ ነው፤ ወንዱ ልጃቸው የቻይናዎች ፋርማሲውቲካል ኢንደስትሪ ኃላፊ ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ የኮምፒውተር (አይቲ) ባለሙያ ነው።
ለቤተሰቡም ሆነ ለእኔ ውጤታማነት የባለቤቴ ሚና መረዳት ከፍ ያለ ነበር የሚሉት ዶክተር ሰለሞን፤ በህይወቴ ስኬት እንዲኖረኝ ያደረጉ ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2015