የአማራ ሕዝብ የገጠሙትን ፈተናዎች በሠለጠነ መንገድ ያልፋቸዋል!

 ለአንድ ሕዝብ ተቆርቋሪ ነኝ የሚል ግለሰብ ሆነ ቡድን ተቆርቋሪነቱ የሚገለጸው ለዚያ ማኅበረሰብ ባለው በጎ ኅሊና፣ አስተሳሰብና ተግባር ነው። ይህ በጎ ኅሊና፣ አስተሳሰብና ተግባር የዚያን ማኅበረሰብ ነገዎች ብሩህ ማድረግን ታሳቢ የሚያደርግ፤ ዛሬን በአግባቡ መኖር እንዲችል ሁለንተናዊ አቅም መፍጠር የሚያስችል ሊሆን እንደሚገባ ይታመናል። ከዚያም በላይ ይህንን እውነት መሸከም የሚችል ትውልድ መፍጠርንም ያካትታል።

በተለይም ከትውልድ ትውልድ ሲገላበጡ በመጡ ችግሮች እየተፈተነ የሚገኝ ማኅበረሰብ ተቆርቋሪ ነኝ ብሎ እራሱን የሰየመ ግለሰብ ሆነ ቡድን በዋነኝነት እነዚህን ችግሮች በአግባቡ አውቆና ተረድቶ ለመፍትሔያቸው በብዙ ትዕግስትና ልበ ሰፊነት መንቀሳቀስ፤ እነዚህ ትውልድ ተሻጋሪ ችግሮች መቋጫ አግኝተው፤ ሕዝቡ ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንዲሻገር በኃላፊነት መንገድ መራመድ ይጠበቅበታል።

ከዚህ ውጪ የሕዝቦችን ትናንቶች በማራከስ፣ ዛሬዎች በማጥቆር፣ ነገዎች በማጨለም የሕዝብ ተቆርቋሪ መሆን የሚቻልበት አንዳችም ተጠየቅ ሊኖር አይችልም። ይህ ዓይነቱ በሕዝብ ስም የመነገድ ጸያፍ የጥፋት ስሌት፤ በተለይም በዚህ ዘመን ሕዝብን ሊያስከፍለው ከሚችለው የከፋ ዋጋ አንፃር በከፍተኛ ደረጃ የሚወገዝ፣ በሕዝብ ዛሬዎች ላይ ጥፋትን አምጦ የመውለድ አደገኛ ተግባር ነው።

አሁን ላይ በሀገራችን በተለይም በአማራ ክልል እየሆነ ያለው ከዚህ የተለየ አይደለም፤ ሕዝቡ ችግር ውስጥ ሲሆን የሕዝቡ ችግር እንደማያገባቸው በአደባባይ ሲምሉ ሲገዘቱ የነበሩ ኃይሎች፤ ዛሬ ስለነገዎቹ ተስፋ ሰንቆ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ሲጀምር፤ በተቆርቋሪነት ስም ክልሉን ለከፋ ሁከትና ብጥብጥ ለመዳረግ ለአመታት የቋጠሩትን የጥላቻ ዘር በሕዝቡ ነገዎች ላይ ጨለማን ለመውለድ እያማጡ ይገኛሉ።

በአንድ በኩል ሕዝቡ ዛሬዎቹን አስተማማኝ፤ ነገዎቹን ብሩህ ለማድረግ ብዙ ሀብት አውጥቶ የገነባቸውን ማኅበራዊ እና የመንግሥት የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን በመዝረፍና በማዘረፍ፤ በሌላ በኩል ሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮውን አሸንፎ እንዳይወጣ መሰናክል የሆኑ ተግዳሮቶችን በመፍጠር ከሕዝብ ተቆርቋሪነት ይልቅ ለሕዝብ ያላቸውን ጠላትነት በተጨባጭ አሳይተዋል።

በርግጥ የፖሊስ ኮሌጅ በመዝረፍ እና በማዘረፍ፤ የከተማ የንግድ ሱቆች በማራቆት፣ የሚጓጓዝ ማዳበሪያን ነጥቆ በመሸጥ፣ የመንግሥት የአገልግሎት ተቋማትን በማውደም፣ የእርሻ ጊዜን እና የ12ኛ ክፍል ፈተናን በማስተጓጎል የሚደረግ የሕዝብ ትግል ስለመኖሩ በርግጠኝነት ለመናገር መድፈር፤ የአእምሮ ጤነኝነትን ከማስጠርጠር ባለፈ ፋይዳ የሚኖረው አይሆንም።

ይህ ከተራ ሽፍትነት የሚቀዳ፤ በሕዝብ ተቆርቋሪነት ስላቅ የተከሸነ፤ በጽንፈኝነት እና ከዚህ በሚመነጭ ጥላቻ የጦዘ፤ የአማራን ሕዝብ ሆነ መላውን ሀገር ለተጨማሪ ችግርና ፈተና የሚዳርግ የጥፋት መንገድ ፈጥኖ ሊገታ፤ የዚህ ዓይነት ጥፋት በዚች ሀገር ዳግም ዕጣ ፈንታ እንዳይኖረው በጥልቀት ተምሶ ሊቀበር ይገባል።

ለዚህ ደግሞ የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆነው የአማራ ሕዝብ ያለ ጎትጓች ፈጥኖ ሊንቀሳቀስ ይገባል። በነዚህ ሽፍቶች እየተዘረፈ እና እየወደመ ያለው በአመታት ልፋት የገነባቸው ተቋሞቹ ናቸው። እየተስተጓጎለ ያለውም የእርሱና ልጆቹ ነገዎች ናቸው፤ ለእነዚህ ፅንፈኞች ሕልም የጦስ ዶሮ እየሆነ ያለው/የሚሆነውም በብዙ ተስፋ የሚጠብቃቸው ከአብራኩ የወጡ ልጆቹ ናቸው።

ሕዝብ በየዘመኑ ያጋጠሙትን ፈተናዎች ያለ ብዙ ዋጋ መሻገር ያስቻሉ እውቀቶች ባለቤት ነው፤ ዛሬ ላይ ያጋጠሙት ችግሮች የቱንም ያህል ፈታኝ ቢሆኑ፤ ፈተናውን ተቋቁሞ፣ ዛሬዎችን ማደስ፤ ነገዎቹን ከትናንት የተሻሉና ብሩህ ማድረግ የሚከብደው አይደለም። የፈተናዎቹን እውነተኛ ምንጭ ብቻ ሳይሆን ፈተናዎቹን በሠለጠነ መንገድ እንደሚያልፋቸውም የሁሉም ኢትዮጵያዊ እምነት ነው ።

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 30/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *