እንደ መነሻ …
በቀድሞው አጠራር ወሎ ክፍለ ሀገር፣ ላስታ አውራጃ፣ መቄት ወረዳ ነው የተወለዱት፤ በ1963 ዓ.ም:: ልጅነታቸውን ያሳለፉት እንደ ዕድሜ እኩዮቻቸው በሜዳ፣ በመስኩ ሲቦርቁ ነው:: ነፍስ ካወቁ ጀምሮ ለወላጆቻቸው በወጉ ታዘውና ተመርቀው አድገዋል:: በአፍላነት ዕድሜያቸው እርፍ ነቅንቀው፣ በሬ ጠምደው የሚያርሱ፣ ጎተራ ሙሉ የሚያፍሱ ብርቱ ገበሬ ነበሩ:: የዛሬው እንግዳችን አቶ ቢራራ አየለ::
ቢራራን አስተውሎ ላያቸው ቆፍጣና ገጽታና ፍጹም አይበገሬነት ከፊታቸው ይነበባል:: ሁሌም ቢሆን ለያዙት ዓላማ ወደ ኋላ ማለትን አያውቁም:: እስካሁን ኑሮን አሸንፎ፣ ሕይወትን ታግሎ ለመጣል ያልሞከሩት፣ ያልሄዱበት መንገድ የለም:: ለሥራ ካሏቸው ሁሌም እጅ እግራቸው ይሰላል፤ ትከሻቸው ይበረታል። ለፍቶ፣ ደክሞ በማግኘትና በማደር ያምናሉ። በመሆኑም፣ ዘወትር ባተሌ ናቸው::
በ1977 ዓ.ም ቢራራ ከሀገር፣ ከቀዬአቸው የሚወጡበት አጋጣሚ ተፈጠረ:: የዛኔ ደህና ጉብል ነበሩ:: ራሳቸውን ችለው ለመቆም የተገኘውን ሠርተው ማደር የሚቻላቸው ጠንካራ:: መቄትን ለቀው ሲርቁ እግራቸው ያመራው በወቅቱ አጠራር ከፋ ወደ’ሚባለው ክፍለ ሀገር ነበር:: ጅማ፣ በሰቃ ከሚባል ስፍራ ሲደርሱ እንግድነታቸው የተሟሸው በግብርና ሥራ ሆነ::
አፍላነት …
ቢራራ በወቅቱ የአስራዎቹን ዕድሜ እያጋመሱ ነበር:: እንዲያም ሆኖ ልጅነት አልያዛቸውም:: ባዕድነት አልተሰማቸውም:: ውለው ሳያድሩ ከግብርናው ሥራ ገብተው መልካም አራሽ ሆኑ:: ጉልበታቸው የድካማቸውን አልነሳቸውም:: የላባቸውን ፍሬ አገኙ::
ዓመታትን በሥፍራው የቆዩት ቢራራ ጉርምስናቸውን በሥራ ገፉበት:: ወጣትነታቸው ጥንካሬን ቢያላብስ መንገዳቸው ሰመረ:: ሀሳባቸው ሞላ:: ይህ ዕድሜ በዚህ ብቻ አልተገለጠም:: ሕይወትን፣ የኑሮ ሸክምን፣ ከሚያቀል አጋጣሚ አገናኛቸው::
በወቅቱ ብርታት፣ መልካምነታቸውን ያስተዋሉ አንዳንዶች ‹‹ይበጃል›› ያሉትን አሰቡ:: ብቸኝነት እንዲቀር፣ ትዳር ይዘው ጎጆ እንዲቀልሱ መከሩ:: ቢራራ በጊዜው በሀሳብ መዋጣቸው አልቀረም:: የእሳቸው ዕቅድ በሥራ መለወጥና ማደግ ብቻ ነው::
የመንፈሳዊ ትምህርታቸውን ጨምሮ የአባታቸው መሞት ለጋብቻ አልጋበዛቸውም:: ታናናሾቻቸው አሁንም በእናታቸው እጅ መሆናቸው ኃላፊነቱን አክብዶታል:: ሀገር ጥለው የወጡት ቤተሰባቸውን ለመርዳት፣ ራሳቸውን ለመለወጥ ነው:: ትምህርቱን ደግሞ እንዳሰቡት አልገፉትም:: ቢራራ ለውሳኔ በእጅጉ ተጨነቁ::
ሁኔታው ድንገቴ ቢሆንም ጊዜ ወስደው አሰቡበት:: በብቸኝነት መኖር መልካም አለመሆኑ ገባቸው:: ውሎ አድሮ ልባቸው ለሰዎቹ ምክር ተገዛ፤ ሀሳቡን ውስጣቸው ፈቀደ:: ለጋብቻው ተስማሙ::
ሦስት ጉልቻ …
በሀገሩ ደንብና ወግ ሽማግሌ ተልኮ ሠርጉ ተደገሰ:: በወቅቱ እሳቸው የሀያ ዓመት ወጣት፣ ሚስታቸው ደግሞ የአስራ አራት ዓመት ታዳጊ ነበሩ:: 1984 ዓ.ም ከታጨችላቸው ወይዘሮ ጋር በትዳር የተጣመሩበት ጊዜ ሆነ:: ጋብቻው የጥንዶቹ ፍላጎት አልዋለበትም:: ሁለቱም በሽማግሌዎቹ ይሁንታ ተፈቃቅደው ተጣመሩ:: ቢራራ ሙሽራቸውን ከልብ ወደዷቸው:: ልጅነት ቢኖርም የጥንዶቹ ጎጆ አልቀዘቀዘም::
ቤቱ በሕጻን በረከት ተሞላ:: ባልና ሚስት የመጀመሪያ ልጃውን አቅፈው ሳሙ:: በዚህ ብቻ አልበቃም:: እያደር ሌሎች ልጆች ተወለዱ:: አምስት ፍሬዎችን ያየው ጎጆ አሁን ብዙ ያሻዋል:: ቤተሰብ ሲጨምር ፍላጎት ያይላል፤ አቅም ጉልበት ይፈተናል::
አባወራው ዝም አላሉም:: የቤተሰቡን ፍላጎት ለመሙላት መሮጥ ያዙ:: ልጆችን አሳድጎ ጎጆን ለመሙላት መድከም፣ መልፋት ግድ ነው:: ቢራራ እጅ አልሰጡም:: በላባቸው ወዝ፣ በጉልበታቸው ዋጋ ለትዳራቸው አብዝተው ታተሩ::
ከጊዜያት በኋላ የሆነው አንድ አጋጣሚ የቤተሰቡን ሕይወት ቀየረው:: ቢራራ በድንገት የውትደርናውን ዓለም ተቀላቀሉ:: የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በተቋጨ ማግስት በተደራጀው የብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይል የተቀጠሩት ቢራራ በሑርሶና በሌሎች ወታደራዊ ተቋማት ለሥልጠና ገቡ:: ለሦስት ዓመታትም ከቤተሰባቸው ተለዩ::
ይህ ጊዜ ቢራራን በበደሌ፣ ጋምቤላና አፋር ምድር አቆያቸው:: የውትድርና ቆይታቸውን ባጠናቀቁ ጊዜም ስለፈጸሟቸው መልካም ተግባራት ተገቢውን ማረጋገጫ አገኙ:: ከግዳጅ መልስ በቀበሌ አስተዳደርነትና በአካባቢ ታጣቂነት ለዓመታት አገለገሉ::
ብቸኝነት …
ከጥር 2005 ዓ.ም በኋላ ቢራራ ወደ ቤተሰባቸው ተመለሱ:: ከዚህ በኋላ የነበረው ቆይታ እንደቀድሞው አልሆነም:: አባወራው አሁን ለመናገር ፈቃደኛ ባልሆኑበት ምክንያት ከትዳራቸው ለመለየት ግድ አላቸው:: በድንገት ሚስትና ልጆቻቸውን ትተው ከአካባቢው ራቁ:: የእግራቸው ምሪት ከአዲስ አበባ ቢያደርሳቸው፣ ራሳቸውን መሐል ከተማ አገኙት::
አሁን እንደቀድሞው አይደሉም:: በዕድሜና አስተሳሰብ በስለዋል:: ሁሌም ልጆቻቸውን እየናፈቁ ትዳራቸውን ያስባሉ:: ዛሬ ቤተሰቦቻቸው ከፋ ዞን፣ ቢጣ ወረዳ ላይ ናቸው:: አሁንም እነሱን በምቾት ለማኖር ያላቸው ብርታት ከእሳቸው ጋር ነው::
ቢራራ የሰው አገር እንግድነትን የተቀበሉት በምቾት አልሆነም:: የእሳቸው የሕይወት ልምድ ከግብርናውና ከውትደርናው ዓለም የሚቀዳ ነው:: ምንም ይሁን ምን ሥራ ይሉትን አይንቁም:: ሁሌም ከሰው ተግባብቶ ለማደር የማይቸግራቸው ቢራራ አሁን የከተማን ኑሮ መላመድ ይዘዋል:: እንዲያም ሆኖ ለእሳቸው ሕይወት ቀላል አልሆነም::
የአዲስ አበባ ኑሮ ለፍተው ቢያድሩበትም ከእጅ መያዝን ያሻል:: በልቶ ለማደር፣ ለቤት ኪራዩ፣ ለዕለት ወጪው የላብ ዋጋን ይጠይቃል:: ይህን የተረዱት አባወራ ልፋታቸው በአንድ አልቆመም:: ከተማ ወጣ ብለው ‹‹ደራ›› ከተባለ ስፍራ ጉልበታቸውን በቀን ሥራ ፈተኑ::
ተመልሰው አዲስ አበባ ሲገቡ የተለየ ዓለም አልቆያቸውም:: ፓስተር ከተባለ አካባቢ ከመንገድ ጥግ እያደሩ በሥራ መባተልን ተያያዙት:: የቢራራን ጥንካሬ ችግርና መከራ አልፈታውም:: ውስጣቸው በእጅጉ በረታ:: ዛሬ ላይ ቆመው ነገን በማሰብ ራሳቸውን አጽናኑ:: አሁን ጎን ማሳረፊያ ቤትና መተዳደሪያ ይሉት ሥራ የላቸውም:: ቢራራ ጥርሳቸውን ነክሰው ቀኑን ሊገፉ ከራሳቸው ጋር መከሩ::
ይህ ሁሉ ሲሆን አንድ ቀን ታሪካቸው እንደሚለወጥ ተስፋ ይዘዋል:: ወታደሩ፣ አራሽ ገበሬው፣ የቀን ሠራተኛው ቢራራ እንደ ዕምነታቸው ሆነላቸው:: ከቀናቶች በአንዱ የአስኮ ገብርኤል ካቴድራል ቤተክርስቲያን የጥበቃ ሠራተኞችን እንደሚፈልግ ጆሯቸው ደረሰ::
ለሥራው የቀደሙት ባልንጀራቸው ነበሩ:: ከእሳቸው ይልቅ ለቢራራ እንደሚመጥን ነግረዋቸዋል:: ከልምድና ሥነምግባራቸው ጋር እንደሚዛመድ ያወቁት ቢራራ ጊዜ አልፈጁም:: ማስረጃዎችን ለሚመለከተው ክፍል አስገቡ:: ጊዜው ሲደርስ ከሌሎች ጋር ተወዳድረው ምዘናውን አለፉ:: ልባቸው በምሥጋና ተሞላ::
አሁን ቢራራ ከቀን ሥራና ከመንገድ ላይ አዳር ሊወጡ ነው:: አመስጋኙ አባወራ ይህን ሲያስቡ ውስጣቸው በሐሴት ሞቀ። ደጋግመው ለፈጣሪ ምስጋና አደረሱ:: ሥራውን በጥንካሬ ለመጀመር ራሳቸውን አዘጋጁ:: ጥቂት ቆይቶ የቢራራን ደስታ የሚያጠይም ጉዳይ ተፈጠረ::
ቢራራ የቤት ካርታ ያለው ተያዥ እንዲቀርቡ ተጠይቀዋል:: ይህን በሰሙ ጊዜም በድንጋጤ ማዘን፣ መተከዝ ይዘዋል:: የተሰጣቸው ጊዜ አጭር መሆኑ ደግሞ ግራ አጋብቷቸዋል:: እሳቸው ‹‹የእኔ›› የሚሉት ወዳጅ ዘመድ የለም:: ሥራውን ሊያጡት መሆኑ ሲገባቸው ከልብ አዘኑ:: እንዳሰቡት ግን ለእሳቸው ቀን አልጎደለም:: ድንገቴው የባዕድ ዘመድ ዋስትናውን አሟልቶ ከእንጀራቸው ተገናኙ ::
የድካም ዋጋ …
ቢራራ በቤተክርስቲያኑ አፀድ የጥበቃ ሥራውን ጀመሩ:: አሁን ስለቤትና ማረፊያቸው አይጨነቁም:: ሲሠሩ ውለው አዳራቸው በግቢው ሆኗል:: ወር ደርሶ ደሞዝ በቆጠሩ ጊዜ ውስጣቸው በሀሳብ ተያዘ:: በእጃቸው የሚገባው ገንዘብ ከእሳቸው አልፎ ለቤተሰብ አይተርፍም:: ጨነቃቸው። በዚህ ሁኔታ ቀን እንደማይገፋ አወቁ:: መፍትሔ አላጡም:: በትርፍ ጊዜ ሌላ ቦታ ተቀጥረው ለሀያ አራት ሰዓት ሥራውን ቀጠሉ:: ጥቂትም ቢሆን ጎናቸው አገገመ::
ጠዋት ማታ ያለ እረፍት የሚባትሉት አባወራ ‹‹ደከመኝ›› አላሉም:: በጥንካሬ መሮጥ ያዙ:: ውሎ አድሮ ግን ሥራቸው ፈተና አላጣውም:: በተጨማሪ የሚሠሩበት ድርጅት ከሁለቱ ሥራ አንዱን እንዲተዉ ምርጫ ሰጣቸው:: ጉዳዩን ደጋግመው ማሰብ አላሻቸውም:: ከቤተክርስቲያን አፀድ መውጣት አይፈልጉም:: በአጭር ውሳኔ ወደ መጀመሪያው ሥራ ተጠቃለሉ::
አሁን ቢራራ ኪሳቸው ጎድሏል:: እንደ በፊቱ በትርፍ ሰዓት የሚያገኙት ገንዘብ የለም:: እሳቸው ግን ዝም አላሉም:: ከመደበኛ ጥበቃቸው ሌላ በቀን ሥራ መዋል ጀመሩ:: እንጀራ እየገዙ፣ ወጥ እየሠሩ፤ አንዳንዴም ጦም እያደሩ ለኑሯቸው ታገሉ:: እንዲያም ሆኖ ቢራራ ሰውነታቸው ይከብዳቸው ያዘ:: መወፈራቸው ተሰማቸው:: እንዲህ መሆኑን አልፈለጉትም:: መፍትሔን ሻቱ:: ላብ የሚያወጡበት፣ የሚደክሙበትን ሥራ ፈለጉ:: የግቢው አትክልተኛ መሆንን ተመኙ::
ሀሳባቸውን ለግቢው አስተዳዳሪ አካፍለው ምላሽ ጠበቁ:: በጥበቃ ተግባር ያላቸውን ጥንካሬ የሚያውቁት ኃላፊዎች ቅር ቢላቸውም አልጨከኑም:: ሥራውን እንዲረከቡ ፈቀዱላቸው:: አሁን ቢራራ ራሳቸውን የሚያደክሙበት ሥራ አግኝተዋል:: በየቀኑ በቁፋሮ፣ አፈር በመዛቅ፣ አትክልት በመትከልና መቁረጥ ሲባትሉ ይውላሉ::
ቢራራ ያዩትን ፈጽሞ አይረሱም። ያሳለፉትን ታሪክ ሲናገሩ በማስረጃና በተለየ ብቃት ነው:: ይህ ልምዳቸው ለአትክልተኝነት ሥራቸው አግዟቸዋል:: ግቢው በባለሙያዎች ሲዋብ ቀረብ ብለው ልምድ ቀስመዋል:: የመቀስ አያያዝን፣ የማሽን አጠቃቀምን ያወቁት አይቶ በመረዳት፣ አስተውሎ በማጤን ነው:: ራሳቸውን በማስተማር ያዳበሩት ዕውቀት ዛሬ ላይ ብቁ ባለሙያ አድርጓቸዋል::
አትክልተኛው …
አሁን የቤተክርስቲያኑ አፀድ የቢራራ እጆች ባረፉባቸው ማራኪ አትክልቶች የተዋበ ነው:: አረንጓዴ ምንጣፍ በሚመስል ሳር የተከበበው ግቢ ለዓይን ይማርካል:: እንደ መልካም ጎፈሬ የተከረከሙት አትክልቶች ሊነኳቸው ያሳሳሉ::
አትክልቶቹ ለቢራራ እንደ ልጆች ናቸው:: ብዙ ደክመውባቸዋል:: ማንም እጅ ቢያሳርፍባቸው፣ ቢነካ ቢቆርጣቸው አይወዱም:: ከእነሱ ያላቸው ፍቅር ቀን ከጨለማ አይልም:: መገኘት ባስፈለጋቸው ጊዜ ሁሉ ከቦታው ላይ ናቸው:: የእጆቻቸውን ፍሬ ዘወትር በስስት እያዩ፡- አብረዋቸው ይውላሉ፤ ያመሻሉ::
ብዙ ጊዜ ቦታው ላይ ጥንዶች ጋብቻ ይፈጽሙበታል:: ተመልካቾች ይማረኩበታል:: ይህ መሆኑ ዓይንን በዓይን የማየት ያህል ለአትክልተኛው ደስታን አቀብሏል:: ዛሬ ጎልማሳው አባወራ የአዲስ አበባን ሕይወት ተላምደዋል:: እንዳሰቡት ቤተሰቦቻቸው ከጎናቸው ባይሆኑም ጎዶሎነት ተሰምቷቸው አያውቅም::
ቢራራ ሀያ ስምንት ዓመታትን ከቆጠሩበት ትዳር አምስት ልጆችን፣ ሁለት የልጅ ልጆችን አፍርተዋል:: መራራቁ በፈጠረው ክፍተት ከቀድሞ ባለቤታቸው ጋር ሕይወትን አልቀጠሉም:: ሁለቱም በያሉበት በራሳቸው ኑሮ ዘልቀዋል:: ይህ እውነታ ግን በመሐላቸው ቅሬታን አልፈጠረም:: በመተሳሰብ፣ በመጠያየቅ ዓመታትን አሻግሯቸዋል::
በ2012 ዓ.ም ባለቤታቸው በጠና መታመማቸውን ሰሙ:: ቢራራ ይህን ባወቁ ጊዜ አዲስ አበባ አምጥተው ማሳከም፣ ማስታመም ጀመሩ:: ወይዘሮዋ ለመዳን አልታደሉም:: ወደ ቤታቸው ሳይመለሱ አጠገባቸው አረፉ:: ቢራራ የልጆቻቸውን እናት ባስታመሙበት፣ ባሳከሙበት አዲስ አበባ ቀብራቸውን ፈጽመው ኃዘን ተቀመጡ::
አዲስ ሕይወት …
ከሀዘኑ ማግስት ልጆቻቸውን ሸኝተው ለአንድ ዓመት ያለ ሥራ ተቀመጡ:: ሙት ዓመታቸውን ካወጡ በኋላ ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው ተመለሱ:: አሁን ቢራራ እንደ በፊቱ የባለቤታቸውን፣ የቤተሰባቸውን መምጣት አይናፍቁም:: በተስፋ አይጠብቁም:: ኑሮን እንደፊቱ ቀጥለዋል::
ውሎ አድሮ የቅርብ ሰዎች ቢራራን መከሩ:: ‹‹ብቸኝነት ይብቃህ፣ ትዳር ያዝ፣ ጎጆ ቀልስ›› አሏቸው:: ልጆቻቸውም ቢሆኑ ሀሳቡን ደገፉ:: ለአባታቸው መልካም የትዳር አጋር ተመኙ:: በጊዜው የቢራራ ሀሳብ ከእነሱ አልሆነም:: እሳቸው ቆርበው መንኩሰው ሊኖሩ አቅደዋል:: እያደር የአሳቢዎቻቸው ምክር ሲገፋ ግን በጉዳዩ አሰቡበት:: የልባቸውን አላጡም:: በቤተክርስቲያን ሥርዓት ጋብቻ ፈጽመው ትዳር መሠረቱ::
አዲሱ ትዳራቸው ያሳለፉትን ችግር በደስታ የሚለውጥ ሆነ:: ሕይወታቸው በመልካም ታደሰ:: ቢራራ በቅርቡ ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ታቅፈዋል:: ይህንን ሕጻን ጨምሮ የዘጠኝ ልጆች አባት የሆኑት አባወራ በሕይወታቸው ደስተኛ ናቸው::
ዛሬን …
ዓመታትን በአዲስ አበባ የገፉት አቶ ቢራራ ዛሬ ላይ የሚኖሩት በቤት ኪራይ ነው:: በየዕለቱ የሚጨምረው የኑሮ ውድነት የእሳቸውንም ሕይወት ማናጋት ይዟል:: የቀድሞውን ችግር በጉልበታቸው፣ በጥንካሬቸው አልፈውታል:: የዛኔ በልቶ፣ ተከራይቶ ለማደር ኑሮ እንዳዛሬው አይደለም:: በሳንቲምና በጥቂት ገንዘብ ሕይወትን መግፋት ይቻል ነበር::
አሁን ግን ትከሻቸው ሊቋቋመው የማይችለውን የኑሮ ውድነት እየተጋፈጡ ነው:: እንደሳቸው ሕይወትን ታግሎ ለማሸነፍ ለሚጥር በተለይ በቤት ኪራይ ችግር የመንገላታቱ እውነት ሁሌም ያሳስባቸዋል::
የቢራራ ጉልበት ዛሬም ብርቱና ጠንካራ ነው:: የያዙትን ሙያ አጠናክረው ለሌሎች ማጋራትን ይሻሉ:: ይህ ብቻ አይደለም፤ አሁንም እሳቸውን በሚመጥን ሙያዊ ተግባር ለመሰማራት ዝግጁ ናቸው::
ጠንካራውን፣ አስተዋዩን አባወራ ስሰናበታቸው የተለየ ብርታት ከፊታቸው አስተዋልኩ:: ሕይወት በብዙ መልኩ ስትፈትን አሸንፎ ለመውጣት ያለውን ትግል ከእሳቸው ማንነት ተረድቻለሁ:: ከልብ አከበርኳቸው:: ባለ መቀሱን፣ ብርቱውን ጎልማሳ ቢራራ አየለን::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2015