ከዓመት በፊት በአሜሪካዋ ኦሪጎን በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ኢትዮጵያ ጣፋጭ ድልን ካስመዘገበችባቸው ርቀቶች መካከል አንዱ የሴቶች ማራቶን ነው። ይኸውም በቻምፒዮናው የኢትዮጵያ ተሳትፎ ታሪክ ሁለተኛው ሲሆን፤ ከአሰለፈች መርጊያ የነሃስ፤ እንዲሁም ከማሬ ዲባባ የወርቅ ሜዳሊያዎች ቀጥሎ የተገኘ ነው። ዓለም በከፍተኛ ጉጉት በሚጠብቀው ተናፋቂው የዓለም ቻምፒዮና ገናና ስም ያላቸውና ውጤታማ የሆኑ ሀገራት ድላቸውን ለማስቀጠልና ታሪካቸውን ለማስጠበቅ ጠንካራ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ። ከእነዚህ ጠንካራ ተፎካካሪ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያም የአምናውን ቻምፒዮናነቷን ለማስጠበቅ ቡድኗን ቡዳፔስት ላይ ታሳትፋለች።
ከሌሎች ርቀቶች አስቀድሞ የተሰባሰበው የኢትዮጵያ ማራቶን ብሄራዊ ቡድን የተለመደውን ድል ለመቀዳጀት ጠንካራና እልህ አስጨራሽ ዝግጅቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። ወቅቱ በክረምቱ ምክንያት በአዲስ አበባ ያለው የአየር ሁኔታ ቀዝቃዛ፣ በአንጻሩ የውድድሩ ስፍራ ከፍተኛ ሙቀትን እያስተናገደ በመሆኑ ሀገራቸውን ለመወከል ጥሪ የቀረበላቸው አትሌቶች ፈታኝ ዝግጅት እያደረጉ ቢሆንም ከድሉ የሚያስቆማቸው ምድራዊ ኃይል ያለ አይመስልም። ይህን የራስ መተማመንም ከአትሌቶቹ አንደበት መረዳት ይቻላል።
በእርግጥም የሴቶች ቡድኑ በልምድ የዳበሩ እና ድልን ደጋግሞ በመቀዳጃት ዓለም ያጨበጨበላቸው እንዲሁም ርቀቱን በቅርቡ ተቀላቅለው ተስፋ ሰጪ አቋም እያሳዩ ያሉ አትሌቶችን አካቶ የያዘ ነው። በመሆኑም አምና በአትሌት ጎይቶም ገብረሥላሴ የተገኘው የወርቅ ሜዳሊያ በቡዳፔስትም እጅጉን ይጠበቃል። ባለ ፈጣን ሰዓቷ የቫሌንሺያ ማራቶን አሸናፊ አማኔ በሪሶ፣ ጸሃይ ገመቹ፣ ያለምዘርፍ የኋላው፣ መገርቱ ዓለሙን እና ወርቅነሽ ኢዴሳ፤ ከ2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ በታች የሆነ የግል ሰዓት ያላቸው በመሆኑ የተዘጋጁትን ሜዳሊያዎች ጠራርገው እንዳይወስዱ በተፎካካሪ ሀገራት ጭምር ስጋትን ፈጥረዋል።
ኦሪጎን ላይ የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ ሀገሯን ያኮራችው ቻምፒዮናዋ ጎተይቶም ገብረሥላሴም ይህንኑ የሚያጠናክር አስተያየት ሰጥታለች። አትሌቷ ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራት ቆይታ ቡድኑ በጠንካራ ስብስብ መዋቀሩ ውጤት እንደሚያመጣ እምነቷ ነው። ወቅቱ ክረምት በመሆኑ ለዝግጅቱ አስቸጋሪ ቢሆንም የሀገር ጉዳይ በመሆኑ ያለውን የአየር ሁኔታ ተቋቁሞ መስራት እንጂ “አይመችም” ብሎ የሚተው ጉዳይ አይደለም። በአምናው ቻምፒዮና ከዚህ የተለየ ዝግጅት አለመደረጉን ያስታወሰችው አትሌቷ፤ ዘንድሮ ቡድኑ ለውጤት እንዲጠበቅ የሚያደርገው ጠንካራ አትሌቶችን ይዟል። እሷም በጥሩ ዝግጅትና ስነልቦና ላይ በመሆኗ ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያው እንደሚመጣ በራስ መተማመን ስሜት ገልጻለች።
ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ማራቶንን ለመጀመሪያ ጊዜ ሃምቡርግ ላይ ሮጣ ያሸነፈችው አትሌት ያለምዘርፍ የኋላውም በማራቶን ቡድኑ ተካትታለች። ጠንካራዋ አትሌት ለንደን ማራቶንንም በአሸናፊነት የተወጣች ሲሆን፤ 2 ሰዓት ከ17 ደቂቃ ከ23 ሰከንድ የሆነ ፈጣን ሰዓት አላት። ለመጀመሪያ ጊዜ በርቀቱ ሀገሯን እንድትወክል መመረጧን ተከትሎም ጠንካራ ዝግጅት በማድረግ ላይ ትገኛለች። ቻምፒዮን ለመሆን ሙሉ ጤናኛና ልምምድን በትክክል ከመስራት ውጪ ምንም አያስፈልግም የምትለው አትሌቷ፤ የሀገሩን መለያ ለብሶ የመሮጫ ጎዳናው ላይ የሚገኘው አትሌት በሙሉ ተፎካካሪ በመሆኑ፣ ብቃት የሚለየው በውድደር ላይ መሆኑን ገልጻለች።
ሌላኛዋ የቡድኑ አባልና ከወራት በፊት በተካሄደው የቶኪዮ ማራቶን ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው አትሌት ፀሐይ ገመቹ፤ ቡድኑ ዝግጅቱን በጥሩ ሁኔታ እና በቡድን መንፈስ እያደረገ መሆኑን ትገልጻለች። ሀገርን ወክላ ስትሳተፍ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ያስታወሰችው አትሌቷ፤ በርቀቱ የካበተ ልምድ ባይኖራትም በትኩረት እየሰራች በመሆኑ ሜዳሊያ እንደምትጠብቅም ገልጻለች።
በርካታ የጎዳና ሩጫ ከዋክብቶችን አሰልጥነው ለስኬት ካበቁ ምርጥ የማራቶን አሰልጣኞች መካከል አንዱ የሆኑት አሰልጣኝ ሃጂ አዴሎ፣ በቡዳፔስቱ የዓለም ቻምፒዮና ብሄራዊ ቡድኑን ይመራሉ። ስለ ቡድኑ ዝግጅት በሚመለከትም የተለመደውን ውጤት ወደ ቤቱ ለማስመለስ የሚያስችል መሆኑንም ይገልጻሉ። ምርጥ የማራቶን ሯጮችን ያሰባሰበው ቡድናቸው ጠንካራ ከመሆኑም ባለፈ አትሌቶች በአንድ መንፈስ፣ መተጋገዝን ልምምዳቸው በማድረግ ላይ ይገኛሉ። የወቅቱ የአየር ሁኔታ በአትሌቶቹ ላይ ተጽዕኖ ካላሳደረ በቀር ቻምፒዮናነቱን እንደሚያስጠብቅም በቡድናቸው ያላቸውን ጽኑ እምነት አመላክተዋል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2015