የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ታላላቅ የግንባታ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ነው:: ኢንተርፕራይዙ ዘመናዊ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችንና በሥራቸው አንቱ የተባሉ ሙያተኞችን በመያዝም ይታወቃል። በተለይም በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጥሮ አቀማመጣቸውና በአየር ፀባያቸው አስቸጋሪ የሚባሉ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ ፍላጎትን የሚያረካ ሥራ በመከወን ታዋቂነቱን ያረጋገጠ ነው።
የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ በአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ በሚያደርገው የግንባታ ተሳትፎውም ባለፉት ዓመታት የልማት አጋርነቱን በተጨባጭ ሲያስመሰክር ቆይቷል። አሁንም እያስመሰከረ ይገኛል። ከሁሉ በላይ ኢንተርፕራይዙ በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ግንባታ ያልተደፈሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ልዩ እውቅና የተቸረውም ነው።
ሌሎች መሰል ድርጅቶች በማይደፍሯቸው ከፍተኛ ሙቀትና ቅዝቃዜ እንዲሁም ውስብስብና ፈታኝ መልክዓ ምድርን በተሳካ ሁኔታ ከመስራት ባለፈ የፀጥታ ችግር ባሉባቸው አካባቢዎች ሳይቀር ውል በማሰር የሀገሪቱን ሕዝቦች የልማት ጥማት ያረጋል። ፅናትና ጀግንነት የተሞላበት ሥራም ያከናውናል።
ኢንተርፕራይዙ የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማ የመከላከያ ሠራዊትን የግንባታ ፍላጎት ማሟላት እንደመሆኑ መጠን በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎችም ይህን ለማሳካት ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል:: እነዚህ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የተቋሙን የመፈፀም አቅም የሚያጎለብቱ፤ የስልጠና ተቋማትን የማሰልጠኛ አቅም የሚያሳድጉና የሠራዊቱን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት የሚያሳኩ እንዲሁም በጤናው ዘርፍ ሠራዊቱ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችሉ ናቸው::
መከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዙ ቀደም ሲልም ለአብነት የድሬዳዋ እና የሽሬ ሪፈራል ሆስፒታሎችን፣ የመቀሌና የአዲስ አበባ የሥራ አመራር ኮሌጆችን ገንብቶ አስረክቧል:: በሀገራችንም ሆነ በምሥራቅ አፍሪካ በዓይነቱ ለየት ያለ የኮንክሪት አስፋልት መንገድም ገንብቷል:: ግንባታቸው ተጠናቀው ወደ ሥራ ከገቡ ፕሮጀክቶች መካከልም የዲቼቶ ጋላፊ በልሆ መገንጠያ መንገድ በሀገሪቱ የመጀመሪያው የኮንክሪት መንገድ ሲሆን፤ አጉላ ብርሃሌ መንገድ ፕሮጀክቶችም ከብዙ በጥቂቱ ሊገለፁ የሚችሉ ናቸው።
ኢንተርፕራይዙ የተረከባቸውን ፕሮጀክቶች በጥራትና በፍጥነት በማከናወን እግረ መንገዱንም ለሕዝቡ ማህበራዊ ተቋማትን፣ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የትምህርት ተቋማት በመገንባት ብሎም አያሌ የሥራ እድል በመፍጠር ከሕዝባዊ ደጀንነቱ ባሻገር ሕዝባዊ አጋርነቱን እያሳየ ይገኛል:: ከከተማ አስተዳደሮችና ከክልሎች ጋር በመቀራረብ ዘመናዊና ከፍተኛ የግንባታ ጥበብና ሙያ የታየባቸው ሕንፃዎች ግንባታ ላይ ይሳተፋል:: ከሕንፃ ባሻገር በመንገድ ሥራ፣ በመስኖ ግድብ እንዲሁም የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክቶችም ላይ ንቁ ተሳትፎ ያደርጋል::
የኢንተርፕራይዙን ጉልህ አሻራ ከሚያስመለክቱ ፕሮጀክቶች መካከልም የመከላከያ ዋና መስሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ፣ የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢንሳ/ ዋና መስሪያ ቤት ግንባታ እንዲሁም የሰሚት አርሚ ፋውንዴሽን የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ተጠቃሽ ናቸው:: በፕሮጀክቶች አፈጻጸሙ መልካም ስም መገንባት የቻለው ኢንተርፕራይዙ፤ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እየገነባቸው ከሚገኙ ፕሮጀክቶች መካከልም የአምቦ -ወሊሶ መንገድ ሥራ ፣የነቀምት አየር ማረፊያ፣ የሃሮ ወንጪ ኢኮ ቱሪዝም ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት፣ የጣርማ በር መለያ ሰፌድ ሜዳ መንገድ ስራም ይጠቀሳሉ።
ኢንተርፕራይዙ በአሁኑ ወቅት ደግሞ እየተሳተፈባቸው ከሚገኙ ፈታኝ ፕሮጀክቶች መካከል በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ-ቧሂት-ድልይብዛ ኮንትራት አካል የሆነው ‹‹የበለስ መካነ ብርሃን›› የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ አንዱ ነው።
የመንገድ ፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ተስፋ ዘለቀ እንደሚገልፁት፤ የመንገድ ፕሮጀክቱ የተጀመረው በ2010 ዓ.ም ነው። በአጠቃላይ መንገዱ 39 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ በዋናነት ደባርቅና ጃናሞራ ወረዳዎችን ያስተሳስራል። ከደባርቅ 27 ኪሎ ሜትር ያህል ገባ ብሎ የሚጀምረው የመንገድ ፕሮጀክቱ አስቸጋሪ በሚባል መልክዓ ምድር እንዲሁም የአየር ፀባይ ውስጥ ይገኛል። በተጨማሪም ግዙፍ የሚባሉ ተራሮችን የመቁረጥና ገደላማ አካባቢዎችን ለመሻገርም በርካታ ድልድዮችን መገንባት ይጠይቃል።
ፕሮጀክቱ በጠቅላላው ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የኤክስካቬሽን ስራን የሚጠይቅ ሲሆን፤ 80 በመቶ የሚሆነውም ድንጋይ ቆረጣ ይፈልጋል። ይህ እንደመሆኑ መጠንም አለቶችን ለመቁረጥ ከባድ መሳሪያዎች ያስፈልጋሉ። በተከታታይ ፈንጂዎች ጥቅም ላይ ሊውሉም ግድ ነው። ይህ እየተደረገም ይገኛል። በተጨማሪም ከተራራዎች ላይ የሚቆረጡ የአፈርና የድንጋይ ክምሮች መዳረሻቸው በታችኛው የመንገድ ክፍል ላይ ነው። ይህ ደግሞ ክምሩን የማንሳትና የማስወገድ ተጨማሪ ስራን ይፈልጋል። እናም ይህ ፕሮጀክት መሄድ ባለበት የጉዞ ፍጥነት እንዳይራመድ እጅጉን ከፈተኑ ችግሮች መካከል አንደኛው እንደሆነ ያነሳሉ።
ፕሮጀክቱ ተራራ ወርዶ መውጣትን ይጠይቃል። የግል ኮንትራክተሮች ከፊትም ከኋላም አቋርጠው ወጥተዋል። ከደባርቅ እስከ በለስ ያለው በሌላ ኮንትራክትር ሲሰራ ነበር። ይህም ‹‹አይ ኬር›› የተባለ ኮንትራክተር ሲሆን፤ ሁኔታው ከብዶት አቋርጦ ወጥቷል። የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ጎንደር ቅርንጫፍ ፕሮጀክቱን ተረክቦ ለማስኬድ ቢሞክርም እንደ ፊተኛው ጥሎ መውጣት ግድ ሆኖበታል። የደባርቅ- በለስ መንገድ ፕሮጀክት በታቀደለት ጊዜ አለመጠናቀቅና ኮንትራክተሮች ፕሮጀክቱን አቋርጠው መውጣታቸው ለበለስ – መካነብርሃን ፕሮጀክት ላይ ከባድ ፈተና ከሆኑ ችግሮች መካከል ሌላኛው እንደሆነም ነግረውናል።
የዚህ ፕሮጀክት ስኬት እስካሁን ያልታየው የጸጥታ ችግርም በመኖሩ እንደሆነ የሚያነሱት ሥራ አስኪያጁ፤ ጸጥታ ለፕሮጀክቱ ከባድ ራስ ምታት ሆኖ ቆይታል። ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ አለመግባባቶችን ተከትሎ የሰው ሕይወት ሳይቀር ተቀጥፋል። በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት፣ምንም እንኳን ጦርነቱ ፕሮጀክት አካባቢ ባይደርስም በደባርቅ አልፈው መግባት የነበረባቸው ነዳጅ፣ ሲሚንቶ እንዲሁም ብረት የመሳሰሉ ግብአቶች ማግኘት አዳጋች እንዲሆን አድርጓል። በዚህ ምክንያት የተለያዩ አቅርቦቶች ማስገባት አስቸጋሪ ሆኖ በመገኘቱ ፕሮጀክቱ በተደጋጋሚ ለመቆም ተገዶም እንደነበር ትናንትን በምን ሁኔታ ፕሮጀክቱ እንዳለፈ አስረድተዋል።
አሁን ላይ የደባርቅ – በለስ መንገድ ፕሮጀክት ፈተና እንዳለ ሆኖ ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ የፀጥታ ችግሮች መልክ እየያዘ በመምጣታቸው መከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ በአስቸጋሪ የመልክዓ ምድር አቀማመጥ ውስጥ የሚገነባውን የመንገድ ግንባታ በማፋጠን ላይ እንደሆነም አብራርተዋል። በአሁኑ ወቅት ተራሮችን በዶዘር እና በስካቫተር የመቁረጥ ሥራ እየተሰራም ይገኛል። አብዛኞቹ የስትራክቸር ስራዎች እያለቁ ናቸው።
ከ3 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው የድጋፍ ግንቦች እየተሰሩ ናቸው። መንገዱ እንዳይንሸራተት ሬቲንግ ሆል ድጋፎችን፣ ፓይፕ ከልበርት ግንባታ ተሰርተዋል። የሰብ ቤዝ፣ የውሃ መፋሰሻ ቱቦዎች ማምረት እና በርካታ ቆረጣ ሥራዎች እየተከናወኑም እንደሆነ ያብራራሉ።
እንደ ኢንጂነር ተስፋ ገለፃ፣ የመንገድ ፕሮጀክቱ አስር ከፍተኛ የኮንክሪት ድልድዮች ግንባታን ያካተተ ነው። ከእነዚህ ድልድዮች መካከል ትንሹ 10 ሜትር ሲሆን፤ ትልቁ 150 ሜትር ርዝመት አለው። በበለስ ቀበሌ በሚገኘው በለገዝ ወንዝ ላይ የሚሠራው 150 ሜትር የሚረዝመው ድልድይ በሰሜን ጎንደር ዞን በርዝመቱም ተከታይ እንጂ ቀዳሚ የሌለው ነው። በአሁኑ ወቅት ከአስሩ ድልድዮች የስምንቱ ግንባታ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀበት ነው። አገልግሎት መስጠትም ጀምረዋል። ቀሪዎቹ ሁለቱ እየተሰሩ ሲሆን፤ አስር ሜትር የሚረዝመው በጅማሮ ግንባታ ሂደት ላይ ሲሆን፤ 150 ሜትር ርዝመት ያለው ድልድይ ደግሞ የግንባታ አፈፃፀም ደረጃው ከ60 በመቶ ላይ ደርሷል። ግንባታው ከ1 ቢሊዮን 18 ሚሊዮን 952 ሺህ ብር በላይ ወጪ ፈሰስ የሚደረግብት ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም አጠቃላይ የመንገድ የግንባታው አፈጻፀም ከ61 በመቶ በላይ ደርሷል።
ይህ ፕሮጀክት ቀደም ሲል የፕሮጀክቱን የማማከርና የቁጥጥር ስራን የተረከበው ማለትም ከ2014 ዓ.ም በፊት ይዞት የነበረው ‹‹ክላሲክ›› የተባለ ድርጅት ሲሆን፤ ኮንትራቱ እንዲቋረጥ በመደረጉ በአሁኑ ወቅት ሀገር በቀሉ በለስ ኮንሰልቲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እያከናወነው ይገኛል። የግንባታው ዘርፍ በርካታ ተዋናዮች የሚሳተፉበትና ከፍተኛ በጀት ተመድቦለት የሚከናወን እንደመሆኑ ልዩ ትኩረትና ጥንቃቄ ተሰጥቶታል:: ግንባታ ሲነሳ የጥራት ጉዳይ መነሳቱ አይቀርምና ኢንተርፕራይዙ በዚህ ፕሮጀክት ላይ ለጥራት የሰጠውን ትኩረት በሚመለከት ለተነሳላቸው ጥያቄ ኢንጂነር ተስፋ፤ ‹‹መከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ በሁሉም የግንባታ ፕሮጀክት ተሳትፎው በጥራት ጉዳይ ትናንትም፣ ዛሬም ሆነ ነገ አይታማም›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል::
ማንኛውም የኮንስትራክሽን ሥራ ከጥራት ውጪ አይታሰብም። መከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝም ከትርፍ ይልቅ ለግንባታ ጥራት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥ ነው። የፕሮጀክቱን ጥራት ለማስጠበቅ በልዩ ትኩረት የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናልም ሲሉ እያደረጉ ያሉትን ነገር በመጥቀስ ያብራራሉ።
የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጁ እንደሚገልፁትም፤ የበለስ- መካነብርሃን መንገድ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ደባርቅን ከጃንአሞራ ወረዳ ያገናኛል። ለአካባቢው ማህበረሰብ ታሪክ ቀያሪም ነው ቢባል የሚጋነን አይደለም። ለዘመናት በመንገድ መሠረተ ልማት እጦት ሲንገላታ ለኖረው የደባርቅ እና ጃንአሞራ ወረዳ ነዋሪ ከማገናኘቱ በላይ የጤና፣ የትምህርት እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን የአካባቢው ማህበረሰብ እንዲያገኝ ያስችለዋል። በሁለቱ ወረዳዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች የአትክልትና ፍራፍሬ እና የሰብል ምርቶቻቸውን በስፋት ለገበያ ማድረስ እንዲችሉም ያግዛቸዋል።
የመንገዱ መገንባት ለሀገር ውስጥና ለውጪ ጎብኚዎችም ቢሆን ከፍተኛ ፋይዳ አለው። ምክንያቱም በዓለም የቅርስ መዝገብ ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እና አጼ ቴዎድሮስ ንግስናቸውን የተቀበሉበትን ጥንታዊ እና ታሪካዊ የሆነችውን የደራስጌ ማርያምን ለመጎብኘት እድሉን ያገኙበታል። ኢንተርፕራይዙ ከሚገነባቸው ፈታኝ ፕሮጀክቱች አንዱ የሆነ የበለስ – መካነ ብርሃን መንገድ ፕሮጀክት ለአካባቢው ማኅበረሰብ በተለይም በሥራ ዕድል ፈጠራም ረገድ ላቅ ያለ አበርክቶ አለው። ለአብነት በአሁኑ ወቅት ከ 560 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ይላሉ ኃላፊው።
ከ11 ዓመታት በላይ ከመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ጋር የሥራ ዝምድና ያላቸው ኢንጂነር ተስፋ ዘለቀ እንደሚያስገነዝቡት፤ ኢንተርፕራይዙ በተለይም ሌሎች መሰል ድርጅቶች በማይደፍሯቸው ውስብስብና ፈታኝ መልክዓ
ምድር ብሎም የፀጥታ ሁኔታ ባሉባቸው አካባቢዎች ውል በማሰር ውሉን በተግባር የሚፈፅም በመሆኑ ይህን ፕሮጀክት በጊዜው ለማጠናቀቅ ሌት ተቀን የሚተጋ ይሆናል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2015