ጦርነት እና ሠላም

ርዕሳችን የቂል ስለመምሰሉ ምንም ጥርጥር የለውም። ርዕሰ ጉዳያችን ግን በተቃራኒው ስለመሆኑ ማንም አይክደውም። “ልካደው” ቢል እንኳን ከራስ ሕሊና ጋር ከመጋጨት የዘለለ ምድር ላይ ያለውን ያፈጠጠ እውነት አይሰርዘውም፤ አይደልዘውምም። እናም ምንም እንኳን እንደ ሊኦ ቶልስቶይ “ዋር ኤንድ ፒስ” (እ.ኤ.አ 1869) ዘመን ተሻጋሪ ሥራ ባይሳካልንም ስለ ችግሩ ማውራት፣ ስለ መፍትሔው መጨነቅ የሁሉም፣ በተለይም የሰው ዘር ሁሉ ተግባር እና ኃላፊነት ይሆናል።

የዓለምን ታሪክ የቀየሩ ጦርነቶች ተብለው በዋና ዋና የታሪክ ሰነዶች ላይ ከሰፈሩት መካከል የተወሰኑትን ወስዶ ማየት ጠቃሚ ስለመሆኑ መከራከር አይቻልም። በተለይም ዘመኑ የ‹‹ዝም ብሎ ጦርነት›› ዘመን እንደ መሆኑ መጠን ይህ አይነቱ አካሄድ ባይጠቅምም አይጎዳምና የተወሰኑትን እየጠቀስን እንጨዋወት። በሰላምና በጦርነት መካከል ያለውን ልዩነት፤ በሰው ልጅ የመማርና ያለመማር ፍቃደኝነት መካከል ያለውን ባዶ ሜዳ መረዳቱን ለአንባቢ በመተው “ምናልባት ቢያስፏጨው” እንዲሉ እስቲ እናውጋ።

በፈረንሳይ ሃይማኖታዊ ማንነትን መነሻው ያደረገው “የመስቀል” ወይም “ቅዱስ ጦርነት” (እ.ኤ.አ 1095 – 1291)፤ ከጥቂት ባለፀጎች ለመላቀቅ፤ በወቅቱ አይነኬ የነበሩትን ሥርዓታት በመቃወም ብዙኃን ገባሮች የቀሰቀሱት ጦርነት (The French Revolu­tion (እ.ኤ.አ 1789 – 1799)፣ በአሜሪካና ሜክሲኮ መካከል የድንበር ግጭት የቀሰቀሰው ጦርነት (The Mexican-American War (እ.ኤ.አ 1846 – 1848) መማር ለፈለገ ከማስተማርም በላይ ናቸው። የአንደኛና የሁለተኛው የዓለም ጦርነቶችንም ያደረሱት ጥፋትና እልቂት ቀላል አልነበረምና በዝምታ እንለፋቸው::

የኃይማኖትና የጂዊሽ ማንነትን መሠረት ያደረገው፣ እ.ኤ.አ ከ1920 ጀምሮ እስካሁን ያላባራው የእስራኤል-ፍልስጤም ግጭት፤ ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ የመጣው ቀዝቃዛው ጦርነት (እ.ኤ.አ 1946–1991)፣ የኢትዮጵያ አርበኞች ሳይቀሩ የተሳተፉበት የኮሪያው ጦርነት (The Korean War (እ.ኤ.አ 1950–1953)፣ ከሁለቱም ወገን ከ2 ሚሊዮን በላይ ንጹሐን ዜጎችን ሲጥ አድርጎ የበላው የቬትናም ጦርነት (The Vietnam War (እ.ኤ.አ 1955 – 1975) ዛሬ ላይ ፀፀትን እንጂ ሌላ ያተረፉት ነገር የለም። የዛሬዎቹን የእርስ በርስ ጦርነት አዋጊዎችንም፤ ለምሳሌ በደቡብ ሱዳን ወደ ፊት የሚጠብቃቸው ተመሳሳይ ፀፀት ስላለመሆኑ ምንም ማስረጃ ባይኖረንም የሩዋንዳ ዜጎችን ያጫረሱ ከየገቡበት ጉድጓድ እየተለቀሙ ወህኒ ሲወረወሩ ግን እያየን ነው።

ሶቪየት ኅብረት በአፍጋኒስታን የሚንቀሳቀሰውንና የሶሻሊስት ርዕዮት የሚከተለውን ወገን በመደገፍ እ.ኤ.አ ሰኔ 1979 መጨረሻ አካባቢ ወደ አፍጋን ሠራዊቷን የላከችበት፣ እነ አሜሪካ ከዛኛው ወገን የተሰለፉበት ለሶቪየት ኅብረት መውደቅ፣ በኦሳማ ቢንላደን የሚመራው አል-ቃኢዳ መፈጠር እና ሌሎች ጉልህ ዓለም አቀፍ ክስተቶች ምክንያት መሆኑ የሚነገርለትና እስካሁንም ቂሙን ያልሻረው የሶቪየት-አፍጋን ጦርነት (The Soviet-Afghan War)፤ እንዲሁም፣ ከ18 ሚሊዮን በላይ በሆኑ ንጹሐን ላይ እልቂት ያስከተለው፣ ከ6.5 ሚሊዮን በላይ በአገር ውስጥ፣ ከ2.3 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ወደ ውጭ ሀገር ያፈናቀለው፣ ከ5 ሰዎች አንዱን ለአእምሮ ሕመም የዳረገው . . . ምኑ ቅጡ፣ የአሁኑ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትና ሌሎችም ለዓለም ሰላም ወዳድ ሕዝቦች ምን አስገኙ?

ኢራቅ ኢራንን በመውረር የአካባቢውን የኃይል የበላይነት ለመያዝ ጥረት ያደረገችበት ጦርነት (The Iraq-Iran War (እ.ኤ.አ 1980–1988) እና The Gulf War (እ.ኤ.አ 1990–1991) እና መሰል ጦርነቶች ያለቀላቸው ይምሰሉ እንጂ አሁንም ድረስ የተዳፈኑ እሳቶች ናቸው::

እርሾው የሶቪየት-አፍጋን ጦርነት መሆኑ የሚነገርለት፤ በአሜሪካ የመስከረም አስራ አንድ የሽብር ጥቃት መከሰት ወደ መጨረሻው ጠርዝ የገፋው የአሜሪካ አፍጋኒስታን ጦርነት (The U.S.-Afghan War (እ.ኤ.አ 2001–-2021) ቢላደንን ብቻ ሳይሆን፣ ጦሱ ለሳዳምም አልተረፈም ለማለት መረጃ የለም። ለሳዳም የተረፈው ይህ ጦስም ሊቢያን አላቆሰለም ማለት አይሆንም። ስለዚህ ጦርነት ያው ጦርነት እንጂ ሰላም አይሆንምና የሚመለከታቸው ሁሉ ሕሊናቸውን ወደ ሰላም ሊመልሱ፤ እጆቻቸውን ወደ ፈጣሪያቸው ሊዘረጉ ይገባል የሚለው ሕዝብ ቁጥር መብዛቱ ያለ ምክንያት አይደለም።

ሳዳም ሁሴንን (እ.ኤ.አ ከ1979–2003) ከሥልጣን ብቻም ሳይሆን ከዚህ ዓለም በሸምቀቆ ገመድ ያሰናበተውና ከ2 ትሪሊዮን በላይ ዶላርን ለጦርነት ዋጋ ያስወጣው የኢራቅ ጦርነት (The Iraq War (እ.ኤ.አ 2003–2011) አንድ ራሱን የቻለና የሰላጤውን አካባቢ የናጠው ጦርነት ዳፋ አሁንም እንዳለ ቢሆንም የተማረበት፤ ወይም እየተማረበት ያለ አካል ባለመኖሩ አካባቢው አሁንም “ያው ነው” ከመባል ያለፈ ታሪክ የለውም።

በአንድነት ኃይሎችና ተቃራኒዎቹ መካከል ተካሂዶ ከነበረውና ከሁለቱም ወገን ከ600ሺህ በላይ ተዋጊ ወታደሮችን ፉት ካደረገው የቻይናው የርስ በርስ ጦርነት (እ.ኤ.አ 1945–1949)፣ እስካሁንም በአሜሪካ የጦርነት ገመና አቻ ካልተገኘለት ዘግናኙ የአሜሪካው እርስበርስ ጦርነት (American Civil War (እ.ኤ.አ 1861–65)፣ ከዚህ ባለመማር የተከሰተውና የመቶ ሺዎችን ሕይወት ነጥቆ፣ ሚሊዮኖችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሎና ሀገሪቷን እንዳትሆን አድርጎ አሻራው እስካሁንም ያልጠፋው የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት (እ.ኤ.አ 2011-2017) ሁሉ እንደው የሚማር ቢገኝ የሚያስተምረው ዐቢይ ጉዳይ ከሰላም የሚገኘውን ሁለንተናዊ ፋይዳና በጦርነት የሚመጣውን ሁለንተናዊ ውድመት ነው። የሚማር ቢገኝ የሚያስተምረው፣ በሱዳን፣ ሩሲያና ዩክሬን እንዳለው ወቅታዊ ፍም እሳት ሳይሆን፤ የሰው ልጅ ምርጫ ከጦርነት ይልቅ ሰላም መሆን እንዳለበት ነበር።

የዛሬዋ ዓለማችንን የዛሬ መልክና ቁመናዋን እንድትይዝ ያደረጉ አስከፊ ጦርነቶች፣ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት የተስተዋለባቸው፤ ንጹሐንን ያለ ንሰሐቸው ስልቅጥ ያደረጉ፤ ከራሳቸውም አልፈው የዓለምን ኢኮኖሚ ያዛቡ፤ እጅግ ሲበዛ የመሪዎች ስሜታዊነት የታየባቸው፤ ስውር ዓላማቸው የበላይነትን ፍለጋ መሆኑ በታሪክ ድርሳናት የሰፈረላቸው ጦርነቶች ናቸው:: እስካሁን ያልተመዘገቡ፣ ወደ ፊት ደግሞ በታሪክ ተገቢ ቦታ የሚኖራቸው የሩሲያ-ዩክሬን አይነቶቹን ጦርነቶች እዚህ ላይ ጨምሮ ማሰብ በራሱ “ሰላም ሆይ ወደ የት አለሽ?” የሚያስብሉ ናቸው።

በጣም የሚያሳዝነው፣ ከእነዚህ ሁሉ ጦርነቶች ጀርባ ያለው ፕሮፓጋንዳ ብሔራዊነት (ናሽናሊዝም)፣ ሉዓላዊነት፣ ዳር ድንበር፣ ሰብዓዊ መብት፣ ሃይማኖታዊ ማንነት ወዘተርፈ መሆናቸው ሲሆን፣ እንደ በርካታ ጥናቶች ድምዳሜ እነዚህ ሁሉ ማስመሰያና መሸፋፈኛ እንጂ ትክክለኛ የጦርነቱ መነሾ ምክንያቶች አይደሉም። ዋና መነሾው የሥልጣን ጥምና አልጠግብ ባይነት ነው።

ነገሩ እውነት ይመስላል። የአፍሪካ ኅብረትን እ.ኤ.አ በ2020 የጠመንጃ ድምፅ የማይሰማባት አፍሪካን እውን የማድረግን መሪ ቃል ለጊዜው ትተን፣ በእ.ኤ.አ በ1994 በሩዋንዳ የደረሰውን የርስ በርስ እልቂትና ሌሎችንም ሳንጨምር፤ እስኪ አሁን ሱዳን ውስጥ እየሆነ ያለው ጉድ የማንን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ነው? የትኛውን ድንበር ለማስከበር ነው? የትኛውን ሕዝብ ለመጥቀም ነው? የትኛዋን ደቡብ ሱዳንንስ ለማበልፀግ ነው?

አዋጊዎቹስ ቢሆኑ፣ እዛው የፈረደበት፣ ብዙም ድካምና ጭንቅላት እማይጠይቀው የብሔር ፖለቲካ ውስጥ ከመወሸቅ ያለፈ ምን አይነት አሳማኝ ምክንያት ሲሰጡ ታይተዋል? ወይም ተሰምተዋል? ናይጄሪያ፣ ሶማሊያ ወዘተ ምን የተለየ ነገር አለ?:: በጣም የሚያሳዝነው ማንም ከማንም መማር ባለመቻሉ ዘልዓለም ዓለሙን ዓለማችን የጦርነቶች አውድማ እንደሆነች የመዝለቋ ጉዳይ ነው። ይህ ነው እጅጉን የሚያሳዝነውና ምናልባትም ተስፋ የሚያስቆርጠው::

በዚህ ጉዳይ ላይ አተኩረው፣ ጉዳዬ ብለው የሚሠሩ በርካታ ሀገር አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማት በርካቶች ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ Vision of Humanity፣ Institute of Economics & Peace፣ ግሎባል ሲቲዝን፣ የዓለም ጤና ድርጅት፣ ዩኤን ተጠቃሽ ናቸው። ከእነዚህ እና ሌሎች ተቋማት በየዓመቱ ለአደባባይ የሚበቁ የጥናትና ምርምር ሥራዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ የሰው ልጅ ከናካቴው የመጥፊያው ጊዜ አልደረሰም ማለት አይቻልም።

እ.ኤ.አ በ2021 ይፋ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው፣ በጦርነት ምክንያት ብቻ እ.ኤ.አ በ2017 በትንሹ ከ14 ነጥብ 76 ትሪሊዮን ዶላር በላይ እያጣች ሲሆን፤ እ.ኤ.አ በ2019 ከ14 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር በላይ አጥታለች። ይህም እየጨመረ መሄዱ እንዳለ ሆኖ፣ እያንዳንዱ የፕላኔቷ ነዋሪ በየቀኑ በትንሹ አምስት ዶላር ያጣል ማለት ነው።

ይኸው ጥናት እንዳመለከተው፣ በከፍተኛ ደረጃ በጦርነት እየተጎዱ ያሉ 10 ሀገራት በየዓመቱ በአማካይ የዓመታዊ የሀገር ውስጥ ምርታቸውን 59 ከመቶ ጦርነቱ ላስከተለው መዘዝ እያዋሉት ይገኛሉ። ለምሳሌ፣ ሶሪያ 60 ከመቶ፣ አፍጋኒስታን 50 ከመቶ፣ ደቡብ ሱዳን 46 ከመቶ ለጦርነት አውለዋል:: ኢትዮጵያም በሰላም እጦት ምክንያት (ዘንድሮ) ኢንተርኔትን በመዝጋቷ በትንሹ 42 ሚሊዮን ዶላር አጥታለች::

ሰላም የሰዎች በሕይወት የመኖር ሰብዓዊ መብት ይከበር ዘንድ፤ ከፍተኛ የሥራ እድል ይፈጠር ዘንድ፣ በጣም ዝቅተኛ ግሽበት ይኖር ዘንድ፣ ሀገርና ሕዝብ ይበለፅጉ ዘንድ፣ የዜጎች ሰላምና ደህንነት ይረጋገጥ ዘንድ፣ መጠነ ሰፊ መሠረተ ልማት ይካሄድ ዘንድ ከፍተኛ እድል ይሰጣል:: ጦርነት ግን የዚህ ሁሉ ተቃራኒ ነው። ይሁን እንጂ “እናውቅላችኋለን” ባዮች ጦርነትን ከመጀመሪያው የበለጠ ሲመርጡት እየተስተዋለ ነውና ጉዳዩ እንዲህ እንደምንፅፍና እምናነበው እዳው ገብስ አይደለም።

መንግሥታት፣ ፖለቲከኞች፣ በየደረጃው ያሉ መሪዎች ይህንኑ ጦርነት በመምረጣቸው ምክንያት ዛሬ በዓለማችን 689 ሚሊዮን ሕዝብ፤ ወይም፣ ከአጠቃላይ የዓለም ሕዝብ 9 ከመቶ የሚሆነው በቀን በአማካይ ከ1 ነጥብ 90 ዶላር በታች ያገኝ ዘንድ ተገድዷል።

ከላይ በወፍ በረር እንደቃኘነው፣ ያለንበት ዘመን ዓለማችን በየእለቱ ከፍተኛ ጦርነቶችን በአይነት በአይነት እያስተናገደች ያለችበት ዘመን ነው። የጦር መሣሪያ እሽቅድድሙ ለጉድ ነው። ፍጥጫው አንዱ አንዱን ለመዋጥ ያሰፈሰፈ መስሎ ነው የሚታየው። በእነዚሁ የማያባሩ ጦርነቶች ምክንያትም ዓለማችን በየዓመቱ በአማካይ ከዓመታዊ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) 10 ከመቶ ያህሉን ለጦርነት ታውላለች። ወጪው ብቻ አይደለም የሚዘገንነው፤ በእነዚሁ ጦርነቶች ምክንያት በየዓመቱ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ንፁሐን፣ አምራችና ትርፋማ የሆኑ ሰዎች ለከፋና ጭካኔ ለተሞላበት ሞት መዳረጋቸው ነው።

‹‹ልክ እንደ አንድ የሚሸጥ እቃ እስኪ ጦርነት እና ሰላም ላይ የዋጋ መግለጫ እንለጥፍ። የቱ የሚበልጥ ይመስላችኋል?›› የሚሉት የIEP መሥራችና ሥራ አስፈፃሚ ስቴቬ ኪሌሌ በገዛ እጃችን እራሳችንን መከራ ውስጥ እየከተትን ያለነው እራሳችን ነን ባይ ናቸው:: ሀገራት ለጦርነት ከሚያውሉት ወጪ 2 ከመቶ ያህሉን እንኳ ቢቀንሱ ከውጪ መበደር የሚኖርባቸውን ከማስቀረት ባለፈ አጠቃላይ የልማት ሥራዎቻቸውን የትና የት ሊያደርሱት እንደሚችሉም ይጠቁማሉ::

ጦርነቶችን በአገራት የአገዛዝ ባሕርያት ለይተው የሚያጠኑ ተቋማት እንደሚያመለክቱት ከዲሞክራሲያዊ አገራት የበለጠ የአገራቸውን ሀብትና ንብረት ለጦርነት የሚገብሩት አምባገነን አስተዳደር ያላቸው ሀገራት ናቸው:: የአምባገነኖቹ ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ምርት 11 ከመቶ ሲሆን፤ የዲሞክራቶቹ ደግሞ 4 ከመቶ ነው። ይህ ብቻ አይደለም፣ እ.ኤ.አ ከ2007 ጀምሮ ዲሞክራሲያዊ አገራት ለጦርነት የሚያውሉትን ወጪ በ16 በመቶ ሲቀንሱ፣ የአምባገነናቱ ሀገራት በ27 በመቶ እየጨመረ መገኘቱም ሌላውና እጅግ አሳሳቢው ጉዳይ ነው።

እ.ኤ.አ በ2019 እየተደረጉ በነበሩ ጦርነቶች ሳቢያ ለከፍተኛ ወታደራዊ የጦር መሣሪያዎች መሸመቻ በአጠቃላይ 5 ነጥብ 9 ትሪሊዮን ዶላር የወጣ ሲሆን፤ ይህ ለሕዝቦች ደህንነት ጥበቃ ከሚውለው በእጅጉ የናረ ነው።

ሌላውና ከጦርነትና ግጭቶች ጋር በተያያዘ የሚነሳው የሰዎች ዋጋ (ሁዩማን ኮስት) ጉዳይ ሲሆን አሜሪካንን ለማሳያ አንስቶ ማየት ይቻላል:: በዚህ “ዓለም አቀፍ” በተባለውና አሜሪካ ከ85 በላይ አገራትን በጠላትነት ፈርጃ በተሳተፈችበት ጦርነት ብቻ በአፍጋኒስታን፣ ፓኪስታን፣ ኢራቅ፣ ሶሪያ፣ ሊቢያ፣ የመን፣ ሶማሊያ እና ፊሊፒንስ ከ38 ሚሊዮን ሰዎች በላይ ተፈናቅለዋል። 7ሺህ 050 የአሜሪካን ወታደሮችን ጨምሮ፣ ከ929ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል።

ለዚህ ጦርነት ብቻ ከላይ የተጠቀሱት ሀገራት ከ8 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ኪሳራን “አሜን” ብለው ተቀብለዋል። በተጎዱት አገራት የተሰከተው ሥራ አጥነት፣ የወደመው ንብረት፣ የጠፋው የሰው ሕይወት … ሲታይ የብዙዎች ቁጭትና “ይህ ሁሉ ገንዘብ ሰዎችን ለመግደል መዋሉ ቀርቶ ለልማትና ብልጽግና ቢሆን ኖሮ …?” የሚያስብል ነው:: ‹‹ይህ ሁሉ ግን ለምን ሊሆን ቻለ?›› የብዙዎች ጥያቄ።

ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው ካለፈው ካለመማር ነው:: ከአንደኛና ሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ያለመማር ነው። ከ1945ቱ የሄሮሽማና ናጋሳኪ አስቃቂ እልቂት አለመማር ነው:: ሀገራትን ለማቆየት አያት ቅድመ አያቶች የከፈሉትን መስዋዕትነት በነጭ ለመሰረዝ ከመፈለግ የመነጨ ነው:: ከ“እኛ”ነት ይልቅ “እኔ”ነት መንገሱ ነው። ቅጥ ያጣ ፖለቲካ የዲሞክራሲውን ምሕዳር መቆጣጠሩ ነው። ውይይትን መፍራት ነው። ባጭሩ፣ ከላይ ከዘረዝረናቸውና ሌሎችም ክስተቶች አለመማር ነው::

ሰላም!!!

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 29/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *