ስለነገው – ዛሬን …

 በከተማችን አንዳንድ ስፍራዎች በመኪና ጉዞ ሲጀምሩ ሁሌም በምቾት ላይሆን ይችላል። አንዳንዴ የመንገዱ ደህንነት ከሥጋት ይጥላል። በተለይ የተሳፈሩበት መኪና ታክሲ ከሆነ መሳቀቁ አያድርስ ነው። ደርሶ በአየር ላይ ይበር የሚመስለው መኪና ያሉበትን ያስረሳዎታል፡፡

በፍጥነቱ ደንግጠው ቁጣ ቢጤ፣ አልያም ተማጽኖ ከሞከሩ ደግሞ ውጤቱን መጠበቅ ነው። ልመናዎን ከጭቅጭቅ የሚያስበው አሽከርካሪ በድርጊቱ ይብሳል። ጆሮ የሚያደነቁር ሙዚቃውን እስከ ጣራ ይለቅና ፍጥነቱን ጨምሮ ቁጭ ብድግ ያሰኝዎታል። ይህኔ ሁሉን ትተው ‹‹አውጣን›› ሲሉ ፈጣሪዎን ሊማጸኑ ይችላሉ፡፡

ለእንዲህ አይነቶቹ ሥርዓት አልባ አሽከርካሪዎች ሲባል በየመንገዱ የሚከተረው የፍጥነት መቆጣጠሪያ ታዲያ የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ አስተዋፅኦው የጎላ ነው። በዚህ ሳቢያ በአንዳንድ ውስጥ ለውስጥ መንደሮች ጭምር በዚህ ስጋት የወደቁ ነዋሪዎች የራሳቸውን መላ መዘየዳቸው አልቀረም፡፡

ነዋሪዎች በአካባቢው ያለ ቅጥ የሚበረውን መኪና ፍጥነት ለመቆጣጠር የሚያስችል ክትር ማዘጋጀትን ለምደዋል። ይህን ቢያደርጉ አይፈረድም። በአንዳንድ ሰፈሮች መሀል የሚያልፉ መኪኖች ሁኔታ በእጅጉ ያስደነግጣል። አሽከርሪዎቹ በመንገዱ ፈጥነው ማለፋቸውን እንጂ ስለነዋሪው ደህንነት ደንታም የላቸው፡፡

እንዲህ መሆኑ ያልታሰበ አደጋ እንዲፈጠር ምክንያት ነው። ይህ አጋጣሚ በመንደራቸው በሚጫወቱ ህጻናት፣ በዝግታ በሚራመዱ አቅመ-ደካሞችና ሌሎችም ላይ አደጋን ያስከትላል። በየመንደሩ የሚሮጡ መኪኖች ፍጥነታቸውን ባለመቆጣጠራቸው ህይወትን ይቀጥፋሉ። አካል አጉድለው ንብረት ያወድማሉ፡፡

በየአካባቢው በሰዎች ፍላጎትና ባልተጠና ዝግጅት የሚሰራው የፍጥነት መቆጣጠሪያ ታዲያ ጊዜያው መፍትሄ ቢኖረውም ምቾት አልባነቱ ያመዝናል። የመኪኖች ጎማ በረገጠው ጊዜ ለተቃና የመንገድ ጉዞ አይጋብዝም። ሲሰራ በጥናቱ ያልታየ ነገር ይሁን እንጃ ችግሩ በግልፅ ጎልቶ ይስተዋላል፡፡

አልፎ አልፎ እንዲህ አይነቱ ተሞክሮ ከውስጥ ለውስጥ መንገዶች አልፎ በዋና አስፓልት ጭምር ይስተዋላል። እንደውም አንዳንዴ ክትሩ ለአደጋ ያጋልጥ ይሆናል። ፍጥነቱ መካከለኛ የሆነ መኪና በላዩ ለማለፍ የሚቸገርበት ሁኔታም ይኖራል። በዚህ አጋጣሚ ግን የፍጥነት መቆጣጠሪያውን እንደ መፍትሄ የተጠቀሙበትን አካላት ተሞክሮ ሳላደንቅ ማለፍ አይቻለኝም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አሳሳቢውን የትራፊክ አደጋ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የፍጥነት መቆጣጠሪያዎቹን በየመንገዱ ማየት ጀምረናል። በግልጽ ማስተዋል እንደሚቻለውም እነዚህ የፍጥነት መቆጣጠሪያዎች ወሳኝ በሚባሉ ስፍራዎች ላይ የተገጠሙ ናቸው፡፡

መቆጣጠሪያዎቹ በእኔ እይታ እስካሁን ከነበሩትና በልምድ ከምናውቃቸው በአይነትና በጥራት ለየት ይላሉ። ዘመናዊነትን የተላበሱ ስለመሆናቸውም መገመት አያዳግትም። በእነዚህ የፍጥነት መቆጣጠሪያዎች ላይ በተለይ ከፍ ያሉ መኪኖች ሲያልፉ ምቾት አልባነት አይሰማም። ክትሮቹ ስለ መኖራቸው አስቀድሞ በግልጽ ማየት ይቻላልና በጥንቃቄ አስተውሎ ለማለፍ አይቸግርም፡፡

እንዲህ አይነቶቹ የፍጥነት መቆጣጠሪያዎች ከከተሞች የመንገድ ግንባታ ጋር የሚስተካከሉ በመሆናቸው ዘመናዊነትን ያመላክታሉ። ለከተማችን ዕድገትም ተጨማሪ እርምጃዎች ናቸው። በእነዚህ ሀብቶች በአግባቡና በወጉ ከተጠቀምንባቸው ደግሞ ዓመታትን ያለትራፊክ ሥጋት መራመድ ያስችሉናል፡፡

በእኔ እይታ በከተማችን የተለያዩ ሥፍራዎች የተገጠሙት የመንገድ ላይ የፍጥነት መቆጣጠሪያዎች ዕድሜ እምብዛም የሚባል አይደለም። ባልሳሳት ቆይታቸው አንድ፣ አልያም ሁለት ዓመት እያልን ግምት የምንሰጥበት ቆጠራ ላይ አያደርሱንም። በአጭር አገላለጽ የፍጥነት መቆጣጠሪያዎቹ የመንገድ ላይ ቆይታ አጭር የሚባል ነው፡፡

እነዚህ ብዙ ያልንላቸው፣ የተሻሉ ናቸው የሚባሉ፣ የፍጥነት መቆጣጠሪያ ክትሮች ከተወሰኑ ጊዜያት ወዲህ ገጽታቸው ተቀይሯል። ቀድሞ በምቾት መኪኖችን ያመላልሱ እንዳልነበር ዛሬ ላይ ራሳቸውን መሸከም ተስኗቸው መፈረካከስ ይዘዋል። ዳርና ዳር ያላቸው ይዞታ መኪኖችን በወጉ የሚያስተናግድ አልሆነም። ቀሪው አካላቸውም አቅም አጥቶ እጅ መሥጠት ጀምሯል፡፡

አስጊው ጉዳይ ይህን ችግር በወቅቱ አስተውሎ የመፍትሄ እርምጃ የሚወስድ አካል ከሌለ ነው። እስካሁን በምናወቀው አብዛኛው ተሞክሮ ለብዙኃን አገልግሎት የሚሰጡ የሀገር ሀብቶች ሲባክኑና ለውጥ ሲያሻቸው በፍጥነት የሚያስተካክል ‹‹የኔ ነው›› ባይ አካል ፈጥኖ አይገኝም። ንብረት ሲበላሽ በአስቸኳይ የሚያነሳና የሚተካ፣ ክፍተቱን በተሻለ የሚሞላ ክፍልም የለም፡፡

ይህን ጉዳይ ስታዘብ ተመሳሳይ የሚባል አንድ እውነታን ላስታውስ ግድ አለኝ። ስፍራው በከተማችን ክልል፣ ከለቡ እስከ ጀሞ አንድ የሚገኝ አካባቢ ነው። ከዓመታት በፊት በዚህ ስፍራ ለብስክሌት ተጠቃሚዎች ተብሎ ከመኪና መንገዱ የተከፈለና የተወሰነ ሜትር የሚጓዝ መንገድ ስለመዘጋጀቱ ልብ ይሏል፡፡

በዚህ መንገድ ላይ ዓላማውን የሚያሳዩና ለታቀደው ሃሳብ የሚመጥኑ ቁሶች በወጉ ተዘጋጅተው እንደነበር አስታውሳለሁ። ተከፍሎ በተለየው መንገድ ላይ መኪኖች ማለፍ ስለማይቻላቸው እግረኞች እየተጋፉ መሄድ ግድ ይላቸዋል።

ስፍራውን ሞልተው የያዙት ድቡልቡል ባለቀለማት ዓይን የሚገቡ ቁሶች ታዲያ ያለአንዳች ተግባር በቦታው ተቀምጠው ቆይተዋል። እንዲህ መሆኑ በአካባቢው የሚያልፉ መኪኖች በጎማቸው እያሽቀነጠሩ እንዲጥሏቸውና ከነበሩበት አደራደር እንዲጓደሉ ምክንያት ሆኗቸው ቆይቷል፡፡

ያለአንዳች ተግባር ሥፍራውን ይዘውት የቆዩት ቁሶች የትራፊክ ፍሰቱን ከማጨናነቅ ባለፈ የታሰበላቸውን ዓላማ ከግብ ሳያደርሱ ያለአንዳች ጥቅም ባክነው መቅረታቸውን አውቃለሁ። አልፎ አልፎ በራሳቸው ፈቃድ ከሚጠቀሙ ህጸናት ብስክሌተኞች በስተቀር ቦታው ያለአንዳች ጥቅም ተከልሎ ቆይቷል፡፡

ቁሶቹ ውሎ አድሮ የነበራቸው ውበትና አቅም ተጓድሎ በአቧራና ጭቃ ተለውሰው በሰዎች እግርና ንክኪ መልካቸው ተቀይሮ ለእይታ ማስቀየማቸው አልቀረም። ማንም በአካባቢው ሲያልፍ ስለሁኔታው መጠየቁ እንደማይቀር እገምታለሁ። ይሁን እንጂ ከግምት የዘለለ ስለቦታው ምንነትና ዓላማ በቂ ምላሽ እንደማያገኝ መገመቱ ቀላል ነው፡፡

እነዚህ ለብስክሌት መንገድ ተብለው የተዘጋጁ ድቡልቡል ባለቀለማት ቁሶች የሀገር ሀብትና ገንዘብ እንደፈሰሰባቸው እሙን ነው። የሚገርመው እንዲህ መሆኑ ብቻ አይደለም። በተገቢው ጊዜ ለሚመለከታቸው ተደራሽ አለመሆናቸው ባልተገባ አካሄድ ሀገርን ለኪሳራ እንደሚዳርጉ ግልጽ ነው።

በከተማችን አንዳንድ ስፍራዎች የሚዘጋጁ አገልግሎት ሰጪ ንብረቶች በወጉ ከተጠቀምንባቸው ጠቀሜታቸው ለትውልድ ይሻገራል። ጀምሮ ከመተው፣ አሳይቶ ከመንሳት ይልቅ ብልሽት ሲያጋጥም ፈጥኖ በመጠገንና መፍትሄ በማበጀትም ዕድሜያቸውን ማራዘም፣ ጠቀሜታቸውን ማስፋት ይቻላል፡፡

የሀገርን ጥቅም በማስከበር የሚደርሱ ኪሳራዎችን ለመታደግ ይህቺን ድሀ ሀገር በዚህ ማሳያ ልንደጉማት ይቻለናል። በየጊዜው በአዳዲስ ሥራዎች ከመታየት በዘለለ በእጃችን ያለውን አክብረን በመያዝ ከብክነት የመዳን ባህልን ማዳበር ግድ ይለናል፡፡

እንዲህ ለማድረግ ግን አሳቢ ልቦና፣ አስተዋይ ዓይኖችና የእኔነት ስሜት ከእኛ ሊሆኑ ይገባል። የነገውን ታላቅ ስልጣኔ የምናየው የዛሬውን በማጥፋትና በማጉደል ሳይሆን ከእጃችን ያለውን በወጉ ስናከብር ነውና። አበቃሁ!

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 29/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *