ኮሎኔል ፍቃደ ገብረየስ የተወለዱት በቀድሞው ምዕራብ ሸዋ መናገሻ አውራጃ በአዲስ ዓለም ከተማና በወለንኮሚ ከተማ መካከል ልዩ ስሙ እሁድ ገበያ ወረብ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነሐሴ 29 ቀን 1946 ዓ.ም ነው ፡፡ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ማለትም በ1954 ዓ.ም ገደማ መርካቶ አማኑኤል መሳለሚያ አጠገብ በሚገኘው የቀድሞው ወሰንሰገድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአንደኛ ክፍል ትምህርታቸውን “ሀ” ብለው ጀመሩ::
በዚህ የልጅነት እድሜያቸው እንደእኩዮቻቸው ትምህርታቸውን መማር ብቻ ሳይሆን፤ ጎን ለጎን ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ለማገዝ የተለያዩ ወረቀቶችን በኪሎ እየገዙ ለእቃ መያዣነት የሚያገለግሉ የኪስ ወረቀቶችን በመሥራትና መርካቶ ወስደው በመሸጥ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ይደጉሙ ነበር::
በወቅቱ በወይዛዝርቶች እጅግ ተወዳጅ የነበረውን የኦጋዴን ዕጣንን ሸጠዋል፤ ለተወሰነ ጊዜም ጋዜጣ አዙረዋል:: በዚህ መልኩ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀድሞ ስሙ ልዑል መኮንን በአሁኑ አዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል::
የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ ትምህርታቸውን በማቋረጥ “የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ባሕር ኃይል” የሚባለውን ተቋም ተቀላቅሉ፡፡ ለአራት ወር ያህል ከቆዩ በኋላ ባጋጠማቸው ቤተሰባዊ ችግር ምክንያት ሥልጠናውን አቋርጠው ወጡ::
የዛሬው እንግዳችን ወደ ወታደራዊ ሙያ በመመለስ እስከ ኮሎኔልነት ማዕረግ ሀገራቸውን አገልግለዋል፤ በሲቪልነትም በአመራር ክህሎት የሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በሥራ አመራር ክህሎት ዙሪያ የተለያዩ መጽሐፍትን በመጻፍ ሥልጠናዎችን በመስጠት ይታወቃሉ::
አዲስ ዘመን ፦ ኮሎኔል አሮጌ መጽሐፍ ተራ ገብተው ሲነግዱ እንደነበር የኔ መንገድ ብለው በጻፉት ግለ ታሪክዎ ላይ አንብበናል:: ስለአሮጌ መጽሐፍ ተራ ያለዎት ትውስታ ምን ይመስላል ?
ኮሎኔል ፈቃደ፦ አዎ! አሮጌ መጽሐፍት ተራ መጽሐፎችን እየሸጥኩ ትምህርቴን በማታው ክፍለ ጊዜ እየተከታተልኩ ነበር:: መጽሐፍት ተራው ላይ በምንውልበት ጊዜ በርካታ ታላላቅ ሰዎችን የማግኘት እድሉ በጣም ሰፊ ነበር:: ለምሳሌ ክቡር አቶ ከበደ ሚካኤል፣ አቤ ጉበኛ እና ሌሎችም እዛው ከሚውሉ ሰዎች መካከል ስለነበሩ በወቅቱ ከእነሱ ጋር በርካታ ሀሳቦችን እንለዋወጥ ነበር:: የያዝነውን መጽሐፍም እናነብ ነበር:: በጠቅላላው የእውቀት ቦታ ነበር ማለት ይቻላል::
ትምህርቴንም 12ኛ ክፍል ካጠናቀቅሁ በኋላ የመጽሐፍ ንግዱን ትቼ ወደ መምህርነት ሙያ ገባሁ:: በሚገርም ሁኔታ እዛ ትምህርት ቤት ሳስተምር ትልቅ እውቀት ያለው ጓደኛ ገጠመኝ:: በዚህም ብዙ ነገሮችን አስተማረኝ፤ የዓለም ትላልቅ መጽሐፎችን ታሪክ እየተነተነ ያስተማረኝም እሱ ነው::
አዲስ ዘመን ፦ ከዛ ወደ ውትድርና ገቡ?
ኮሎኔል ፈቃደ፦ አዎ! 1969 ዓ.ም በሀገር ላይ ጦርነት ተከፈተ፤ በሀገር ውስጥ ቀይ ሽብር ነጭ ሽብር የሚሉ ነገሮች ተፈጠሩ:: እኔና ጓደኞቼም” መንገድ ላይ ከምንሞት ለምን ወታደር ሆነን ለእናት ሀገራችን አንሞትም” በሚል ውትድርና ገባን:: ሆለታ ገነት ቃዴት ሠለጠንን::
የውትድርና ሕይወት ባሕር ማለት ነው:: እኔም ብዙ ነገሮችን የቀዳሁት ከዛ ነው:: ብዙዎቻችን ውትድርና ከውጪ ሲያዩት ክላሽ መተኮስ ብቻ ይመስለናል:: ነገር ግን የዓለም ሳይንስ ያለው ውትድርና ውስጥ ነው:: ዳኛ፣ ኢንጂነር፣ አካውንታንት፣ አስተዳደር፣ አይ ሲቲ በጠቅላላ ሁሉም ሙያ ውትድርና ውስጥ አለ:: ይህንን ሁሉ ነገር እንማራለን ማለት ባይሆንም እግረ መንገዳችንን ሁሉንም እንነካዋለን:: ከውድርና ወጥተን በሌላ ሥራ ዓለም ላይ ስንሰማራ ሁሉም ሙያ ቀላል የሚሆነው ለዚህ ይመስለኛል::
ከወታደር ቤት ሥልጠናዬን አጠናቅቄ ስወጣ ሀገሪቱ በኤርትራ እንዲሁም በሶማሌ ጦርነት ውስጥ የነበረችበት ወቅት በመሆኑ እዛ ላይ የመሳተፍ እድል ነበረኝ:: በሌላ በኩል ግንባር ላይ ቀልጣፋ ወታደር መሆን ከተቻለ እና ዓይን ውስጥ ከተገባ ተጨማሪ ትምህርት ቢያገኝ የበለጠ ያገለግላል ተብሎ ስለሚታሰቡ የተለያዩ የትምህርት እድሎች ይመቻቻሉ:: እኔም በዚሁ መልኩ ሶቭየት ኅብረት ለመማር የመጣውን እድል ተወዳድሬ በማለፌ፤ በ1971 ዓ.ም ለተሻለ ትምህርት ወደ ሶቭየት ኅብረት እንድሄድ ተመረጥኩ::
አዲስ ዘመን ፦ በሶቭየት ኅብረት የነበረዎት ቆይታ ምን ይመስላል ?
ኮሎኔል ፈቃደ፦ ከውትድርና ሌላ ሕይወትን የሚጠይቅ ሙያ የለም፤ በመሆኑም ከምንወጣው ከባድ ኃላፊነት የተነሳ ሥልጠናውም ከሲቪል የተለየና የትኛውም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከሚሰጠው በላይ ነው:: በነገራችን ላይ ሀገራችንም ውስጥ ይሁን ሌላው ዓለም ላይ የሚሊተሪ አካዳሚዎች የሚሰጧቸው ሥልጠናዎች በጣም የተደራጁና ጠንካራ ናቸው:: ብዙ ነገሮችን ለመማር የሚገፋፉ ናቸው:: በተለይም ስብዕናን በሚቀርጸው ትምህርት አሰጣጣቸው ይለያሉ:: የውሳኔ አሰጣጥ ብቃትን የሚጨምሩ፤ ማዳመጥን እና ችግር የመፍቻ ጊዜን በአግባቡ የመጠቀም ነገሮችን በጥልቀት የማየት ክህሎቶች ሁሉ ያሉበት ሥልጠና ነው::
በወቅቱ ሶቭየት ኅብረት ትልቅ ሀገር ስለነበረች፤ የሠለጠነውን ዓለም እንዳይ አግዞኛል የሚል እምነት አለኝ:: ሥልጠናው ቀላል አልነበረም:: የሚያሳዝነኝ ግን እንደዛ በፌዴራሊዝም መርሕ ተገምዳ እስከ መገንጠል ድረስ በሚል አካሄድ እየተመራች፤ የነበረች አስራ አምስት ቦታ መከፋፈሏ በጣም አሳዛኝ ነው:: እንግዲህ ሀገራችንም ከዚህ ታሪክ ብዙ መማር የምትችል ይመስለኛል::
አዲስ ዘመን ፦ ከትምህርት ከተመለሱ በኋላ የሥራውን ዓለም የት ተቀላቀሉ?
ኮሎኔል ፈቃደ፦ በማሠልጠን በማማከር የተለያዩ ሥራዎችን ሠርቻለሁ:: ለምሳሌ አዋሽ 40 የሚባል ቦታ ላይ ሜካናይዝዶችን ማለትም ታንክና መድፍ የማሠልጠን ኃላፊነት ተወጥቻለሁ:: አዲስ አበባ “ቤላ” ላይ የተለያዩ ኮሎኔልና መኮንኖችን በማስተማርም ተሳትፌያለሁ:: እንደዚህ እያልኩ እያስተማርኩም እየተማርኩም ከቆየሁ በኋላ፤ የመንግሥት ለውጥ መጥቶ ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ አገሪቱን ሲቆጣጠር ሁሉም ነገር ተለወጠ::
በወቅቱ ብዙ ቤተሰብ ያለው ሠራዊት ተበተነ፤ አብዛኛውም ለሀገር ምንም እንዳላበረከተ ሆኖ ለልመና ተዳረገ :: የተወሰኑት ደግሞ እየተፍጨረጨሩ ራሳቸውን ቻሉ፤ ተፍጨርጭረው ራሳቸውን ከቻሉት መካከል አንዱ እኔ ነኝ:: በወቅቱ ኢሕአዴግ ከተቀናሽ የቀድሞ ሠራዊት ውስጥ የተሻለ አቅም አላቸው ብሎ ያመነባቸውን 6ሺ ያህል ወታደሮች ሲመልስ፤ እኔም አንዱ ሆንኩኝ::
በሻለቅነት ማዕረጌ ተመልሼ መከላከያ ውስጥ ባገኘሁት የትምህርት እድል ሁለተኛ ዲግሪዬን ተማርኩ:: በዚህም የውትድርና እውቀትና የትምህርት ማስረጃዬ የሥራ ልምዴ ተደማምሮ የተለያዩ ሥራዎች በመሥራት እስከ ኮሎኔልነት ማዕረግ ደረስኩ ::
አዲስ ዘመን ፦ ወደ መጽሐፎችዎ እንምጣና እና እስካሁን ስንት መጽሐፎች ጽፈዋል፣ የሚያተኩሩትስ በምን ላይ ነው ?
ኮሎኔል ፈቃደ፦ እንግዲህ በሲቪሉም እስከ ሁለተኛ ዲግሪ አለኝ በሚሊተሪውም እንደዛው፤ እንደው ተምሮ ለራስ ብቻ ከመያዝ በሚል መጀመሪያ አምስት ያህል መጽሐፍትን ጽፌያለሁ:: የሥራ አመራር ስትራቴጂ ላይ የሚያተኩር መጽሐፌ የመጀመሪያው ሲሆን፤ መጽሐፉ ስትራቴጂ ከውትድርና የመጣ ስለመሆኑ እንዴት ተደርጎ ደግሞ ለሲቪል ሥራ መዋል እንደሚችል የሚያሳይ ነው::
ትንሽ ቆይቼ ደግሞ ድርጅቶችን ልክ እንደ ሰዎች ጤና ሁሉ ያሉበትን ደረጃ መመርመር ያስፈልጋል በማለት “ድርጅታዊ የጤና ምርመራ” የሚል መጽሐፍ ጻፍኩኝ:: ለዚህ መጽሐፍ መነሻ የሆነኝ ደግሞ በሀገራችን በብዛት የሚታየው የድርጅቶች ውጫዊ ገጽታና ውስጣዊ አገልግሎት አለመገናኘት ነው:: ተቋሞቹ ራዕይ እና ተልዕኮ እያሉ የሚያስቀምጡትና በተግባር የሚያከናውኑት ሥራ ፍጹም የተለያየ መሆኑ ነው:: ለምሳሌ አንዳንድ ድርጅቶች ውጫቸው በጣም አንጸባራቂ የሚስብ ይሆንና፤ አገልግሎታቸው የሠራተኛ አስተዳደራቸው እንዲሁም ሌሎች ነገሮቻቸው ጋር ሲመጣ ሰማይና ምድር ይሆናሉ:: በመሆኑም አንድ ድርጅት ያለው ምን ደረጃ ላይ ነው? የሚለውን ለማወቅ ድርጅታዊ የጤና ምርመራ በጣም አስፈላጊ ነው::
የጤና ምርመራው ከተደረገ በኋላ ደግሞ ከችግሩ በምን መንገድ እንደሚወጣ በቀጣይ ተመሳሳይ ችግር ውስጥ እንዳይገባም ምን ማድረግ ያስፈልጋል? የሚለውን ለማየትም መጽሐፍ ትልቅ አቅም አለው:: “የአመራር ሳይንስ እና ጥበብ” ሦስተኛው መጽሐፌ ነው:: ምክንያቴ ደግሞ ለማንኛውም ነገር መነሻው እድገቱም ሆነ ጥፋቱ የሚለካው በአመራሩ ድክመትና ጥንካሬ ውስጥ በመሆኑ ነው:: አራተኛው የዓለም ሀገሮች የሚሰኝ ሲሆን አምስተኛውና አሁን በቅርቡ ያስመረቅሁት ደግሞ የእኔን የሕይወት ጉዞ ከሌሎች ነገሮች ጋር አሰናስሎ የሚተርከው “የኔ መንገድ” የተሰኘው መጽሐፌ ነው::
አዲስ ዘመን ፦ እንደሰው ይታመማል፤ ከሕመሙ እንዲያገግም ይታከማል የሚለው መጽሐፍዎ ተቀባይነቱ እስከ ምን ድረስ ነበር ?
ኮሎኔል ፈቃደ፦ አዎ! ለመታከምም ታምሜ ይሆን እንዴ? ብሎ መጠራጠር እና ማሰብ ያስፈልጋል:: ብዙ ድርጅቶችን መጽሐፉ ላይ ባለው አካሄድ መሠረት መመርመር ችያለሁ:: መጽሐፉ የያዘውን ያህል ጥቅም ግን ሰጥቷል ብዬ አላምንም:: ምናልባት ወደፊት የሥራ አመራሩም ባለድርጅቱም ባለሀብቱም ነገሩን ሲረዱና ሲገባቸው ይጠቀሙበታል የሚል እምነት አለኝ::
አዲስ ዘመን፦ የአንድ የድርጅት ሥራ አስፈጻሚ አልያም ባለሀብት የሚመራውን የሚያስተዳድረውን ድርጅት ጤነኝነት ለመመርመር ቢፈልግ መጀመሪያ ምን ማድረግ አለበት?
ኮሎኔል ፈቃደ፦ እዚህ ላይ ችግሩ ሰዎች ስንባል መስማት የምንፈልገው የሚያሞግሰንን ጎበዝ የሚለን ሰው አስተያየት ብቻ ነው:: ነገር ግን እንድንሻሻል ብሎ የሆነ ክፍተታችንንን ለመንገር የሚሞክር ሰው ላይ ቅሬታ እናሳድራለን:: በመሆኑም የትኛውንም ሥራ የሚመሩ ሰዎች በተለይም በእኛ ሀገርና ባሕል ሁሉም ሃሳብ ለመስጠት የሚነሱት ‹‹ልክ ነው፤ ጥሩ ነው፤ አንደኛ ደረጃ ላይ ነህ›› ብለው ነው ።
ከዚህ አንፃር ድርጅታችሁን እስኪ በዚህ በዚህ ፈትሹት ሲባሉ “አይ ይሄ ጽሑፍ ላይ ያለ ነው፤ እኛ ራሳችንን የምንገልጸው በተጨባጭ በሥራ ነው” ይላሉ:: በመሆኑም ባሕላችን ራሱ በችግሮቻችን ዙሪያ ተወያይቶ ተደማምጦ መፍታት ላይ ገና ብዙ የሚቀረው ነው::
አዲስ የመሰለንን ሀሳብ ቶሎ ከመገፍተር፣ አይሆንም የፈረንጆች ሃሳብ ነው ለእኛ አይሠራም ብሎ ከማጣጣል እና በሩቅ ከመሸሽ ይልቅ ቀረብ ብሎ በማየት ከራስ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ መቀበል ይበጃል:: የሚመሩትንም ሆነ የሚያስተዳድሩትን ተቋም፣ ድርጅት ሌላም ሌላም አንድ እርምጃ ከፍ ያደርግ ይሆናል እንጂ ጉዳት የለውም::
መጽሐፉ የሚማር ድርጅትና አመራር ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና ያለው ነው:: እኔ እስከ አሁንም የጻፍኳቸው መጽሐፍት እኔ ያለፍኩበትን ሌሎች ይማሩበታል ብዬ ያሰብኩትን ነው:: ዛሬ ባይጠቅም የሚቀበለው ቢያጣ ነገ ደግሞ የሚፈልገው ይኖራል ብዬም አስባለሁ::
የሚገርመው ይህንን ችግር ተቀብሎ ወደመፍትሔ ያለመሄድ ሁኔታ እስከ አሁንም መድረስ የሚገባን ቦታ እንዳንደርስ ጎትቶናል:: ለምሳሌ የመንግሥት ድርጅት ሲሆን በጀት ይመደብለታል፤ ይህ በጀት ደግሞ ሀብትን በአግባቡ ተጠቅሞ ግብን ለማሳካት የሚውል ነው:: ግባችንን መታን ይላሉ:: ግን ደግሞ እዛ ግብ ላይ የሚደርሱት ብዙ ሀብት አባክነው ነው::
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ግቡን ሳያሳኩ በጀቴን በአግባቡ ተጠቅሜያለሁ የሚሉም አሉ:: በመሆኑም ችግራችንን አምነን ስለማንነሳ ሀብታችንን ከሰው ኃይላችን ጋር አቀናጅተን ለመሥራት እንቸገራለን፤ በዛው ልክ ደግሞ ተፎካካሪ በመሆን ግብን መምታት ላይ ክፍተት ይታይብናል::
የነቃ የበቃ ሠራተኛ ሥራውን በእኔነት ስሜት አድምቶ እንዲሠራ ለማድረግ ተቋምን መመርመር ያስፈልጋል:: አመራሩም ችግሩን አምኖ ተቀብሎ ለለውጥ መነሳት ይኖርበታል:: ይህ ሳይሆን በቀረ መጠን ግን አስር እርምጃ መራመድ የነበረበት ሁለት እርምጃ ተራምዶ ስምንቱን ጥሎ መፈንጠዝ ይጀምራል ::
አዲስ ዘመን፦ ይህንን ሃሳብ ለተለያዩ ፍቃደኛ ለሆኑ፤ እውቀቱን ለሚፈልጉና መለወጥ ለወሰኑ ተቋማት ያካፈሉበት አጋጣሚ አለ ?
ኮሎኔል ፈቃደ፦ አንድ ቀን አልያም ሳምንት አሠልጥኜ ስወጣ፤ እኔ ራሴ የምወጣው ብዙ ነገሮችን ተምሬ ነው:: በማሠልጠን ዘመኔ በርካታ ድርጅቶችን አይቻለሁ አማክሬያለሁ:: በዚህ ሥራዬ ደስ የሚለኝ የአመራር ሳይንሱንም ሆነ ድርጅታዊ ጤና ምርመራን አሠልጥኜ ስጨርስ፡ እነሱ ደግሞ ወደራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ለውጠውት በተወሰነ ሁኔታ ለውጥ አምጥተው ወዳጆችን ሳፈራ የሚሰማኝ ደስታ ወደር የሌለው ነው:: አብዛኞቹ ተቋማትም በሠለጠኑት መሠረት ውጤታማ በመሆን ላይ ናቸው:: ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ሥልጠናው ውጤት የሚያመጣ የማይመስላቸው ባለሀብቶች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች አሉ :: ይህ በጣም ያሳዝነኛል::
አዲስ ዘመን ፦ አምስተኛው መጽሐፍዎ “የኔ መንገድ” ይሰኛል፤ ምን ማለትዎ ይሆን?
ኮሎኔል ፈቃደ፦ “የኔ መንገድ” ማለት እስከ ዛሬ የተጓዝኩበት የወጣሁበት የወረድኩበት፤ የተማርኩት ያስተማርኩት ያፈራኋቸው ጓደኞች፤ መጥፎና ጥሩ ጊዜያት በጠቅላላው ሁሉንም መንገዶቼን የዳሰስኩበት ነው::
አንዳንድ ሰው እኔ ብቻ ትክክል ነኝ ይላል:: ይህ መሠረታዊ ስህተት የተሞላበት አስተሳሰብ ነው:: አንዱ ሰው የሄደበትና ሌላው የተጓዘበት መንገድ ፈጽሞ የተለያየ ነው:: እኔ በሄድኩበት ወቅት የነካካኋቸው ሰዎች እንዲታወሱ ከማድረግ ባሻገር፤ እኔ ያሳለፍኩት ነገር ለወጣቱ ትንሽ ነገር ያበረክት እንደሆነ በሚል ነው አሻራዬን ለማኖር የሞከርኩት::
ሁሉም ሰው የራሱ የተለየ ታሪክ አለው:: እያንዳንዱ ሰው የተጓዘበት የሕይወት ልምዱ የአንዱ ከሌላው ፈጽሞ የተለየ ነው:: ልክ እንደ እጃችን አሻራ የአንዱ ከሌላው ጋር በምንም አይመሳሰልም:: አሁን ላይ የዕድሜዬ ቆጣሪው 69ኛው ዓመት ላይ ያሳያል:: በዚህ ረጅም ዓመታት እኔ የተጓዝኩበትና የመጣሁበት መንገድ፣ የኖርኩበትና ያለፍኩበትም የሕይወት ልምድ እንዲሁ ከሌላው የተለየ ነው:: ለዚህም ነው የመጽሐፌን ርዕስ ”የኔ መንገድ” በማለት የሰየምኩት::
አዲስ ዘመን ፦ በተለያዩ ጊዜያት የሀገሪቱን ከፍተኛ አመራሮች የማግኘት እድል ገጥሞታል፤ አጋጣሚዎቹ እንዴት ነበሩ?
ኮሎኔል ፈቃደ፦ እንዳልኩት በልጅነቴ መጽሐፍ እነግድ ነበር:: እናም አንድ ቀን ሜክሲኮ ላይ መጽሐፌን ይዤ ቁጭ ብዬ የትራፊክ መብራቱ ላይ የጃንሆይ መኪና ቆሟል እንዴ ብዬ በቀጥታ መጽሐፌን ይዤ ሄድኩና መጽሐፍ ግዙኝ አልኳቸው፤ “መጽሐፍህ ምንድ ነው?” ሲሉኝ የጆን ኤፍ ኬኔዲን ታሪክ የተመለከተ መጽሐፍ ነበረኝና እሱን አውጥቼ ሰጠኋቸው “ስንት ነው” ሲሉኝም አራት ብር አልኳቸው እሳቸውም ” ዋጋውስ ግድ የለም አንተ ግን ለማን ምን መስጠት እንዳለብህ የምታውቅ ነህ” ብለው አስር ብር ሰጥተውኝ ሄዱ::
ሌላው በደርግ ጊዜ ወታደር ሆኜ ዘመቻ ሄጄ መጣሁና በቤተ መንግሥት ውስጥ እሠራ ነበር:: ሥራ ላይ ሆኜ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ወደ እኔ መጥተው ጦርነቱ እንዴት ነው? ብለው ሲጠይቁኝ የማውቀውንና የተሰማኝን ምንም ሳላስቀር ነገርኳቸው:: ወዲያውም ወደግንባር በመነጋገሪያ በመደወል መልዕክት አስተላለፉ፤ በዛም ምክንያት ብዙ ነገሮችን ማትረፍ ተቻለ::
ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋርም በወታደርነቴ በሚመሯቸው ስብሰባዎች ላይ እየተገኘሁ ለሀገሬ ይበጃል የምለውን ሃሳብም በመሰንዘር ተሳትፌያለሁ:: ዶክተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋርም በባድማ ጦርነት ወቅት አብረን ብዙ ነገሮችን አሳልፈናል::
አዲስ ዘመን ፦ አሁን ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ እንዴት ያዩታል? ካለንበት ችግሮች መውጣት የምንችለው በምን መልኩ ነው ይላሉ?
ኮሎኔል ፈቃደ፦ በየሥርዓቱ የተለያዩ ታሪኮች አሉ:: በእርግጥ አሁን ያለንበት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ሆኗል:: አስቸጋሪነቱ ደግሞ በብሔር የተደራጀ የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ የሚነዛበት ወቅት በመሆኑ ነው:: በተለይም ማኅበራዊ ሚዲያው መብዛቱ ጥላቻን እያባባሰ በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፈ ነው::
እርስ በእርስ ጥላቻ ሲባባስና መጓተት ሲበዛ ችግሩ እየጨመረ ይሔዳል:: በመሆኑም ኅብረተሰቡ ችግሩን የሚፈታው በአንድ በመንግሥት ብቻ ነው ብሎ ኃላፊነቱን ሙሉ በሙሉ ለእሱ ከመስጠት በመቆጠብ ሁሉም በሚችለው ልክ ጥረት ማድረግ አለበት::
እኔ በመጽሐፌ ላይ ‹‹ከሶቭየት ኅብረት ምን ልንማር ይገባል?›› ብዬ ያሰፈርኩት ሀሳብ አለ:: በመሆኑም የሚጠበቅብን መደማመጥ መከባበር እንጂ አንተ አንቺ እየተባባሉ መገፋፋት ጥሩ አይደለም::
በመንግሥት በኩል ደግሞ የጋራ ተጠቃሚነትን በሀገር ላይ ለማስፈን መሥራት አለበት፤ እያንዳንዳችን የምንሠራት መጥፎ ነገር ተደማምራ ትልቅ ስህተት ውስጥ ይከተናል:: ምናልባትም ሀገራችንን የምናጣበት ሁኔታ ውስጥ ሊያስገባን ይችላል:: በመሆኑም ሰላምን ለሚያደፈርሱ ኃይሎች ጆሮ ባለመስጠት፤ ሀገራችንን በመጠበቅ ትውልድን በማነጹ በኩል ሁላችንም አንድ አንድ ጠጠር መወርወር ይገባናል::
አዲስ ዘመን ፦ የግልም ይሁኑ የመንግሥት ተቋማት የሥራ አመራራቸው ሳይንሱን የተከተለ እንዲሆን ምን መደረግ አለባቸው ?
ኮሎኔል ፈቃደ፦ ብዙ አመራር ትምህርቱን ወይም ሳይንሱን ሳያውቀው ቀርቶ አይደለም:: ሁሉም ያውቃልም ለማለት አያስደፈርም:: ነገር ግን በተቻለ መጠን እርስ በእርስ የመማማር ራስን በእውቀት ክህሎትና አመለካከት ማብቃት ላይ መሥራት ያስፈልጋል:: በተለይም አመለካከት ላይ መሠራት አለበት:: ምክንያቱም አንድ ተቋም ላይ ያለ አመራር በሠራበት ዘመን የሠራው መጥፎም ጥሩም ነገር ለእሱ መጠሪያ ሐውልቱ ነው:: በመሆኑም አመራርነት ትልቅ ነገር መሆኑን ተገንዝቦ ራስን አብቅቶ አጨብጫቢ ሳይሆን እውነተኛ የሥራ ተከታዮችን ማፍራት ይጠበቅበታል:: ለዚህም እራሱን በበቂ መንገድ ማዘጋጀት ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን ፦ ስለጊዜዎ በጣም አመሰግናለሁ::
ኮሎኔል ፈቃደ ፦እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ የመሰለንን ሀሳብ ቶሎ ከመገፍተር፣ አይሆንም የፈረንጆች ሃሳብ ነው ለእኛ አይሠራም ብሎ ከማጣጣል እና በሩቅ ከመሸሽ ይልቅ ቀረብ ብሎ በማየት ከራስ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ መቀበል ይበጃል:: የሚመሩትንም ሆነ የሚያስተዳድሩትን ተቋም፣ ድርጅት ሌላም ሌላም አንድ እርምጃ ከፍ ያደርግ ይሆናል እንጂ ጉዳት የለውም
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2015