የክልሉ ሕዝብ ነገዎቹ እንዲጨልሙ መፍቀድ የለበትም !

 መንግሥት በሕዝብ ይሁንታ ሥልጣን መያዙን ተከትሎ፣ የትኛውንም የፖለቲካ ፍላጎት በሰላማዊ መንገድ ማስፈጸም የሚያስችል አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት ሰፊ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። በሀገሪቱ የፖለቲካው መድረክ ለዘመናት የቆየውን በጠላትነት የመፈራረጅና የመፈላለግ ባሕል ለመለወጥም ረጅም ርቀት ተጉዟል። በዚህም ለውጦች ተመዝግበዋል።

ቀደም ባለው ጊዜ የሀገር እና የሕዝብ ጠላት ተደርገው የተፈረጁ ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና በብዙ ተግዳሮት ውስጥ ሆነው በሀገር ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃት የሚንቀሳቀሱበትን ሀገራዊ የፖለቲካ መድረክ በመፍጠር፤ በሀገሪቱ አዲስ የፖለቲካ ባሕል መጀመር የሚያስችል መሠረት ጥሏል።

ይህንንም ተከትሎ በሀገሪቱ ታሪክ ባልተስተዋለ መልኩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ፕሮግራሞቻቸውን /አስተምህሯቸውን ያለ አንዳች ችግር ማሰራጨት ችለዋል። ከባሕሉ አዲስነት የተነሳም አንዳንዶች የተፈጠረውን እድል ባልተገባ መንገድ በመጠቀም የሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት ችግር ሆነው ተስተውለዋል።

መንግሥት በአንድ በኩል የፖለቲካ ባሕሉ ስር ሰድዶ እንዲጎለብት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሀገር እንደ ሀገር ከመጣችበት የግጭት አዙሪት ተመልሳ እንዳትገባ፤ ክስተቱን በሆደ ሰፊነት በመያዝ ረጅም ርቀት ተጉዟል። ይህም በአንዳንዶች ዘንድ የደካማነት/የአቅመ ቢስነት ምልክት ተደርጎ ተወስዶ ‹‹የእንፈታተን›› ድፍረትን ፈጥሮ ሀገራችንን ወደ ፈተና አስገብቷል፣ ዛሬም እያስገባ ነው ።

የተለያዩ ስሞችና መገለጫ የሚሰጣቸው፣ እውነተኛ መነሻና መድረሻቸው ከግልና ከቡድን የሥልጣን ፍላጎት የሚመነጩ ኃይሎች የሀገራችንና የሕዝባችን የሰላምና ደህንነት ስጋት ሆነዋል፡፡ እነዚህ ኃይሎች ላለፉት ስድስት አስርተ ዓመታት ኢትዮጵያውያን ብዙ ዋጋ የከፈሉለትን የሕዝባችንን የፖለቲካ ነጻነት የሚሸከም የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ ፈተና፤ ሥርዓቱን ለመገንባት የተጀመረው ሀገራዊ ጥረት ተግዳሮት በመሆን ላይ ናቸው።

ከሀገሪቱ ብሔር፣ ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ እና መንፈሳዊ እሴቶች ባፈነገጠ መልኩ ጽንፈኛ አስተሳሰብ በሚወልዳቸው የጥላቻ ፖለቲካ የሚነዱት እነዚህ ኃይሎች፤ የሥልጣን ጥማታቸውን በአቋራጭ ለማርካት ሕዝብን በሕዝብ ላይ፤ ሕዝብን በመንግሥት ላይ በማነሳሳት ሀገራዊ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ብዙ ርቀት ሄደዋል፤ ዛሬም በዚሁ እኩይ መንገዳቸው ላይ ናቸው ።

ይህ የጥፋት ተልዕኳቸው እንዳሰቡት ውጤታማ መሆን ሲሳነው፤ ዛሬ ላይ በቀደሙት ዘመናት ሆነ ትናንት ላይ ለሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት፤ ለሕዝቦች ነፃነት እና ብሔራዊ ክብር ከፍ ያለ ዋጋ በመክፈል የደማቅ ታሪክ ባለቤት የሆነውን የ”ፋኖ” ስም ለከንቱና ጽንፈኛ ዓላማቸው መጠቀሚያ በማድረግ እየተንቀሳቀሱ ነው። በአማራ ሕዝብ ስም የአማራ ሕዝብን ሰላምና መረጋጋት አደጋ ላይ ለመጣል እየሠሩ ነው። ክልሉንም የትርምስ አውድማ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡

የአማራ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ከጦርነትና ከግጭት ዘላቂ የፖለቲካ ትርፍ ይገኛል ብሎ አያምንም። ጽንፈኝነትና ከዚህ የሚመነጨው የጥላቻ ፖለቲካም ለአማራ ሕዝብ ሆነ እንደ ሀገር ለመላው ኢትዮጵያዊ አይጠቅምም፡፡ የጽንፈኝነት መንገድ የአማራ ሕዝብ የሚወዳትን ሀገር ከማሳጣትና ሕዝብን ከመበተን ባለፈ ሊያስገኝ የሚችለው አንዳች ጥቅም እንደሌለ በተጨባጭ ይረዳል።

ላለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት በላይ በሀገሪቱ ሰፍኖ የነበረውን በጥላቻ ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ አስተሳሰብ ሲቃወም የነበረው፤ ብዙ ዋጋ ለመክፈልም የተገደደው የችግሩን አሳሳቢነት በአግባቡ መረዳት ስለቻለ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ሀገር እንደ ሀገር የቆመችበትን መሠረት የሚያናጋ የጥፋት መንገድ መሆኑን ስለተገነዘበ ነው። ለውጡንም ከፍ ባለ ተስፋ የተቀበለው ከዚሁ እውነታ በመነጨ ነው ።

በተለይም እነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዳይሰፍን የጀመሩትን ክልሉን የማተራመስ እኩይ ተልዕኮ እንዳይሳካ፤ ስምሪት እየወሰደ ባለው የመከላከያ ሠራዊት ላይ ለጀመሩት የስም ማጥፋት የተቀናጀ ዘመቻ ጆሮውን በመንፈግ፤ የጀመረውን የልማት ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን ለሰላም መረጋጋት ከማንም በላይ እራሱ ዘብ ሊቆም ይገባል ።

መከላከያ ሠራዊታችን ከሕዝባዊ ባሕሪው በመነጨ፤ በደስታውም ሆነ በኃዘኑ ከሕዝብ ጎን የሚቆም፣ አብሮ የሚያለማ፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ፈጥኖ ደራሽ፣ ለኢትዮጵያ ሕልውና ከማንም ቀድሞ ሕይወቱን የሚገብር የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓታችንና አንድነታችን ጠባቂ ስለመሆኑ ለአማራ ሕዝብ የሚነገረው አይደለም ፡፡

ይህንን እውነታ ወደ ጎን በመተው የመከላከያ ሠራዊቱን ጀግና አመራሮች እና የሠራዊቱን ስም የሚያጎድፉ፤ የአማራ ሕዝብ ሠራዊቱን እንዲጠራጠር የሚያደርጉ የፖለቲካ ነጋዴዎች ተፈጥረዋል፡፡ ነጋዴዎቹ ከማኅበራዊ ሚዲያ የፖለቲካ ንግድ አንስቶ ያተርፋል ያሉትን ሁሉንም ስም የማጥፋት ዘመቻ በሠራዊቱ ላይ እያካሄዱ ይገኛሉ ።

የመከላከያ ሠራዊታችን የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ከየትኛውም አካባቢ በላይ መስዋዕትነት ከፍሏል ፤ ዛሬም እየከፈለ ነው። ይህም ሠራዊቱ ለአማራ ሕዝብ ሰላምና ደህንነት ያለውን አጋርነት በተጨባጭ በመስዋዕትነት ማረጋገጥ ያስቻለ ነው ። በክልሉ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥም መንገድ የሚከፍት ነው ።

አሁን ባለው ሀገራዊ እውነታ ከሰላማዊ አማራጭ ውጪ የትኛውንም አይነት ፖለቲካዊ ፍላጎትና ዓላማ ማሳካት እንደማይቻል በቅርቡ ከተከሰቱ ድርጊቶች አስተማሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታመናል፡፡ በስክነትና የወል እውነቶች ላይ በመቆም ብቻ የተናጠል ጉዳዮች መፍትሔ እንደሚያገኙ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በደቦ፣ በግርግርና ግጭት እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያ ጋጋታ የትኛውም አይነት ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ አይችልም ፡፡

የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያ የነፃነት ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ አለው፡፡ የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን ባለውለታ በሆነው በ”ፋኖ ” ስም፤ በዘመናት ብዙ ዋጋ የከፈለለትን የሀገር ሉዓላዊነትን እና የሕዝቦችን አንድነት እየተገዳደሩ ያሉ የጽንፈኞችን ስብስብ በቃችሁ ሊላቸው ይገባል፤ በነዚህ ጽንፈኛች ነገዎቹ እንዲጨልሙም መፍቀድ የለበትም ።

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 29/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *