የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ዝግጅት በረጅም ርቀት

ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የተሳትፎ ታሪኳ ካስመዘገበቻቸው ሜዳሊያዎች የሚልቁት በታወቀችበት የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ርቀቶች የተገኙ ናቸው። በሜዳሊያ የደረጃ ሰንጠረዡ ከዓለም ሃገራት 6ኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ ያደረጓት የሰበሰበቻቸው 95 ሜዳሊያዎች ሲሆኑ፤ ከዚህ ውስጥ 69 የሚሆኑት በሁለቱ ርቀቶች የተመዘገቡ ናቸው። 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሊካሄድ ሁለት ሳምንት ብቻ የቀረው መሆኑን ተከትሎም በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ የእነዚህ ርቀቶች ድል እንደተለመደው የኢትዮጵያ ይሆናል በሚል ይጠበቃል።

የማጣሪያ ውድድር መካሄዱን ተከትሎ አትሌቶች ከተመረጡ በኋላ ብሄራዊ ቡድኑ በሆቴል ተሰባስቦ ዝግጅቱን ማድረግ ከጀመረ ሶስት ሳምንታትን አስቆጥሯል። በሃንጋሪዋ ከተማ ቡዳፔስት የሚካሄደውን የዓለም ትልቁን የአትሌቲክስ ውድድር እንደ አምናው ሁሉ በስኬት ለማጠናቀቅ የሚያስችል ዝግጅት እንደሆነም የቡድኑ አባላት ይገልጻሉ። እአአ በ2019ኙ የዶሃ ዓለም ቻምፒዮና በ5ሺ ሜትር የብር፤ እንዲሁም፣ በ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር አሸናፊው አትሌት ሰለሞን ባረጋ ያደረገው ዝግጅት ለውጤት የሚያበቃ መሆኑን ያረጋግጣል።

ዓመቱ የዓለም ቻምፒዮና የሚካሄድበት እንደመሆኑ ፌዴሬሽኑ ብሄራዊ ቡድን ከማዋቀሩ አስቀድሞ በግሉ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። ቡድኑ ከተሰባሰበ ወዲህም አትሌቶች በተመሳሳይ መንፈስ ዝግጅታቸውን ቀጥለዋል። በተለይ በ5ሺ ሜትር በቅርቡ አስደናቂ አቋሙን ካሳየው አትሌት በሪሁ አረጋዊ ጋር በመሆን አሸናፊ ለመሆን የሚያስችላቸውን ልምምድ እያደረጉ መሆኑንም ይጠቅሳል።

ባለፈው ዓመት በኦሪጎን በተካሄደው ቻምፒዮና ኢትዮጵያ ከዓለም ሃገራት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ አኩሪ ታሪክ ማስመዝገቧ የሚታወስ ነው። ይሁንና ባልተጠበቀ ሁኔታ በሁለቱ ርቀቶች በወንዶች በኩል የበላይነቱን የያዙት የኬንያ እና የኡጋንዳ ዜጎች ነበሩ። በዚህ ዓመትም ይኸው ሁኔታ እንዳይደገም በትኩረት እየሰሩ መሆኑን የሚናገረው ወጣት አትሌት፤ ስፖርት ወዳዱን ህዝብ ለመካስ ጥረት እንደሚያደርጉም ጠቁሟል።

በብሄራዊ ቡድኑ የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር አሰልጣኝ ኮማንደር ቶሌራ ዲንቃም በተመሳሳይ ቡድኑ ከተሰባሰበበት ጊዜ አንስቶ ውጤታማ የሚያደርገውን ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ይጠቅሳሉ። የስፔኑን የሰዓት ማሟያ ውድድር ተከትሎ የ10ሺ ሜትር አትሌቶች በጊዜ ወደ ሆቴል የገቡ ሲሆን፤ የ5ሺ ሜትር አትሌቶች ደግሞ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች መጠናቀቅን ተከትሎ በሰዓታቸው መሰረት ቡድኑን ተቀላቅለው ወደ ዝግጅት ገብተዋል። በተቀመጠው የዝግጅት መርሃ ግብር መሰረትም ቡድኑ ከክረምቱ የአየር ሁኔታ ጋር በሚስማማ መልኩ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ፣ እንጦጦ፣ ቃሊቲ፤ እንዲሁም፣ ሰንዳፋ በመሄድ ዝግጅቱን ቀጥሏል።

እንደ አጠቃላይ ሲገለጽም ቡድኑ ባለበት ሁኔታ በቻምፒዮናው ስኬታማ ሊያደርገው የሚችል አቋም ላይ እንደሚገኝ አሰልጣኙ ይጠቁማሉ። ይኸውም የአውስትራሊያውን የዓለም ሃገር አቋራጭ እንዲሁም በተለያዩ የዓለም ከተሞች የተካሄዱ የዳይመንድ ሊግ ውጤቶችን መነሻ በማድረግ ነው። አምና በወንዶች በኩል በርቀቶቹ ሜዳሊያ ባለመገኘቱ ያስቆጭ የነበረውን ሁኔታ በድል ለመቀየር ቡድኑ በጥረት ላይም ነው። ዓመቱን በአስደናቂ አቋም እያሳለፈ የሚገኘው አትሌት በሪሁ አረጋዊ፣ ዮሚፍ ቀጄልቻ፣ ሃጎስ ገብረህይወት፣… ያሉበት ርቀት ተስፋ ሰጪ ነው። በ10ሺ ሜትርም ቢሆን በማጣሪያው ላይ ልቆ የታየው በሪሁ እና ሰለሞን የዓመቱን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገባቸው ለአሸናፊነት እንዲጠበቁ ያደርጋቸዋል።

በሴቶች በኩልም ቢሆን ማጣሪያውን በአሳማኝ ብቃት ያለፈችው ጉዳፍ ጸጋዬ እና የአምናዋ የ10ሺ ሜትር ቻምፒዮናዋ ለተሰንበት ግደይ የሚገኙበት ወቅታዊ አቋም ቡዳፔስት ላይም ድሉን በድጋሚ ለማጣጣም የሚያስችላቸው መሆኑንም አሰልጣኙ ይገልጻሉ። በአንጻሩ በቻምፒዮናው ቀላል የማይባሉ ተፎካካሪዎች ከኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ኔዘርላንድ፣ ኖርዌይ እና ስፔን አትሌቶች ይጠብቃቸዋል።

በመሆኑም የሚጠበቀውን ትንቅንቅ በኢትዮጵያውያን የበላይነት ለማጠናቀቅ ቡድኑ በተለየ ቅንጅት ልምምድ በማድረግ፣ ውድድሩም ላይ በጥንቃቄ እና አንዱ ለሌላው መስዋዕት ሊሆን በሚያስችላቸው መልኩ እየተዘጋጁ እንደሆነም አሰልጣኙ አብራርተዋል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚታወቁበት የቡድን ስራ ኦሪጎን ላይ በሴቶች የታየ ቢሆንም በወንዶች በኩል ጉድለት ነበረው፤ በመሆኑም ይህንን ለማረም አሰልጣኞች በጋራ አትሌቶችን እያሰሩ ይገኛሉ። ልምድ ያላቸው አትሌቶችም ውድድርን በምን መልኩ መምራት እንዳለባቸው ስለሚያውቁ ለውጤታማነት የሚያግዛቸውን መንገድ እንደሚከተሉም እምነታቸው ነው።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *